የተባረኩ ሀገራት ወይስ የተረገሙ? የተባረኩ ሕዝቦች ወይስ የተረገሙ? (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ብዙ ጊዜ በብዙኃን መገናኛዎች ሳዳምጥና ስመለከት አንድ እጅግ የሚገርመኝን ነገር በተደጋጋሚ አዳምጣለሁ እመለከታለሁ፡፡ ነገሩ ምን መሰላቹህ፡- በስደትም በሥራም በተለያየ ምክንያት ከሀገር ወጥተው በባዕድ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖቻችን በተለይም ፕሮቴስታንቶች (ተቃዋሚዎች) እንዲያ በምቾት በድሎት የሚኖሩበትን ሀገር “እግዚአብሔር አብዝቶ የባረከው ሀገር!” በማለት በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ የእኛ ሀገር ደግሞ ሕዝብ በረሀብ በችግር በስቃይ የሚኖርበት ሀገር ስለሆነች እግዚአብሔር የረገማት የጠላት ሀገር እንደሆነች መጠላት መረገሟም ሲጀመር ጀምሮ እንደሆነ “መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያደራል ክፉ ዛፍ ክፉ ፍሬን ነው የሚያፈራው፣ እንክርዳድ ተዘርቶ ስንዴ አይበቅልም እንክርዳድ የበቀለው የተዘራው እንክርዳድ ስለሆነ ነው፣ አባቶቻችን ክፉዎች ስለነበሩ ነው ትውልዱ ክፉ የሆነውና በችጋር በረሀብ በእርዛት በቸነፈር በጦርነት እየጠቀጣ ያለው” በማለት ይገልጻሉ፡፡

ለእነሱ “የተባረከ ሀገር!” ማለት እንደልብ የሚበላበት እንደልብ የሚጠጣበት ከዚህም የተነሣ እንደ ድልብ ከብት የሚሰባበት የሚደለብበት የሚጨፈርበት የሚታበድበት ሀገር ማለት ነው፡፡
እጅግ እንጭጮች እጅግ ያልበሰሉ እንደሆኑ ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ አስተሳሰባቸውም ፍጹም ሥጋዊና ምድራዊ ነው፡፡ ምንም የገባቸው ነገር የለም፡፡

ቅንጣትም እንኳ ብትሆን መንፈሳዊነቱ የነገረ ሃይማኖቱ ነገር የገባቸው ቢሆኑ ኖሮ ሰው እንደልብ የሚበላበት የሚጠጣበት ከጥጋቡ የተነሣም ሌት ተቀን የሚጨፍርበት ኃጢአት እርኩሰት በደል ክህደት መርገም ያለ ለከት በገፍ የሚፈጸምበት የኃጢአት የእርኩሰት የበደል የክህደት የመርገም መፈልፈያ መፈጠሪያ መናኸሪያ መርከሻ መጉደፊያ ማደፊያ ሀገር “ሰዶም እና ገሞራ” እንጅ “ሀገረ እግዚአብሔር የተባረከ የተቀደሰ ሀገር” ማለት እንዳልሆነ ጠንቅቀው በተረዱ ነበር፡፡ እንዴት እንደሚያስቡ አይገባኝም ሁሉንም ነገር በሆዳቸው ነው የሚተረጉሙት፡፡ ቃሉ ግን እንዲህ ይላል፡-

“ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” 1ዮሐ. 2፤15-17
“የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና” ዕብ. 13፤7-9
“በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” ማቴ. 16፤24-26
እያለ እነሱ ዋጋ የሰጡት የሆድ ነገርና ምቾት ድሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ከንቱ እንደሆነ፤ ከእግዚአብሔርም የሚያርቅ እንጅ የሚያቀርብ እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ከሐዋርያትና ከመቶሃያው የወንጌል ቤተሰብ አንዳቸውም እንኳን ምቾትንና ድሎትን ሳይሹ ራሳቸውን ክደው መስቀላቸውን በመሸከም ሕይዎታቸውን በመከራ ያሳለፉት፡፡
“በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ” የሐዋ. 14፤21-22 እነ ከንቱ ሆይ! እውነቱ ይሄ ባይሆን ኖሮ ታዲያ መከራንና የእግዚአብሔርን መንግሥት ምን አገናኘው?

