የኦባማ የአፍሪካ አዳራሽ ንግግርና መልዕክቱ በወፍ በረር ሲቃኝ፤ Girma Bekele
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትርና የአሜሪካው ፕሬዝዴንት በጋራ በሰጡትን መግለጫ በማስመልከት በእንግሊዝኛ በጻፍኩት አስተያየቴ ላይ ኦባማ መንግስታችን ‹‹ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተሰየመ መንግስት›› ማለታቸው ብዙ ወገኖችን ማስቆጨቱንና የቁጭታቸው መነሻም የፕሬዝዳንቱ አባባል የ‹ሰለጠኑት ›ና የበለጸጉት ከሚነግሩን እሴታቸውና መርሃቸው ጋር የተጣረሰ መሆኑን አንስቼ አሜሪካም ሆነች መሪዋ ከምድራዊ ‹‹ብሄራዊ ጥቅማቸው›› የሚበልጥባቸው እሴትም ሆነ መርህ እንደሌላቸው ወይም ለጥቅማቸው ሲሉ እንደሚረማመዱባቸው ገልጬ ነበር፡፡ ከመሰረቱ በተሳሳተ የውጪ ፖሊሲ መርሃቸው አንጻር ወዳጅነታቸውና መስማት የሚፈልጉትም ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ብቻ ስለሆነ ለመደመጥ ከፈለግን እኛም በብሄራዊ አጀንዳችን ዙሪያ በአንድነት ተሰባስበን ጠንክረን ስንገኝ መሆኑን አስምሬበታለሁ፡፡ በመጨረሻም ፕሬዝደንት ኦባማ በንግግራቸው ያነሷቸው ጠቃሚ ነጥቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ/እንዲፈጸሙ ማድረግ በርሳቸውና በአገራቸው ጫንቃ ላይ ሳይሆን የእኛ ሸክም መሆኑን አንስቻለሁ፡፡ ይህን አመለካከቴን በማጠናከር ዛሬ ደግሞ ፕ/ት ኦባማ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ያደረጉት ንግግር መልዕክት በሚመለከት በመፍ በረር እቃኛለሁ፡፡
በቅድሚያ አንድ ነገር አሳስቤ ልለፍ– ያለፈውንም ሆነ የዛሬውን አስተያየቴን ስጽፍ ፕ/ት ኦባማ ከጠ/ሚኒስትራችን ጋር በግል በተወያዩት እና በአደባባይ በነገሩን መካከል ያለውን/ሊኖር የሚችለውን ልዩነት ከዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ እና አንድ ወዳጄ ከአሜሪካዊ ዲፕሎማት ወዳጁ የሰማውን በጥቅሉ ‹‹ ከአገራችሁ (ኢትዮጵያ ማለት ነው) የከፉ አምባገነኖች ጋርም ሰርተናል፤ እንደናንተ መሪዎች ስህተቱ በአደባባይ/በግልጽ እንዳይነገርበት የሚፈልግ/ሲነገርበት የሚንገሸገሽ አላጋጠመንም/የለም›› የሚለውን ታሳቢ ማድረጌን ነው፡፡
ፕ/ት ኦባማ በአፍሪካ አዳራሽ ባደረጉት ንግግርም የተለመደውን ዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ እና የዘመኑን አድናቆታዊ መጠይቅ ( Appereciative Inquiry) ስልት (ጥቂትም ቢሆን የተገኘውን ውጤት በማድነቅ ጀምሮ ወደ ችግሩና ውስንነቱ የመዝለቅ አካሄድ) እንደተጠቀሙ ይስተዋላል፤ ብዙ ውስጠ-ወይራ አነጋገርም ተጠቅመዋል፡፡ ቢሆንም -ቢሆንም ለማግባቢያ ከተገለጸው አድናቆት በግልጽና በውስጠ ወይራ የቀረበው እውነት በእጅጉ የላቀና ከጠ/ሚስትሩ ጋር ከሰጡት መግለጫ የጠነከረ እንደሆነ ማንም በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡ የርሳቸውን ዲፕሎማሲያዊ አቀራረብና ውስጠ- ወይራ አባባል ገልጠን ካየነው የአፍሪካ መሪዎች ‹መረን የለቀቀ› የዕድሜ ልክ የሥልጣን ፍላጎትና ‹መጠን ያለፈ› የሃብት ማካበት /ሙስና/ ጊዜው ያለፈበት መሆኑንና ከበቂ በላይ ድሃውን ህዝባቸውን ‹ከዘረፉም› በኋላ ለምን ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ማለት እስገራሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ለሁሉም