አንዳርጋቸው ፅጌን በሉት ወይስ አስበሉት?
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ
ሰሞኑን አንድ ዜና ብቅ ብላ ጥፍት ብላለች ። “ለአንዳርጋቸው መያዝ ምክንያት ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ የሕወሐት ቀኝ እጅ በአስመራ ተያዙ” የሚል ርእስ ነበራት ። ባለፈው ሳምንት ኦገስት 4 ቀን ወጥታ የነበረችው ይህች ዜና ፤ ዛሬ በአዳዲሶቹ የሻእቢያ ወዳጆች ጎጂ ዜና ተብላ ተቆጥራ ነው መሰለኝ ከዜና ቋቱ (archive) ላይ እንኳ እንድትነሳ ተደርጋለች ።ለማንኛውም በሚቀጥለው ሊንክ ላይ ተለጥፋ ነበር ። ዜናዋ ትጠቅማለች በሚል በራሴ የሰነድ መዝገብ ውስጥ አኑሪያት ስለነበር ፤ ለዚህ ፅሁፌ መነሻ ይሆነኛል ያልኩትን ፍሬ ሃሳብ ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀንጨብ ቀንጨብ አድርጌ አቅርቤዋለሁ ። (ሙሉውን ጽሁፍ እዚህ ላይ በመጫን ማንበብ ይቻላል።)
«ከወደ አስመራ አዳዲስ ወሬዎች እየተሰሙ ነው የመላዋ ኤርትሪያ የፀጥታ ኃላፊ በቁጥጥር ስር ውለዋል ። ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስን ከስልጣን ለማውረድ አሲረዋል በሚል አስራ አምስት ባለስልጣናት ወህኒ አስገብተው የነበሩት የኤርትሪው የፀጥታ ሹም ተራቸው ደርሶ ወህኒ ወርደዋል፡፡ከአስመራ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የጸታው ሹም ለበርካታ ዓመታት የኤርትራን መረጃ ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያ ሲያቀብሉ ኖረዋል ። …የአንዳርጋቸው ፅጌ በወያኔ እጅ መውደቅ ሚስጥሩም በእኚህ ሰው እጅ ነው አጠቃላይ እኚህ ሰው ለወያኔ ወሳኝ ሰው የነበሩ ሲሆን ለኤርትራ ደግሞ ራስ ምታት የነበሩ ናቸው ። ግለስቡ በወንድማቸው ስም አዲስ አበባ ላይ ባለ አሥር ፎቅ ህንፃም ማስገንባታቸው አስመራ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል ። በኤርትራው ፕሬዝደንት ክፉኛ ጥርስ የተነከሰባቸው እኚህ ሰው… የፀጥታ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን አብረሃ ካሳ ናቸው ። እኚሁ ሰው ከትናንት በስቲያ ባልታወቀ ቦታ ታስረዋል ፤ ይላል ዜናው ። ቀጥሎም ሹም አብረሃ ካሳ ዛሬ የወያኔ ሰላይ ሆነው በውል የተረጋገጠ:-
1. አዲስ አባባ ላይ ባለ አስር ፎቅ ህንጻ ፣
2. ጋምቤላ ሰፊ እርሻ ፣
3. አፍዴራ የጨው ማምረቻ እንዲሁም ፤
4. አዲስ አበባ ቦሌ መድኃኒዓለም ጀርባ ቋሚ ነዋሪነቱን ሱዳን ካደረገ ነቢል አልቁሙስ (አል-ኩሙስ) ከተባለ ግብፃዊ ጋር በሽርክና ዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅት ፤ በወንድማቸው ስም ከፍተው ቢዝነሱ ውስጥ ሲጨማለቁበት በምላሹም ወያኔዎች የኤርትሪያን ፣ የግንቦት ሰባትን የአርበኞች ግንባርን መረጃዎች አንድ በአንድ ሲዘረግፉ ኖረው ተደርሶባቸው በተራቸው ጨለማ ቤት ተዘግቶባቸዋል ።» ትላለች ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያውያን የዜና አውታሮች ላይ ብቅ ብላ ጥፍት ያለችው ዜና። የአንዳርጋቸውን መያዝ አስመልክቶ ኤልያስ ክፍሌ በEthiopian Review ላይ በጊዜው ለቆት የነበረው ዜናስ ምን ይል ነበር ? ለማስታወስና ለግንዛቤ ያህል ቀጣዩን ይህን ሊንክ ይመልከቱ ።