እርግጥ ነው ቃሉ “እሽ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላቹህ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላቹሀል” ኢሳ. 1፤19-20 ይላል፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ ግለሰቦች “እግዚአብሔር አብዝቶ የባረከው ሀገር!” እያሉ የሚጠሯቸው እነዚያ ሀገራት እንደልብ የሚበላ የሚጠጣባቸው ተድላ ደስታ የሚኮመኮምባቸው ሕዝባቸው እግዚአብሔርን እሺ ብሎ ለእግዚአብሔር ስለታዘዘ እግዚአብሔርን አምላኪ አክባሪ አወዳሽ አገልጋይ አመስጋኝ ሕዝብ ስለሆነ፣ በቅድስና በንጽሕና ሕይዎት የተዋጀ የተባረከ ሕዝብ ስለሆነና አባቶቻቸውም የተባረኩ ስለነበሩ የመልካም ዛፍ ፍሬዎች ወይም የእንክርዳድ ሳይሆን የስንዴ ዘር መልካም ፍሬዎች ስለሆኑ እንዳልሆነና ኃጢአት በደል ክፋት እርኩሰታቸው በአንደበት ለመግለጽ በጆሮ ለመስማት እጅግ በሚከብድ ደረጃ ያደፉ የጎደፉ የረከሱ፣ “እግዚአብሔር የለም!” የሚል ሰይጣናዊ የክህደት ትምህርትን ፈጥረው ዓለምን በክህደት መርዝ የሚበክሉ፣ ከጅምሩም የመልካምና የቅድስና ታሪክ ኖሯቸው የማያውቁ የእንክርዳድ የአባቶቻቸው ልጆች፣ እግዚአብሔርን ፈጽሞ የማይፈራ የማያፍር የሚዳፈር የሚገዳደር የሚዘባበት እርጉም፣ ዕኩይ፣ ቆሻሻ ሕዝብ፤ አመንን ካሉም በሃይማኖት ተቋሞቻቸው ደረጃ ሁሉ እጅግ በሚገርምና ጋራ በሚያጋባ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ የሚያስቀይም ጸያፍ የግብረ ሰዶማዊነትን ኃጢአት ተቀብለው ሕጋዊ አድርገው ዲያብሎሳዊ ግብር በመፈጸም ጋብቻ የሚፈጽሙ፣ ለሰይጣን የመመለኪያ ቤት በመሥራት በግላጭ በይፋ ሰይጣንን እስከማምለክ ድረስ ድፍረት የሚፈጽሙ፣ በእግዚአብሔርና በክብሩ የሚሳለቁ የሃይማኖትን ምንነትና ዓላማ ጨርሶ የማያቁ የክፉ ዛፍ ፍሬዎች የዓመፃ ሕዝብ እንደሆኑ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

እዚያው አብረው ሲኖሩ ዘወትር በዓይናቸው የሚያዩት በጆሯቸው የሚሰሙት በእጃቸው የሚዳስሱት ጉዳይ ነውና፡፡ ነገር ግን እነዚህ ግለሰቦች ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው ስለሆነ ይሄ ሁሉ ጉዳቸው ሳይታያቸው ሀገሩን እንደልብ ስለበሉበት ስለጠጡበት ተድላ ደስታ ስለኮመኮሙበት ብቻ “እግዚአብሔር አብዝቶ የባረከው ሀገር!” ይላሉ፡፡

