ብኩን አፍሪካውያን ዕንስቶች (በወርቁ ለገሠ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ብኩንነታቸው ላይ አፅንዖት ለመስጠት ዲስ-ግሬስ የሚል ቅፅል የተሰጣቸው የሮበርት ሙጋቢ ባለቤት- ግሬስ ሙጋቢ የባለቤታቸውን 85ኛ የልደት በዓል በ2009 አክብረዋል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ሚስ ሙጋቢ የሚጠቀሙባቸው መጫሚያዎች ከ3000 በላይ ሲሆኑ እንደየቀለማቸው የፅዳት ቀለም ሳይኖራቸው አይቀርም። ልዕልቷ በየቀኑ አዲስ ጫማ እንዲጫሙ ቢደረግ መጀመሪያ የተደረገውን ጫማ እንደገና ለማጥለቅ ቢያንስ 8 ዓመት ይወስድባቸዋል ማለት ነው። ባለፈው ዓመት እግር ጥሏቸው ፓሪስ በሚገኙ ሱቆች ጎራ ቢሉ 2 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ሺህ ዩሮ እንዳወጡ ይነገራል።

በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ብኩን አፍሪካዊ ልዕልት ሰሞኑን ከቱኒሲያ የፈረጠጡት ለኢላ ትራቤልሲ ናቸው። እኝህ አፍሪካዊ ንግሥት ባለቤታቸውን የቱኒሲያው ዐብዮት ከሥልጣን ኮርቻ ላይ አስፈንጥሮ ሲጥላቸው የነበራቸውን ንብረት በሙሉ ለማሸሽ ጊዜ ቢከዳቸውም ለስደት ኑሯቸው የሚያገለግል 1.5 ቶን የሚገመት ወርቅ በጆሯቸው፣ በአንገታቸው፣ በብብታቸው፣ የተረፈውን ደግሞ በካርጎ አስጭነው ጠፍተዋል።

በተመሳሳይ ጋናዊቷ ልዕልት ኧርነስቲና ናዱ ሚልስ የጋናው ፕሬዚዳንት ሚስት ሲሆኑ እኝህ ንግሥት የሁዋይት ሃውስን የመጎብኘት ዕድል ከገጠማቸው ጥቂት የአፍሪካ ብኩን ዕንስቶች አንዷ ናቸው። “ካልሰጡ አይሰደቡ” የሚለውን የአማርኛ ብሂል እንዴት እንደሰሙት አላውቅም ለሚስ ሚሼል ኦባማ ያበረከቱት ስጦታ ጠቀም ያለና ጥራቱ በካራት ሲለካ ወደር የማይገኝለት ከከበሩ ድንጋዮች የተሠራ የዕጅ ሰዓት መሆኑ ጭምጭምታ ተሰምቷል። ልዕልት ሚልስ ለሚሼል ኦባማ በስጦታ ያበረከቱት የወርቅ ሰዓት ዋጋ ከ48 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደማያንስ ተገምቷል። የጋና ቸኰሌት ወይም የአገሪቱን የባህል ልብስ በስጦታ ማቅረብ የተሻለ ክብር የሚይቀድጅ ነገር ግን በዋጋ አንፃር እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ እያለ የውጭ ሰዓት ዋጋውን ለመክፈል ቀርቶ ለመጥራት የሚያስፈራ ዕጅ መንሻ መስጠት የብኩንነት መገለጫው ነው።

የኛዋም ልዕልት አዜብ መሥፍን በብኩንነት ተርታ ረድፍ ተገቢ ሥፍራቸውን ይዘዋል። እጅግ ውድ በሆኑ የፋሽን ሱቆች በመመላለስ 1ሺህ 200 ሚሊዮን ዩሮ ለባህር ማዶ ነጋዴዎች እንዳቀበሉ ተዘግቧል። አገር ውስጥ የሚጠፋውን ብር ለመተመን በቂ መረጃ ስላላገኘ ይመስላል የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ቤት ይቁጠረው በማለት በዝምታ አልፎታል። ልዕልት አዜብ ያ ሁሉ የወጣትነት ዕድሜያቸው በታጋይነት ባያልፍማ ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሁኑ በባሰ መልኩ የሚላስ የሚቀመስ አያገኝም ነበር። ተመስገን ማለት ደግ ነው። ይህንኑ ማን አየበት?

የደቡብ አፍሪቃዋ ኖምፑመሌሎ ንቱሊ ዙማ፣ ካሜሩናዊቷ ቻንታል ቢያ፣ የኮንጎ ብራዛቪሏ አንቶኒ ሳሱ ንጌሶ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የሃገር ሀብት የዘረፉ ብልሹ አፍሪካዊ ዕንስቶች ናቸው ተብሏል። የብክነት ሚዛን እንደመሥፈርት ከተወሰደ የስዋዚላንዱ ንጉሥ ምስዋቲ ሳልሳዊ ከመሰል አቻወቻቸው ሻል ብለው ተገኝተዋል። በ2009 ዓ.ም 13 ሚስቶቻቸውን በጋራ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ዱባይና ታይዋንን እንዲጎበኙ ላኳቸውና ሲመለሱ ለንጉሡ ያቀረቡት የወጭ ደረሰኝ 5 ሚሊዮን ዩሮ ብቻ ነበር። ለ13 ልዕልቶች ይህ ብዙ ወጭ አይደለም። ብዙ ነው ከተባለም የአወጣጥ ዘዴው ይሁንታ ሊሰጠው ይገባዋል። መቼም አንዷ ብቻዋን ከምታጠፋው ለ13 ዕንስቶች ማከፋፈል ብልህነት ነው።

አይዘገንንም? እርግጠኛ ነኝ እያንዳንዱ አገር ያፀደቀው ህገ መንግሥት “የሀገርን ሀብት የሥልጣን ከለላ በመጠቀም ማባከን ወንጀል ነው” የሚል አንቀጽ ይኖረዋል። የዚህ ዓይነቱ ገደብ የለሽ ስግብግብነት በሰው ልጆች ዘንድ የሚከሰት ብልሹ ሥነ ምግባር ከመሆን አልፎ ባህርያተ እንስሳ የተላበሰ እኩይ ድርጊት በመሆኑ ውጉዝ ከመ አርዮስ ልንለው ይገባል ። ከዚያ ሁሉ ድሃ ጉሮሮ ላይ እየነጠቁ መዋዕለ ንዋይ እንደውሃ ማፍሰስ ብኩን የሚለው ቃል አይገልጸውም። በላዔ ሰብ መሆን ነው።

በወርቁ ለገሠ(1/29/11)
ምንጭ፡ ኤቢሲ ኢንተርናሲዮናል