ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ላገራቸው ሲሉ የሞትን ዕዋ የተቀበሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ታላቁ ያገር ባለውለታ ጄኔራል መኮንን

Achamyeleh Tamiru's photo.

በ1927 አመተ ምህረት በበለሳ ወረዳ በሊቦ አውራጃ በጎንደር ክፍለ ሀገር ተወለዱ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት አጠናቀቁ። በ1945 አመተ ምህረት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ተቀጥረው ለአንድ አመት ያህል የሬድዮ መገናኛ ትህምርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ወደ በረራ ትምህርት ቤት ተዛውረው በዚ

ህ ዘርፍ ባገኙት የላቀ ውጤት የ«ፌሪ ትሮፌ» ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል።

ከዚያም በአሜሪካን አገር ሴንት ሉዊ ዮኒቨርሲቲ በኤሮኖቲክል አድሚኒስትሬሽን የባችለር ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ባገኙት ከፍተኛ ውጤት የዩኒቨርሲቲው የክብር ተማሪ በመሆን በማኔጅመንት ሳይስን ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። በትራንፖርት ስኳድሮን በበራሪነት ሰርተዋል። በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ በብዙ ቦታዎችና የኃላፊነት ደረጃዎች ተዘዋውረው ሰርተዋል። በበረራ አስተማሪነት ከማገልገልም በላይ ከአነስተኛ ተዋጊና የመጓጓዣ አውሮፕላን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ዘመናዊ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ያበረሩ የአቬሽን መኮንን ነበሩ።

በ1967 በሁለተኛ አየር ምድብ አዛዥነት፤ በ1969 በአንደኛ አየር ምድብ አዛዥነት፤ በሶማሊያ ወረራ የድሬድዋ ቀጠና የአየር ዘመቻ አስተባባሪና የበላይ አዛዥ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሆነው ሰርተዋል። በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ የሰላሳ አራት አመታት ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ ስመጥር የአቬሽን ጀኔራል መኮንን በመሆናቸው የስራ ችሎታቸውና የረጅም ዘመን አገልግሎታቸው ተገናዝቦ «የረጅም ዘመን የአገልግሎት ኒሻን የኢትዮጵያ የመኮንን ደረጃ«፣ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኒሻንና የየካቲት ስድሳ ስድስት ኒሻን ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።

ጄኔራል መኮንኑ ግንቦት 8 ቀን 1981 አመተ ምህረት

በመንግስቱ ኃይለማርያም ላይ ተሞክሮ የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማቀነባበር ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ታሪካቸው ያስረዳል። ጄኔራል መኮንኑ መፈንቅለ መንግሥቱን የጠነሰሱት በ1977 አመተ ምህረት ክረምት ላይ በተካሄደው «ዘመቻ ባህረ ነጋሽ» ወቅት እንደነበር መፈንቅለ መንግስቱ ከከሸፈ በኋላ ለምርመራ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል። ዘመቻው ምዕራባዊውን የኤርትራ አውራጃዎች ከሻዕቢያ [EPLF] ነጻ የማውጣት ዓላማ ነበረው። በዘመቻው የኢትዮጵያ ጦር ድል ቢቀዳጅም የተከፈለው መስዋእትነት ከተጠበቀው በላይ ሆኖ ተገኘ። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች [በተለይም በአንደኛው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ፕሮግራም የዘመቱ] አለቁ። ጄኔራል መኮንኑ የዚህ አሳዛኝ ትራጄዲ መንስኤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በሀገራቸው የጦር መኮንኖች የተወጠነውን የዘመቻ ስትራቴጂ በመግፋት ከሶቪየት ህብረት አማካሪዎቻቸው የተሰጣቸውን እቅድ መተግበራቸው ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ።

በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ የነበሩት እኒህ ጄኔራል መኮንን የዘመቻ ባህረ ነጋሽን ውጤት ሲሰሙ «ይህ ሰውዬ ዘወትር እኛን እየገፋን የሀገራችንን ወጣቶች እንደ ማገዶ እንጨት የሚቆጥሩትን የሶቪየት አማካሪዎችን ሃሳብ የሚተገብረው ለምንድነው? በዚህ ዓይነትስ እስከ መቼ ልንዘልቅ ነው?» እያሉ መፍትሔ የሚሉትን ማሳላሰል ጀመሩ። ብዙ አውጥተው ካወረዱ በኋላ መፍትሄው ሰውዬውን ማስወገድ ብቻ እንደሆነ አመኑ። የታያቸው መፍትሔም በከፍተኛ መኮንኖች የሚመራ መፈንቅለ መንግሥት በመንግስቱ ኃይለማርያም ላይ ማካሄድ እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ደረሱ።