ታዲያ የእነዚያ ሀገራትና ሕዝባቸው ማንነት እንዲህ ከሆነ ማለትም መልካም ዛፍ ያፈራቸው መልካም ፍሬዎች ከተባረኩ አባቶቻቸው የተገኙ የብሩክ ዘር ልጆች ካልሆኑና እርጉሞች እኩዮች የዐመፃ ልጆች እንክርዳዶች ከሆኑ እንዴት ሀገራቸው ችግር የሌለበት የተድላ የደስታ ሀገር ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ፡- እውን ግን መናፍቃኑ እንዳሉት ሀገራችን ኢትዮጵያና ሕዝቧ እግዚአብሔር የረገማቸው ያዘነባቸው ስለሆሁ የክፉ እንጅ የመልካም ዛፍ ፍሬ ስላልሆንን እንክርዳዶች እንጅ ስንዴዎች ስላልሆንን አባቶቻችን ክፉዎች ስለሆኑና ከዚህም የተነሣ እኛም ክፉዎች የተረገምን ሆነን ነው ወይ በድርቅ በረሀብ በቸነፈር በእርዛት በጦርነት በችጋር መከራ እያየን ያለነው? ካልሆነ እንዴት በመከራ ልንኖር ቻልን? የሚል ጥያቄ ይነሣል ብየ እገምታለሁ፡፡

እነኝህ ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ጥያቄ እንደመሆናቸው ጥያቄዎቹን የሚመልሰው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

ከዚያ በፊት ግን ይህ የችጋር የረሀብ የርዛት የድህነት ታሪካችን የሀገራችን ታሪክ ሀ ብሎ ሲጀመር ጀምሮ ከጥንቱም አብሮን የነበረ እንዳልሆነ፤ መንስኤ ከሆኑ የቅርብ ምዕት ዓመታት ከባባድና ረጃጅም ጦርነቶች በኋላ የተፈጠረ ችግር መሆኑንና ከረጅሙ ታሪካችን ሦስት አራተኛውን ዘመን በወቅቱ ከነበሩት አራት የዓለም ኃያላን ሀገራት አንዱ ሆነን የኖርንበት ዘመን እንደሆነ ልብ እንዲባል መጠቆም ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ይሄንን ካልኩ በኋላ እኛ በድርቅ በረሀብ በርዛት በድህነት በችጋር መቀጣታችን ከምን የተነሣ ነው? የሚለውን እንመልስ፡-
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡-

“ልጄ ሆይ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል” ዕብ. 12፤5-11
እንግዲህ ይሄው ነው ምሥጢሩ፡፡ እግዚአብሔር ሀገራችንንና ሕዝባችንንም ስለጠላ ሳይሆን የተለያዩ መቅጫዎችን እራሳችን እየፈጠርናቸው ሁሉ እንድንቀጣባቸው የሚያደርገን ከላይ በቃሉ እንደተናገረው ሁሉ ከፍቅሩ የተነሣ፣ ስናጠፋ ልጆች እንጅ ዲቃሎች ስላልሆንን ተቀጥተን መመለስ ስላለብን ከጥፋታችን ለመመለስ፣ በመቀጣታችን በምናሳልፈውና በምንቀበለው መከራ የጽድቁ ተካፋዮች እንድንሆን ነው የምንቀጣው፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን የእግዚአብሔር ልጆች ነን ሀገራችንም ሀገረ እግዚአብሔር ናት ብለን ስንል ፈጥረን ፈልስፈን ሳይሆን ቅዱስ ቃሉን ምስክር አድርገን ነው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡- “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላቹህምን? ይላል እግዚአብሔር” ትን. አሞጽ 9፤7, በተጨማሪም መዝ. 67(68)፤31, መዝ. 71(72)፤9, መዝ. 73(74)፤14, መመልከት ይቻላል፡፡

ስለሆነም በቃሉ ምስክርነት መሠረት እኛ መልካም ዛፍ ያፈራን ከስንዴ ዘር የተገኘን መልካም ፍሬዎች፤ ከቅዱሳን አባቶቻችን የተገኘን የተባረክን ሕዝብ እንጅ ክፉ ዛፍ ያፈራን የክፉ አባቶቻችን ልጆች አይደለንም፡፡ ይሄ የእግዚአብሔር በሆኑ ነገሮች ላይ የሚቀናውና በጠላትነት የሚነሣው የዲያብሎስና የአገልጋዮቹ ወሬ ነው፡፡ በእርግጥ ከስንዴ መሀል እንክርዳድ አይጠፋምና ጌታ በወንጌል እንዳለው፡-

“መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም። ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን። እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች። ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች። ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም። በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው። የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” ማቴ.13፤24-43