ከላይኛዋ ዜና መውጣት በኋላ ባለፈው አመት ከአንዳርጋቸው ፅጌ መያዝ ጋር ፤ ከተለያዬ አቅጣጫ የተሰጡ አስተያየቶችንና የመረጃ ዜናዎችን መልሼ መላልሼ ደግሜ ደጋግሜ ተመለከትኳቸው ። እያንዳንዳቸው እንደ አቅራቢዎቻቸው በውስጣቸው ያዘሏቸው እውነቶችን አግኝቼባቸዋለሁ ።
ከግብፅ አብዮት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው የሞሃመድ ሙርሲ እስላማዊ መንግስት ፤ ሁሉንም የግብፅ ተቃዋሚዎች ፓርላማው ላይ ጋብዞ ፤ ኢትዮጵያ ለአባይ ግድብ ያቀረብንላትን ስምምነት የማትቀበል ከሆነ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች እንረዳለን ሲል ዝቶ ነበር ። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳርጋቸው አስመራ ከሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ የመረጃ ሰዎች ጋር ተነጋግሯል ። አንዳርጋቸው ያቀረበውን ጥያቄ ግብፆች ለመንግስታቸው እንደሚያሳውቁ ተስፋ ሰጥተውት ይለያያሉ ። ግብፆች ኤርትራ ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ለመርዳት ቢስማሙም በአገራቸው በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ የተነሳ ከኢትዮጵያ ጋር ግልፅ ፍጥጫ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት አልነበራቸውም ።
ሆኖም ግን አንዳርጋቸው ከግብፆች መልሱን ያገኘበት መንገድ የሚደንቅ ነበር ።መልሱ በቀጥታ ለራሱ ለአንዳርጋቸው ሳይሆን በኤርትራ መንግስት በኩል ነበር የመጣለት ። ሻእቢያ ለግንቦት ሰባት በየ6 ወሩ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ሊሰጥ መዘጋጀቱን ግልፅ ያደርጉለታል ። አንዳርጋቸው ለአመታት ኤርትራ ውስጥ በመኖር የተረዳው ሁኔታ አለ ። ኤርትራ ባላት የኤኮኖሚ ችግር የተነሳ ፤ አንድ ሚሊዮን ዶላር በየአመቱ ለተቃዋሚ ልትሰጥ ይቅርና ለራሷም ብትሰጣት እጅ ነስታ የምትቀበል አገር እንደሆነች ያውቃል ።
በኤርትራ በኩል የሚደረገው ትግል በሻእቢያ እንቅፋትነት የተጠበቀውን ይህል መራመድ አልቻለም ። ስለዚህ አንዳርጋቸው ወደ ኡጋንዳ በመሄድ በኡጋንዳና በደቡብ ሱዳን በኩል ትግሉ ሊገፋ የሚችልበትን ሁኔታ አጠና ። ስለዚህም ከጉዞዎቹ በአንዱ ወደ ካይሮ ጎራ ብሎ ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር ስለ እርዳታው ጉዳይ ይነጋገራል ። ግብፆቹም እርዳታውን በቀጥታ ለእናንተ መስጠት አንችልም ። ይህን የፋይናንስ እርዳታ ማድረግ የምንችለው እናንተን እስፖንሰር በሚያደርግ መንግስት በኩል በሚደረግ የሽፋን ስምምነት ብቻ ነው ። ለዚህም የኤርትራ መንግስት ፈቃደኝነቱን አስይቷል ። እርዳታውን በኤርትራ መንግስት በኩል ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እየላክን ነው ፤ ይሉታል ። የገንዘብ እርዳታውን አስመልክቶ አንዳርጋቸው ካይሮ ድረስ በመምጣት ከእነሱ ጋር መነጋገሩንም ግብፆች ለሻእቢያ አሳወቁ ። ይህ አንዳርጋቸውን ሻእቢያ ጥርስ ውስጥ ያስገባ አጋጣሚ ሆነ ።
አንዳርጋቸው ከመያዙ ከወራት ቀደም ብሎ !
