ሁለቱ ጽንፎች ሲጓተቱ– አልነጋ አለ ሌ’ቱ// – ግርማ በቀለ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአንድ ወገን — ብቸኛ የኢትዮጵያ ባለቤቶችና ጠበቆች — በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት የማይዋጥላቸው//
ሁለቱም በትናንት ላይ ተቸክለው በአንድ በኩል ራሳቸውን የኢትዮጵያ መስራች፣ በሌላ በኩል ራሳቸውን በግዳጅ ኢትዮጵያዊ የተደረጉ አርገው የሚያስቡ ዛሬን መኖር፣ ነገን መመልከት ያልቻሉ፤ ሁለቱም ወገኖች ከዓለም የአገር አመሰራረት ታሪክ ለመማር አዕምሮኣቸውን የዘጉ፤በአገራችን ታሪክ የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ትስስር፣ማኅበረሰባዊ ቁርኝት፣ አብሮነትና በጎውንም ደጉንም ቀን በጋራ ማሳለፍ፣…የዘነጉ ከአዎንታዊውና በጎው ጎን ይልቅ በአሉታዊውና ክፉው ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡
የሚገርመው በሁለቱም ጽንፎች ያሉት ወገኖች ባልነበሩበትና ባልዋሉበት በተሳሳተ የታሪክ አረዳዳቸው ራሳቸውን የዚያ ዘመን ታሪክ ተዋናይና ‹‹ወራሽ›› አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ መሆናቸው ነው፡፡ በዚህም በጊዜው በነበሩ ህዝቦች መካከል የነበረውን አብሮነት፣ ጤናማ ግንኙነትና ዛሬም በአባት እናቱ /በወላጆቹ/ ቀዬ ያለው ህዝብ ተረጋግቶ የመኖሩን፣ለሌላው ወገኑ ያለውን አክብሮትና መተሳሰብ፣ መፈናቀልና ግጭት የስርዓቱ ሴራ ውጤት መሆኑን ለማመዛዘን የማይፈልጉ፣ ስለህዝቦች አብሮና ተከባብሮ መኖር ያለውን መረዳት መስማት የማይፈልጉና ያለፈውን ታሪክ ለራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚ ፕሮፖጋንዳ ለመጠቀም የሚታትሩ ‹‹ልህቃን›› መሆናቸው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሥቃይና ጭቆናው እገሌን ከእገሌ ሳይለይ አገዛዙን ‹‹አሜን›› ብለን እስካልተቀበልን ከህግና ሥርዓት ውጪ (ያውም ከራሳችን በወጡ ‹‹በራሳችን ›› ወንድሞችና እህቶች ፈጻሚነት) በሁሉም ዜጋ ላይ ያለገደብ እየተፈጸመ በመሆኑ የሁለቱ ጽንፈኞች ጨዋታ ወቅቱን አልተረዳም፤ አይመጥንምም፡፡


ዛሬ ዓለም መንደር እየሆነች በመጣችበት ዘመን፣ አገራት ወደ ትልቅነት ማደግ ግዳጅ መሆኑን በመረዳት አህጉራዊና አካባቢያዊ ኅብረት እየመሰረቱ ባሉበት፣ ወደ ትንሽነት ለመጓዝ የሚተጉ መሆናቸውን ስንመለከት ነው እነዚህን ወገኖች የ‹‹አልነጋ አለ ሌ’ቱ›› አጋፋሪዎች ለማለት የምንደፍረው፡፡ በተለይ ትናንት ራሳቸውን ተጎጂ አድርገው የመብትና ፍትህ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖችን ጠባብና ዘረኛ ብለው ሲያወግዙ የነበሩ የኢትዮጵያዊነት ጋሻ ጃግሬዎች ከሰሞኑ ራሳቸውን ከቤተ-ኢትዮጵያ (ሙሉ ሜዳው) ወደ ‹‹ቤተ አማራ›› (የራሳቸው ግማሽ ሜዳ) አጥብበው አደረጃጀታቸው፣ዓላማቸውና ግባቸውን ለመረዳት በሚያስቸግር ሁኔታ ‹‹መጣን›› ማለታቸውንና ከትናንት ‹‹ተከሳሾቻቸው›› ጎራ መቀላቀላቸውን ስንሰማ ‹‹ጨዋታውን›› ሁሉ ምጸት ያደርገዋል፡፡ ጌታቸው ረዳ የሚባሉ ድንቅ ኢትዮጵያዊ /የትግራይ ተወላጅ/ በአማራ/በተለይ ሸዌ/ ላይ የተሸረበውን ሴራ ከመነሻው እስከዛሬ /ህወኃት/ የገለጹት ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡ ይህ መውረድ ለአገርና ህዝብ ጥቅም መከበር ከምናደርገው ትግል ሜዳ ወጥተን ‹‹ልቡና ይስጣቸው›› ብለን ለመጸለይ ፊታችንን ወደ ቤተ-እምነት እንድናዞር ይገፋፋል ፡፡ ማን ነበር የረገመን ??? ከዚህ በፊት ንስኃና ሱባኤ ያስፈልገናል ማለቴን አስታውሱልኝ፡፡…


ሁለቱም ወገኖች ጨዋታውን ከውድድሩ ሜዳ ውጪ እያደረጉ መሆኑን አልተረዱም፣ለመረዳት አይፈልጉም ወይም አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ‹‹በአጥፍቶ መጥፋት ፕሮጄክት›› ተሳትፎ እያደረጉ ነው ፡፡ የወቅቱ የአገራቸውና ‹‹እንወክለዋለን›› የሚሉት ህዝብ ጥያቄ ከዚህ ያለፈ የ‹‹አገር ህልውና እና የሰውነት- የዜግነት መብትና ክብር ጉዳይ›› መሆኑን ለመረዳት የገቡበት ጉርጓድ ቀዳዳ መጠን አስተሳሰባቸውንና የአመለካከት አድማሳቸውን አጥቦታል፤ ‹‹አይጥ ዓለምን የምትመለከተውና መረዳቷ በቀዳዳዋ ልክ ነው›› እንዲሉ፡፡ የወቅቱ ትግል የተወሰኑ የአንድ መንደር ልጆች በህዝባቸው ስም በአገርና ከቡድናቸው ውጪ ባለው ኢትዮጵያዊ በሙሉና በተለይ እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብ ላይ በከፋ ሁኔታ እያደረሱ ያለውን ጥፋት መከላከል ከእነርሱ የ‹‹ቡድን›› ጥያቄ የሚቀድም መሆኑን መረዳት ተስኗቸው፣ ለሌላው የተመኙት የመከፋፈል በሽታ ራሳቸውን ተጣብቷቸው በማይድን በሽታ ለሚሰቃዩትና ዕለተ-ሞታቸውን በመጠባበቅ ላይ በሚገኙት የመንደር ልጆች የሚዘወር ሥርዓት የዕድሜ መቀጠያ መድሃኒት እያቀበሉ መሆኑን መገንዘብ አልቻሉም፡፡ በዚህ መንገድ ከቀጠሉ በገቡበት ‹‹በአጥፍቶ መጥፋት ፕሮጄክት›› በትግላችን ላይ ጥፋት ይፈጽማሉ፣ የለውጡን ቀን ያዘጉዩት-የሥቃይ ቀናችንን ያረዝሙት ፣ ራሳቸውም ይጠፉ እንደሆን እንጂ ለውጡ አይቀሬ ነው፡፡
በብሄራዊ ውይይት የብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ስንል ሌ’ቱ እንድነጋ ከገባንበት አዘቅት ለመውጣት፣ከተያያዝነው የገመድ ጉተታ ለመላቀቅ፣ እውነታውን ለማየት/መረዳት የሸፈነን ግርዶሽ ለመግለጽ፣…እንድንሆን ስለሚረዳንና ‹‹ሁላችንም አሸናፊ/ዊን-ዊን/›› የሚያደርገው አማራጭ ስለሆነ ነው፡፡ በቸር ያገናኘን//