” ደሙን ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት ” ( ሄኖክ የሺጥላ )
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በእውነት ወያኔ ምን በደለ ? እንደው ሀገር ባለማ ! ድልድይ በሰራ ፣ ግድብ በቆፈረ ! ውይ የሰው ነገር ! አሁን ማን ይሙት ወያኔ የደርግን ያህል ጨካኝ ሆኖ ነው እንዲህ የምትረባረቡበት ? እናንተ እኮ አታፍሩም ይሄኔ ፣ ከግድብ የመናገር ነጻነት ይቅደም ፣ ከውሃ ማቆር የሰው ልጆች እኩልነት ይቅደም ፣ ከልማታዊ አርሶ አደርነት የሰብአዊ ክብር ና የመንፈስ ልዕልና ይቅደም ፣ የተጻፈ ከማንበብ ( ዘላለማዊ ክብር ለክቡር ጥቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሚለውን አይነት ማለት ነው ) የመጻፍ መብት ይከበር ፣ በየመንገዱ ሥራ አጥቶ ከመደርደር ፣ የመሰለፍ መብታችን እውቅና ይሰጠው ፣ አስራ አራት ክልል በካርታ ላይ ከማስቀመጥ ፣ በፈለግነው ክልል ሄዶ የመስራት መብታችን ይጠበቅ ፣ የዜጎች እኩልነት በዜና እና በዝና ሳይሆን በነባራዊው ዓለም ፣ በለት ተለት ሕይወታችን ይተግበር እና ወዘተ ትሉ ይሆናል ። በእውነት አታፍሩም ! አሁን እስኪ ማን ይሙት ፣ ድልድይ ይበልጣል ፣ የህዝቦች እኩልነት ? ለኛ የመጻፍ ነጻነት ይሻለናል ወይስ የማቃጠር መብት ? ዜጎች ደሞ እኩልነት ፣ እኩልነት ፣ እያላችሁ የምታላዝኑት ፣ እንኳንስ ይቅርና በዜግነት መብት በቁመት እኩል የሆኑ ሰዎች ማግኘት ዘንድሮ ቀላል ነገር ነው ወይ ? ደሞ በተወደደ ወረቀት መጻፍ ፣ መጻፍ ፣ መጻፍ ። አማራ ድሮም መጻፍ ይወዳል ! ክስ ይወዳል! ምናለ ባትጽፉ አትሞቱ ፣ እውነት ባትናገሩ አትሞቱ ፣ ስለ ሚኒሊክ ባትናገሩ አትሞቱ ፣ ስለ በላይ ዘለቀ ባታወሩ አትሞቱ ! አሁን የደደቢት ታሪክ አልበቃ ብሎ ነው አዳሜ የ አጼ ቴዎድሮስን ታሪክ የሙጥኝ ያለው ? አረ ምን እሱ ብቻ ፣ ሀገር ፣ ሀገር ፣ ሀገር ትላላችሁ ? ሀገር ምንድን ነው ? ባንዲራ ፣ ባንዲራ ፣ ባንዲራ ? ባንዲራ ድልድይ አይሆን ? ምንነት አይበላ ! ነጻነት አይሸጥ ። ይህ የአማራ ተረት ነው ። አሁን እስኪ ማን ይሙት ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ኮብል ስቶን ነው ወይስ አክትቪስት ? “እኛ ( ወያኔ-ትግሬዎች ) እኩል ሳትሆኑ እኩል አደረግናችሁ ፣ ከጨቋኝ ፊውዳል እጅ ታደግናችሁ ፣ ዛሬ በራሳችሁ ቋንቋ መናገር ስትችሉ ፣ የፈቀዳችሁትን ባንዲራ አወጣችሁ ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ያለገደብ ተከበረ ፣ ታዲያ ይሄም አልበቃም ብሏችሁ ፣ እኛ ታግለን ባመጣነው ፣ ስልጣን ላይ መቀመጥ አማራችሁ ? ” ። ታዲያ ለምንድን ነው ይህን ” ደሙ ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት የምትፈታተኑት ? ” ተዉ ግን ፣ ተው ? እኔ ልሙት አሁን የወያኔ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው ? ይሄኔ እኮ << ምርጫ 100% አሸነፈ ፣ ነብዩን ገደለ ፣ የእስልምና ኮምቴዎችን አሰረ ፣ በስልጣን ላይ ያሉት አብዛኛው ካንድ ብሔር የተመረጡ ናቸው ፣ በዘር ተደራጅተው ሀገሪቷን ተቀራመቷት ፣ ወያኔ እጁ ላይ ደም አለ ፣ መንግስት ሳይሆን ቃሊቲ ( ዘብጥያ ) መውረድ ያለበት ስርዓት ነው ፣ ይህ ስርዓት ቢያንስ የቃልቻ ያህል እንኳ ለሀገር ሰላም አይጸልይም ፣ ይህ ስርዓት ሳይሆን የእባብ ስሪት ነው ” እና ወዘተ ትሉ ይሆናል ። ቆይ ቆይ << 17 ዓመት የታገለ ስርዓት አንድ ነብዩን ቢገል ምን አለበት ፣ ሀገር በማልማት ላይ ያለ መንግስት ፣ የህዝቡን ድምጽ ቢሰርቅ ምን አለበት ? ቆይ አሁን አባይን እየገነባ ያለ ኃይል ፣ መጅሊስን ቢያፈርስ ያን ያህል መጅሊስ ትልቅ ነገር ሆኖ ነው ፣ እንኳን መጅሊስ << ቲዊን-ታወር ፈርሶ የለም እንዴ ? >> ። ደሞ- መጅሊስ መጅሊስ አትበሉ ፣ በየሰፈሩ ህውሃት መጅሊስ አረቢ አስነጥፎ ሺሻ ያለገደብ እንዲገባ ያደረገውን ረስታችሁ ነው ስለሌላው መጅሊስ የምታወሩት ? ምን ታካብዳላችሁ ? ደሞ ተቃዋሚ የምትባሉት ሁሉ ትልቁ ችግራችሁ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ? ትልቁ ችግራችሁ ንገረኝ ካላችሁ << ወሬኞች ናችሁ !>> እኛ ደሞ በወሬ አንፈታም ። አንድም ቆራጥ በመሃከላችሁ የለም ! <<ፈሳም ሁላ !! >> << ወያኔ እንዳንቺ አማሪካን ሀገር በርገር እየበላች መሰለሽ ስልጣን ላይ የወጣችው ? ታግላ ነው ፣ ከገባሽ >> ደሞ እኛ ልማት ላይ ነን ! አንቺን የሚያስጨንቅሽ ያንድ ጋዜጠኛ መሞት ነው አይደል ? እኛን የሚያስጨንቀን ግን ያርማታ ሙሌት ነው ? አንቺ እስክንድር ለምን ታሰረ የሚለው ነው አይደል እንቅልፍ የሚነሳሽ ? እኛን ወያኔዎችን እንቅልፍ የሚነሳን የሲሚንቶው መቡካት ወይም አለመቡካት ነው ፣ እኛን የሚያስጨንቀን የአበባ እርሻው ነው ፣ እኛን የሚያስጨንቀን የኦባማ በሰላም ወጥቶ መግባት ነው ፣ እኛ የልማት ኃይሎች ነን ። አሁን አንድ አቡበከር ተፈታ አልተፈታ ለኢትዮጵያ ምን ይጠቅማታል ? ከገባሽ እኛን የሚያስጨንቀን እንዴት ለቀጣዩ 100 ዓመት ያለ ተቀናቃኝ እንደምንገዛሽ ነው ።
