“ዴምሕት” የሻእቢያ የትሮይ ፈረስ !


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ።

እንደምን ከረማችሁልኝ ክቡራትና ክቡራን አንባቢዎቼ ። ይኽው በቀጠሮዬ ብቅ ብያለሁ እንደገና ።

“በሚቀጥለው ፅሁፌ በ“ድምሕት”ና በአወቃቀሩ ላይ እመጣበታለሁ ብዬ ነበር “ሻእቢያ ለምን?” የሚለውን ቁጥር 1 ፅሁፌን የዘጋሁት ።

የግሪክን አፈ-ታሪክ ታስታውሱ እንደሆነ ግሪኮች ትሮይን ወረሩ ። ትሮይ የግሪኮችን ጥቃት ገትራ ተቋቋመች ። ምሽጓን መስበር አልተቻለም ። ትሮይ የማትደፈር መሆኗን ለማስታወስ በአቴና የጦርነት አምላክ ስም ፤ግሪኮች ትልቅ የእንጨት ፈረስ ሰርተው ከትሮይ መግቢያ በር ላይ ጥለውት በርቀት የሸሹ መስለው ተደበቁ ። ምንም እንኳ የትሮይ ዜጎች የሆኑት ላኦኮንና ካሳንድራ ፤ ፈረሱ የትሮይን በር አልፎ እንዳይገባ ቢከራከሩም ፤ የትሮይ ሰዎች የጦርነት አምላካቸው መታሰቢያ የሆነውን ይህን የግሪኮች የእንጨት ፈረስ ስጦታ በራቸውን ከፍተው አስገቡት ። ሌሊት ላይ በእንጨቱ ፈረስ ሆድ ውስጥ ፤ ተደብቀው የነበሩት ግሪኮች ወጥተው የትሮይን ቅጥር በር ከፈቱት። በርቀት ተደብቀው የነበሩት ግሪኮችም በፍጥነት ተመልሰው በተከፈተላቸው በር ገብተው ትሮይን ደመሰሷት ። ጠላትን በውስጡ ተሸክሞ የነበረውን ፈረስ በፈቃዳቸው ወደ ከተማቸው ያስገቡት ማስተዋል የተሳናቸው የትሮይ የራሷ ዜጎች ነበሩ ።
\\\

ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ “ዴምሕት” ።

ይህን ድርጅት ትረዱት ዘንድ የአፈጣጠሩን ታሪክ በጥቂቱ ላንሳ ። የ1998 እስከ 2000 እ ኤ አ ከዘለቀው ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ፤ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ከሚል መርኅ በመነሳት ወደ ኤርትራ የገቡ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ተሰባስበው “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት ድርጅት”ን (ኢዲኃአድ)ን ይመሰርታሉ ። ይህ ድርጅት ሲመሰረት መርህ አድርጎ የወሰደው የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች የሆኑ ሁሉ ያለ ምንም ዘር ልዩነት በዚህ ድርጅት ስር በመሰባሰብ ሊታገሉ ነበር ። በዚህም መሰረት ድርጅቱ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ያካተተ ድርጅት ሆኖ ተመሰረተ ።

ከዚህ ድርጅት ምስረታ ጥቂት ወራት በኋላ ሻእቢያ የራሱን እቅድ ይዞ ብቅ ይልና አዲሱ ድርጅት እቅዱን ይቀበል ዘንድ ይጠይቃል ። የተወሰኑት ሰዎች እቅዱ የድርጅት ነጻነት እንደማይሰጣቸው በመገንዘብ ብሎም ሻእቢያ ባቀረበው እቅድ መሰረት መንቀሳቀስ ባለመፈለጋቸው እቅዱን ይቃወማሉ ። እነዚህ ሰዎችም በሻእቢያ አስቸኳይ ትእዛዝ ከኤርትራ እንዲወጡ ተነግሯቸው አገሪቱን ለቀው ይወጣሉ ።
መውጣት የሚችሉት ሰዎች ኤርትራን ለቀው ከወጡ በኋላ መሄጃ የሌላቸው እዚያው ይቀራሉ።ሻእቢያም እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይጀምራል ። ኤርትራ ውስጥ ከቀሩት “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት ድርጅት” (ኢዴኃአድ) አባላት ወስጥ ፤ ሻእቢያ የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑትን ወደ ኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እንዲገቡ ያስገድዳቸዋል ፤ ተግባራዊም አድርጎታል ። የትግራይ ተወላጅ የሆኑትን ደግሞ በሙሉ ነቅሶ አውጥቶ ወደ አልታወቀ ቦታ ይወስዳቸዋል ። ለምን እንደወሰዳቸውና ምን ያሰራቸው እንደነበር ማንም የሚያውቅ አልነበረም ። ሻእቢያ ትግራዮቹን ነቅሶ ካወጣ በኋላ ጥቅምት 7 ቀን 1993 እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር የተረፉትን ሰብስቦ ያለፈው ድርጅት ፈርሶ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር (ኢሕአግ) ተብላችኋል ሲል ያውጅላቸዋል ። ይህም ከግንቦት 7 ጋር ቅልቅል እስከተደረገበት ቀን ድረስ በየአመቱ የ“ኢሕአግ” የምስረታ ቀን እየተባለ ሲከበር ቆይቷል ።

ይሕ ከተደረገ ከ5 ወራት በኋላ ሻእቢያ እነዚያን በትግራይ ተወላጅነታቸው ነቅሶ ያወጣቸውን ሰዎች አምጥቶ የካቲት 11 ቀን 1993 ዓ.ም ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምሕት)ን አቋቋመ ። (እዚህ ላይ አስተውሉ ቀኑ፤ ወያኔ ከተቋቋመበት ቀን ጋር ፍፁም አንድ አይነት ነው ።) የዚህ ድርጅት መሪም ተብሎ የማነ ድምፁ የሚባል ሰው በሻእቢያ ይሾማል ። (ስለየማነ ድምፁ ከሚቀጥሉት ፅሁፎቼ ባንዱ ላይ አወጋችኋለሁ።)

ይህ ድርጅት እንደ ድርጅት ለመቆም በቂ የሰው ሃይል ምንጭ ያስፈልገው ነበር ። ለዛሬው ዝርዝር ወስጥ ባልገባም ፤ አንባቢዎቼ እንደምትረዱት ፤ በአገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፤ ድርጅቱ በቂ የሰው ሃይል የማግኘት እድሉ በጣም የጠበበ ነው ። ስለዚህ ይህን ለማካካስ በሻእቢያ በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ። የሰው ሃይል ምንጮቹን በዝርዝር ተመልከቱ ።
“ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ሕዝቢ ትግራይ ፤ ዴምሕት” የሰው ሃይል ምንጮቹ የሚከተሉት ናቸው ።

1ኛ) ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ለስራ ወደ ኤርትራ ሄደው ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ያልቻሉና እዚያው ተቀርቅረው የቀሩ ኢትዮጵያውያን በተለይ ደግሞ የትግራይ ተወላጅነት ያላቸው ወገኖች በብዛት በእስር ላይ ይገኙ ነበር ። በነገራችን ላይ ጦርንርቱ እንደ ተጀመረ በተለያዩ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በገመድ እጆቻቸው ወይም እግሮቻቸውን እየታሰሩ በመኪና እየተጎተቱ ህይወታቸው አልፏል ።(ይህ ግፍ ጣሊያኖች የኤርትራ ገዢዎች በነበሩ ጊዜ በኤርትራውያን ላይ ይፈፅሙት የነበረ ነው ) ። ከዚህ መሰል ግፍ የተረፉት ደግሞ በየኮንቴነሩ ውስጥ እስረኞች ነበሩ ። ከእስር እያወጡ ማሽላ ቆረጣ ፤ መንገድ ግንባታ ፤ የውኃ ማቆሪያ ጉድጓድ ቁፋሮና የተገኘውን የጉልበት ስራዎች ሁሉ ያሰሯቸው ነበር ። በእስሩ ወቅት ከሚደርስባችው ውርደትና ተስፋ መቁረጥ የተነሳ ቅስማቸው ተሰብሮ ፤ ማንነታቸው ተገፎ ፤ ህይወት ትርጉም አልባ ሆናባቸው ሳለ በሻእቢያ ወኪሎች አማካይነት እየተቀሰቀሱ ወደ ዴምሕት እንዲቀላቀሉ ይጋበዛሉ ። በነዚህ በሞትና በህይወት መካከል ካሉት የትግራይ ተወላጆች ውስጥ ፤ ጉልበት ያላቸው ሁሉ የድምሕት ወታደር ለመሆን ፈቃደኛ ከሆናችሁ ከእስር ትፈታላችሁ የሚል ምርጫ ይሰጣቸዋል ። ። እነሱም የእስር ቤት ኖሮ ያንገሸገሻቸው ስለነበሩና ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ለ“ዴምሕት” ተዋጊነት ገብተዋል ።

