ስምን ተግባር ሲያወጣው (ጌታቸው ሺፈራው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አንድ ጓደኛዬ የሚከራይ ቤት ጠይቅልኝ ብሎኝ ወደ አንድ ደላላ ዘንድ አቀናሁ፡፡ በቦታው ስደርስ ቀጫጫውን ደላላ አንድ ወፍራም በግምት 40 አመት እድሜ ያለው ጎልማሳ ይዞ ጠምዝዞ ያስጮኸዋል፡፡ ‹‹አይለምደኝም!›› ያሰኘዋል፡፡ ሰው እያየ አልፎ ይሄዳል፡፡ እኔም ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ እስኪለቀው ድረስ ቆሜ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ጥሩ ውሳኔ ነው የወሰንኩት፡፡ ሲለቀው የደላላው ፊት ቀልቷል፡፡ ንዴት ይታይበታል፡፡ አቅመ ቢስነትም ጭምር፡፡ ጉልበታሙ ሰው ደላላውን እንዲያ ቀጥቶም ቢሆን ዝም አላለውም፡፡ ይዝትበታል፡፡ እንደገና ተመልሶ ሊይዘው ይቃጣል፡፡ ተመልሶ ድንጋይ ይወረውርበታል፡፡ ደላላው ሮጦ ከዚህ ሰው ይርቃል፡፡ ጉልበታሙ ሰው ጮክ ብሎ እየተሳደበና እየፎከረ ሲሄድ ወደ ደላላው ቀርቤ ለምን እንዲህ እንደሚያደርገው ጠየኩት፡፡ መቼም ሰው እንደዛ ተጠምዝዞ፣ ፊቱ ቀልቶ፣….. ‹‹የሚከራይ አንድ ክፍል፣ ለአንድ ሰው ብቻ…….ጠበብ ያለች ቤት አለህ?›› ብሎ መጠየቅ ይከብዳል፡፡ ራስ ወዳድነትም ነው፡፡

እናም በቅርቡ ስለተከሰተው ነገር ብቻ ጠየኩት፡፡ ‹‹ምን አድርገኸው ነው እንዲህ የሚያሰቃይህ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ባክህ ተወው!›› አለኝ በንዴት፡፡ ተጎጅው እኔንንም ሳይናደድብኝ አልቀረም፡፡ በእርግጥ ማስለቀቅ ይችል ነበር ብሎ አይመስለኝም፡፡ ከእኔ በላይ ያውቀዋላ! እኔም ከእሱ በላይ ቀጫጫ ነኝ፡፡ ከተረጋጋ በኋላ እንደነገረኝ ደላላው ከዚህ ሰው ጋር በእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ በሚደረግ ጨዋታ ተወራርደው ኖረዋል፡፡ በእርግጥ ደላላው እንደሚለው እንወራረድ ብሎ ያስገደደው ይህ ጎልማሳ ነው፡፡ ደላላው ይሸነፋል ያለውን ቡድን ጎልማሳው ሰው ይደግፈዋል፡፡ ግን ደላላው ያለው አልቀረም ያ ቡድን ተሸነፈ፡፡

የውርርዱን ገንዘብ ካስያዙ በኋላ ይህ ጉልበታም ሰው ከገንዘብ ያዡ ተቀብሎታል፡፡ ገና ቡድኖቹ ሳይሸናነፉ፡፡ አሁን ደላላውን እንዲህ ጠምዝዞ የሚያዛዛው ‹‹ይሸነፋል›› ያለው ቡድን በመሸነፉ ነው፡፡ እንግሊዝ ውስጥ የሚገኘው ቡድን የተሸነፈው አንተ አሟርተህበት ነው ብሎ ነው የሚያሰቃየው፡፡ ‹‹አይለምደኝም!›› ያሰኘውም ዳግመኛ ይሸነፋል ብሎ ‹‹እንዳያሟርት›› ነው፡፡ ምስኪን ገንዘቡንም፣ ዱላውንም ቀመሰ፡፡ ማሟረት ብቻ ሳይሆን እሱ የሚደግፈው ቡድን ታሪካዊ ባላንጣ ነው ያለውን ቡድን ቲሸርት የለበሰውን ሁሉ በክፉ አይን ነው የሚያየው፡፡ የባላንጣ ቡድንን ቲሸርት ለብሶ የተገኘ ህፃን ሳይቀር ‹‹አሁን አንተ ምን አባህ አውቀህ ነው? አያሳድግህ! ገና ስታድግማ….›› እየተባለ ይኮረኮማል፡፡ ጭራሽ በጨዋታ ላይ እሱ የሚደግፈው ቡድን ላይ ጎል ሲገባ ከአጠገቡ ሆኖ የጨፈረ እንደ ወቅቱ ሁኔታ የሚገባውን ቅጣት ወዲያውኑ ይወሰንበታል፡፡ ቦክስም፣ ጥፊም…..ብቻ እንደ ሁኔታው፡፡

