‹‹ቀጣዩ ትግል›› በጋራ አገራዊ አጀንዳ ላይ መቆም አለበት ስንል ፡-‹‹ አሮጌው እንዲሞት ፣ አዲሱም እንዲወለድ እስካልተባበርን የአገሪቱን የወደፊት ብሩህ ሕልም እውን ለማድረግ አንችልም›› ሙሉጌታ ሉሌ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Girma Bekele 
‹‹ቀጣዩ ትግል›› በጋራ አገራዊ አጀንዳ ላይ መቆም አለበት ስንል ፡-‹‹ አሮጌው እንዲሞት ፣ አዲሱም እንዲወለድ እስካልተባበርን የአገሪቱን የወደፊት ብሩህ ሕልም እውን ለማድረግ አንችልም›› ሙሉጌታ ሉሌ

ለዛሬ እንዲህ ልጀምር፡፡ ከዚህ በፊት አንድ ቦታ ላይ ከአንድንድ ‹‹ፓርቲዎች›› ባልተናነሰ ለትግሉ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን አሉ ማለቴን አስታውሳለሁ ፡፡ በእኔ እምነት ከነዚህ አንዱ ያለፉትን 24 ዓመታት ሳይታክትና ሳይደክም አንድነትን ሲሰብክ፣ ስለአገር ፍቅር ሲያስተምር፣ ስለ ስር ነቀል ለውጥ አስፈላጊነትና እንዴትነት ሲተነትን … የስብከቱንና ትግሉን ውጤት ለማየት ሳይታደል በድንገት የተነጠቅነው ዕውቁና አንጋፋው የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ‹‹ አሮጌው እንዲሞት ፣ አዲሱም እንዲወለድ እስካልተባበርን የአገሪቱን የወደፊት ብሩህ ሕልም እውን ለማድረግ አንችልም›› ያለውን በመጥቀስ አንድም ለእርሱ ያለኝን ክብር መግለጫ እንዲሆነኝ ፣ ሌላም በእርሱ ጥቅስ የተለመደውን ጩሄቴን ማሰማት ፈለግሁ፣ በስሙ መጮህ አንዳች የሚጠቅም ከሆነ በሚል ፡፡


ከሰሞኑ ‹‹ለቀጣዩ ትግል›› በፓርቲዎች የሚደረግ ግንኙነት /ትብብር ስንል የብዙዎች ስጋት ሆኖ እንደሚቀርበው በየቱም አንድ ፓርቲ የሚመራና ለየቱም ፓርቲ ፍላጎት ማስፈጸሚያ የሚደረግ ግንኙነት፣ ወይም የፓርቲዎችን መዋቅራዊ ግንኙነት የግድ የሚል ሳይሆን በአንድ ‹‹የአገር ማዳን ስር ነቀል ለውጥ የማምጣት›› የጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተና ይህንኑ ለማስፈጸም የሚደረግ ግንኙነት ማለታችን ነው፡፡ይህ ህወኃትን ጨምሮ ሁሉንም አሸናፊና ተጠቃሚ በሚያደርግ ‹‹አገር አድን አጀንዳ›› ብሄራዊ መግባባት ተደርሶ ፣ ዕርቅ ወርዶ ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ፣ ትክክለኛ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣… የሚሰራ አካታችና አሳታፊ የሽግግር መንግስት መመስረት ነው፡፡ መነሻው አንድም ከዚህ በኋላ በምርጫ ለውጥ የማምጣቱ በር ተዘግቷል በሚለው ላይ በህዝቡና በአብዛኛው ፓርቲዎች ከተወሰደውና ከተገለጸው የጋራ ግንዛቤ፣ እንዲሁም ህወኃት/ኢህአዴግ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አገሪቱን በህገ መንግስቱና በዲሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መንገድ ሊመራት አልቻለም፣ አይችልም፤ በተቃውሞ ጎራውም የቱም አንድ ፓርቲ በተናጠል ለአገሪቱ ችግሮች የሚመጥን መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል አመኔታ ያገኘ አቅምና አቋም የለውም (ይህ እኔ ዛሬ የምለው ሳይሆን በ ‹‹33ቱ›› ጊዜም ሆነ በ‹‹14ቱ ፓርቲዎች ጥናት›› ላይ የተደረሰ የጋራ ግንዛቤ ነው)፡፡ ይህን ሃቅ መቀበል ለሁለቱም ወገን አልፎም ለመላው ህዝባችንና አገራችን የመጥቀሙን ያህል መካድም ‹‹ ቢያንስ ›› የዚያኑ ያህል ጎጂ ይሆናል፡፡


የሽግግር መንግስት ስንል ህወኃት/ኢህአዴግ ጥያቄውን በደስታ ይቀበላል ከሚል የፖለቲካ የዋህነት አልተነሳንም፡፡ ይልቁንም አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግስት ‹‹ ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መዳበር በአገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከሰላማዊ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ምርጫን ሳንጠብቅ ተቀራርበን እንመካከራለን፣እንሰራለን ›› ያሉትን እንዲፈጽሙ በኅብረት ቆመን ተጽዕኖ ለማሳደር/ለማስገደድ የሽግግር መንግስት ምስረታ ለእኛ ዋና ጉዳይና የጋራ ግባችን መሆኑን በመተማመን ለተፈጻሚነቱ የተባበረ ህዝባዊ ትግል በማድረግ የሚመጣ መሆኑን በመረዳትና ‹‹ይቻላል›› ብለን በማመን ነው ፡፡ አይቻልምን ? እንነጋገርበት፣ እንወያይበት//


ከጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ሃሳብ የሚመሳሰልና የሚያጠናክረውን ከዘር አጥር ተሻግረው በመስበክና በመታገል የሚታወቁት አንጋፋው ፖለቲከኛ የተከበሩ ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ ስለትብብር ሲያስረዱ ‹‹ፓርቲዎች/መሪዎች የኪስ ዘውዳችንን በመጣል፣ እንደ ዘር በስብሰን ብዙ ፍሬ እንደሚያፈራው ችግኝ /ቡቃያ ጠንክረን መውጣት አለብን›› ያሉትን ኃሳብ በማስታወስ ኃሳቤን አጠቃለልኩ፡፡ በስብሰን ጠንክረን ለመውጣትና ለአገራችን በምንለው ልክ ለመቆም ቁርጠኝነቱን የኢትዮጵያ አምላክ ያላብሰን፡፡
የጋሽ ሙሉጌታን ነፍስ በገነት ያኑርልን ፡፡ ለአድናቂዎቹ፣ባልደረቦቹ፣ እንደእኔ ላሉ ‹‹ተማሪዎቹ›› ፣ወዳጅ ዘመዶቹና ቤተሰቦቹ ፣እንዲሁም አስተዋጽኦውንና አበርክቶውን በድንገት ለተነጠቅን፣ ለመላው የለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን በእርግጥም አጉድሎብናልና ጽናቱን ይስጠን፡፡ በቸር ያገናኘን//