2ኛ) ከላይ የጠቀስኳቸው ምልምሎች ፤በሻእቢያ የበታች ሹማምንት አዝማችነት በአፈሙዝ ኢላማ ስር እየተጠበቁ ወደኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግዛት ሰርገው ይገቡና ከመንደሮች ብዙም ሳይርቁ ያደፍጣሉ ። ለእርሻ ፤ለከብት ጥበቃ ፤ ውሃ ለመቅዳት ወይም ለገበያ በጠዋት ወይም አመሻሽ ላይ የወጡ ወጣቶችን እንደባሪያ እየፈነገሉ በፍጥነት ድንበር እንዲሻገሩ ያደርጓቸዋል ። ተፈንጋዮቹ እነማን እንዳፈኗቸው ወዴትስ እንደሚወስዷቸው ምንም አትነይ ግምት የላቸውም ። የፈንጋዮቻቸው ቋንቋ የሚያውቁት የአካባቢያቸውን ትግርኛ ነው ። የማይገባቸው ግን ታፍነው ወደ ኤርትራ እየተጋዙ መሆኑን ነው ። የሚኖሩት በድንበር አካባቢ ስለሆነ የራሳቸው የወያኔ መንግስት ሚሊሻዎች ሰርጎ ገቦችን ለማጣራት ሲል የያዟቸው አድርገው ያስባሉ ። እናም ምርመራውን ጨርሶ ንፅህናቸው ሲረጋገጥ ወደቤታቸው የሚመለሱ ይመስላቸዋል ። መፈንገላቸውን የሚያውቁት በኋላ ነው ። እነዚህ ሰዎች ተከዜን ሲያሻግሯቸው ነው መጠርጠር የሚጀምሩት ። ኤርትራ ውስጥ ከገቡ በኋላ ወዲያውኑ ለሃብታም የግለ-ሰብ እርሻ ጣቢያዎች እየተሰጡ ያለ ክፍያ ማሽላ ቆረጣ፤ አዝመራ ስብሰባ ፤ ጉልጓሎና አረም ነቀላ ስራ እንዲሰሩ ሲደረግ ፤ ብሎም ፍየልና ከብት ጠባቂዎች ሲሆኑ ነው የት እንዳሉና ምን እየተፈፀመባቸው እንደሆነ የሚገነዘቡት ። ከብቶቹና ፍየሎቹ በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ወጣቶቹ ሲፈነገሉ አብረው የተዘረፉ ናቸው ። ከአመት ላላነሰ ጊዜ በዚህ አይነት እንዲሰሩ ተደርገው ፤ ቅስማቸው ፤ ማንነታቸውና ሰብዕናቸው ተሰብሮ ተስፋ ቆርጠው ሳለ ለነዚህም ሻእቢያ አዲስ አማራጭ ይሰጣቸዋል ፤ የዴምሕት ወታደር መሆን ። ሌላ ተስፋም ስለሌላቸው የዴምሕት ወታደር መሆን የገደዳሉ ።

3ኛ) ከትግራይ የተነሱ ቤተ-እስራኤሎች (ፈላሻዎች) ወደ እስራኤል የሚያደርጉትን ፍልሰት ፤ ለማፋጠን ሲሉ ድንበር አቋርጠው በሺዎች የሚቆጠሩ ወደኤርትራ እየገቡ ሜዳ ላይ ፈሰው ይኖራሉ ። እነዚህ ሰዎች በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም ፤ ወደ ኤርትራ ከገቡ መመለሻ ስለማይኖራቸው የአለም ሕ/ሰብና እስራኤል አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ወደ እስራኤል ቶሎ ያሻግሩናል ከሚል ህሳቤ ኤርትራ ውስጥ ተቀርቅረው የቀሩ ናቸው ። የኤርትራ መንግስት እነዚህ ቤተ-እስራኤላውያን (ፈላሾች) በአገሩ ምድር ላይ መኖራቸውን ለአለም ሕ/ሰብ አላሳወቀም ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ለዴምሕት ወታደራዊ ምልመላ ምንጮች ናቸውና ። ጭው ባለ በረሓ ላይ እነሱም በረሓብና በችጋር ቅስማቸው ፤ ማንነታቸውና ሰብዕናቸው ተሰብሮ የእስራኤል ጉዞ ተስፋቸው ተሟጦ ሳለ የዴምሕት ወታደር የመሆን አዲስ አማራጭ ይሰጣቸዋል ። “እልፍ ሲሉ ዕልፍ ይገኛል” እንዲሉ ከዚህ የማይሻል የለም በማለት እነሱም የተሰጣቸውን አማራጭ እየተቀበሉ የ “ዴምሕት” ተዋጊዎች ይሆናሉ ።