ይህን ምስኪን ሲያሰቃይ ቆይቶ የሄደውን ሰው ከአስፓልቱ ማዶ አንድ ሰው ባልተለመደ ስም ጠራው፡፡ ይህን ስም በሀገራችንም አንድ ቡድን ብቻ ነው የሚጠራበት፡፡ ጉልበታም ቡድን፡፡ ምስኪኑ ሰው ላይ ካደረገውም በላይ ስሙ ስቦኛል፡፡ የሚገርም ስም ነው! በዛው አስታክኬ ደላላውን ጠየኩት፡፡ እንዴት በዚህ ስም ሊጠራ ቻለ? በውል አያውቀውም፡፡ ‹‹እኔ እንጃ ሁሉ ሰው ነው እንዲህ የሚጠራው፡፡ ማን እንዳወጣለት አይታወቅም፡፡ እብድ ነገር ነው፡፡ እኔን ብቻ መስሎህ ነው?! ኧረ ስንቱን ነው የሚያስለቅሰው….›› እሱም ለማልቀስ እየቃጣው ነው፡፡ ሆድ ብሶታል፡፡ የተጠመዘዘውን እጁንና አንገቱን ያሻል፡፡

ማን አወጣለት? ለምን ወጣለት? ለሚለው በቀጥታ ቁርጥ ያለ መልስ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ ስለ ባህሪው ቢያወራኝ ይሻላል ብዬ ምን አይነት ሰው እንደሆነ ጠየኩት፡፡ ምን አልባት ስሙ ከባህሪውና ከተግባሩ የመጣ እንደሆነ በሚል ነው፡፡ ይህ ጉልበታም ሰው እውነትም እንደ ቅፅል ስም ተጀምሮ አሁን ዋናውን ስሙን ያስረሳው የ‹‹የጉልበታም ቡድን›› መጠሪያ ስም ይገባዋል፡፡

ይህ ጎልማሳ በአካባቢው በሆነ ባልሆነው ምክንያት ፈልጎ የሚደባደብ፣ የሚዝት፣ ገንዘብ የሚቀበል (የሚቀማ) ሰው ነው፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ባህሪው ያው ነው፡፡ በዚህ ባህሪው በትምህርቱም ከአንደኛ ደረጃ በላይ አልገፋበትም፡፡ ሴት ወንድ፣ ህፃን አዛውንት ሳይል የሚያሰቃይ፡፡ ወደ ሱቅ ከተላኩ ህፃናት ሳይቀር ገንዘብ የሚያጭበረብርና የሚቀማ ‹‹ታዋቂ›› ሰው ነው፡፡ ሲጋራ፣ ጫትና የመሳሰሉትን የሚሸጡ አይመስሉትም፡፡ ሳይከፍል ይወስዳል፡፡ በፈቃደኝነት ‹‹እኔ ከፍያለሁ!›› የሚል ‹‹ጋባዥ›› ከሌለ በቀር፡፡

በግድ እንወራረድ ይልና ራሱ ገንዘብ ያዥ ይሆናል፡፡ ከእኔ ግምት በላይማ አይሆንም ብሎ ገንዘቡን የራሱ ያደርገዋል፡፡ ገና የውርርዱ ውጤት ሳይታወቅ ገንዘቡን ይወስዳል፡፡ ሳይጠናቀቅ ያሸንፋል፡፡ ከፈለገም ወስዶ ‹‹አላየሁም! ሰጥተኸኛል?!›› ብሎ መዓት ያወርዳል፡፡ የአብዛኛው ሰው መልስም ‹‹ቀልዴን ነው! ይቅርታ! ይመችህ! ኧረ ውሰደው! 300 ብር እኮነው፣ 100 ብር ምን አላት?›› ነው፡፡ በፍርሃት የሚጨምርለትም አለ፡፡ አንዳንድ ደረቆች ብቻ ተጋፍጠው ስቃያቸውን ይበላሉ፡፡ ያለ ገላጋይ፡፡ የቅርብ ጓደኛ እና የሚያውቃቸው ሁሉ ሲደበደቡ፣ ሲጠመዘዙ፣ ሲሰደቡ፣ ሲሮጡ እያየ እንዳላየ ያልፋቸዋል፡፡ ማን ከእሱ ጋር ተወራረዱ አላቸው ተብለው ቅልብልብ፣ ቅሌታም ተደርገው ይሰደባሉ፡፡ አርፈው ቁጭ አይሉም እያለ ይወቅሳቸዋል አልፎ ሂያጁ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ‹‹የት አባቱ በለው!›› እያለ ለጉልበታሙ ሽፋንና የ‹‹ሞራል›› ድጋፍ ይሰጣል፡፡ እሱ እብድ መሆኑ እየታወቀ እነሱ እብድ ተብለው ይወረፋሉ! ተደብዳቢው ጉልበታሙን ሰው ያላለውን እንዳለ አድርገው በፈቃደኝነት የሚመሰክሩም አይጠፉም፡፡ ይህ ሰው በስጋትም ቢሆን ብዙ ‹‹ደጋፊ›› አለው፡፡ ለመደብደብ ቀድሞ የሚከላከል፡፡ ጉልበቱ ያስገኘለት! ዛሬ ተደብድቦ ሌላው ሲደበደብ ‹‹በለው! በለው!…. ምን አቅለበለበው ወትሮስ?!›› የሚለው ይበዛል፡፡ እሱ ላይ የሆነውን ረስቶ!

