ዜና መድረክ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ልዩና አስቸኳይ ጉባኤ ለሁለት ቀናት ያካሄዳል፡፡
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ዜና መድረክ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/ በ2007 ዓ ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሂደትና ከምርጫው ጋር በተያያዘ በአባላቱ ላይ በተፈጸሙት ግድያዎችና የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ባለሥልጣናት እየፈጸሙና እስከ አሁንም እያባባሱ ባሉት ዘርፈብዙ የማዋከብና የማሰቃየት ተግባራት ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ልዩና አስቸኳይ ጉባኤ ከነሐሴ 2-3/2007 ዓ ም ለሁለት ቀናት ያካሄዳል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የመድረክ ዋና ጽ/ቤት ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በሚካሄደው በዚሁ ስብሰባ ከአራቱም የመድረክ አባል ድርጅቶች የሚወከሉ 80 ጉባኤተኞች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን ጉባኤው መድረክ በምርጫው ሂደት ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የነበሩትን ጠንካራና ደካማጎኖች በመገምገምና ግንባሩና አባል ድርጅቶቹ በሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴያቸውና በምርጫ ተሳትፎአቸው ባጋጠሙትና እያጋጠሙ ባሉት ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ በስፋት በመወያየት ለቀጣዩ ድርጅታዊ እንቅስቃሴ አመራር እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
መደረክ በ2007 ምርጫ ከገዥው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የተወካዮች ም/ቤትና የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ የተወዳደረና ከፍተኛ እንቅስቃሴም ያደረገ ግንባር ሲሆን ከምርጫው ጋር በተያያዘ አምስት አባላቶቹ በተለያዩ አከባቢዎች ሲገደሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት ለእስራት፣ ለድብደባ፣ ለንብረታቸው ውድመት፣ ከሥራና ከእርሻ መሬት መፈናቀልና ለከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት መዳረጋቸው እንደዚሁም እነዚህን በደሎች በአባላቱ ላይ ካደረሱት አካላት አንዳቸውም ለሕግ አለመቅረባቸው ይታወሳል፡፡