ቻይንዬ ቻይንዬ ፣ ቻይኑካ ፣ ቻይንሻ (ሄኖክ የሺጥላ )


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አቶ ኢሳያስ በታዲያስ አዲስ ጋዜጠኞች ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን ቻይና እንደቀጠረ ሲጠየቁ ፣ በፈረንጅኛ እንዲህ ነበር ያሉት <<China is the biggest humanity >> ፣ በመጀመሪያ ይህ አርፍተ ነገር ምን ማለት ነው ? ብሎ መጠየቅ አይቻልም ። ሁለተኛ ምንም ማለት ቢሆን ፣ እነሱ እንደሆነ ቻይና ቀጥረዋል ።

ስለ ደሞዛቸው ሲጠየቁ ደሞ << ያው ባለም ገበያ መሰረት ነው ፣ እነዚህ ሰዎች ባሮች አይደሉም >> ይላሉ ። ምን ማለት ነው ? ኢትዮጵያውያን ሆስተሶች ባሮች ናቸው ማለት ነው ? ወይስ ኢትዮጵያዊ ከዓለም ጠርዝ ዳር ሄዶ ቁጭ ያለ አንደርቢ ነው ? አልገባኝም ።

ስለ ጥቅሙ ሲጠየቁ << ይህ ነገር ቱሪዝምን ያስፋፋል ፣ አበባ ያመጣሉ እና ወዘተ >> ። ባንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ስለ 11 % እድገት ለማስረዳት ፣ ጃፓንን ብናያት ፣ ኮሪያን ብናያት ፣ እንትናን ብናያት ፣ ብናያት ብናያት ፣ ያለው ትዝ አለኝ ።

ቆይ ግን ቻይና ለምን ቀጠራችሁ ምክንያታችሁ ምንድን ነው ሲባሉ << ቻይንኛ የሚናገር ሆስተስ ስለሌለ!>> ይላሉ። ግሩም መልስ ነው ። እስኪ ይህንኑ ጥያቄ ለአዲስ አበባ እና ክፍለሃተ ሃገራት ዩንቨርስቲ ( ወይም ባጭሩ ለትምህርት ሚንስቴር ልጠይቅ ) << ለምንድን ነው የህንድ ሌክቸረር በዩንቨርስቲው ውስጥ የቀጠራችሁት ፣ የራሳችን ሰው ጠፍቶ ነው ? መልስ << የዩንቨርስቲ መምህሮች ህንድኛ ስለማይችሉ >>! እሺ ሌላ ጥያቄ << ለምንድን ነው አብዛኛውን የመንገድ ግንባታ ለቻይና ኮንትራክተሮች ከመስጠት አልፎ ፣ የጉልበት ሰራተኞቹ ሳይቀሩ ከቻይና ተጭነው መጥተው የሚሰሩት ? በኛ ሀገር ለጉልበት ሥራ የሚሆን ሰው ጠፍቶ ነው ? መልስ << መንገዱ ቻይና ካልሰማሁ ፣ መንገድ አልሆንም ስላለ !>>።
እሺ ለምንድን ነው በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ የሩሲያ የጦር ጀት አብራሪዎች እና መምህሮች በአሁኑ ሰዓት ተቀጥረው የሚሰሩት ? << ምክንያቱም ይህንን ሕዝብ በሰማይ ናዳ ( ቦምብ ) ልናፈነዳው ስናቅድ ፣ ቦምቡን በሩሲያኛ ብንወረውረው ገድሉን ማራኪ ስለሚያደረገው ። ሌላ ጥያቄ << አቶ ሰውነት ቢሻውን የተካው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ፣ ምን አዲስ ወይም የተሻለ ነገር አመጣ ? መልስ << ምንም ባያመጣም የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ስለሆነ ታላቅ ፣ ዘላለማዊ ክብር ይሰማናል >>። እና ወዘተ አይነት መሳ ለመሳ የሚሄዱ መልሶች ናቸው ።
ለማንኛውም ፣ ምን ታመጣላችሁ ! የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻይናዊ ሆስተሶች ቀጥሯል ። እነ ከበቡሽ አረብ ሀገር ሄደው ገረድ ይሁኑ ፣ እነ ሮማን ፣ አማሪካ እና አውሮፓ የፈረንጅ ዳያፐር ይቀይሩ ፣ እነ ተሎሳ እና አንቃንቀው በራሳቸው ላይ ቦድነው አንተ አማራ ፣ አንተ ኦሮሞ እያሉ ይቧጨቁ ፣ ሀገርሽን ግን ጉግ ማን ጉግ ተቀባብሎሻል ።

ስለዚህ እንዲህ እንላለን

ቻይና በሰማይ ላይ
ቻይና በምድር
ክንፍ አውጥቶ ሲከንፍ
አየሁት ሲበር ።

ቻይና ጉዱ ካሳ
ቻይንዬ ቴዎድሮስ
በመተከል አርገህ ፣ ኃሙሲት ድረስ !

ቻይና በአላማጣ ፣ ቻይና በጨጨሆ
ውሻ ያበላሃል ፣ እንደ አንበሳ ጩሆ !

ቻይና ነን ፣ ቻይና ነን ፣ ቻይና ነን ያላችሁ
ሳቁ ፣ ሳቁ ፣ ሳቁ ፣ ሳቁ እንያችሁ !

አይናችሁ ሲጨፈን ፣ በፈገግታ ሰክሮ
እናሾፍ ነበር ያኔ ድሮ ድሮ !

አሁንማ ቻይና ፣ ነገሰ ባገሬ
ሺን ሿ እና ኩን ፉ
ያዙት ባለ ክንፉን
በአይናቸው ስቀው ፣ በልብ እያሾፉ !

ቻይንዬ ቻይንዬ ፣ አንቺ የኔ ደርባባ
ሀገሬን ቀማሽኝ
ስራዬን ቀማሽኝ
አረ ወዴት ልግባ ?

አሞራ በሰማይ ፣ አሞራ በምድር
እኛ ብሎ ሀበሻ አቤት ስንደብር !

ቻይንዬ ፣ ቻይንዬ ፣ ቻይኑካ ፣ ቻይንሻ
ሼም የለሽም አሉ ፣ ለኔ አይነት አበሻ !

Henoke Yeshetlla's photo.