የትኩረት አስፈላጊነት — ውይይቱም ቢሆን ከስብርባሪና ሽርፍራፊ ጉዳዮች ወደ አንድ አገራዊ አጀንዳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


 

Girma Bekele

በሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያው የአገር ህልውና በ ‹‹አደገኛ›› ሁኔታ ውስጥ ነው በምንልበትወቅት ላይ ሆነን በቋንቋ፣ ታሪክ፣ አከላለል፣ አደረጃጀት፣ የትግል ስልት፣የፖለቲካ እምነት፣ ኃይማኖት፣ …ጉዳዮች ስንነታረክ፣ የዜግነትና ሰብዐዊ መብታችን ባልተከበረበት ፣ በጨቋኞች አገራዊ ራዕይና እምነት ላይ የጋራ ጥያቄ እያነሳን ባለንበት ስለ መልካም አስተዳደር እጦት፣ ስለአገልግሎት ጥራት …. እያነሳን ዋናውን ጥያቄ ወደ ‹‹ስብርባሪና ሽርፍራፊ›› ጥያቄዎች እያወረድንና በነዚህም እየተለያየን የምንራኮትበት ሁኔታ ይታየኛል፡፡ይህ ሁኔታ ዋናውን ሃዲድ ስተን ባልተፈለገ አቅጣጫ እየተጓዝን መሆኑን ያሳየኛል፣ ወይም በነገው ሥራ ዛሬ ላይ ተጠምደን የዛሬውን ተግባር ለነገ ያሳደርን ይመስለኛል፡፡ በዚህ ንትርክና መከፋፈል ባለማወቅም ሆነ በማወቅ ሃብታችንን /ጊዜ፣ ጉልበት፣ዕውቀት፣፣ገንዘብ…) እያባከንን ፣አቅማችንን እያቀጨጭን ለጨቋኞች የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት እያቀረብን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ በአንድ አገራዊ አጀንዳ ላይ ተስማምተን በኅብረት መቆም አለብን፣የ‹‹ስብርባሪና ሽርፍራፊ›› ጥያቄዎችን ጉዳይ እናቆያቸው ወይም ለባለሙያዎች እንተው እላለሁ፡፡ ይህም ‹‹ጨቋኝ ሥርዓትና ጭቆና እንዲያበቃ፤ ሁሉም (ጨቋኝም ተጨቋኝም) ነጻ እንዲወጣ ›› የሚያስችል አገራዊ አጀንዳ ነው፡፡ ለብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ መወያየት ፣ በዚህ ውይይት በሚደረሰው አገራዊ መግባባትና በሚወርደው ዕርቅ ተመስርተን ኢትዮጵያን ሁላችንም ለእርሷ፣ እርሷም ለሁላችን ለማድረግና የተለመደውን በኃይል የሚደረግ የጨቋኝ ስርዓት መተካኪያ የመንግስት ለውጥ ልማድን የሚቀብር ‹‹የሽግግር መንግስት›› መመስረት፡፡ በዚህ ኃሳቤ አንዳንድ ወዳጆቼ (ለህወኃት) ርህራሄህ የበዛ ነው ብለውኛል፡፡
የጨቋኝነት መሰረት የተጨቋኝነት/የበታችነት ስሜት ነው፡፡ የማስፈራራት ምንጩ ፍርኃት ነው፡፡ በመሆኑም ይመስላል እንጂ ከእኛ/ከተጨቋኞች በላይና በከፋ ሁኔታ በፍርሃት የሚንቀጠቀጡት፣ በጥላቻ ህመም የሚሰቃዩት እነርሱ/ጨቋኞች ናቸው፡፡ እንደ ህዝብና ዜጋ እርስ በርሳችን ግን አንፈራራም፣ በተቃራኒው እነርሱ ‹‹ተባሉ፣ተጨራረሱ›› ብለው አስተምረው /አንቅተውና አስታጥቀውም እርስ በርስ አልተባላንም፣ አልተጨራረስንም፡፡ በቀደመው ማኅበራዊ እሴቶቻችን መሰረት ላይ በቆመው ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነታችንና በታሪክ በተፈጠረው የደም ትስስራችን ….