ከሻእቢያ ጋር በመተባበር የተጀመረው የግንቦት 7 ን ሰራዊት የማቋቋም ጥረት ፤ አመርቂ ውጤት ባለማሳየቱ አንዳርጋቸው በሻእቢያ ላይ ተስፋው እየተሟጠጠ ነበር ። ግልፅነትና መተማመን በሌለበት ሁኔታ አብሮ መስራት እንደማይቻል ተረድቶታል ። ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎችም መልስ ይነፈገዋል ። በተለይ ተዋጊ ወታደር ለማዘጋጀት ኤርትራ የወረደው አንዳርጋቸው ፅጌ ሰራዊቱ ይገኝበታል ወደሚባለው ወደ ሃሬና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ እንዳይወርድ መከልከሉ ተስፋ አስቆርጦታል ። በነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት አንዳርጋቸው ምናልባትም ወደ ኤርትራ እስከነአካቴው እንደማይመለስም ለራሱ ሳይወስን አልቀረም ።ለመጨረሻ ጊዜ ከአስመራ ሲወጣም ሻእቢያ አንዳርጋቸውን ኤርፖርት ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ካልሲውን ሁሉ አስወልቀው በሚያዋርድ መልኩ ፈትሸውታል ። አስመራን ለቆም ወደ ለንደን በርሯል ።
በነገራችን ላይ ሻእቢያዎች እንዴት ሰው እንደሚያዋርዱ አንድ አጋጣሚ ላቅርብ ። ስለ ደረሰው ድርጊት ሁላችሁም ሰምታችኋል ። ግን በይፋ ሳይነገር አየር ላይ ሲንሳፈፍ የነበረ ዜና ነው ።
(2009 ዓ.ም እ.ኤ.አ. አቆጣጠር ፤ አስመራ ላይ አንዳርጋቸው ከምሽቶቹ ባንዱ ቀን መኖሪያ ቤቱ ይንኳኳል ። የሚጠብቀው እንግዳ ስላልነበረው ግራ ቢጋባም በሩን ከፍቶ ሲመለከት ፤ በዚያ ሰአት ሃሬና ማሰልጠኛ ጣቢያ መገኘት የሚገባቸው ሁለት የግንቦት 7 አባላት በሩ ላይ ቆመዋል ። ሰዎቹ ወደ አስመራ እንደሚመጡ ለአንዳርጋቸው የነገረው አልነበረም ። እንዴት ወደ አስመራ እንደመጡ አንዳርጋቸው ሰልጣኞቹን ይጠይቃል ። ኮለኔል ፍፁም እንዳመጣቸው ይነግሩታል ። ወደ ውስጥ እንዲገቡ ይጋብዛቸዋል ። ስሜታቸውም አንደበታቸውም ለጠብ የተዘጋጀ ነበር ። ኮለኔል ፍፁም ሰዎቹ ቅሬታ እንዳላቸው ቀድሞ ተገንዝቧል ። በራሱ መኪና አስመራ ድረስ አምጥቷቸዋል ። ከሃሬና ማሰልጠኛ ጣቢያ እስከ አስመራ ድረስ በመኪና ስምንት ሰአት ይወስዳል ። በዚያ ጉዞ ላይ ኮለኔል ፍፁም እነዚህን የሃሬና ሰልጣኞች ምን እየመከረ እንዳመጣቸው ከድርጊታቸው መረዳት ቢቻልም ፤ በቀጥታ ምን ምን ሲላቸው እንደነበር ዛሬ ማወቅ አይቻልም ። ወደፊትም አይታወቅም ምክንያቱም ከዚህ ድርጊት በኋላ የነዚህ ሰዎች መዳረሻ በትክክል እስካሁን አይታወቅም ።
