ለምንለው ሁለንተናዊ ለውጥ —- ደንቃራ የሆኑት ሌሎቹ ሁለት ጽንፎችና መፍትሄው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Girma Bekele  

ከዚህ በፊት ስለ ‹‹የኢትዮጵያዊነት ብቸኛ ባለአደራዎች›› ና ‹‹ ኢትዮጵያ ሲባል አልስማ ›› ጽንፎች መጻፌ ይታወሳል፡፡ ሌሎቹ ሁለቱ ጽንፎች በአስተሳሰባችንና በተግባራችን የሚስተዋሉት ደግሞ በአንዱ ጥግ ቆሞ ቀርነት/ኋላ ቀርነት ሲሆን በሌላው ጫፍ ደግሞ ጥራዝ-ነጠቅነት ነው፡፡ በትውልድ መካከል ያለውን መሳሳብ ይመስላል እንጂ አንድ አይደሉም፤ ወጣት ‹‹ቆሞ ቀሮቸ››ና አዛውንት ‹‹ጥራዝ ነጠቆች›› ይስተዋላሉና፡፡ ሁለቱም በመጠየቅና በመመርመር ያልታገዙ በዕውቀት ላይ ያልተመሰረቱ ናቸውና እግር ከወርች አስረውን ወደፊት ከመራመድ ከገቱን ውስጥ ይካተታሉ፡፡
ቆሞ ቀርነት/ኋላ ቀርነት፡- ካለፈው የወረስነውን ሳንመረምርና ለዘመናችን በሚሆን መልኩ ሳናሻሽል፣ ሳናጓድል እንደ አደራ ዕቃ በ‹‹ክብር ›› ለማቆየት ሳንነካና ሳናስነካ ይዘን ለመቀጠል/ለመዝለቅ ያለን አስተሳሰብና የምንፈጽመው ተግባር ነው፡፡ አዲሱንና ከእኛ ውጪ ያለውን ሁሉ አፍራሽና አጥፊ አድርገን በክፋት መመልከትና እንዳይደርስብን መከላከል ማለት ነው፡፡ የእኛው ‹‹አይነኬ ››ስለሆነ ተቸካይ ሆኖ መቅረት ነው፡፡


ጥራዝ ነጠቅነት፡- የራሳችን የሆነውን ሁሉ በኋላ ቀርነት ፈርጀን ሙሉ በሙሉ አራግፈን ፤ የሌላውንና ‹‹አዲሱን›› አክብረንና አግዝፈን እንደወረደ (ሳንጠይቅና ሳንመረምር) እንዳለ ተቀብለን በራሳችን ማፈር በሌላው መኩራትና ራሳችንን በውጪው/በሌላው ሚዛን መመዘን ነው፡፡ይህንን በሥልጣኔ ስም ‹‹መሠይጠን›› ልንለው እንችላለን፡፡ አዲሱና የውጪው በሙሉ ጠቃሚና ስልጡንነት ነውና የሚያኮራ ስለሆነ እሴቶቻችን ሁሉ በመናቅ የእነሱን እንዳለ ቃራሚ ማለት ነው፡፡
ተቸክለን ለመቅረታችን፣ ባለንበት ለመርገጣችን በእነዚህ ሁለት ጫፎች ሆነን ‹‹የእኔው ብቻ ነው ትክክል›› በሚል ሁላችንን አሸናፊ የሚያደርገውን አማራጭ ለመመልከት ዓይናችንን ጨፍነን የተያያዝነው የገመድ ጉተታ ነው፡፡


መፍትሄው ሥልጣኔ ማለትም አስተሳሰባችንና ተግባራችንን ማዘመን ነው፡፡ ሁላችንን አሸናፊ የሚደርገውን መንገድ በጋራ መቀየስ፡፡ በዚህ ‹‹ከጥላቻ ፖለቲካ ›› መላቀቅ ይቻላል፡፡
ሥልጣኔ፡- የራሳችንንም ሆነ የውጪውን መርምረን ከራሳችን አርፉን ይዘን- ጎጂውን አራግፈን ፣ ከውጪው የሚጠቅመንን ብቻ ተቀብለን የሚጎድለንን በመሙላት ለእኛ በሚስማማ መንገድ አዋህደን/ቀምመን ‹‹ የተሻለ›› ወደፊት የሚያራምደንን ኃሳብ ቀምረን በተግባር የማዋል ዕውቀትና ጥበብ ነው፡፡
ለሁላችንም ከጽንፎች ወጥተን በመሰልጠን ለሁለንተናዊ ለውጥ ለማበርከት ከቆምንበት የየራሳችን ማማ አርቀን ለመመልከት ብቻ ሳይሆን ተያይዘን ለመጓዝ ብሄራዊ መግባባት ላይ በመድረስ- ላለፈው ዕርቅ አውርደን፣ ለአገራችንና ህዝባችን በአንድነት ለመቆምና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዘላቂና ልማትና ሰላም ፣ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር … በጋራ ለመስራት የጋራ መንገዳችንን በጋራ ባለቤትነት ስሜት ማመቻቸት ነው፣ በአካታችና አሳታፊ የሽግግር መንግስት፡፡ ይህ የማይቻል ሊመስል ቢችልም ‹‹ ይቻላል›› ወይም ለአስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ የግድ መቻል አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ማንም በምንም መንገድ ያለፈውንና ያለንበትን የአሸናፊ/ተሸናፊ ጠቅላይና አግላይ አካሄድ ከመድገም ውጪ የተለየና የተሻለ አስተማማኝ ዘላቂ መፍትሄ ላይ አያደርሰንም፤ያለውም ባለበት አይቀጥልም፣ ረጅም ርቀት አይጓዝም፤ ‹‹ተረኛው›› መሪዎቻችን ከማሳደድና በመቃብራቸው ላይ ቆሞ ከመፎከር ወደ ዕውቅናና ክብር መስጠት አይሸጋገርም፤እኛም ‹‹ይበለው›› ለማለት እንገደዳለን፤ ያለንበት አሳዛኝና አሳሳቢ ሁኔታ በተመሳሳይ አቆራኝ ቀለበት ዙሪያ እንዲሽከረከር ይፈቀድለታል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡


ስለዚህ በዚህ በያዝነው የብሄራዊ መግባባት፣ ዕርቅና የሽግግር መንግስት ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን እስከሚሆንና እስከሚተገበር ከመጮህ ወደኋላ አንልምና ሳንሰለች ደግመን ደጋግመን እንጮሃለን፤ በአገርና ወገን ጉዳይ ተስፋ አይቆረጥምና፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡ 25/01/08