ጄኔራል መኮንኑ ኩዴታውን በጸነሱሱበት ማግስት ሶስት ከፍተኛ መኮንኖችን በጉዳዩ ላይ በማወያየት ስምምነታቸውን አገኙ። እነርሱም ሜ/ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ [የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም]፣ ሜ/ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ [የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ] እና ሜ/ጄኔራል አበራ አበበ [በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ] ነበሩ። አራቱ ጄኔራሎች እቅዳቸውን ለተወሰነ ጊዜ በሚስጢር ይዘውት ቆዩ። ይሁንና ሁለት አደገኛ ሀይሎች ሚስጢሩን አገኙት። እነርሱም ኬጂቢ የተሰኘው የሶቪየት ህብረት የስለላ ተቋም እና የደህንነት

ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ናቸው። ኩዴታ ሊደረግባቸው እንደሆነ መረጃው የደረሳቸው ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃይለማርያምም ምንም እንኳ ኩዴታው ጎላ ብሎ ባይታያቸውም ጄኔራል መኮንኑን ግን «እንዲያው ለምናልባቱ» በሚል ከአየር ሀይል አዛዥነታቸው አንስተው “የኢንዱስትሪ ሚኒስትር” አድርገው ሾሟቸው።

ማክሰኞ ግንቦት 8/1981አመተ ምህረት የቁርጥ ቀን ሆነ። ጄኔራሎቹ በመጋረጃ ጀርባ ለአራት ዓመታት ሲያንከባልሉት የነበረውን የመፈንቅለ መንግሥት ሀሳብ በዚህ ቀን ወደ ድርጊት ሊቀይሩት ተነሱ። በእለቱ ወደ ጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ [ምስራቅ ጀርመን] የሚጓዙትን ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ከሸኙ በኋላ እኩለ ቀን ላይ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ተገናኙ። ጄኔራል መኮንኑ በወቅቱ በአዲስ አበባ ይገኙ የነበሩትን ዋና ዋና የጦር መኮንኖች ሰበሰቡና ስለመፈንቅለ መንግሥቱ ነገሯቸው።

ጄኔራል መኮንኑ ሰብስበው ስለስዒረ መንግስቱ ሊነግሩ ከሰበሰቧቸው ጄኔራሎች በስተቀር በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ የነበረ የደርግ ሰው ስለስብሰባው ያወቀው ነገር አልነበረም። ይሁንና ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የጄኔራሎቹን ጉዳይ ስራዬ ብሎ መከታተል የጀመረው የደህንነት ሚኒስትሩ ስብሰባው “የመፈንቅለ መንግሥት አድማ” እንደሆነ ወዲያውኑ ነበር ያወቀው። ለዚህም የረዱት ሶስት ነገሮች ናቸው። አንደኛ ጄኔራል መርእድ ንጉሤ [ኤታማዦር ሹሙ] በጠዋቱ የፕሬዚዳንት መንግሥቱ አሸኛኘት ፕሮግራም ላይ መገኘት ሲኖርባቸው አልተገኙም። ሁለተኛ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሜጀር ጄኔራል ሀይለ ጊዮርጊስ ሀብተ ማሪያም በስብሰባው ቦታ አልነበሩም። በመሆኑም መከላከያ ሚኒስትሩ ያልተሳተፉበት ስብሰባ የርሳቸው እውቅና እንዳልነበረው ለደህንነት ሚንስትሩ ታይቶታል። ሶስተኛ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት ጄኔራል መኮንን በስብሰባው ላይ ተገኝቷል። በወቅቱ ሲቪል የነበሩት ጄኔራል መኮንን በዚያ ቦታ መገኘታቸው ለደህንነት ሚኒስትሩ አንድ ፍንጭ ሰጥቷል።

የደህንነት ሚኒስትሩ እነዚህን ነገሮች ካገናዘበ በኋላ በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በረረና የደረሰበትን ሁሉ የፕሬዚዳንቱ ልዩ ረዳት ለነበረው ሻምበል መንግሥቱ ገመቹ ነገረው። ሁለቱ ሰዎች በነገሩ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ከተማከሩ በኋላ የመከላከያ ሚኒስትሩን አስጠርቶ መጠየቅ እንደሚበጅ ከስምምነት ላይ ደረሱ። በዚሁ መሰረት ሚኒስትሩ ተጠርተው ሲጠየቁ ስለስብሰባው የሚ

