ፖለቲካ ቆሻሻ የሚሆነው ቆሻሻ አእምሮ ያላቸው ሲነኩት ነው! (የትነበርክ ታደለ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Politics is a dirty game የሚለውን የፖለቲካን ቆሻሻነት የሚነግሩን ብዙ ሰዎች አሉ። ይህን ከሚያወሩት ዋናዎቹ እኛ ወደ ፖለቲካ እንዲች ብለን እንዳናይና ስለ ፖለቲካ እንዳናወራ በሚፈልጉ ነውረኛ ፖለቲከኞች የሚነዛ ቧልት ሲሆን ሌላው ደግሞ ብዙ የፖለቲካ ብልግናን የሚፈጽሙ ባለጌ ፖለቲከኞችን ያዩና የተመለከቱ የዋሀን የሚናገሩት ነው።
ነገር ግን ፖለቲካ ቆሻሻ ጨዋታ የሚሆነው ቆሻሻ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እጅ ሲገባ ብቻ ነው። እስከዚያው ግን ፖለቲካ የሰው ልጆችን ኑሮ ለማቅለል፣ የተወሳሰበውን ለማፍታታት፣ ለችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግና የሰው ልጆችን የአብሮነት ኑሮ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በሰው ልጆች ፍላጎት የተፈጠረ ምድራዊ የአስተዳደር ጥበብ ነው።
እርግጥ ነው ፖለቲካ የሰው ልጆች ክብር በማይገባቸው ራስ ወዳድ አውሬዎች እጅ ሲገባ አስፈሪ ይሆናል። እነዚህ አውሬዎች ደግሞ ስራቸው ሰዎችን ከታች ወደ ላይ ከፍ ማድረግ ሳይሆን የራሳቸውን መሀይምነት መሸፋፈኛና ከወንጀለኛነት ማምለጫ ያደርጉታል።
በተለይ እንደኛ ባለች ሶስት ሺ አመት ሙሉ በመንግስት አስተዳደር ስር የቆየች ነገር ግን ዛሬም እንደ ጀማሪ “መንግስት ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ህዝብ ባለባት ሀገር የምናያቸው ፖለቲከኞች የሚሰሩት ውርዴ ሴራ ልጆቻችንን ወደ ፖለቲካ ዞር ብለው እንዳያዩ የሚያደርግ ነው።
እነዚህ ሰዎች (ተቃዋሚም ደጋፊም ቢሆኑ) አብዛኞቹ የሰው ክብር ፈጽሞ የማይገባቸው፣ በስድብና በንቀት የተሞሉ፣ ከራሳቸው ሀሳብ ሌላ ለመስማት ያልተዘጋጁ፣ የልዩነት ሀሳብ የማይቀበሉ ከመሆናችውም ባሻገር የተለየ ሀሳብ ያለውን እንደ አውሬ የሚፈሩ ድንጉጣን ናቸው።
እነዚህ የሀገርና የህዝብ ልዩነትና አንድነት ሳይገባቸው ስለሀገር የሚደሰኩሩ ኩርማን እውቀት የተሸከሙ ሲሆኑ አጠገባቸው ስላለ ወንድማቸው ምንም የማይኮረኩራቸው ነገር ግን በቅዠት በሚስሏት “ሀገር” የተመሰጡ፣ ሰለኔ ወይም ስላንተና ስላንቺ ሳይሆን በሀሳባቸው ስላለ “ኢትዮጵያዊ” የሚባዝኑ ባተሌዎች ናቸው።
ይህን ሁሉ ያየ የተመለከተ “እውነትም ፖለቲካ ቆሻሻ ጨዋታ ነው!” ቢል እንዴት ይፈረድበታል? አንተን እና ችግርህን አጠገቡ አስቀምጦ “ሀገሬ!” እያለ ቢያላዝን እንዴት ታምነዋለህ? ኢትዮጵያዊኮ አንተ ነህ! ኢትዮጵያዊኮ አንቺ ነሽ!
ጠቅለል ባለ ንግግር፤ ፖለቲካ የጋራ ችግራችንን የምንፈታበት የንግግር ማሽን እንጂ እንደሚባለው የሚገድል ኤሌክትሪክ አይደለም። የሚያስፈልገን አንድ ነገር ብቻ ነው። ሰፋ ሰፋ አድርጎ ማሰብ።
ሀገር ማነች? ሀገር የት ነው ያለችው? ይህ ከጎኔ ያለው ወገኔ ምን ጎደለበት? ለሀገሬ የኔ ድርሻ ምንድነው? የጋራ ችግራችንን እንዴት ነው መፍታት የምንችለው?….ፖለቲካ እሱ ነው። ይሄ ደግሞ እንዴት ቆሻሻ ጨዋታ ሊሆን ይችላል? ዋናው ነገር ቆሻሾች እንዳያቆሽሹት መከላከል መቻላችን እንጂ ፖለቲካስ ምርጥ የችግር መፍቻ ዘዴ ነው!