የኢህአዴግ ካድሬዎች በሕዝቡና በመድረክ አባላት ላይ እየወሰዱ ያሉትን ኢ-ሰብአዊ እርምጃ አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ዜና መድረክ –
የኢህአዴግ ካድሬዎች ከ2007 ዓ ም ሀገር አቀፍ ምርጫ በኋላ በሕዝቡና በመድረክ አባላት ላይ እየወሰዱ ባሉት ኢ-ሰብአዊ እርምጃ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል አርሶ አደሮችን ከእርሻ ይዞታቸው የማፈናቀልና በኦሮሚያ ክልል መኖሪያ ቤቶችን አፍርሶ ሕዝቡን በክረምቱ ዝናብ ሜዳ ላይ የመበተን ተግባራቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡
በዚሁም መሠረት በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ማሌ ልዩ ወረዳ ሌሞ ገንቶ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ብቻ 650 አርሶ አደሮች እንዲትገዙ የታዘዛችሁትን ማደበሪያ ስላልገዛችሁ መሬታችሁን ለእንቬስተር ልቀቁ ተብለው ለብዙ ዓመታት ሲያርሱ ከኖሩበት መሬታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በጋሞ ጎፋ ዞን በኡባ ደብረ-ፀሐይ ወረዳ የከንቾ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር አባላት የሆኑ ከ400 በላይ አርሶ አደሮች ያለአግባብ ከይዞታቸው እንዳይፈናቀሉ ለመንግሥት ሲያቀርቡ የቆዩት አቤቱታ ችላ ተብሎ ለዘመናት እያረሱ ከኖሩበት መሬታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጎ ይዞታቸው ለእንቬስተር መሰጠቱን ከዞኑ ከደረሰን ሪፖርት ለማወቅ ተችሎአል፡፡ እንደዚሁም በዚሁ ወረዳ ውስጥ የዛባ ቀበለ ገበሬ ማህበር ነዋሪ የሆኑና የኢማዴ-ደህአፓ/ መድረክ አባላት የሆኑ 15 ገበሬዎች እንዲገዙ የታዘዙትን ማዳበሪያ ለመግዛት ባለመቻላቸው በአሁኑ ወቅት በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሚገኙ ዘጠን ከተሞች የሚኖሩ 5,801 አባወራዎችና እማወራዎች ሕገወጥ ቤት ሠርታችኋል በምል ሰበብ መኖሪያ ቤታቸው ፈርሶ ከነቤተሰቦቻቸው በክረምቱ ዝናብ ሜዳ ላይ እንዲበተኑ ተደርገዋል፡፡ በቡራዩ፣ በሰበታ፣ በሱልልታ፣ በዱከም፣ በገላን፣ በብሾፍቱ፣ በለገጣፎ፣ በነቀምት እና በአጋሮ ከተማ ነዋሪ ሆኑት እነዚሁ ዜጎች እየተፈጸመባቸው ያለው ኢሰብአዊ ተግባር እንዲቆም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አቤቱታዎችን ቢያቀርቡም ሰሚ እንዳላገኙና በበርካታ ዜጎች ላይም የእስራትና የገንዘብ ቅጣት እንደተወሰነባቸው ለማወቅ ተችሎአል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሜታ ሮቢ ወረዳ የዋራቦ ቀበሌ ነዋሪ የኦፌኮ/መድረክ አባላት የሆኑ 14 ወጣቶች በ2007 ምርጫ ወቅት ኢህአዴግን በመቃወም ለመድረክ ቅስቀሳ አካሄዳችኋል በምል የበቀል እርምጃ ማናቸውንም መንግሥታዊ አገልግሎት እንዳያገኙና ከመከሰስ በስተቀር ለየትኛውም መሥሪያ ቤት የሚያቀርቡት ክስ ተቀባይነት እንዳይኖረው በቀበሌው አስተዳደርና ማሕበራዊ ፍርድ ቤት ተወስኖባቸዋል፡፡ በሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ማሕተምና አቶ ካቤ ኃይሉ በሚባሉ የቀበሌው ሊቀመንበር ፊርማ ተረጋግጦ ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት በተጻፈውና በተሰራጨው በዚሁ ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሰው ውሳኔ የተላለፈባቸው ወጣቶች 1- ወጣት ጥበቡ ላዬ፣ 2- ወጣት ፍቅር ዳባ፣ 3- ወጣት ቃጄላ በቀላ፣ 4- ወጣት ጥላሁን ለገሰ 5- ወጣት ደጀኔ ድርብሳ፣ 6- ወጣት መገርሳ በቀለ፣ 7- ወጣት ድርባ ኦላና፣ 8- ወጣት ፋይሳ ኦላና፣ 9- ወጣት አስረስ ኦላና፣ 10- ወጣት ጋዲሳ ቶሎሳ፣ 11- ወጣት ነጋሳ ቶሎሳ፣ 12- ወጣት ዳባ መልካ፣ 13- ወጣት ጌቱ ቀጄላ እና 14- ወጣት ምልክሳ ፉፋ ናቸው፡፡ ይኼው የዜጎችን ሕገመንግሥታዊ መብት የሚገፍ ሕግ ወጥ ደብዳቤ የተጻፈላቸው የመንግሥት አካላት የዜጎቹን መብት ለማስከበር እስከአሁን የወሰዱት የእርምት እርምጃም እንደለለም ለማወቅ ተችሎአል፡፡
ከዚህም ሌላ በኢሉባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ በምርጫው መድረክ ደጋፊ የነበሩ 10 ዜጎች በመንግስት ላይ ሕዝብን አነሳስታችኋል በምል የፈጠራ ክስ ከ1 እስከ 2 ዓመት እስራት በዳሪሙ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲወሰንባቸው ሌሎች 10 ዜጎች ደግሞ ከ600 እስከ 1500 ብር ድረስ የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