ሼህ ሙሃመድ አላሙዲ እንዳይሰሙ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከአባይነህ ተገኝ
የሰሞኑ የሶርያ እና የኢራቅ ስደተኞች አውሮፓን ማጥለቅለቅ ለአውሮፓውያን ራስ ምታት፣ለአለም ደግሞ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሗላ ያልታየ አሳሳቢ እና አሳዛኝ ክስተት ሆኗል። በተለይ በተለይ በባህር ዳርቻ ወድቆ ከታየው ከዚያ የብዙዎችን ልብ ከሰበረ ጨቅላ ህጻን ሞት በሗላ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ፍንትው ብሎ ታይቷል። በሽር አል አሳድ እንኳን ልቡ ራርታ ነው መሰል” ደህና ተቃዋሚ ከተገኘ ስልጣኔን ለማካፈል ዝግጁ ነኝ”ሲል ተደምጧል።
ከዚህ በላይ አለምን ያነጋገረው ጉዳይ ግን የግብጻዊው ቢሊዬነርን ጉዳይ ነው።
ነገሩ እንዲህ ነው ፤-Naguib Sawiris ይባላል።ወደ 2.9 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚገመት ገንዘብ ያለው ግብጻዊ ነው ። እናም እንዲህ ሲል በትዊተር ገጹ ላይ አሰፈረ ” ጣልያን እና ግሪክ በሜዲትራኒያን ባህር ካሏችሁ ከአንድ ደርዘን በላይ ደሴቶች አንዱን ሽጡልኝ።ስደተኞቹን በሙሉ እዚያ አስፍሬ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልቼ አኖራቸዋለሁ” ሲል። ይህ ሃሳቡ “ሊፈጸም የማይችል ” (Crazy idea)ተብሎ ተተችቷል። ይሁን እንጂ ትናንት ምሽት ሰውዬው በ CNN ቴሌቪዥን ጣቢያ በስልክ ቃለመጠይቅ ተደርጎለት “ይህ ሃስብህ የሚፈጸም ይመስልሃል?” ተብሎ ሲጠየቅ–” የኔ እመቤት እያወራሁ ያለሁት ዝም ብሎ ተራ ነገር አይደለም። ለዝናም አይደለም።ገንዘብ አለኝ ገንዘቡን ወደመቃብር ይዤው አልሄድም።ለልጆቼ በቂ የሆነ ነገር አለኝ ቀሪውን ለንደዚህ አይነት ችግር ባውለው ለእኔም ለልጆቼም ታሪክ ነው። ደሴቱን ገዝቼ ለስደተኞቹ መኖሪያ ቤት፣ትምህርት ቤት፣ሆስፒታል እና የመሳሰሉትን አሟልቼ ማኖር እችላለሁ አለምም ከጭንቀት ይገላገላል ፣ስደተኞቹም ያርፋሉ አገራቸው ሰላም ሲሆን ከፈለጉ ይመለሳሉ ካልፈለጉም እዚሁ መኖር ይችላሉ። ለእናንተም ይህን የምናገረው ለጉራ ሳይሆን ለአለም መልእክቴን እንድታስተላልፉ ነው ” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። አለም በንግግሩ ተደንቋል። ይፈጸም አይፈጸም እንደሁ ወደፊት እናያለን።እንዲህ ነው ባለሃብት ማለት!! አለም በጭካኔ እና በስግብግብነት ዝም ብሎ ሲመለከት ከኪሱ መዥረጥ አድርጎ “ምን ያንጫጫችሗል?ያውላችሁ ገንዘብ ደሴት ግዙና አስቀምጧቸው” የሚል ጀግና።
እኔ ግን አንድ ነገር ፈርቻለሁ። የእኛው ሚሊዬነር ይህንን ሰምተው ነሸጥ አድርጓቸው “ማን ከማን ያንሳል። በዝናብ እጥረት ምክንያት አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 4 ሚሊዬን ኢትዮጵያዊያን በጣና ሃይቅ አንዱ ደሴት ላይ ጠቅልላችሁ አስቀምጡልኝ ዝናብ እስኪዘንብ ድረስ እቀልባቸዋለሁ” እንዳይሉ ነው።
