ሁሉን አካታች ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ሲባል– Girma Bekele


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የለውጥን በተፈጥሮኣዊነት፣ የዓለምን ነባራዊና የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስናገናዝብ የለውጥ አይቀሬነት ብቻ ሳይሆን በየቱም መንገድ ባይታወቅም በቅርብ ርቀት መገኘቱንና የሚመጣውን ለውጥ በአዎንታዊነትና በዘላቂነት ሊሸከም የሚችል ገዢውን ፓርቲ ህወኃትን ጨምሮ አስተማማኝና ታማኝ የፖለቲካ ኃይል ያለመኖሩን ታሳቢ በማድረግ የብሄራዊ መግባባት፣ ዕርቅና የሽግግር መንግስት ምስረታ በአገራዊ ዕይታ ለሁሉም ወገኖች የሚከተሉት ጥቅል ጥቅሞች አሉት፡፡

1. ገዢው ፓርቲ በየምርጫው ወቅት የሚያጣውን ድምጽ/ቮት-በሁሉም ምርጫዎች/ እና መቀመጫ (1992 እና 97) ለምን ብሎ ከልቡ እንዲጠይቅና ራሱን ወደ ውስጥ እንዲመለከት፣ከፕሮፖጋንዳ መፍትሄና አፈናውን ከማጠናከር ያለፈ/ውጪ ትክክለኛና ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግ በማስገደድ ራሱን ለብሄራዊ ውይይት እንዲያዘጋጅ፣ በቀጣዩ የሥልጣን ዘመን /የህዝቡን ፍላጎት ያገናዘበ የፖሊሲ ለውጥ፣ ለህዝቡ የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ– የኅሊና እስረኞችን መፍታት፣.መልካም አስተዳደር፣ የህዝቡን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ…/ እርምጃዎችን በመውሰድ የፖለቲካ መረጋጋት ለመፍጠር ያስችላል፡፡

ታይቶ የነበረውን የተቃዋሚዎች ማሸነፍና ተሳትፎ እያደገ ቢመጣ ኖሮ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበትና ለዲሞክራሲ እየተጠናከረ መምጣት የነበረውን አስተዋጽኦ ህወኃት ከ1997 በኋላ የቀለበሰው መሆኑን ከህወኃት ውጪ ያሉት የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እንዲረዱት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ምርጫውን ተኣማኒና ተቀባይነት ያለው በማድረግ ፣ የህዝቡን በፖለቲካውና በልማቱ ያለውን ተሳትፎ ያሳድጋል፡፡
ይህ ባለመሆኑ ማለትም ህወኃት ያለውን ኃይል ሁሉ ለአፈና በማዋል አገዛዙን ወደ ፍጹም አምባገነንነት በመለወጡ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ተስተጓጉሏል/ተቀልብሷል፡፡

2. የቀድሞው ጠ/ሚ/ር ህልፈት የፈጠረውን ‹‹መልካም አጋጣሚ ›› ከርሳቸው ብቸኛ አመለካከትና እምነት በተለየ መንገድ ማሰብ እንዲቻል፣ ይህንንም የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ለለውጥ እንዲጠቀሙበት የሚያበረታታ የፖለቲካ ዋስትና ይሰጣል፡፡
የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የወከሉት ህዝብ ትክክለኛ ተወካይ መሆናቸውን ያረጋግጣል ፣ተኣማኒነታቸውን፣ ተቀባይነታቸውንና ተወዳዳሪነታቸውን ያሳድጋል፡፡ ከህወኃትውጪ ያሉ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎችና አጋሮች ከአጃቢነትና ጉዳይ ፈጻሚነት ‹‹ፍረጃ›› ነጻ ያወጣቸዋል፡፡ ለህወኃትም እስከዛሬ የሚከተለውን የጠባብ ብሄረተኝነትና ዘረኝነት ፖለቲካ ተከትሎ የተፈጠረው በውስጡና ከሌሎች አባል ፓርቲዎችና አጋሮች እንዲሁም ህዝብ ጋር የገባበትን ውጥረት ያረግባል፣ የመተማመኛ ፖለቲካዊ ዋስትና ያስገኝለታል፡፡

3. የተቃውሞ ጎራው ባልተከፋፈለ መንገድ በአንድ ላይ ቆሞ የምርጫ ድምጽ ሳይከፋፈል ለተወሰኑ የፓርቲ የፓርላማ ወንበሮች በተናጠል ከመሄድ ወደ ውህደት/ግንባር/ትብብር በመቆምና በምርጫ በመሳተፍ መንግሥት ለመመስረት የሚስችል አቅም እንዲፈጥር ዕድል ይሰጣል፡፡

የእስከዛሬውን የፖለቲካ መፈራረጅና የአንጃነት ውርስ ያስቀራል፣የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች በቃላቸውና ተግባራቸው የሚመዘኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፣ በህዝብ ስም በሚነግዱ ፓርቲዎችና በፓርቲ ስም ለመነገድ በሚጥሩ የፖለቲካ አመራሮች ላይ በር ይዘጋል፡፡ ….

4. በአገሬ/ኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉትን ሁሉ በማሳተፍ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች ተከትለው የተፈጠሩ ድርጅቶች /ፖርቲዎች፣ሲቪክና ሙያ ማኅበራት …./ መካከል መተማመን፣…በመፍጠር ሁሉም ወገን ወደ ሰላማዊ ትግል አማራጭ እንዲመለስበማድረግ የሰብዐዊ ክስረትንና የሃብት ውድመትን ይከላከላል፤ ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን እንዲሆን የሁሉንም ተሳትፎ ያረጋግጣል፡፡ በአገሪቱ የተንሰራፋው የኃይል አምልኮና ይህንን ተከትሎ የሚታየውን በአጥፍቶ ማጥፋት የሚደረግ የሥልጣን ሽግግር አዙሪት ያበቃል፡፡ ህዝብ የመወሰን መብቱን የሚጠቀምበትን፣ ፓርቲዎች የህዝብን ውሳኔ ለማክበር የሚገደዱበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ስለዚህ እኔ ለአገራችን ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ማንም የማይጎዳበት ይህ ብቸኛው መንገድ ነው እላለሁ፣ እናንተስ? በቸር ያገናኘን፡፡