በዚያን ጊዜ ኮለኔል ፍፁም ከአንዳርጋቸው ጋር ያልተግባቡበት ሁኔታ እንዳለ ግልፅ ነበር ። ኮለኔል ፍፁም አንዳርጋቸውን ቅስሙ ሰብሮ በታዛዥ ሰራዊቱ ፊት ሙሉ የበላይነት እንዳይኖረው ማድረግ ዋና ግቡ ነው ። በሰራዊቱ እምነት የሌለው መሪ ደግሞ ሁሌ ከለላ ይጠቃል ። ኮለኔል ፍፁም ይህን መሰል ድርጊት በተደጋጋሚ በተለያዩ መሪዎች ላይ ፈፅሟል ። ስለዚህ ከሓሬና የመጡት ሰዎች የራሳቸው ብሶት ቢኖራቸውም ፤ ኮለኔል ፍፁም ለቀቅ ብሎ ለአካላዊ ድብድብ እያበረታታ አዘጋጅቷቸው ነበር ። ሰዎቹም በብልግና ከአንዳርጋቸው ጋር መደባደብ ይጀምራሉ ። አንዳርጋቸው ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶበትም “እንዳ ኮርያ” በሚገኘው “ሰንበል” ሆስፒታል ህክምና ተደርጎለት የዛኑ ቀን ወደቤቱ ተመልሷል ። በሁኔታው ላይ ላፕ-ታፑን ሰብረውበታል ፤ ከኪሱ ውስጥ የነበረውንም $800 ዶላር ዘርፈውታል ። ፀቡ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ኮለኔል ፍፁም ከአንዳርጋቸው መኖሪያ አጥር ውጪ መኪናው ውስጥ ሆኖ ተደባዳቢዎቹ ተልእኳቸውን ጨርሰው እስኪመጡ ይጠብቅ ነበር ። ኮለኔል ፍፁም ይህን የመሰለ የወረደ ሰብእና ያለው ሰው ነው ። አንዳርጋቸው ይህን ድርጊት ያቀነባበረው በኮለኔል ፍፁም አማካይነት ሻእቢያ እንደሆነ እዚህ አሜሪካ ላሉና ለነበሩ የስራ ባልደረቦቹ በግልፅ ተናግሯል ።)
ወደ ጀመርኩት አቢይ ጉዳይ ልመለስ ። ከላይ እንደገለፅኩት ሻእቢያዎች አንዳርጋቸውን በአስመራ ኤርፖርት ካልሲውን ጭምር አስወልቀው ፈትሸውታል ። ከዚህ ጋር ይያያዝ አይያያዝ ባላውቅም ያን ሰሞን የግንቦት 7ቱ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፤ አንዳርጋቸው ፅጌ ወደ ለንደን ከተመለሰ በኋላ ፤ “አንዳርጋቸው የኤርትራ ተልእኮውን አጠናቋል” ሲል መግለጫ መስጠቱም ይታወሳል ።
አንዳርጋቸው ፅጌ ወደ ለንደን ከገባ ባኋላ ለወራት ወደ ኤርትራ አልተመለሰም ። አስመራ ላይ ኑሮውን ከመሰረተ ጀምሮ ይህን ያህል ለረዘመ ጊዜ ከአስመራ ጠፍቶ አያውቅም ። ሻእቢያ አንዳርጋቸው ፅጌ ማኩረፉን ቢረዳም ፤ የት ይደርሳል ከሚል ግምት መጀመሪያ ላይ ከጉዳይ አልጣፈውም ነበር ። በኩርፊያ መቅረቱን ግን አልወደደለትም ፤ በተለይ ደግሞ ከግብፅ ከኡጋንዳና ከደቡብ ሱዳን በኩል እንቅስቃሴ ለማድረግ የጀመረው ጥረት ሻእቢያን በእጅጉ አስቆጥቶታል ። አንዳርጋቸው ስለሻእቢያ ብዙ ነገሮችን አውቋልም ተረድቷልም ። አንዳርጋቸው በዚያው ቀልጦ ከቀረና ፤ በተለይ ከግብፅ ጋር የፈጠረው ግንኙነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ ብዙ ነገሮች ሊበላሹ ስለሚችሉ ፤ ባስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ተገቢ እንደሆነ ሻእቢያ አምኖበታል ።
