ኢሕአዴግ ያቋቋመው ፍፁማዊ አምባገነን መንግስት ለኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጥ አይችልም!!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ኢሕአዴግ ያቋቋመው ፍፁማዊ አምባገነን መንግስት ለኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጥ አይችልም!! ==============
ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ
የኢፌድሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 54/1፣የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛና ትክክለኛ በሆነ፣ ድምፅ በምስጢር በሚሰጥበት የምርጫ ስርዓት በየአምስት ዓመቱ ይመርጣሉ ይላል፡፡ነገር ግን ኢህአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ይህን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌና ሌሎችንም አግባብነት ያላቸውን ሕጎች እየጣሰ በየአምስት ዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የሀገርና የህዝብ ሀብት እያባከነ ምርጫ ተብዬ ድራማዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ኢህአዴግ ይህንን ድራማ በየአምስት ዓመቱ የሚያካሂደው ከአለም አቀፍ ለጋሽና አበዳሪ ሀገሮች ዴሞክራት የመሆን እውቅና አገኛለሁ ከሚል የማምታቻ ዓላማው እንጂ በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ሰፍኖ ሰላማዊ የመንግስት ስልጣን ሽግግር እንዲኖር ባለው አቋሙ እንዳልሆነ ሕገ-ወጥ ተግባሩ እያጋለጠው እንደኖረ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ማሳያው ራሱ ያፀደቃቸውን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች የሚጥሱ የህዝብ ድምፅ መንጠቂያ ስልቶች እየቀየሰ በስራ ላይ በማዋልና ‹‹በምርጫ አሸነፍሁ›› በማለት የአምባገነንነቱን ዙፋን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ዘርግቶ ከህዝቡ ፈቃድ ውጪ ፍፁማዊ አገዛዙን ማስፈኑ ነው፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው የምርጫ ድራማ ወቅትም እንደለመደው የምርጫ አፈጻጸሙን ሂደት በህገ-ወጥ ካድሬዎቹና ከፖሊስ እስከ ልዩ የታጠቀ ሀይል በማዝመት ሙሉ በሙሉ በጉልበት ተቆጣጥሯል፡፡ ይህንን ህገ-ወጥ ተግባሩን ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ነፃ የህዝብ ታዛቢዎችና የዓለም-አቀፍ ታዛቢዎችም በሌሉበት አከናውኗል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮችንም በጉልበት አባርሮ፣አስፈራርቶና በገንዘብ ገዝቶ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ለቀው እንዲሄዱ ባስገደደበት ሁኔታ የህዝብን ድምፅ ቀምቶ ‹‹ መቶ በመቶ ›› እንዳሸነፈ በማወጅ አስነዋሪ የምርጫ ድራማ መጫወቱ እስከ ዛሬም መራጩን ህዝብ እያስቆጨው ያለ ጉዳይ ነው፡፡
ስለሆነም በግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ስም የተካሄደው ክንዋኔ በህገ-መንግስቱና በምርጫ ሕጉ የተደነገጉት የነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መርሆች የተጣሱበት መሆኑን በማስረገጥ፣ መድረክ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበል ግንቦት 19 እና ሰኔ 19 ቀን 2007 ዓ.ም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ማሳወቁ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ሰኔ 19 ቀን 2007 ዓ.ም ለጠ/ሚንስትሩ በፃፍነው ደብዳቤ ከዚህ በታች የተመለከቱትን 5 ጥያቄዎች አቅርበን ምላሽ እየተጠባበቅን ቆይተናል፡፡ ጥያቄዎቹም፡-