ያውቁት ነገር እንደሌለ ተናገሩ። ሁለቱ ሰዎችም [ሻምበል መንግሥቱና ኮ/ል ተስፋዬ] እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ሚኒስትሩ ወደ መከላከያ ሄደው ተሰብሳቢዎቹን ቢያነጋግሩ የተሻለ እንደሚሆን ሀሳብ አቀረቡ። ሚኒስትሩም ከአንዴም ሁለቴ መኪናቸውን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እየነዱ ተሰብሳቢዎቹን ለማነጋገር ሞከሩ። ይሁንና በሁለቱም ጊዜያት ከተሰብሳቢዎቹ ዘንድ ለመድረስ አልቻሉም። ይባስ ብሎም የመፈንቅለ መንግሥቱ የዘመቻ መኮንን ተብሎ በተመደበው ጄኔራል አበራ አበበ ተገደሉ።

የጄኔራል ሀይለ ጊዮርጊስ [መከላከያ ሚኒስትሩ] መገደል መፈንቅለ መንግሥቱ ጥርጣሬ ብቻ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ድርጊት ሆነ። ከዚህ ክስተት በኋላ የዘበኛውን ቱታ አስገድዶ በማስወለቅ ይለብስና ዘበኛ መስሎ ጄኔራል አበራ ከቢሮ ውስጥ ለተሰበሰቡት ጄኔራሎች አድራሻውን ሳያሳውቅ ከግቢው በበር በኩል ወጥቶ ተሰወረ። ቤተ መንግሥቱን የሚጠብቀው የልዩ ጥበቃ ብርጌድም [በተለምዶ አጠራር «ቅልብ ጦር» የሚባለው] ሳይታሰብ የመከላከያን ግቢ በታንክና በብረት ለበስ ከበበው። ከአስመራ በነጀኔራል ደምሴ ቡልቶ አዲስ አበባ ያሉትን መፈንቅለ መንግስት አድራጊ ጄነራሎች ለመርዳት የተላከው የአየር ወለድ ጦርም ለመሪው ለጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ ጥርት ያለ አመራር ስላልተጠው በነመንግሥቱ ገመቹና ተስፋዬ ወ/ሥላሴ በቀላሉ ተጠለፈ። ይሄኔ በመከላከያ ግቢ «ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ» ሆነ። ለጥበቃቸው አንድ ሻምበል ተጠባባቂ ጦር እንኳ ያላዘጋጁት ጄኔራሎች ተዋከቡ። እዚያው ቡድን አበጅተው መጣላት ጀመሩ። «የህጻን እቅድ አውጥታችሁ እንድናንቦጫረቅ አደረጋችሁን» ተባባሉ።

ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ሁሉም ነገር ያበቃለ

ት መሰለ። ለግማሽ ቀን ያህል መከላከያን ከበው የዋሉት የቅልብ ጦር ኮማንዶዎች ወደ ግቢው መግባት ጀመሩ። በዋናው ህንጻ ላይ ወዳለው የሚኒስትሩ ቢሮ ሲደርሱ አስራ ሁለት ጄኔራሎች ተቀምጠው በስጋት ዓይናቸውን ሲያቁለጨልጩ አገኟቸው። ሁሉንም አውጥተው ለሻምበል መንግሥቱ ገመቹ አስረከቧቸው።

ሻምበል መንግሥቱ የተያዙትን ሰዎች ትክ ብሎ ሲያይ አራት መኮንኖች ከጄኔራሎቹ ቁጥር መጉደላቸውን አረጋገጠ። ለኮማንዶዎቹም «እያንዳንዱን ክፍል እየከፈታችሁ ፈትሹ» የሚል ትዕዛዝ ሰጣቸው። ኮማንዶዎቹም በተባሉት መሰረት ክፍሎችን መፈተሽ ሲጀምሩ ከዋናው ህንጻ ምዕራባዊ ጥግ አካባቢ “ድው” የሚል የተኩስ ድምጽ ሰሙ። ድምጹ ወደተሰማበት አቅጣጫ በዝግታ እያማተሩ ሲጓዙም “ድው” የሚል ሌላ ድምጽ ተሰማ። በዚህን ጊዜ ወታደሮቹ ሁለት ረድፍ ሰርተው በጥንቃቄ እያዘገሙ ከቦታው ደረሱ። ሁለት ከፍተኛ ጄኔራሎች ሽጉጣቸውን ጠጥተው ተገኙ። ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ- የኢህዲሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ እና ሜጀር ጄኔራል አምሐ ደስታ- የኢህዲሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ነበሩ።

ግንቦት 8/1981አመተ ምህረት ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት [ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሬዲዮ] እንዲህ የሚል ዜና አስተላለፈ፤