4ኛ) መሬታቸውን ያለአግባብ የተቀሙ ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ በወያኔ የቀበሌና የአካባቢ ካድሬዎች ግፍ የተፈፀመባቸው ፤ እናም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች በራሳቸው ፍላጎት ዴምሕትን ለመቀላቀል የመጡና የሚመጡ ጥቂት ሰዎችም ሌሎቹ የ”ዴምሕት” የሰው ሃይል ምንጮች ናቸው ።

5ኛውና እጅግ ከፍተኛው የዴምሕት የሰው ሃይል ምንጭ ሻእቢያ ነው ። ከአክለ-ጉዛይና ከሰራዬ አካባቢ ለብሄራዊ ውትድርና የሚመለምላቸው ኤርትራውያን ወጣቶችም የዴምሕት ወታደሮች ናቸው ። በአክለ-ጉዛይ እና በሰራዬ ደቡባዊ ግዛት የሚኖሩ ኤርትራውያን የትግርኛ አነጋገር ዘይቤ ከትግራይ ሰሜናዊ ትግርኛ ጋር ይመሳሰላል ። ስለዚህ ከትግራይ ተወላጅ የ“ዴምሕት” ወታደሮች ጋር በዘይቤ በቀላሉ መግባባት ይችላል ።

እነዚህ ኤርትራውያን ወጣት የብሄራዊ ውትድርና ተመልማዮች በትግራይ ተቃዋሚ ስም ከ “ዴምሕት” ተዋጊዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ይደረጋሉ ። አማርኛ መናገር የሚችሉ የውትድርና ተመልማዮችም እጅግ ተፈላጊዎች ናቸው ። የብሔራዊ ውትድርና ተመልማዮቹ ወደ “ዴምሕት” ወታደራዊ ካምፖች ከመበተናቸው በፊት ፤ተሰነይ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ የባህርይ ስልጠና ለተወሰኑ ቀናት ይሰጣቸዋል። ይህ የባህርይ ስልጠና እንዴት አድርገው ከትግራይ ተወላጆች ጋር መቀላቀል እንደሚገባቸው ፤ አዳዲስ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ እንዴት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውና አስፈላጊና አስቸኳይ ወታደራዊ ትእዛዝ ሲመጣ ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚችሉ የሚሰለጥኑበት ነው ።

ያም ሆኖ ታዲያ በደንብ ላስተዋለ በ“ዴምሕት” ሰራዊት ወስጥ ያለ ሰብአዊ ስሜት-አልባነትና የዝምታ ድባብ እጅግ ጠንካራ ነው ። ይህ ሁኔታ በአርበኞች ግንባርም ወስጥ ያለ ቢሆንም እንደ “ዴምሕት” ግን ጎልቶ አይታይም ። የ “ዴምሕትን” ወታደሮች አይናቸውን አትኩረህ ስትመለከት፤ በተለይ የትግራይ ተወላጆቹ በአብዛኛው አንድ ስውር ጥቁር ጥላ ይከተላቸው ይመስል ባስቸኳይ አይናቸውን ይሰብራሉ ።

በዴምሕት ሰራዊት ውስጥ በኔ ግምት ፤ እዚህ ላይ ይሰመርልኝ ፤ አዎ በኔ ግምት፤ ከ 60% እስከ 70% የሚሆነው ቁጥር የሻእቢያ ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ወታደር ነው ። ይህ የ“ዴምህት” ጦር ሜካናይዝድ ጦር ሆኖ እንዲቀጥል የታለመ ስለሆነ በሻእቢያ ሁለ-ገብ እገዛ ይደረግለታል ።

ማንም የኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳስበኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፤ ይህ ለምን ሲል ሊጠይቅ ይገባዋል ብዬ አስባለሁ ። ሻእቢያ የራሱን ሰራዊት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሰራዊት ነኝ ከሚል ቡድን ጋር በመቀላቀል የሚያሰለጥንበት ምክንያት ለሁላችንም ግልፅ ሊሆን ይገባል ።