በጋራ ከተገለጸው ጎልቶ የወጣው ሲሆን በእኛ በኩል ደግሞ- በጋራ መግለጫው የተነሳውንና ብዙዎችን ያሳዘነውን ‹‹ በምርጫ የተሰየመ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት›› በማለት ለመንግስታችን ያቀረቡትን መወደስ የዲፕሎማሲ ጨዋታ መሆኑን ‹‹ሠላማዊ ምርጫ ማካሄድ ዲሞክራሲያዊነት አይደለም›› የሚል ይዘት ባለው አባባላቸውና በበጎ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ላይ ናቸው በማለት ከገለጹዋቸው አገራት በተቃራኒ መሆናችንን አዋዝተው አሳይተዋል፡፡ ይህ ከላይ የጠቀስኩትን ወዳጄ የነገረኝን የአሜሪካዊ ወዳጁን አስተያየት ያስታውሰኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገራችን በኢህገመንግሰታዊ ሦስት አዋጆች የታፈኑትንና ከእነዚህ ጋር ተያይዘው የሚነሱትን መሰረታዊ ጥያቄዎች– የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ መገደብ/ምህዳር መጥበብ፣ የሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መታፈን እና የዲሞክራሲያዊ ተቋማት/ሲቪክ ድርጅቶች/ አፈና በሚመለከት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በጅምር ላይ መሆናችንና ሳይሸራረፍ መከበራቸው ለዘላቂ ዲሞክራሲ የማይታለፍ መሆኑን አውስተዋል፡፡ እንዲህ በማለት ‹‹….Likewise, our host, Ethiopians have much to be proud of — I’ve been amazed at all the wonderful work that’s being done here — and it’s true that the elections that took place here occurred without violence. But as I discussed with Prime Minister Hailemariam, that’s just the start of democracy. I believe Ethiopia will not fully unleash the potential of its people if journalists are restricted or legitimate opposition groups can’t participate in the campaign process. And, to his credit, the Prime Minister acknowledged that more work will need to be done for Ethiopia to be a full-fledged, sustainable democracy.›› በተጨማሪም እርሳቸውን ለማየት ያጎነበሱ መሪዎቻችን የተመለከቱት፣በአገራችን ያለውን የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ረገጣ ከዓለም አቀፍ ተሟጋች ድርጅቶችና ከውጪ ጉዳይ ሚ/ር መስሪያ ቤታቸው አንብበው የመጡት ኦባማ የተለመደውን ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት‹‹ ን ተጠቅመዋል፤ ‹‹… በአግባቡ /በትክክል እያደመጥናችሁ ነው፣ … በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አጋርነት… ›› በተናገሩበት ቋንቋ ‹‹As President, I’ve worked to transform America’s relationship with Africa — so that we’re truly listening to our African friends and working together, as equal partners.›› በማለት፡፡.