፤ በሰላም አብረን እየኖርን ነው( የዚሁ ጽሁፍ መነሻ የሆኑትን የጥቂት ልህቃኖችን በህዝብ ስም ለመነገድ የሚደረገውን ጥረትና የቃላት ጦርነት ወደ ጎን ብለን)፣ በየቱም የአገራችን ክፍል ያለአጃቢና ሰላይ፣ያለፍርሃትና ስጋት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ‹‹ግጭቶችም›› ቢሆን የነርሱ/የጨቋኞች ‹‹ ሴራ ስሪት ውጤት›› እንጂ ህዝብ በህዝብ ላይ ያነሳው ያለመሆኑ በመረጃና ማስረጃ ተደግፎ እየቀረበ ነው፡፡ እነርሱ ግን የምንሰራውና የምንመራው የህዝብ ይሁኝታ በማግኘታችን ነው (መቶ በመቶ ያሸነፍነው ህዝብ እምነቱን ጥሎብብን ድምጹን ስለሰጠን ነው ) ይበሉ እንጂ ይህን ‹‹ ይሁንታ›› የሰጠውን ‹‹እምነቱን የጣለባቸውን›› መራጭና ‹‹የምመሩትንና የሚሰሩለትን›› ህዝብ አያምኑትም፡፡ ከድምጽ መስጫ ካርዱ በቀር ባዶ እጁን ያለውን (ግፋ ቢል ብዕርና ማምረቻውን የጨበጠ) ‹‹የመረጣቸውን›› ህዝብ በእጅጉ ይፈሩታል፣ የትኛውም እንቅስቃሴኣቸው በአጃቢና ሰላይ የሚመራ በሆነበትም እንቅስቃሴውን ይገድባሉ፣ መንገዶችን ይወጥራሉ….. ፡፡ የሰሩትን ስለሚያውቁ በምናባቸው በፈጠሩት ‹‹ጠላት›› ከሰላማዊው ህዝብ አልፈው ጥላቸውን ጭምር ይጠራጠራሉ፡፡ እርስ በርሳቸውም ይፈራራሉ፣ አንዱ ሌላውን ይጠረጥራል፣ ይሰልላል፡፡ በዚህም የተነሳ በወረራ የያዙትን አገር፣ በቅኝ የያዙትን ህዝብ የሚገዙ እንጂ እንደሚሉት የመረጣቸውን የራሳቸውን አገር ህዝብ የሚያስተዳድሩ አይመስልም፡፡ እኛ ተጨቋኞችማ የነርሱን ጉዳይ ፈጻሚ ታጣቂ ኃይሎች፣ሰላዮችና ፍትህ-በላ ፍርድ ቤቶች ብንፈራ ‹‹እውነት›› አለን፤ ሁሌም ተፈርቶ ያለመዘለቁ ሃቅና ፍርኃቱም እያበቃ የመሆኑ እውነታ ከየአቅጣጫው በተጨባጭ እየታየ መሆኑ እንደተጠበቀ፡፡
ስለዚህ የትግላችን( የሃሳብ ማጥራት ውይይታችንን ጨምሮ) አንድና አንድ አጀንዳ ‹‹ሁላችንም›› ነጻ የምንወጣበት፣ ጭቆናን ከመሰረቱ በዘላቂነት የምንነቅልበት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ተጨቋኞች (በተለያየ አደረጃጀት ያለን ፓርቲዎች፣ የሙያና ሲቪክ ማኅበራት፣ወጣቶችና ሴቶች ፣የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾችና …) በአንድነት ብንቆም፣ የየተቋቋምንበትን ዓላማ ለመፈጸምም ሆነ ለማስፈጸም በቅድሚያ ‹‹ሁላችንም›› ከጭቆና እንድንላቀቅ ለ‹‹ፈሪዎቹ/ ጨቋኞች›› ‹‹የማሪያም መንገድ›› በመስጠት ከፍርኃታቸው ማላቀቅ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ቢወዱ በሰጠናቸው ‹‹የማሪያም መንገድ›› ተጠቅመው ለብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ መድረክ ራሳቸውን አዘጋጅተው እንዲቀርቡ፣ የአምባገነን ባህሪያቸው አሸንፏቸው ይህን መንገድ/ዕድል ለመጠቀም ካልፈቀዱ ሥርዓቱን ለማስወገድ እርስ በርስ ሳንጠላለፍ ብቻም ሳይሆን በተናጠል ሳይሆን ያለችንን ውስን ሃብትና አቅም ሳናባክን ተደማማሪ ውጤትና ተመጋጋቢ አስተዋጽኦ ስለምናደርግበት መወያየት አለብን፡፡ይህም የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባራችን መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ወቅታዊ ባልሆኑ ወደ ዘላቂ መፍትሄ የማያደርሱን ‹‹ ስብርባሪና ሽርፍራፊ ጉዳዮች›› መነታረክ ‹‹መንገድ የሚያርስ›› ገበሬ ዓይነት ውጤት አልባ ከመሆኑም በላይ ለጭቆናና ጨቋኞች የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት ማቀበል ነው፡፡ በእነዚህ ሽራፊ ጉዳዮች ለመወያየትና ለመከራከር ‹‹ ነገ›› በቂ ዕድል፣ ጊዜና የአየር ሰዓት ይኖረናል፡፡ በቸር ያገናኘን/