አባትን ከልጁ ፊት፣ ወጣቱን ከፍቅረኛው ፊት፣ አሰሪን ከሰራተኛው ፊት….የሚያዋርድ፣ የሚዘልፍ፣ የሚጠመዝዝ፣ የሚቀማ ሰው ነው፡፡ ምግብ ቤት ገብቶ በልቶ የሚከፍልለት ሌላው ሰው ነው፡፡ ካልሆነም አስተናጋጆቹ በፍርሃት እየሳቁ ይከስራሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ‹‹ከእሱ ተቀበይው!›› ይባላሉ፡፡ ክፍል የተባለው ሰው እስከነ ‹‹ቲፑ›› ይከፍላል፡፡ ሰውዬው እያለ ከከፈለ ግን መልሱ የዛ ጉልበታም ሰው ነው፡፡ እራሱ እንደከፈለ መልሱን ይወስዳል፡፡ አጅሬ ዋዛ? መጠጥ ቤትም ገብቶ ተመሳሳይ ነው፡፡ አንዳንዴ ቢራም አስከፍቶ ‹‹አይጣፍጥም! ውሰድ! ውሰጅ!›› ሊል ይችላል፡፡ ልክ እንደ ሻይ፣ ወይንም ቡና እዛው ቤት ካዘዘው ውጭ የተሰራበት ይመስል፡፡

ምንም ያላደረገውን ሰው ከምንም ተነስቶ በድሎኛል እያለ ያስወራል፡፡ ሲያገኘው አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣው ይናገራል፡፡ ታዲያ ይህ ‹‹ወንጀለኛ›› ቶሎ መጥቶ ሰውዬውን ማባበል አለበት፡፡ የሚከፈለውን ከፍሎ ነፃ መውጣት የግድ ነው፡፡ ከቅጣት (ድብደባ) ለመዳን! ቢያንስ ለትንሽ ጊዜ ጓደኛው ይሆናል፡፡ ይላላካል፡፡ በየ መጠጥ ቤቱ፣ በየ ጫት ቤቱ እሱን አጅቦ ይዞራል፡፡ በእርግጥ እሱን የተከተለ ሁሉ ስልጣን አለው፡፡ እሱን ወክሎ ሌላ ሰው ያስከፍላል፣ የእሱን ያህል ባይሆንም በአቅሙ ሰው ላይ ደስ ያለውን ያደርጋል፡፡ በስሙ ይሰራበታል፡፡ እስኪጣላው ድረስ፡፡ ሲጣላው ከጉልበታሙ ሰውም ዱላን፣ ከቀሪውም ጥላቻን መቀበል የግድ ነው፡፡ ከባለ ጊዜው ሰው ጋር ሆኖ ብዙ ሰው አሰቃይቷልና፡፡

ይህ ጉልበታም ሰው ፊት ለፊቱ እየሄደ ያለን ሰው ከኋላው ጠርቶ ‹‹ምን አባህ ታየኛለህ?!›› ቢል ‹‹ብልጥ›› የሆነ ‹‹ያየበትን›› መልካም ምክንያት ማቅረብ አሊያም የፀባይ ማብረጃ ከፍሎ መገላገል ነው፡፡ የእኔ ቢጤ አዲስ ወይንም አንዳንድ ደረቅ ግን ‹‹እንዴት ከኋላዬ ሆነህ አይሃለሁ!›› ቢል አይቀጡ ቅጣቱን ይቀበላል፡፡ ያው ሰው እያየ ያልፈዋል፡፡ ፖሊስም ቢሆን፡፡