«በጥቂት ከሀዲ ጄኔራሎች የተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የኢህዲሪ የመንግሥት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አስታወቁ።» የሚል።

በዚያች ምሽት ሁለት ጄኔራል መኮንኖች የገቡበት ሳይታወቅ ጠፍተዋል። ከአስር ቀናት በኋላ የዘበኛ ልብስ ለብሶ ከመከላከያ ግቢ አምልጦ የወጣው አንደኛው ጄኔራል የነበረበት ቦታ በውስጠ አዋቂ ተደረሰበትና አዳኝ ጦር ተላከበት። ጄኔራሉ በጦር እንደተከበበ ሲያውቅ ጣሪያ ለጣሪያ እየሮጠ ለማምለጥ ሞከረ። ግን አልቻለም። ሰፈሩን በድርብርብ ጦር ያጠረው አዳኝ ጦር የጀኔራሉን የማምለጥ እድል አጨናገፈው። ጄኔራሉም ልክ እንደ ጓደኞቹ ወደቀ። ሜጀር ጄኔራል አበራ አበበ- የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ የጥይት ራት ሆነ።

ጀኔራል አበራ አበበ ከመሞቱ ከአንድ ሳምንት

በፊት መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት ሁለተኛው ጄኔራል መኮንን በራሳቸው ፍላጎት ከተደበቁበት ቦታ ወጥተው ለመከላከያ ሚኒስቴር የጥበቃ ዘቦች እጃቸውን ሰጥተዋል። እኒህ ሰው በዚች አጭር ጽሁፍ እያስተዋወቅኋቸው ያለሁት ጀኔራል መኮንን ናቸው። እኒህ የቀድሞው የኢህዲሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ፣ በወቅቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር እጃቸውን ከመስጠታቸው በፊት ለሶስት ቀናት ያህል በኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው መቆየታቸውን ገልጸዋል። ጄኔራል መኮንኑ ለሶስት ቀናት ያለ ምግብና ውሃ መቆየታቸው ያስደነቀው የአዲስ አበባ ህዝብ በወቅቱ እንዲህ የሚል ስንኝ ቋጥሮ ነበር፤

ፔፕሲ ኮካ ኮላው ከከተማው ጠፍቶ፣
ፋንታ ተገኘ አሉ በኮንቴነር ሞልቶ።

በመፈንቅለ መንግሥቱ ጦስ ከተያዙትና ከሞቱት ጄኔራሎች መካከል ነገሩን ከውጥኑ ጀምሮ የሚያውቁት እኒህ ጀኔራል መኮንን ብቻ ነበሩ። ይሁንና ምርመራ ሲደረግባቸው አጠቃላይ ነገሮችን ከመናገር ውጪ ዝርዝር የሆኑ ጉዳዮችን ከማውጋት ተቆጥበዋል። ጀኔራል መኮንኑ የተናገሩት አንድ ትልቅ ሚስጢር ቢኖር የደህንነት ሚኒስትሩን ከሃዲነት ብቻ ነው። በማዕከላዊ ምርመራ ላነጋገሯቸው ኦፊሰሮች «ሚኒስትሩ ከናንተ ጋር ነኝ ብሎን ነበር፤ እኛም አምነነው በእርምጃችን ቀጠልንበት። በኋላ ላይ ግን ከዳን» በማለት ገልጸዋል። ታዲያ የደህንነት ሚኒስትሩ ይህንን ሲሰሙ እጅግ በጣም በመደናገጣቸው መናገር ሁላ አቅቷቸው እንደነበር በወቅቱ በቦታው የነበሩት መርማሪዎች ተናግረዋል።

በመጨረሻም ከሁለት ወር የእስር ቆይታ በኋላ እኒህ የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ ጄኔራል መኮንን ከነሚስጢራቸው ተገደሉ። ሀምሌ 13/1981 አመተ ምህረት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት እንዲህ የሚል ዜና አስተላለፈ፤

«በግንቦት 8/1981 አመተ ምህረት ተካሂዶ የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያቀናበሩት ከሀዲው ጄኔራል መኮንን ጠባቂያቸውን በካራቴ መትተው ለማምለጥ ሲሞክሩ በሌሎች ዘቦች ተገደሉ።» የሚል።

እኒህ በግፍ የተገደሉ የአገር አለኝታ ጄኔራል መኮንን ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ይባላሉ። ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ የሁለት ልጆች አባትና ላገራቸው ሲሉ የሞትን ዕዋ የተቀበሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና ናቸው። የኒህ ታላቅ ሰው ፎቶ ከዚህ ጽሁፍ ጋር ተያይዞ የተለጠፈው ነው!