ትሮይ ሆይ ! ጠላትሽን የተሸከመውን የእንጨት ፈረስ በከንቱ ልጆችሽ ፈቃድ አስገባሽ ። ብትትንሽ ወጥቶ ድል ሆነሽ ተቃጠልሽ ።

“ዴምህት” የሻእቢያ የትሮይ ፈረስ ነው ። ይህን የትሮይ ፈረስ በራሳችን ሰዎች ትከሻና ተሸካሚነት ቅጥሩን ሰብረን እያስገባነው ነው ። ከ“ዴምህት” ጋር የሚደረግ ማንኛውም አይነት ትብብር ሆነ ውል ከሻእቢያ ጋር እንደተደረገ ሊቆጠር ይገባዋል ።

ከወደ አስመራ እየነፈሰ ያለው ራዳር የጠቆመኝ ጉዳይ ስላለ ዛሬም አንድ ትንቢት ልናገር ። ከሰሞነኛው የሻእቢያ አቀባበል በኋላ ፤ በሓሬና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ፤ የልብ ማሞቂያ ወታደራዊ ሰልፍ ተደርጎ ሁሉም በፊልም ተቀርፆ ተቀምጧል ። እንዴት እንደሚቀርብልንም ከአንጋፋ ጠበብቶች ተብዬዎች እስከ ሰሞነኛ አጋፋሪዎች ራስ እያሳከከ ያለ ጉዳይ ሆኗል ። አስፈላጊ ሲሆንም እየተመነዘረ ይቀርብልናል ። እንደ አመጣጡ አብረን እንከታተለዋለን ።

ትንቢቱ እንዲህ ነው ። በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ፤አርበኞች ግንቦት 7 ለፍትህና ዴሞክራሲ ንቅናቄ (አግ7ፍዴን) ፤ ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምሕት) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኅይሎች ንቅናቄ (አዴኀን) ፤ የጋምቤላ ሕዝቦች ሐርነት ንቅናቄ (ጋሕሐን) ፤ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ሐርነት ንቅናቄ (ቤሕሐን) እና የደቡብ ሕዝቦች ለፍትህና ለእኩልነት ግንባር (ደሕፍእግ) አንድ ላይ በመሆን ምንልባት ስማቸው ተቀይሮ አለያም ቁጥራቸው ተቀንሶ ወይም ተጨምሮ አንድ ትብብር alliance እንዲፈጥሩ ይደረጋል ። ቁጥራቸው ሊቀንስና ሊጨምር የሚችልባቸው ምክንያቶችም አሉ ። አንዳንዶቹ በምርኮኛ ወታደሮች ከሜዳ ላይ የተፈለፈሉ ሆነው ከሊቀ-መንበሩና ከፀሃፊው ሌላ አባላት ስለሌላቸው በሻእቢያ ፈቃድ እንደ አስፈላጊነታቸው ከኦርኬስትራው ተወዛዋዥነት ሊቀነሱም ሊጨመሩም ይችላሉ ። ( አስተውሉ እነዚህ ድርጅቶች በሙሉ አዎ በ…ሙ…ሉ ፤ በዚህም በሉት በዚያ እዚያው ኤርትራ ውስጥ ተጠፍጥፈው በሻእቢያ ሳንባ ለመተንፈስ የተቀረፁ ናቸው ።)

የአዲሱ ትብብር ሊቀ-መንበርነት ስልጣን ለቀድሞው ግንቦት 7 መሪ ይሰጣል ። የወታደራዊ አዛዥነት ስልጣኑን ደግሞ ዴምህት የ(ሻእቢያ የትሮይ ፈረስ) መሪ እንዲይዘው ይደረጋል ። ከውክልና በላይ ስልጣን የማይኖረው የምክትል ሊቀ-መንበርነት ስልጣን ለቀድሞው የአርበኞች ግንባር መሪ ይቸረዋል ። የትብብሩ ፀሃፊነትም ለቀድሞዎቹ አርበኞች ግንባር አንድ አባል ሊጨመር ይችላል ። የውጪ ጉዳይ ሃላፊነቱ ስልጣን ደግሞ አዲስ ከአሜሪካ ከሄዱት እንግዶች ላንዱ ለቀድሞው ግንቦት 7 አመራር ሰው ይታከልለታል ።

ውድ አንባቢዬ ፤ በሰው ደረጃ ኤርትራ የሚኖሩትንና አዳዲሶቹን የአሜሪካ እንግዶች አንድ ላይ ቀላቅለው ማን የትኛውን ሹመት እንደሚያገኝ ይገምቱ ዘንድ ቀሪውን ለርስዎ ግምት (imagination) እተወዋለሁ ።
ለሚቀጥለው ፅሁፍ ደግሞ ቸር ይግጠመን !

ኦገስት 5/ 2015 እ.ኤ.አ.
ላስ ቬጋስ ኒቫዳ ።