በአጠቃላይ ሲታይ የአፍሪካ አዳራሹ ንግግራቸው የአገራችንን ብሎም የአህጉራችን ማኅበረኢኮኖሚና ፖለቲካ ገጽታ በትክክል ያሳየ ነበር ፡፡ ግን-ነገር ግን ይህ አባባላቸውና አገላለጻቸው በዚህ ጉብኝት ያወቁት/የተረዱት ያለመሆኑ፣ ከዚህ ያለፈ ስለእያንዳንዱ አገር የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት አፈና እና ሌሎች ማኅበረ-ኢኮኖሚ ጉዳዮች ከእኛ የማይተናነስ መረጃ በእጃቸው እንደሚገኝ ፣…ወዘተ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ይህን ሁሉ ካወቁ ለምን ከእንደዚህ ዓይነት ‹‹ሙሰኛ የዕድሜ ልክ መሪዎች›› ጋር ይሞዳሞዳሉ ሲሆን መልሱም ‹‹ ጥቅማቸው›› እስከተጠበቀ (የአገራቸውን ጥቅም በእኛ ደም እስካስጠበቁ– ) ድረስ ስለምን ይጨነቃሉ የሚል ይሆናል፡፡ የእኛን ኑሮ መልሰው እየነገሩንና እያጨበጨብናላቸው እንዲሁ መዝለቅን እስከመረጥን ድረስ ለእነርሱ ምን-ተዳቸው፡፡ ከዓመታት በፊት እኚሁ በንግግር ችሎታቸውና ስለሚናገሩት ጠንቅቀውና ጠልቀው በማወቃቸው የሚታወቁት ‹‹ድንቅ›› ፕ/ት በጋና ያደረጉትንና እዚህም የደገሙትን ንግግር‹‹ አፍሪካ ጠንካራ ተቋማትን እንጂ ጠንካራ ግለሰቦችን አትሻም›› እና በተግባር አገራቸውና እርሳቸው ከተናገሩበት እስከዛሬ እየፈጸሙ ያሉትን ማየት ለዚህ አስረጂ ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻ የጉብኝቱን ዓላማ መልዕክት ሳጠቃልል ኦባማ በንግግራቸው መካከል ‹‹ Now, the United States isn’t the only country that sees your growth as an opportunity. And that is a good thing. When more countries invest responsibly in Africa, it creates more jobs and… ›› በሚል ላስቀመጡት ስጋት በመጨረሻው መዝጊያ ዐረፍተ ነገር ላይ‹‹ To which I would simply add, as you build the Africa you believe in, you will have no better partner, no better friend than the United States of America. ››በሚል ያስቀመጡት ነው፤ ‹‹ ማንም ይሁን ማን አብሮ ለመስራት ከእኛ የሚሻል/የሚበልጥ ጓደኛና አጋር የላችሁም››፡፡
ይህ ከአንድ አገርና መሪ አንጻር ጥፋት ነው እያልኩ አይደለም፡፡ በዛሬው የዓለም ሁኔታ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ጥቅም የለውምም ሆነ እንደ ‹‹ቅመም›› ለትግላችን አስፈላጊ አይደለም አላልኩም፡፡ ይልቁንም እኛም እንደዚህ ያለ የራሳችን አገርና መሪ እንዲኖረን በጋራ አገራዊ አጀንዳ ላይ ተባብረን እንቁም፣ በብሄራዊ ዕርቅ አገራዊ ስምምነት እንፍጠር፣ያን ጊዜ እኛም እንደ አሜሪካና መሪያችንም እንደ ኦባማ በዓለም ፊት ክብርና ሞገስ ይኖረናል፤ ፍላጎታችን/ድምጻችንም በግልጽም ሆነ በውስጠ- ወይራ ሲገለጽ ዓለም ወዶም ሆነ ተገዶ ያጨበጭብልናል፣ ተፈላጊ እንጅ ፈላጊ አንሆንም፣ ይህም ባለፉ መንግስታት ዘመን የታየና በታሪክ የተመዘገበ ነው፡፡ አገራችን የተስፋ ምድር ናትና በዲቪ ወደእኛ ይመጣሉ እንጂ በበረሃ/በሞት ውስጥ /አልፈን ወደ እነርሱ አንሰደድም ፡፡
ባዶ ምኞት እንዳይመስልብኝ ይህ እንዲሆን የፈጣር ፈቃዱ እንደሆነ አጥብቄ አምናለሁ፡፡ ቀኑም ሩቅ እንዳልሆነ ይሰማኛል፤ ፈቃዱ ይፈጸም ዘንድ በመተባበር በአንድነት መትጋት ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ፡፡ሁላችንም በየተሰለፍንበት የትግል መስክ ‹‹ጉዞኣችን እስከ ቀራንዮ ነው›. በማለት ኃላፊነታችንን የምንወጣ እንዲንሆን እርሱ ዕውቀቱንና ጥበቡን፣ ፍቅርና አንድነትን …ያቅርብ፤፣ጥላቻና መጠላለፍን፣ ንቀትንና ውርደትን ያርቅ፡፡ አሜን፡፡ አበቃሁ//