ውክልና የሌለው “የተወካዮች ምክር ቤት” ! (ይድነቃቸው ከበደ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ለዲሞክራሲ ብርታትና ለእውነተኛ ውክልና ማመላከቻ ነፃ እና ቀጥተኛ ምርጫ ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡ይህ ሲሆን በህዝብ ለህዝብ የተመረጡ ተገቢውን ውክልና ያገኙ፣ የህዝብ ተወካዮችን ማገኘት እና “የተወካዮች ምክር ቤት” አለ ለማለት ከዋና መመዘኛዎች ወስጥ ማመላከቻ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ በዲሞክራሲ አፈና እንዲሁም የውከልና ስብጥር በሌለበት፤ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ባላቸው፣ ለዛውም የሚናገሩት ብቻ ሣይሆና የሚያስቡት ጭምር የአንድ ፋብሪካ ምርት በሚያስመስላቸው ተሰብሳቢዎች መካከል፣ ተገቢ የሆነ የሕዝብ ውክልና አለ ማላት ፈፅሞ የማይቻል ነው ! አለ ከተባለ የእኛው ጉድ የሆነው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” ብቻ ነው፡፡

የተመጣጠነ ውክልና የሌለው !እንዳይኖረውም ሆነ ተብሎ ሲሰራበት የቆየው የተወካዮች ምክር ቤት ፣መስከርም 24 ቀን 2008 ዓ.ም ስራ ጀመረ መባሉ ከዜና ፍጆታ ባለፍ፤ በአገራችን ወቅታዊ ፖለቲካ እንድምታ፣ ዉሃ ቢወቅጡት እንቦጭ አይነት ነገር ነው፡፡ህውሓት/ኢህአዴግ ካለምንም የሃሳብ ልዩነት አጨብጭበው እና እጅ አውጥተው እንዲሁም እጅ ነስተው በአንድ ድምፅ የሚደግፉ ወይም የሚቃወሙ፣ ተሰብሳቢዎች መሰብሰባቸው የድርጅቱ የመጨረሻ ትልቁ ግብ አድርጎት ይሆናል፣ በዲሞክራሲ ሥርዓት ሂደት ግን በምንም የማይጣፋ ትልቅ ኪሣራ ነው፡፡

አሁን ስራውን ጀመረ የተባለው የተወካዮች ምክር ቤት “እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን” ወይም “ከሕዳሴው ጉዛችን ለአፍታም አንቆምም” ሌላው ደግሞ “የታላቁ መሪ……….” እና የመሳሰሉ ልማታዊ እና ድርጅታዊ ቅርፅ ያላቸው ንግግሮች፣ ከሰብሰባ መጀመሪያ እና መጨረሻ በንቃት እና በታታሪነት ከማሰማትና ከማሳየት ያለፈ፣ የተሰብሳቢዎቹ ከፍ ያለ ሚና ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም፡፡እርግጥ ነው ለእነሱ በታማኝነት ይሄን ማድረጋቸው ማረጋገጥ ከሥራም በላይ ሥራ ነው !

እኔ የተመረጥኩት የህውሓት/ኢህአዴግ አባል በመሆኔ፣ድርጅቴም ባደረገው የምርጫ ማጭበርበር ትጋት ታክሎበት ነው፡፡ይሁን እንጂ ከእውነት እና እውነትን በተግባር ለማዋል “ከህሊና” በላይ አለቃ የለኝም ! የሚል ለህሊናው ያደረ አንድ ወይም ሁለት ምን-አልባትም ከዚህ በላይ ከእነሱ መካከል “ሰው የሆነ ሰው !” ከተገኘ እሱን ውይም እሷን ምን አልባትም እነሱን ለማየት ፤ እኛም እሰይ ፣ደግ አደረጋችሁ ብለን ለመመስከር ያብቃን ብሎ መመኘት ክፋት የለውም፡፡ ግን የማይመስል ነገር እንደሆነ ልቤ ይነግረኛል፡፡

5ኛ የሕዝብ ተወካዮች መስራች የምክር ቤት ስብሰባ ላይ የመንግስታቸውን የቀጣይ የፖለቲካ አቅጣጫን ለማመላከት የተገኙት ፕሬዝዳንት ፣የህውሓት/ኢህአዴግ የተለመደው ድርጅታዊ ዲሱኩር በፁሑፍ እና በቃል ከማነብነብ ያለፈ ለሕዝብ እና ለአገር የሚጠቅም አቅጣጫ ማመላከት አልተቻላቸውም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ድርጅታቸው የቆመለት ዓላማ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ለዚህም ነው ውክልና የሌለው “የተወካዮች ምክር ቤት” የሚያስብለው፡፡

አንድ ቀን ሙሉ በተካሄዴው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ፣ በጓዳ ያለቀውን የሹመኞች የሥልጣን ክፍፍል ፣በአደባባይ እውቅና ለመስጠት የተደረገ የማስመሰያ ስብሰባ ለመሆኑ ብዙ ማመላከቻ ማቅረብ የሚያዳግት አይደለም፡፡በዚህ አጋጣሚ የሰብሰባውን ሂደት ለተከታተለ ከብሔራዊ መዝሙር አዘማመር ፣የስበሰባው አጀንድ ቅደም ተከትል፣የመድረከረ አመራር፣ውሳኔ/ድምፅ አሰጣጥ እንዴት መላ ቅጡ እንደጠፋባቸው፤ በእነሱ ቲቪ የእነሱ ውርደት ! “ያየንበት ሁኔታ ላይ እነገኛለን”፡፡

በተለይ ደግሞ ታማኝ አገልጋይ መሆናቸውን ለማስመስከር፣ ደፋ ቀና የሚሉት ጋዜጠኛ ነን ባዮች ፣የስብሰባው ሂደት ከተሰብሳቢዎችሁ በላይ የጉዳዩ ባለቤት እንደሆኑ ጭምር ለማመላከት ያደረጉት ጥረት ፤የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር እና ጋዜጠኝነት በእነሱ ዘንድ ዉሃ የበላው ጉዳይ ለመሆኑ ጥሩ ማሣያ ሆነው ታይተዋል፡፡

ይድነቃቸው ከበደ (24/1/2008 ዓ.ም)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!