የተካሄደው የ5ኛው ዙር ምርጫ የሀገሪቱ ህገ-መንግስትና ሌሎች የምርጫ ሕጎች በተጣሱበት ሁኔታ የተከናወነ በመሆኑ የተፈፀሙትን የምርጫ ህግ ጥሰቶች የሚያጣራ አንድ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም፣
በምርጫው ዕለትና ከዚያም በኃላ በ4 የመድረክ አባሎች ላይ ግዲያ የፈፀሙ ወንጀለኞች ህግ ፊት ቀርበው ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ፣
በምርጫ ወቅት ቤታቸው የተቃጠለባቸውና የፈረሰባቸው፣ እንዲሁም ሀብት ንብረታቸው የተዘረፈባቸው የመድረክ አባሎች ንብረቶቻቸው እንዲመለሱላቸውና ህገ-ወጥ ድርጊቱንም የፈፀሙት ካድሬዎችና የፀጥታ ሀይሎች በህግ እንዲጠየቁ፣
የኢህአዴግ ካድሬዎች ከምርጫ በኃላ በማንአለብኝነት በመድረክ መራጮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ በበቀል ስሜት የሚፈፅሙት የማሸበርና የማስፈራራት ወከባዎች እንዲቆሙ፣
በ2007 ዓ.ም ምርጫ ወቅት መንግስታዊ ስልጣንን መከታ በማድረግ መራጩን ሕዝብ በማስፈራራትና በማስገደድ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ታዛቢና ድምፅ ቆጣሪ በሆኑበት ሁኔታ የተካሄደው ምርጫ ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ባለመቻሉ፣ ገዢው ፓርቲ ምርጫዎች በገለልተኛ የምርጫ አስተዳደር ስለሚመሩበትና ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሊካሄድ ስለሚችልበት ሁኔታ ከሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር አመቺ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር፡ የሚሉ ነበሩ፡፡
ኢህአዴግ ግን መድረክ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ነፍጎ፣ 4 ወራት ያህል ባስቆጠረበት ወቅት፣ ዛሬም ድምፁን በሰጠን ህዝባችን ላይ የበቀል እርምጃዎች እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ምክንያቶቹም ኢህአዴግን ለምን አልመረጥክም፣ ለመድረክ የምርጫ ጣቢያ ተወካይ ሆነሃል፣ በምርጫው የመድረክ እጩ ሆነህ ቀርበሃል ወዘተ መሆናቸው፣ መሰረታዊውን የዜጎች በነፃነት የመደራጀትና የፈለጉትን ፓርቲ የመደገፍ ዴሞክራሲያዊ መብት የጣሱ መሆናቸው&በእውን በህገ-መንግስቱ መሰረት የተቋቋመ መንግስት በሀገሪቱ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ይበልጥ የሚያጎላው ደግሞ መጠነ-ሰፊ በደል እየደረሰበት ያለውን አባላችንና ደጋፊያችንን አቤቱታ ሰምቶ የሚዳኝ አካል መጥፋቱ ነው፡፡ በዚህ መልክ ከህግ በላይ በመሆን ተጠያቂነት የሌላቸውን ምግባረ ብልሹና ለጥቅም አደር ቦዘኔ ካድሬዎችን ህዝቡ ላይ ካለቁጥጥር በመልቀቅ፣ ግብር ከፍሎ መንግስትን የሚያስተዳድር ዜጋን የኢህአዴግ ስርዓት እየበደለው ይገኛል፡፡
እንግዲህ ሀገራችንን በእንደዚህ አይነቱ ስርዓት-አልበኛ ሁኔታ ውስጥ ዘፍቆት ነው፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት የሚባለው ለይምሰል እንኳን አባላቱ በምርጫ ተብዬው እንኳን ውስጥ ያላለፉትን