እንዳለው ሁሉ ጠላት ዲያቢሎስ የዘራቸው ጥቂት የማይባሉ እንክርዳዶች ሊኖሩብን ይችላሉ፡፡ እነሱ ግን ቅዱስ ቃሉ የተባረከች ሀገርና የተባረከ ሕዝብ እንደሆኑ የመሰከረላትን ሀገርና ሕዝብ በፍጹም የሚወክሉ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እናም የዚህች ሀገርና ሕዝቧ ማንነትና የምንቀጣበትም ምክንያት ከረጅም ባጭሩ ከብዙ በጥቂቱ ይሄንን ይመስላል፡፡ ባልገባቹህ ነገር ላይ ችጋራም፣ ረሀብተኛ፣ ድሀ ናት ብላቹህ ሀገራቹህን አትጥሏት አትርገሟት ከአምላኳ ጋር ትጣላላቹህ፡፡ ይሄ ሁሉ በእግዚአብሔር የተደረገና እሽ ስንል ወይም የእግዚአብሔር ቀን ሲደርስ በቃ! ሲል የሚለውጥና የሚወገድ በእጁ የተያዘ ጉዳይ ነውና፡፡

እነዚያ ደግሞ መናፍቃኑ እንደልባቸው ስለበሉበት ስለጠጡበት ብቻ “እግዚአብሔር አብዝቶ የባረከው ሀገር!” የሚሏቸው ሀገራትና ሕዝቦች ደግሞ በእጅጉ እያጠፉ እያሉ የማይቀጡበት ምክንያት ከላይ ከቃሉ እንደተረዳነው ልጆች ስላልሆኑና ዲቃሎች ከመሆናቸው የተነሣ እግዚአብሔር የማይቀጣው ሕዝብ ስለሆኑ እንጅ የተባረኩ የተቀደሱ ከመሆናቸው የተነሣ የምድርን በረከት እንዲበሉ ስለተፈቀደላቸው እንዳልሆነ ከታሪካቸው ከተግባሮቻቸው ከማንነታቸው ተረድተናል፡፡ እነሱ ከተቀጡም የሚቀጡት እንደ ሰዶምና ገሞራ ከኃጢአት እርኩሰታቸው ብዛት ዓይነት ክፋትና ክብደት እግዚአብሔርን ክፉኛ ከማስቆጣታቸው የተነሣ ለቅስፈት ነው የሚቀጡት እንጅ ከላይ በተገለጸው ልጆች በሚቀጡበት ምክንያት አይደለም የሚቀጣቸው፡፡
እናም ለእኛ እንደተመሰከረልን ሁሉ ልጆች መሆናቸውን እግዚአብሔር በቃሉ ያልመሰከረላቸው ሀገራትና ሕዝቦች እጅግ የሚቀፍ የሚከብድ የሚዘገንን ኃጢአት እርኩሰት በደል ድፍረት እየፈጸሙ ሳይቀጡ በምቾት በተድላ ደስታ በድሎት የሚኖሩበት ምክንያት ከጥቅሱ እንደተረዳቹህት ዲቃሎች እንጅ ልጆች ስላልሆኑና እንደ ዲቃላነታቸውም ስለማይቀጣቸው ነው፡፡ ከላይ እንዳልኩት እነሱ ከተቀጡም የሚቀጡት ለቅስፈት እንጅ የጽድቁ ተካፋዮች እንዲሆኑ አይደለም፡፡ እነሱ ተስፋቸው በምድር እንጅ በሰማይ አይደለምና ከሁለቱም ዓለም ሳይሆኑ እንዳይቀሩ በሁለቱም ዓለም እንዳይጎዱ የመረጡትን የምድርን ተድላ ደስታ ምቾት አይነፍጋቸውም፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ቃሉ እነዚህን አሕዛብ “የምድር ባለጠጎች” ሲል የሚጠራቸው መዝ. 45፤12 ተድላ ደስታቸው ምቾት ድሎታቸው በምድር ነውና፡፡

በተጨማሪም ለእነዚህ ሐሳባቸው ምድራዊና ሥጋዊ ለሆኑ ሰዎችና ሁሉንም ነገር በሆዳቸው ለሚለኩ መናፍቃን ከዚህ በታች ያለውን ጌታ በወንጌሉ የተናገረውን ትምህርት ልብ እንዲሉ ልጠቅስላቸው ወደድኩ፡-

“ ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ አብርሃም አባት ሆይ! ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። አብርሃም ግን ልጄ ሆይ! አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ እንደተቀበለ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ። እርሱም እንኪያስ አባት ሆይ! ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ። አብርሃም ግን ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው። እርሱም አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ! ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሔድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ። አብርሃምም ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው ” ሉቃ. 16፤19-31

እናም በዚህች ምድር በመከራ በችግር የሚኖር ቢኖር እንደ አልዓዛር በሰማይ ተድላ ደስታ ይጠብቀዋልና አይከፋ አይዘን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በዚህች ምድር ተድላ ደስታቸውን የሚኮመኩሙት በምቾት የሚምነሸነሹት አሕዛብና አረማዊያን እንደ ባለጸጋው ነዌ በሰማይ ተስፋ የላቸውምና ወዮ! ለነሱ፡፡

እናም የሚቀጣ ሕዝብ ሁሉ “እሱ ስለወደደው ነው” ባይባልም ቅሉ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ከነመኖሩ እንኳን የማያውቁት እንዲሁም መኖሩንም መቀበል የማይፈልጉትም ይቀጣሉና፡፡ እግዚአብሔር እነሱን የሚቀጣበት ምክንያት ከአመጻቸው ከእርኩሰታቸው ከበደላቸው ብዛትና ክብደት አንጻር በመቅሰፍት እንዲጠፉ ስለፈለገ ነው እንጅ ስለ ፍቅር አይደለም፡፡ ስለሆነም የሚቀጣ ሕዝብ ሁሉ “እሱ ስለወደደው ነው” ባይባልም የማይቀጣ ሕዝብ ሁሉ ግን ዲቃላ እንጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሕዝብ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቤ ልጀ ያለውን ሕዝብ የጽቅዱ ተካፋይ ለማድረግ፣ አባት የሚወደውን ልጁን ይቀጣልና ስለ ፍቅሩና ልጅነቱን ለማረጋገጥ ከመቅጣት እንደማይመለስ በቃሉ አረጋግጧልና፡፡ በመሆኑም ነው እንደ እስራኤልና ኢትዮጵያ በመቀጣት መከራ ያየ ሕዝብ የሌለው፡፡

ከበፊት ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች “ክርስቲያን ነን” የሚሉትን ጨምሮ ወደ ሀገራችን የሚመጡ የውጭ ዜጎች ሕዝባችን ረሀብ፣ ሰይፍ (ጦርነት)፣ ቸነፈር (ወረርሽኝ)፣ ተምች፣ ኩብኩባ ወዘተረፈ. በመጣበትና ህልውናው አደጋ ላይ በመደቀ ጊዜ ይህ ችግር በኃጢአቱ ምክንያት ለቅጣት ከእግዚአብሔር እደታዘዘበት እንደመጣበት እንደተከሰተበት በማሰብ እግዚአብሔር ይቅር ይለው ምሕረቱን ይሰጠው ዘንድ በምሕላ በጾም በጸሎት በስግደት ሲጠይቅ በሚመለከቱበት ጊዜ እንዲህ በማሰባችንና በማድረጋችን ስሕተት እንደሆነ በማሰብ እጅግ ሲገረሙብን ይታያሉ፡፡ ይሄንን ሁኔታም በየ መጻሕፍቶቻቸው አስፍረውት ይገኛል፡፡