አንዳርጋቸው የተማረ ሰው ነው ። አንዳርጋቸው በ60ዎቹ የተማሪ ትግል ተሳትፎ የነበረው ሰው ነው ። አንዳርጋቸው ፖለቲካ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው ። አንዳርጋቸው ከወያኔዎችም ጋር አዲስ አበባ የገባ ሰው ነው። ብዙ ነገሮችን መረዳት የሚችል ሰው ነው ። በአጠቃላይ አናሊቲካል ሰው ነው ። ቀላል ግምት የምትሰጠው ሰው አይደለም ። ስለዚህ አንዳርጋቸው አኩርፎ ከኤርትራ እንደወጣ መቅረት የለበትም ። ዝርዝር ሁኔታዎች ባይቀመጡም ፤ ያለብዙ ግርግር እና ጫጫታም አንዳርጋቸውን ዝም የማሰኘቱ ተገቢነት በሻእቢያ ታምኖበታል ። ስለዚህም እንቅስቃሴውን መቆጣጠር ይቻል ዘንድ አባብሎ መመለስ ተገቢ ነው ፤ የሚል እቅድ የሻእቢያ የስለላ ድርጅት ይነድፋል ። በዚህ መልክ ነው አንዳርጋቸው እንደገና ወደ ኤርትራ እንዲመለስ የተጋበዘው ። ወደ ኤርትራ የተጋበዘው አንዳርጋቸው ብቻ አልነበረም ። ሌሎችም የግንቦት 7 ስራ አስፈፃሚ አባላት ነበሩ ። እነዚህ ሰዎች ከአንዳርጋቸው ጋር አብረው አስመራ ለመጓዝ ትኬታቸው ተቆርጦ ቪዛቸውም ተዘጋጅቶ ነበር ። (አንዳርጋቸው ወደ አስመራ ሲያቀና ለምን እነሱ ወደኋላ እንደቀሩ ወደፊት የምንመጣበት ጉዳይ ይሆናል ።)
የመጨረሻይቱ ቀን!
ጁን 23 ቀን 2014 እ.ኤ.አ. ከለንደን ቤተ ሰቦቹን የተሰናበተው አንዳርጋቸው ፅጌ ፤ በሰላም ዱባይ ይገባል ። የአውሮፕላን ትኬቱ የተቆረጠው በኤርትራ ኤርላይንስ ትኬት ኦፊስ (Eritrean Airlines ticket office) በኩል ነው ። ተስፋየ ገ/አብ ዲሴምበር 12 /2014 የአንዳርጋቸውን ጉዳይ በተመለከት በአስመራ ከወዳጁ አገኘሁት ያለውን መረጃ ጠቅሶ እንዲህ ብሎ ነበር። (ወዳጅ ተብሎ የተጠቀሰው የሻእቢያ መረጃ ሰው ይሆን?)
“…ትኬቱ በኤርትራ አየር መንገድ ከዱባይ በቀጥታ ወደ አስመራ የተቆረጠ ነበር። ለምን በየመን በኩሌ እንደቀየረው አልገባኝም?”ይላል። ሙሉውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ።
በእውነት አንዳርጋቸው ራሱ ነው ትኬቱን የቀየረው? ወይስ በተቀናበረ መልኩ የዱባይ አስመራ በረራ ሞልቷል በሚል ትኬቱ ወደ ሰንዓ የመን እንዲቀየር ተደረገ ? ከዚህ በኋላ ነው የተለመደ በሚመስል መልኩ አንዳርጋቸውን የአዞው አፍ ውስጥ እንዲማገድ የተዘጋጀው ።
///
ቀኑ ረቡዕ ነው ። ከሰአት አኋላ ። እንደተለመደው የፀሃዩ ሙቀት ሲበረታ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ከቤት ስለማይወጣ ከተማይቱ ፀጥ እረጭ ብላለች ። የከተማይቱ ውሾች እንኳ በየዛፉ ጥላ ስር ዝርግትግት ብለው ያሸልባሉ ። ይህን በመሰለ ሰአት ግን የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ሁሉ ቆሟል ማለት አይደለም ። በየቤቱ ለጫት ተፈርሿል ። በየትኛዋም የከተማይቱ ክፍል የሚገኙት ትናንሽ መደብሮች እንኳ ለቂምኻው ማዳመቂያ የሚለኩሷቸው ሰንደሎች ሽታ ከየትም አቅጣጫ ያውዳል ። አንዳንዱ መርቅኗል ፤ሌላው ለምርቃና እየተንደረደረ ነው ። የድሬዳዋ እብዶች እንኳ የሰበሰቡትን ገራባ ከዛፎች ስር አርፈው የሚቅሙበት ሰአት ነው ። በዚህ ሰአት ነበር ከድሬዳዋ አየር ማረፊያ ባልተለመደ መልኩ ቅጠልያ ወታደራዊ ቀለም ያለው የአየር ሃይል አውሮፕላን ወደምስራቅ አቅጣጫ የነጎደው ። የአውሮፕላን ድምፅ ለድሬዳዋ አዲስ ስላልሆነ ማንም ከቁብ የቆጠረው አልነበረም ። ቀስ እያለ ድምፁም አውሮፕላኑም በሞቃታማው ምድር አየር ላይ ተሰወሩ ። ወዴት እያመራ ይሆን? ይህ ለድሬዳዋ ሰው ጥያቄ አልነበረም ። አውሮፕላኑ የመዳረሻውን አየር ማረፊያ ጎማው ሊነካ የ45 ደቂቃ በረራ ማድረግ ይጠበቅበታል ። ከአብራሪውና ከረዳቱ ሌላ አውሮፕላኑ ጥቂት ሲቪል የለበሱ ሰዎችን አሳፍሯል ። ማንም የሚነጋገር አልነበረም ። ከአውሮፕላኑ ሞተር በስተቀር የሚሰማ ድምፅ አልነበረም ።
///
ዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ለአንዳርጋቸው ፅጌ አዲስ አይደለም። ደጋግሞ አይቶታል። ስለዚህ የሚያስደንቀው አዲስ ነገር አልነበረም። ወደ አስመራ የሚበርበት የአውሮፕላን የበረራ ሰአት እስኪደርስ ድረስ በዱባይ ኤርፖርት ከሚገኙት ካፌዎች በአንዱ ከሁለት ኤርትራውያን ጋር ቡናውን ፉት እያለ ቁጭ ብሏል። እነዚህ ኤርትራውያን ዱባይ ኤርፖርት ሲያርፍ ጀምሮ አልተለዩትም።
የዱባይ አስመራ በረራ ሰአት ደረሰ ። አንዳርጋቸው ተራውን ለመጠበቅ ተሰለፈ ። ቦርዲንግ ፓሱን (boarding pass) አሳይቶ እቃዎቹን ማስፈተሽ ሊጀምር ሲጠጋ ፤ አስተናጋጇ በዚህ በረራ የመንገደኞች ዝርዝር ውስጥ የእርስዎ ስም ፤ የለም ትለዋለች ። ከአስተናጋጇ ጋር የሚደረግ እሰጥ አገባ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ አንዳርጋቸው ያውቃል ። በዚህ ሰአት የተፈጠረውን ሁኔታ በአይናቸው ይከታተሉ የነበሩት ሁለቱ ኤርትራውያን አንዳርጋቸውን ለመርዳት ይንደረደራሉ ። ሁኔታውን ከገለፀላቸው በኋላ ማናጀሩ እንዲጠራለት መጠየቁን ይነግራቸዋል ። አንደኛው በተለመደው አበሻዊ ዘይቤ “ለኔ ተወው” አይነት የአንዳርጋቸውን ፓስፖርት ይቀበለዋል ። ሌላኛው ኤርትራዊ ጓደኛው ጉዳዩን እስኪጨርስ ድረስ አንዳርጋቸውን ገለል ያደርገዋል ። የመጀመሪያው ኤርትራዊ ፓስፖርቱን ይዞ ከማናጀሩ ጋር መነጋገር ጀመረ ። ሌላኛው ኤርትራዊና አንዳርጋቸው ሁኔታውን በርቀት ይከታተላሉ ነበር ። ከተወስኑ ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያው ኤርትራዊ ወደ አንዳርጋቸው ተመልሶ ፤ ያንተ ትኬት በስህተት ተደርቦ ተመዝግቧል (double-booked)። ስለዚህ እዚሁ ከኛ ጋር ቆይና በሚቀጥለው በረራ ትሄዳለህ ይለዋል ። የሚቀጥለው በረራ ከሶስት ቀናት በኋላ መሆኑንም ይገልፅለታል። ጨምሮም ፤ የለም ዛሬውኑ አስመራ መግባት አለብኝ የምትል ከሆነ ደግሞ በየመን ሰንዓ በኩል ሌላ በረራ ስላለ ያንን ሊረዳን እንደሚችል ማናጀሩ ቃል ገብቶልኛል ፤ ይለዋል ። ( ለመሆኑ ማነው ወደ አሰበበት ቶሎ ለመድረስ የማይጓጓ!!) አንዳርጋቸው እየቀፈፈውም ቢሆን ቶሎ ወደ አስመራ ለመግባት ባለው ጉጉት የተነሳ ይስማማል ። ታዳኙን ወደ አዞው አፍ ውስጥ ሊያስገቡት አዘጋጁት ።