ጨምሮ፣ የ5ኛውን ዙር ፓርላማ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም በመሰየምና አዲስ መንግስት በመመስረት፣ የአንድ ፓርቲ ፍፁማዊ አምባገነንነቱን ያለምንም ማድበስበስ፣ አይን ባወጣ መልኩ፣ ኢህአዴግ ያወጀው፡፡ ይህንንም ያገጠጠ እውነታ ለመሰወር፣ ኢህአዴግ 501 የፓርላማ መቀመጫዎችን ብቻ ነው ‹‹ያሸነፈው›› የቀሩትን 46 መቀመጫዎች ሌሎች አጋር ፓርቲዎች ‹‹አሸንፈዋል›› የሚል ሀሰተኛ ወሬ ያስወራሉ፡፡ ህዝባችን ግን አጋር ፓርቲዎቹ በይዘታቸውም ሆነ በአፈጣጠራቸው ከኢህአዴግ እንደማይለዩ ያውቃቸዋል፡፡
በዚህ ዓይነት በኢትዮጵያ ጉዳይ “ከእኔ ሌላ ለአሳር” በሚል ትዕቢትና ትምክህት በተወጠረ ተመፃዳቂ አቋም የሚመራውና በስልጣን ፍቅር ልቡ የናወዘው የኢህአዴግ ቡድን፣ አገሪቱን እንደ ምርኮ ይዞ ከፍተኛ በደል በህዝቦቿና በሀገር ጥቅም ላይ እያደረሰ ይገኛል፡፡ ይህም ቡድን በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የተዘፈቀውን የሀገርና የውጭ ሀገር ባለሀብት በአካባቢው ይዘ ይጓዛል፡፡
በሌላው አንፃር ደግሞ ኢህአዴግ የተያያዘው የሰፊውን 85% ከመቶ በላይ የሆነውን አርሶ አደሩና የከተማውን ስራ-አጥ ወጣት ህይወት ሲቀይር የማይታየውን የሁለት አሃዝ ልማት አመጣሁ እያለ በተምታታና በተጋነነ ፕሮፖጋንዳ ህዝቡን ማሰልቸት ነው፡፡ በመንግስት ሙሉ ለሙሉ የሚካሄዱትንም በሙስና የተዘፈቁ ግንባታዎች እንደ ትልቅ ተአምር አጉልቶ በማሳየትም የአለምን ለጋሽና አበዳሪ አካላት እይታ ለመሳብ በከፍተኛ የህዝብ ግኑኝነት ተግባር ላይ ተጠምዶ ይገኛል፡፡
በኢህአዴግ ውሎ ትልቁን ስፍራ በያዘው የግምገማ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሏቸው ስራ-አስፈች የሆኑ ስብሰባዎችም ሆነ በማራቶን ድርጅታዊ ስብሰባዎቻቸው ማጠቃለያ መልካም አስተዳደርን ስለማስፈንና ሙስናን ስለማጥፋት ሲምሉና ሲገዘቱ መታየታቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ከይስሙላ አልኩ ባይነት ያለፈ ሆኖ ላለፉት 24 ዓመታት አልታየም፡፡ በዚህ ረገድ አሁን የተቋቋመውም መንግስት በሁለንተናዊ መልኩ ሲታይ ለችግሮቹ መፍትሔ መስጠት የሚያስችለው ቁመና የለውም፡፡ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፣
1ኛ/ የህዝብን ይሁንታ አግኝቶ ውክልና የሌለው መንግስት እንደመሆኑ፣ ህዝብን አስፈራርቶ፣አስገድዶና ዋሽቶ አሳካለሁ ብሎ ያስቀመጣቸውን የህልም ግቦች ሊያሟላ እንደማይቻለው የያለፉት የ24 ዓመታት ተመክሮ ፍንቱው አድርጎ ያሳያል፡፡ የሰውን ልጅ ክብሩንና መብቱን ጠብቆና አሳምኖ እንጂ ከዚያ ውጪ ለውጤት እንዲንቀሳቀስ ማድረግ የሚቻል ያለመሆኑን ማስተዋል ያለመፈለጋቸው ትልቁ የኢህአዴግ ቡድን ድክመት ነው፣
2ኛ/ በኢህአዴግ የማምታቻ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ የህዝቡ ምሬት እጅግ በከፋበት በአሁኑ ወቅት፣ በየመግለጫቸው መጠነ-ሰፊ ችግሮች እንፈታለን፣ ሀገሪቱን
እናለማለን እያሉ መፎከር፣ ኢህአዴግ ባለበት መሰረታዊ ችግሮች ምክንያት የማይሳካ ነው፡፡ ከችግሮቹም ውስጥ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡-
ሀ/ የኢህአዴግ የፖለቲካ መስመር ፀረ-ዴሞክራሲ በመሆኑ ብዙሃኑን አግላይ እንደመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት የብዙሀኑን ህዝብ ይሁንታ ማግኘት የማይቻለው መሆኑ፣
ለ/ ለአዲሱ መንግስታቸው አመራር እንዲሰጥ ያሰባሰቡት የሰው ሀይል ስብጥርም ሲታይ ‹‹የፍራሽ አዳሽ›› አይነት ስብስብ እንጂ ለአዲሱ መንግስታቸው ህይወት የሚሰጥ ‹‹የጀግና መሪያችንን ራዕይ እናስቀጥላለን›› የሚል መፈክር ከማሰማት ያለፈ ብቃት ያለው ሀይል ተጨምሮበት ያለመታየቱ ሌላው ነው፡፡