በእነሱ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይተዋወቁ ወይም እጅግ የራቁ ከመሆናቸው የተነሣ ጉዳዩን ከእግዚአብሔር ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ የረሀቡ ምንስኤ ድርቅ ነው ለድርቁ መንስኤ ደግሞ እንደ ኤምሚኖ ካትሪና ያሉ የአየር መዛባቶች ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ለቸነፈሩ መንስኤ ደግሞ የአየር መዛባትን ተከትሎ የሚፈጠር ወረርሽኝ ነው፡፡ ለጦርነት መንስኤ ደግሞ አለመግባባት ነው በማለት “እግዚአብሔር ነው” ብለን ማሰባችንን እጅግ የበዛ ሞኝነት ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
እኛ ለረሀቡ ድርቅ፣ ለቸነፈሩ የአየር መዛባት፣ ለጦርነቱ አለመግባባት ለሌላውም ሌላ መሆኑ መቸ ጠፋን? ያልገባቸው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር መቅጣት ሲፈልግ እራሱ ወርዶ አርጩሜ ቆርጦ በመግረፍ አለመሆኑን ነው፡፡ ይሄንን ከሆነ የሚጠብቁት እጅግ ሲበዛ የዋሀን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አንዳች ነገር ማድረግ ሲፈልግ አንድን ነገር ምክንያት መንስኤ ያደርግና ነው ማድረግ የሚፈልገውን የሚያደርግ እንጅ ወርዶ በእጁ አንዳች ነገር በማድረግ አይደለም፡፡

ለምሳሌ ሰው ሲሞት ለሞቱ ምክንያት ወይ ሕመም ወይ አደጋ ወይ ደግሞ አንዳች ነገር ሳይኖር አይሞትም፡፡ እኛ እያልን ያለነው ከመንስኤዎቹ ከምክንያቶቹ ጀርባ እግዚአብሔር ነው ያለው ነው እያልን ያለነው፡፡ እኛ እንደዚህ ብለን ማመናችን ከታላቁ መጽሐፍ (ከመጽሐፍ ቅዱሱ) ቃል የተነሣ ነው፡፡ እኛ ስናምን ከልብና ቃሉንም እውነት ነው ብለን ነው የምናምው እንደነሱ ለይምሰል አይደለም፡፡ ቃሉ የሚለው ድርቅና የርድቅ ልጅ ረሀብ፣ ቸነፈር (በሽታ)፣ ሰይፍ (ጦርነት) ችጋር ወዘተረፈ. ሕዝቡ ባመፀ ጊዜ ተቀጥቶ ንስሐ በመግባት ምሕረቱን በመጠየቅ ይመለስ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚታዘዙ የቁጣው መቅጫ መሆናቸውን ነው የሚናገረው፡፡ ዘዳ. 28፤15-24, ኤር. 14፤10-18, አሞጽ 4፤6-10, 2ኛ ሳሙ. 24፤1-25, ዮና. 3፤1-10, አስ. ከም. 3-7

በመሆኑም እኛ ታዲያ እንዲህ ብልን በማሰባችንና በማመናችን የተሳሳትነው ምኑ ላይ ነው? እርግጥ ነው የውኃ አሥተዳደር (water manegment) ያስፈልገናል፡፡ በብዙ ምክንያቶች፡፡ የእኛ የክረምት ወቅት አጭር ስለሆነና እንደነሱ እረጅም ስላልሆነ በዚህ አጭር የክረምት ወቅት የሚገኘውን ዝናብ በግድቦች በመያዝ ዓመቱን ሙሉ ልናመርት የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር የግድ ይኖርብናል፡፡ የክረምት ወቅታችን አጭር ይሁን እንጅ የምናገኘው የውኃ መጠን ግን ለብዙ ሀገራት የሚተርፍና ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ሀገራችንን የአፍሪካ የውኃ ማማ (the water tower of Africa) የሚል ሥያሜ አሰጥቷታል፡፡