አንዳርጋቸው ወደ አውሮፕላኑ ከመግባቱ በፊት በነበረው ሰአት በረራው መለወጡንና በየመን በኩል ወደአስመራ ለመሄድ መዘጋጀቱን ለዚህም የተቀበሉት ኤርትራውያን ሁኔታዎችን እንዳመቻቹለት ለቅርብ ወዳጆቹ ለክፉም ለደጉም ሲል በስካይፕ አሳውቋቸዋል ።
///
የአንዳርጋቸውን መያዝ አስመልክቶ ከወያኔ ዜና ማሰራጫዎች ከዚህም ከዚያም የተሰባሰቡት ዜናዎች የፈጠሩት ስዕል ደግሞ ይህን ይመስላል ። ከዱባይ የመን ሰንዓ የሚበረው አውሮፕላን ከዱባይ ሲነሳ ፤ ከድሬዳዋ የተነሳው ወታደራዊ አውሮፕላን የመን ሰንዓ አየር ላይ ለማረፍ እያንዥዣበበ ነበር ። ሰንዓ አውሮፕላን ጣቢያ ከኤርፖርቱ አስተዳዳሪና ሴኩውሪቲ መኮንን ጋር አንድ ኢትዮጵያዊ እየተነጋገረ ነበር ። በድንገት የኢትዮጵያዊው ስልክ አቃጨለ ። ስልኩን አነሳና “ሃሎ” አለ ። ከስልኩ የወዲያኛው ጫፍ “እቃው ከአስር ደቂቃ በፊት ተነስቷል ። ወደ ሰንዓ እየመጣ ነው ። በሰአቱ ይደርሳል” የሚል መልእክት አስተላልፎ ይዘጋል ። እንደማይደርስ የለም የዱባዩ አውሮፕላን ሰንዓ አረፈ ። የየመን ሴኩሪቲ ሰዎች ወደ አውሮፕላኑ ገቡ ። አንዳርጋቸውን እንደሚፈልጉት ገልፀው ከአውሮፕላኑ ይዘውት ወረዱ ። ብዙም ሳይርቅ ቆሞ ወደነበረው የኢትዮጵያ አየር ሃይል አውሮፕላን ወሰዱና ለአበሻዎቹ ሰዎች አስረከቡት ። ታዳኙ በታቀደው መሰረት ወደ አዞው አፍ ገባ ። ሞተሩን ሳያጠፋ ታዳኙን ይጠባበቅ የነበረው የጦር አውሮፕላንም ከመንደርደሪያው ላይ ተነስቶ ወደ ምእራብ አቅጣጫ ሲከንፍ ጊዜ አልወሰደበትም ።
የፅሁፌ መግቢያ ላይ የጠቀስኳት ዜና ከዚህ አጋጣሚ ጋር ትያያዝ ይሆን? የሻእቢያው የደህንነት ሹም አንዳርጋቸውን አሳልፎ በመስጠት የሻእቢያን እቅድ በሚገባ ፈፅመዋል ። ከወያኔ ለሚያገኙት ጥቅም ሲሉ ደግሞ አንዳርጋቸውን ወደ አዞው ሆድ ውስጥ ከተውታል ብየ ብጠረጥር ጥፋት ይሆንብኝ ይሆን? እናንተም ሁኔታውን አጢኑት ።
በዚህ ሁኔታ ላይ በአንዳርጋቸው ጭንቅላት ውስጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት ። ምንድነው እየሆነ ያለው ? ማነው አሳልፎ የሰጠኝ? የትግል ጓዶቼ ናቸው? ወይስ ሻእቢያ ነው? ለምን? ልጆቼ ቤተሰቤ እንዴት ይሆኑ ይሆን? ወያኔዎቹስ ምን ያደርሱብኝ ይሆን? አይ ኤርትራ! አይ ሻእቢያ!
አንዳርጋቸውን ወኔዎች በሉት። ሻእቢያዎች ደግሞ አስበሉት። አለቀ አበቃ ኦሮማይ!!
ኦገስት 12/2015
ላስ ቬጋስ ኒቫዳ ።