አሁን እስኪ ማን ይሙት ወያኔን የመሰለ ስርዓት በኢትዮጵያ ምድር ተፈጥሮ ያውቃል? አንድ ዘር ፣ አንድ ዘር የምትሉት ደሞ ትግሬ ስለምትጠሉ ነው እንጂ ፣ ትግሬ ቢገዛ ምን አለበት ? ትግሬ ምን አረገ ? እኛ ከዘረኛ አማራ አድነናችሁ ፣ ትግሬ ፣ ትግሬ ትላላችሁ ? ደሞ ስልጣኑ አይ ማን ነው ያለው ? ሃይለማርያም ትግሬ ነው ? ነጋሶ ገዳዳ ትግሬ ነበር ? ግርማ ወልደጊዮርጊስ ትግሬ ነው ? ደመቀ መኮንን ትግሬ ነው ? አንድ ትግሬ ስልጣን ላይ የነበረ መለስ ብቻ ነበር ፣፣ እሱም በጭንቅላቱ ነው ፣ አሁን ደሞ እሱ ሞተላችሁ ( ሞቶም አልተዋችሁትም እንጂ !) ፣ ሃይለማርያም ጠቃላይ ሚኒስትር ሲሆን ደሞ ምን እንደምትሉ እናያለን ዘረኞች ! ስለ ጀነራሎች የምታወሩት ደሞ እኮ ፣ እነሱ ታግለው ነው ፣ ለ 17 ዓመት አፈር በልተው ፣ ታዲያ አንድ ባለ እስክርቢቶ አማራ መጥቶ ይውሰደው ? ደርግ ይምጣ እና ይግዛን ነው የምትሉት ? ይልቅ አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች ይኖራሉ ፣ እነሱም በሂደት የሚስተካከሉ ናቸው ። እኛ በዲሞክራሲ ስርዓት ላይ መጏዝ ከጀመርን ገና 25 አመታችን ነው ። ዲሞክራሲ ምን እንደነበር ለማያውቅ ሕዝብ ፣ ሁሉንም ባንዴ ብንፈቅድለት ቀስ እያልን እናድርገው ብለን ነው ፣ ደሞ እናንተስ እንኳን የኛን ዲሞክራሲ ፣ የባቄላ ፈስ በቅጡ መቆጣጠር የሚችል መቀመጫ ሳይኖራችሁ ዘላችሁ ወንበር ላይ ቁብ ማለት ምን የሚሉት ችኮላ ነው ።
አንዳንድ ሽብርተኞች ፣ ህገ መንግስቱን ለመናድ ከውጭ ኃይሎች እና ሰርጎ ገቦች ጋ በማበር ፣ ድርጅታችን ኢህአዲግ ቀን ከሌት ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየተጋበት ያለውን የወደ ልማት ጎዳና ባጭር ለመቅጨት ቢሞክሩም ፣ የድርጅታችንን አላማ በተረዱና ፣ በድርጅታችን ላይ ላለፉት ሃያ አመታት ትልቅ እምነት በጣሉ ግለሰቦች ( በግል ተነሳሽነት ) ይህ የወንጀል ተግባር በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል ። ከዚህም ውስጥ እንደምሳሌ የዚህ የሽብር ቡድኑ መሪ እና ዋነኛ ተዋናይ የነበረውን ሰው ( አንዳርጋቸው ጽጌ ) በቁጥጥር ስር አውለናል ። ያም ቢሆን ድርጅታችን ፣ አንዳርጋቸው ለመጽሐፍ ያለው ፍቅር ፣ የኛን የባለ ራዓዩን ጠቅላይ ሚንስትር ፍቅር ስላስታወሰን ፣ በራሳችን ተነሳሽነት ፣ ሙሉ ወጪውን ሸፍነን << አንዳርጋቸው ሆይ ኤርትራ ውስጥ ቦምብ ከምታፈነዳ ፣ እዚህ እኛ ጋ መጽሐፍ አሳትም >> ብለነው ፣ እሱም ምክራችንን ተቀብሎ መጽሐፍ እየጻፈ ነው ። ካላመናችሁ ጠይቁት ፣ እንደውም ዛሬ ገጽ 180ን ጽፎ ጨረሰ ! እንዴትም ብሎ ለጉምቦት ሃያ አለበለዚያ ለባዕለ የካቲት ወይም ፓርላማ ተመርቆ ከመከፈቱ አንድ ሳምንት በፊት ለአንባብያን እንደሚደርስ በዚህ አጋጣሚ መግልጽ እንፈልጋለን ።
እና አባካችሁ ፣ ይህን ” ደሙን ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት አትፈታተኑት ! አረ ተው ታማኝ ተመከር ! አሁን ወያኔን አሜን ብለህ ብትቀበል እኮ፣ እንደ ንዋይ ደበበ ጥሬ ስጋ ስትበላ ፎቶ ተነስተህ ትለጥፍ ነበር ፣ ደደቢት ታንክ ላይ ሆነህ ፎቶ ትነሳ ነበር ፣ ከፈለካት አይነት ሴት ጋ እንደፍለክ ትሆን ነበር ፣ አንተ ግን ዝም ብለህ ነጻነት ፣ እኩልነት ፣ የህዝቦች መብት እና ወዘተ ትላለህ ። ህዝቡ ራሱ ( በብላሽ !) ፣ በኪሳራ ነው ኑሮውን ለባርነት ፣ ህይወቱን ለጭቆኛ አሳልፎ የሰጠው ። ታዲያ አንተ ምን አገባህ ! ? ይልቅ እንደ ሰለሞን ተካልኝ ፣ ለጥሬ ስጋ ስትል ሀገርህ ላይ ፣ ለቀይ ወጥ ስትል ሕዝብህ ላይ ፣ ለሆድህ ስትል እውነትህ ላይ ተገልብጠህ ፣ የቀበሌ ስብሰባ መጥሪያ ” ሃሎ- ሃሎ ” ይዘህ ” ትናንት አንድ በሉ ፣ እሪ በል ቦሌ እሪ በል ፒያሳ ” ባልክበት ጉሮርሮህ ” ቅንድቡ ፣ እጁ ፣ አይኑ ፣ አፍንጫው” እያልክ ብትዘፍን አይሻልም ? አረ ተው ታማኝ ! አረ ተው !
አሁን አበበ ገላው ታላቁ መሪያችን ላይ ፣ ሊያውም በዓለም አደባባይ ፣ ትላልቅ ሰዎች በተገኙበት ፣ እንደዚያ መጮህ ነበረበት ? ማን ተዋረደ ? አበበብ ራሱ ! ያንን የሚያህል አስተዋይ መሪ ያዋረደ መስሎት ፣ ተሳስቷል !
አና አሁንም እኛ ልማት ላይ ነን
ከሰው ሕይወት የድንጋይ ቁመት የማረከን
እኛ አለታውያን
እኛ ኮንክርታውያን
እኛ ድልድያውያን
ከሀገር ውርደት የኛ ሆድ የበለጠብን
ከህዝብ ክብር ፣ ንዋይ እንደ ኩይሳ የደም ሲሳይ የጫነብን
ከነጻነት እና ፍቅር ፣ ጥላቻ መንገድ የሰራብን
የጥፋት ልማተኞች
የክፋት መንገደኞች
በሰው ደም የሰከርን
በአልኮል የሰከርን
በጥላቻ የሰከርን
ይህንንም በ 100 % ምርጫ ውጤት ያስመሰከርን
አስክሬኖች ነን
እና ታዲያ ምን አረግን ?
ተው ፣ አረ ተው ፣ ይህንን ” ደሙን ሰጥቶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ፣ የስኬት ማማ ላይ ያስቀመጣችሁ ጀግና ስርዓት አትፈታተኑት !