ይሁንና ውኃውን በግድቦች በመያዝና ውኃን ተጠቅመን በማምረት ከረሀብ ለመላቀቅ የምንፈልገው ይሄንን በማድረግ እግዚአብሔር እኛን ለመቅጣት ከሚያመጣብን ረሀብ ማምለጥ እንችላለን ብለን ከማሰብ ሳይሆን 1. የውኃ ሀብታችንን ጨምሮ እግዚአብሔር የሰጠንን ሀብት ሁሉ በከንቱ ሳይባክን መጠቀም ስላለብን፡፡ 2. ከአዳም ኃጢአት የተነሣ ወደተረገመችውና በእኛም ላይ “እሾህና አሜኬላ ታብቅልብህ!” ወደ ተባልንባት የመከራ ምድር ስንመጣ ጥረን ግረን እንድንበላባት ስላዘዘን ዘፍ. 3፤17-19፡፡ 3ኛ. ሐዋርያት በትምህርታቸው “ሊሠራ የማይወድ አይብላ!” ብለው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስላዘዙንና ድንቅ አቅምና ብቃትን አድሎ በፈጠረልን ጭንቅላት እጅና እግር በመጠቀም ሠርተን መብላት ስላለብን ነው እንጅ ከእግዚአብሔር ቁጣ ማምለጥ የሚቻል ሆኖ ለማምለጥ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እሱ መቅጣት ከፈለገ አንድ ክረምት አይደለም ለዘለዓለሙም እንዳይዘንብ ማድረግ እንደሚችል በሚገባ እናውቃለንና፡፡
እንግዲህ ወገኖች ሆይ! ቅጣቱ ከመረረንና የምድርንም በረከት መብላት ከፈለግን ንስሐ በመግባትና ከሱ ጋር በመታረቅ እሱን እሽ በማለት እንደፈቃዱ በማደር በኦሪትም በሐዲስም እግዚአብሔርን ይፈሩ ያከብሩ ይባርኩ ይቀድሱ እንደነበሩትና እሱም ኃይል ጥበብ ሥልጣኔ ሰጥቷቸው በጥበቃው በረድኤቱ በበረከቱ ሳይለያቸው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ከፍ ባለ ኃያልነትና ክብር ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ እንዳደረጉት ቀደምት እናት አባቶቻችን እግዚአብሔርን “እሽ” በማለት ከችጋር ከመከራ መላቀቅና በቀደመው የኃያልነትና የክብር ቦታችን መልሰን መቀመጥ ነው መፍትሔው፡፡

እንዲህም ስል የእግዚአብሔር ልጆች የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን እሽ ስላሉ እሱ የምድርን በረከት እንዲበሉ በረከቱን በሰጣቸው ጊዜ እንደልብ እንዲበሉና እንዲጠጡ ይፈቀድላቸዋል ማለቴ እንዳልሆነ ልብ እንዲባል እፈልጋለሁ፡፡ እንደልብ እየተበላና እየተጠጣ እግዚአብሔርን እሽ ማለት ፈጽሞ አይቻልምና፡፡ መብል የኃጢአት ሁሉ መንስኤ በመሆኑ በልክ በመጠን እንጅ እንደልብ ያለ ልክ ያለ መጠን ተበልቶና ተጠጥቶ እየተፈረጠመ፣ እየተሰባ፣ እየተደለበ፣ ሰውነት በሥጋዊ ስሜትና ግብር ቀንዝሮ ሰክሮ፣ ጥጋብ እብደት እስኪፈጥርና የምንሠራውን እስከማናውቅበት ድረስ ለኃጢአት ምክንያት እስኪሆን እንዲበላ እንዲጠጣ እንዲጠገብ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡ የሰጠንን በረከት በመጠን በልክ በመጠቀም ስለ ሰጠን በረከት እንድናመሰግነው እንጅ፡፡

ከአዳም ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ ወደፊትም የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣላው በመብል የተነሣ ነውና ከአቅላችን ጋር ሆነን በማስተዋል እየተራመድን የተቀደሰ ሕይዎት እንዲኖረን ከፈለግን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ካሻንና መንግሥቱንም ለመውረስ ከፈቀድን የመብልን ነገር ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ቃሉ “ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና” ዕብ. 13፤9 በማለት ከአዳም ጀምሮ መብልን የወደዱ የደረሰባቸውን ዕጣ፣ መብልን ያልተጠነቀቁ ያልተቆጠቡና ልክ ያላበጁ ይልቁንም ያስተሳሰባቸውን ማዕከል ሆዳቸውን በማድረግ በሆድ ፍቅር የወደቁ ሁሉ እንዳልተጠቀሙ በመናገር ያስጠነቀቀው፡፡ መድኃኔየዓለም ክርስቶስ ልቡና ማስተዋልን ሰጥቶንና ለንስሐ አብቅቶን በቀደመው ክብራችን ኃያልነታችን ላይ ያስቀምጠን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!!! ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው [email protected]