ፍፁም አሻንጉሊት፤ ፍፁም ፈንጋይ፤ ፍፁም ነጋዴ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ
የጉዞ ማስታወሻ ቁ.3

ውድ አንባቢዎቼ «ሻእቢያ ለምን?»  በሚለው የጉዞ ማስታወሻዬ ላይ በሚቀጥለው ፅሁፌ ቁጥር 2 ን”በድምህትና በአወቃቀሩ ላይ እመጣበታለሁ ።” ብዬ ነበር የተለዬኋችሁ ። አንዱን ሁኔታ ሌላው እየወለደው አዳዲስ ክስተቶች በተገኙ ቁጥር ፤ ጋዜጠኛ ከአዳዲስ ሁነቶች ጋር ይነጉዳል። እኔም ከዛ አልፌ ዛሬ ከቁጥር ሁለት ይልቅ ይህን  ቁጥር 3ን ፤ ቀድማችሁ ብታነቡ ስለ ሻእቢያና ስለተዋጊዎቹ  ሁኒታ ግንዛቤ  ያስጨብጣችኋል እዚያ ስለሚደረግውም የተሻለ ሰእል ይኖራችኋል በሚል ህሳቤ ቁጥር 3 ን አስቀድማችሁ ታነቡ ዘንድ እጋብዛችኋለሁ ። መልካም ንባብ!

///

ቼዝ ጨዋታ የምታውቁ ሰዎች ትኖራላችሁ ። ጨዋታውን ባታውቁትም የቼዝ አሻንጉሊቶችን ታውቋቸዋላችሁ ብየ እገምታለሁ ። ንጉሱ ፤ ንግስቲቱ ፤ ጳጳሳቱ ፤ ፈረሶቹ ፤ ግንቡና ወታደሮቹ ። እነዚህ አሻንጉሊቶች በራሳቸው የቼዝ ጨዋታን መጫወት አይችሉም ። የሚጫወትባቸው ሰው ይፈልጋሉ ። የሚጫወትባቸውም ሰው ልቡ እንደፈቀደ በቼዙ ገበታ ላይ ያሰማራቸዋል ። የምነግራችሁ የቼዝ አሻንጉሊቶች ግን አለም ላይ ከሚታወቁት የቼዝ አሻንጉሊቶች ለየት ያሉ ናቸው ። አሻንጉሊት የነበሩት ህይወት ይዘሩና እነሱም በተራቸው ሌሎች የቼዝ አሻንጉሊቶችን ፈልፍለው የተሰጣቸው ቦርድ ላይ መጫወት ይጀምራሉ። እነዚህ አሻንጉሊቶች ታዲያ ልክ ጠፍጥፎ እንደሰራቸው ጌታቸው ፤ የጨዋታ ህግና ስርአት የሚባል ነገር አያውቁም ። ተራ ጠብቀው አይሄዱም ፤ በፈለጋቸው ጊዜ ይዘላሉ ። ባሻቸው ጊዜ አክሮባት ይሰራሉ ። በጨዋታ በልጠህ ያገኘኽውን አሻንጉሊትም ከእጅህ ላይ ይነጥቃሉ ። ተቃራኒው ተጫዋች ጥያቄ ካነሳባቸው በጃቸው ያለውን ገድለው ፤ ሙሉ ለሙሉ በነሱ ቁጥጥር ስር ያልሆነውን ደግሞ ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ በማለት በታትነው ሌላ አሻንጉሊቶች ፍለጋ ይሄዳሉ ።

ዋናው ቼዝ ተጫዋች ኢሳኢያስ አፈወርቂ ነው ። የኢሳኢያስ አሻንጉሊቶች ግኡዞች ናቸው ። ኢሳኢያስ ዘንድ በተጠንቀቅ የቆሙም አሻንጉሊቶች ናቸው ። አይጠይቁ ሃሳብ አይሰጡ የተባሉትን ሰምተው ብቻ ነው የሚሄዱት ። ሲወጡ ግን በራሳቸው ህይወት ዘርተው ብቅ ይሉና ህዝቡን ወደ አሻንጉሊትነት እስኪለወጥ ድረስ ይቀጥቅጣሉ ። ኢሳኢያስ ኤርትራን ለመግዛት ህገ-መንግስት እንደሌለው ሁሉ ፤ የሱ አሻንጉሊቶችም ህዝቡን የሚገዙት ልባቸው በፈቀደ በጫካ ህግ ነው ። የዛሬዋ የቼዝ ገበታ ኤርትራ ናት ። ከኤርትራም ሃሬና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ።

