ታሪክን የኋሊት = መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ ም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ጳጉሜ 4 ቀን 1966 ዓም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ በድምፅ ብልጫ ከተወሰነና ቅድመ ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ ኋላ የህዝቡን ቁጣ ለመቀስቀስ ይረዳል ከተባሉ ፕሮፖጋንዳዎች ዋነኛው የነበረው ዜና ተላለፈ።

” …በዛሬው እለት የዘመን መለወጫ ለኢትዮጲያ ሕዝብ የማይሆን ተስፋ ማቅረብ አንፈልግም። ምክንያቱም የአንገበገባቸው መሆኑን እናውቃለን። በዛሬው ቀን እርጥብ አበባ ወይም የዘንባባ ገፀ በረከት አናቀርብለትም። ምክንያቱም የአገራችን መልካምድር በተፈጥሮ አጋጣሚ ተመካኝቶ ተግጧልና…በዛ ምትክ በዛሬው ምሽት የወሎን የረሃብ እልቂት የሚያሳይ ፊልም በቴሌቭዥን እናቀርባለን…”

የፊልሙን ትእይት ተከትሎ ” ንጉሡ ከሥልጣን ይውረዱ!” የሚል መፈክር ያነገቡ ወጣቶች

የአዲስ አበባን መንገዶች አጥለቀለቁ። በወቅቱ ፊልሙ ሲተላለፍ የንጉሡን ሁኔታ እንዲከታተሉ የታዘዙ ቤተ መንግስት የሚሰሩ የደርግ ደጋፊዎችም ጃንሆይ ፊልሙን በሚያዩበት ግዜ በከፍተኛ ሐዘን ወድቀው ነበር። ፊልሙን መጨረስ አቅቷቸው በሐዘንና በዝምታ በግዜ ወደ መኝታ ቤታቸው መግባታቸውን ገልፀዋል።

በማግስቱ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓም በሻለቃ ደበላ ዲንሳ የሚመራ 9 የደርግ ቡድን በንጉሡ ዘንድ ተገኝቶ ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረዳቸውን የሚገልፀውን ደብዳቤ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ አነበቡ። ጃንሆይ ያሉት ነገር ቢኖር ” የኛ ከአስተዳደር መወገድ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ከተባለ የተነበበውን ተቀብለናል። የሀገሪቱን ነገር ግን አስቡበት!” ብቻ ነው።

ጃንሆይ ከዙፋናቸው ወርደው በሰማያዊ ቮልስ ወደ 4ኛ ክፍለ ጦር ሲወሰዱ በቤተ መንግስት ዙሪያ ጎርፎ የነበረው ህዝብ ለዘመናት ሲሰግዱላቸው…በስማቸው ሲምል…ከፈጣሪ ሲያጠጋጋቸው የነበረው እንዳልነበር “ሌባ ሌባ” ሲል አወገዛቸው። በመውረዳቸውም እልልታውን አቀለጠው። ደራሲ ከበደ ሚካኤል “ህዝብ ማለት ምንግዜም እውር…የማያመዛዝን…ወረተኛ…ግዜ የሰጠውን ብቻ ደስ ለማሰኘት የተዘጋጀ ነው” እንዳሉት ሆነ።

በታሪክ ብራና ላይ በዛሬው ቀን ተከትቦ ያለው ቅንዲል ታሪክ ይህ ነው። ከ3000ኣመታት በላይ በኢትዮጲያ የነበረው የዘውድ ሥርዓት ተወግዶ ወታደራዊ መንግስት ሀገሪቱን የተረከበበት ቀን ነው የዛሬው ቀን።

ይኸው ነው ያለንም እኛ የሚትንም እኛ!

ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር!

* ማጣቀሻ…
_ ትግላችን…ሌ/ኮ/ መንግስቱ ኃይለማርያም
_ እኛና አብዮቱ… ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ
_ ነበር_ ዘነበ ፈለቀ