ኢህአዴግና ፕሮፓጋንዲስቶቹ አደብ ቢገዙ ጥሩ ነው ፡፡ ጥላሁን እንደሻው /መድረክ/
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የተሳሳተው የአዲስ ዘመን ዘገባና የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ
መስከረም 4 ቀን ማሕሌት የሚትባል የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ በአዲሱ ዓመት መድረክ በመድበለፓርቲ ሥርዓት ግንባታና በሰላማዊ ትግል አንጻር ምን ነገሮችን ለመሥራት እንዳሰበና በ2ኛ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዝግጅት ላይ ያለውን አስተያየት ጠይቃኝ የመድረክን የትኩረት አቅጣጫና በሀገራችን በአሁኑ ወቅት በገዥው ፓርቲ እየተፈጸሙ ያሉ ፀረ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ ተጽናዎችን አብራርቼላት ነበር፡፡ ጋዜጠኛዋ በመጨረሻ ስለአቶ ሞላ አስገዶምና ጓደኞቹ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን በሚመለከት አስተያት ጠይቃኝ ‹እኔም ሆንኩኝ ፓርቲያችን/መድረክ/ እንደማነኛውም ዜጋ በመገናኛ ብዙኃን ዜናው ሲወራ ከመስማታችን በስተቀር ስለጉዳዩ በቂ መረጃ የለለን ስለሆነ እንደዚሁም በጉዳዩ ላይ በአመራር ደረጃ ስላልተወያየንበት ማብራሪያ መስጠት አልችልም፣ ወደፊት መረጃዎቹን ግራና ቀን ተመልክተን አስፈላጊ ሆኖ ካገኘን አቋማችንን የምንገልጽ ይሆናል፣ መድረክ ሰላማዊ የትግል አማራጭ የሚከተል በመሆኑ ቀደም ሲል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገራችንን ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚካሄድ ሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉና ገዥው ፓርቲም በሀገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታን በሚመለከት የዘጋቸውን በሮች እንዲከፍትና ሕጋዊ መሥመርን ተከትለው በሚሄዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ እያደረሰ ባለው ተጽኖ የሰላማዊ ትግል ሜዳውን በማጥበብ ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ እያደረገ ያለውን ተግባር እንዲያቆም ሲናቀርብ የቆየነውን የሰላም ጥሪ ከምንደግም በስተቀር በእነአቶ ሞላ አሰገዶም መምጣት ምክንያት የሚናቀርበው አዲስ የሰላም ጥሪም አይኖርም› በማለት መልስ ሰጠኋት፡፡ ይህ መልሴም መስከረም 7 ቀን 2008 ዓ ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፖለቲካ አምድ ላይ ‹ስለትህዴን መመለስ ፓርቲዎች ይናገራሉ› በሚል ርዕስ መጻፉን ተመልክቻለሁ፡፡
በሌላ በኩል ግን ከዚሁ ቃለመጠይቅና ምላሼ በተሠራውና መስከረም 6 ቀን በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት ‹ፓርቲዎቹ የትህዴንን ፖለቲካዊ ውሳኔ ደገፉ› በሚል ርዕስ ስር ሌሎች ሀሳቦች እኔ በገለጽኩት መልኩ ከሰፈሩ በኃላ የእነአቶ ሞላን መመለስ በሚመለከት ከእኔ ፈጽሞ ያልተገለጸ ሀሳብ አቶ ጥላሁን እንደሻው የመድረክ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ‹ትህዴንም ወደሰላማዊ መስመር መግባት ትክክለኛና ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትም ጥያቄአቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እንደሚገባቸውና ወደሰላም እንዲመጡም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡› ተብሎ ተዘግቦአል፡፡ እንግዲህ በአንድ ቃለመጠይቅ በእነአቶ ሞላ ጉዳይ ላይ የሰጠሁትን መልስ በጋዜጣው ተለያዩ እትሞች /በዜናና በፖለቲካ አምድ ላይ/ እርሰበርሱ የሚቃረን ሀሳብ የአዲስ ዘመን አዘጋጆች አስፍረዋል፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎችም ይህንኑ የእኔ ያልሆነ ሀሳብ በእኔ ስም እንደሰተጋቡ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ በመስከረም 6 በታተመው ጋዜጣ የወጣውና ከእኔ ያልተገለጸው አጻጻፍ እራሳቸው መስከረም 7 ላይ በታተመው ጋዜጣ ከጻፉት ጋር የሚቃረን ለፕሮፓጋንዳ በመቻኮል ይሁን ወይስ በምን ምክንያት እንደዚህ እንደተጻፈ ፈጽሞ ያልገባኝ ስለሆነ እኔ በእነአቶ ሞላ አስገዶም መመለስ ጉዳይ መግለጫም ሆነ ጥሪ ፈጽሞ ያላቀረብኩ መሆኔን አንባቢያን እንደረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡
የአቶ ሞላ አስገዶም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በማስመልከት ሰሞኑን በኢህአዴግ በኩል የፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቹ በሆኑት መገናኛ ብዙሃን ብዙ እየተወራ ይገኛል፡፡ በበኩሌ አንድ ዜጋም ሆነ የተወሰኑ ዜጎች ወደ ውጭ ሄደው ከቆዩበት ወደ ሁገራቸው ሲመለሱ በሰላም ተመልሰዋል የሚል ዜና ከማስተላላፍ ያለፈ ምክንያታዊ ያልሆነ ብዙ ፕሮፓጋንዳ ከማሰራጨት አልፎ በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ ስላላገኘን አሁን መግለጫ ለመስጠት አንችልም በማለት ለአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ የጥያቄ መልስ የሰጠውን ሰው ሀሳብ በማዛባት የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ የሚገባበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ሆኖብኛል፡፡ ኢህአዴግና ፕሮፓጋንዲስቶቹ አደብ ቢገዙ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡
ጥላሁን እንደሻው የመድረክ ም/ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