ኢህአዴግ ይህንን ፍፁማዊ አምባገነን ስርዓት በኢትዮጵያ እያሰፈነ ያለው፣ በሀገራቸው የመድብለ ፓርቲን ስርዓት በመቅበር በህዝባቸው ላይ ፍፁማዊ የአንድ ፓርቲ አምባገነን ስርዓት ጭነው ሲገዙ የነበሩ የሩቅ ምስራቅ ኤሽያ ሀገሮችና የቻይና ተምሳሌት የሆነውንና ለልማት ጠቅሞአል የሚሉትን ስርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለመጫን ነው፡፡ ይህ የእንደ ወረደ ኩረጃቸው የብዝሀዊነት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያ ሊሰራ እንደማይችል ኢህአዴጎች ያለማጤናቸው ለሀገራችን አደገኛ ነው፡፡ ለሀገራችን መዳኛዋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት ብቻ ነው እንላለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በየቦታው የሀገራችንን መሬት፣ ጥሬ ዕቃዎች እና የሰው ጉልበትና ሀብት በእርካሽ በመቀራመት ላይ ያሉት የውጭ ሀገር ባለሀብቶች የሚፈልጉት ጥቅማቸዉን የሚያስጠብቅ መንግስት እንጂ፣የስርአቱ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት እና ኢ-ህዝባዊነት ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይቅርና የሰራተኛ ማህበራት እንኳን ባለመኖራቸው የሚጨነቁ ያለመሆናቸው፣ ለኢህአዴግ የአንድ ፓርቲ ፍጹማዊ አምባገነን መንግስት ለመመስረቱ አደፋፋሪ ዓለምአቀፋዊ ድጋፍን ፈጥሮለታል፡፡
እንደዚሁም ራሱን የዓለም የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠባቂ አድርጎ የሚቆጥረው የአሜሪካ መንግስት፣ ‹‹ሽብርተኝነትን በጋራ ለመለከላከል›› በሚል ሰበብ ከኢህአዴግ ጋር ባደረገው ስምምነት ምክንያት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመን እንዲራዘም ቡራኬ በመስጠቱ እና ሌሎች ለጋሽ አገሮችም ቢሆኑ የአሜሪካንን አቋም በማየት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስቀደም ባላቸው ፍላጎት የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ጥያቄ ትኩረት ያለመስጠታቸው ተጨማሪ አደፋፋሪ ዓለምአቀፋዊ ሁኔታን ፈጥሮለታል፡፡
ነገር ግን የኢህአዴግ መሪዎች ከታሪክ መማር ያለባቸው ትልቅ ሀቅ፣ አንድ ፍፁማዊ አምባገነን መንግስት ከስልጣን ላለመውረድ የህዝቡን ሰላማዊ የትግል መንገድ የዘጋ እንደሆነ፣ ያን ህዝብ ከሚኖርበት አምባገነናዊ ስርዓት በአመፅ ሰብሮ ከመውጣት የሚያግደው
አንዳችም ምድራዊ ሀይል አለመኖሩን ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የኢትዮጵያ ህዝብ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ አፄአዊውን ስርዓትና ሌሎችንም በመገርሰስ አዋርዶ ከስልጣን ያስወገደበት ሁኔታ አኩሪው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ ስለሆነም ኢህአዴጎች የኢትዮጵያን ህዝብ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ መንግስት የማቋቋም ህገመንግስታዊ መብትን በማክበር የከረቸሙትን የሰላማዊ ትግል በር እየከፈቱ ቢሄዱ፣ አገራችንን ከጥፋት፣ ራሳቸውንም ከውርደት ማዳን እንደሚችሉ ሊገነዘቡ ይገባል እንላለን፡፡
በመጨረሻም፣ኢህአዴግ ሀገራችንን በማንአለብኝነት በአንድ አምባገነን ፓርቲ ፍፁማዊነት ለመግዛት የወሰደው አቋምና የፖሊሲ አቅጣጫ በአገራችንና በህዝባችን ሉአላዊነትና ሰላም ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ መድረክን በእጅጉ አሳስቦታል፡፡ ስለሆነም ህዝባችን ይህን ሁኔታ በዝምታ ማለፍ እንደማይገባውና መብቱንና ክብሩን ለማስጠበቅ ኢህአዴግና መንግስቱ ላይ በሰላማዊ አግባብ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናደርጋለን፡፡
በሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ/መድረክ/
መስከረም 27 ቀን 2008ዓም
አዲስ አበባ