ሰውዬው የ‹‹ደንብ›› አስከባሪዎቹም፣ የደላላዎቹም፣ የታክሲ ረዳቶችም፣ …አለቃ ነው፡፡ ወይንም ባልደረባ፡፡ ስለሆነም ሳይሰራም ቢሆን ይከፈለዋል፡፡ ከፈለገ ደርሶም ያዝባቸዋል፡፡ ለስሙ ከፖለስ ጋርም ይሰራል፡፡ ፖሊስ አጣሁት ያለውን ሰው ‹‹አፈላልጌ አመጣዋለሁ!›› ብሎ ቃል በገባው መሰረት እየደበደበ ፖሊስ ጋር ያቀርባል፡፡ ወንጀለኛ የተባለውን ባያገኘው እንኳ ‹‹ይኸም ያው ነው፣ ጓደኛው ነው፣ የአክስቱ ልጅ ነው፣ አረማመዱ እሱን ይመስላል….›› ብሎ ለፖሊስ ባለውለታ ለመሆን አንዱን ምስኪን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ፖሊስ ሰረቀ ብሎ የሚደበድበውን እሱም ተደርቦ ይደባደባል፡፡ እናም ከፖሊስም ጋር እጅና ጓንት ነው፡፡ ለዚህ ስራው የፈለገ ቢያደርግ ማንም አይጠይቀውም፡፡

ይህ እየቀማ፣ እያጭበረበረም፣ እየደበደበም የሚኖር ሰው ሌላውን ወንጀለኛ አድርጎ ይቀጣል እንጅ አይቀጣም፡፡ ሲፈልግም አዳዲስ ቅጣት የሚለውን እየቀጣ ‹‹እንትናንኮ እንዲህ አደረገው!›› እያስባለ ያስወራል፡፡ የራሱ የሆነ ህግም ያወጣል፡፡ በተከታዮቹ ዘንድ ያስፈፅማል፡፡ አሊያም ፈፅሞ ‹‹ህግ ነው!›› ካለ አይደለም የሚል፣ የሚቃወምም የሚተች አይገኝም፡፡ አሊያም ‹‹የዋጋውን ያገኛል››፡፡ እሱ አዛዥ ናዛዥም ነው፡፡ መሃሪም ቀጭም እሱ ነው!

ይህ ሰው ነው እንግዲህ አንዱን ምስኪን እጁን ጠምዝዞ፣ አንገቱን አንቆ ሲያሰቃየው የደረስኩት፡፡ አለመገልገሌ፣ ወይንም አስተያየት አለመስጠቴ፣ አለመቅረቤም ጠቀመኝ እንጅ፡፡ የዚህ ጉልበታም ሰው ሰለባ ሲሆን በአይኔ ያየሁት ሰው እንደተረከልኝ ያ ሰው ስሙ ይገባዋል፡፡ ስሙን እናቱ ያወጣችለት አይደለም፡፡ እናትማ መላዕክ የሚያወጣውን ስም ነው የምታወጣለት፡፡ በእርግጥ አሉታዊ የሆነ ስምም ሊወጣ ይችላል፡፡ ይህን ለዚህ ሰው ማንም አያወጣለትም፡፡ የዚህን ሰው ስም ያወጣለት ተግባሩ ነው፡፡ እሱም አያውቀውምና አይቃወምም፡፡ ቢያውቀውም በመልካም ስምነቱ ነው የሚያውቀው፡፡ ማንም የማያዘው፣ ሰርቆ የማይታሰር፣ ታሳድቦ የማይገሰፅ፣ ተደባድቦ የማይገረፍ፣ በልቶና ጠጥቶ የማይከፍል አምባገነን፡፡ ማን አለብኝነት የወጠረው ሰው፡፡

ለዛም ነው ከአስፓልቱ ማዶ ያለው ሰው ሲጠራው የገረመኝ በሀገራችን አንድ ቡድን የሚጠራበት ስም አሁን ይገባዋል የምለው፡፡ ገዥው ፓርቲ! ኢህአዴግ የሚባል አንድ ቡድን የሚጠራበት ስም፡፡

‹‹ገዥው ፓርቲ! ገዥው ፓርቲ! ኧረ ገዥው… ገዥያችን…..››

እየተባለ አልፎ ይምዘገዘጋል! ከአስፓልቱ ማዶ ቢጠራ፣ ቢጠራ አይሰማም፡፡ ምን አልባት የሚደበድበው ሌላ ምስኪን ይኖረዋል፡፡ ነገሩ የሚደባደብበት ጡንቻ፣ እና የሚጮህበት አፍ እንጅ ጆሮ የት አለውና ይሰማል?

‹‹ገዥው ፓርቲ›› የዛ ተደባዳቢ ሰው ስም ነው፡፡ የአባቱን ስም ሳይጨምር!