///

ተወልዶ ያደገው አስመራ ከተማ ውስጥ ነው ። ገና በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ላይ ሲገባ “”ቀይህ እንባባ’’” ወይም ቀይ አበባ” የሚባለው የኢሳኢያስ የግል  ምልምል ወጣቶች ውስጥ አንዱ ሆነ ። ትዳር ይዞ ልጆች ከወለደ ገና ጥቂት አመታት ነው ያሳለፈው ። መጓጓዣው ቶዮታ ፒካፕ መኪና ናት ። ሽጉጥ ከወገቡ ካላሽ ከመኪናው አይለዩም ። አዲስ አበባን በደንብ የሚያውቃት አይመስልም ፡ ሆኖም ግን በ1991 እ.አ.አ. ግንቦት ላይ ወያኔዎች አዲስ አበባን እንደተቆጣጠሩ የሻእቢያን ጦር ይዞ ለተወሰኑ ወራት የአዲስ አበባውን ቤተመንግስት ጥበቃ ተቆጣጥሯል (እንደራሱ አባባል) ። እንደ አስገደ ገ/ ስላሴ መፅሃፍ ደግሞ ወያኔን ተከትላ የመጣች አንዲት ነጠላ የሻእቢያ ሻለቃ ጦር አጣዬ ላይ ሰፍራ ነበር ። ኢሳኢያስ የሻለቃው ጦር አጣዬ ላይ መቅረቷን ሲሰማ ያብዳል ። ባስቸኳይ አዲስ አበባ ገብታችሁ የኤርትራን ኮምዩኒቲ የቅስቀሳ ስራ አጠናክሩ የሚል ትእዛዝ ይሰጣል ። ይህ ሰው ታዲይ መሆን የሚችለው የዚች ሻለቃ ጦር መሪ ብቻ ነው ። ከኤርትራ ጉዞዎቼ በአንዱ ላይም የአስገደ ገ/ስላሴን መፅሃፍ ከአሜሪካ ገዝቼ እንዳመጣለት ጠይቆኝ ይዤለት ሄጃለሁ ። አስገደ ገ/ስላሴ የሚለውና ኮለኔል ፍፁም ቤተ-መንግስቱን ስለመቁጣጠሩ የሚያወራው በጭራሽ አይመሳሰልም ። ያም ሆነ ይህ ይህን ስራውን እንደጨረሰ ወዲያውኑ ወደአስመራ ተመልሷል ። ስለ አዲስ አበባ አንስተህ ስታወራው ደጋግሞ የሚነግርህ ይህን እውቀቱን ብቻ ነው ። ስለዚህ አዲስ አበባን በቅጡ እንደማያውቃት መረዳት ይቻላል ።

ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን የተሻልን ስልጡን ነን የሚለው ባዶ ጉራው ፤ አዲስ አበባን በቅጡ ባያውቃትም አስመራም ከአዲስ አበባ የተለየች አፍሪቃዊት ሮም ነች የሚለው የስብስቴ ጊዜ ተረት ትእቢቱ ግን ሁሌ በንግግሩ ላይ ይንፀባረቃል ። ትልቅ ሰው ፈረንጆቹ (Big Shot) የሚሉት አይነት መስሎ የመታየት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው ። ከምንም ነገር ተነስቶ ፤ ደረቅ ፈገግታ ሊያስይህ ይችላል ፤ወዲያው ደሞ ካለቦታው ፊቱ ልውጥ ብሎ ኮስተር ሊልብህ ይችላል ። ምንም ቢንጠራራ ታዲያ ቀልቡ የተገፈፈ ቀትረ-ቀላል የሚሉት አይነት ሰው ስለሆነ የግዝፈት ህልሙ አይሳካለትም ።

Fitusm Yesehak and Meazaw Getuይህ ሰው ኮለኔል ፍጹም ይስሃቅ ይባላል (ከዚህ ፎቶ ላይ በስተቀኝ የሚታየው)። “በኤርትራ በኩል ለምን” በሚለው የጉዞ ማስታወሻ ቁ. አንድ ፅሁፌ ላይ እንደገለጽኩት «ኮለኔል ፍፁም ይስሃቅ በቅፅል ስሙ “ሌኒን’ የአርበኞች ግንባር ፤ የድምሕትና፤ የግንቦት 7 ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ዋና አዛዥ ። በወታደራዊ ሰንሰለቱ “በስሪት አሃደ” በጀነራል ተክሌ ማንጁስ ስር መተዳደር የሚገባው ፤ ግን ከወታደራዊ ሰንሰለት ውጪ በቀጥታ ከፕሬዚደንቱ ፅ/ቤት ዋና ሹም ከኮለኔል ተስፋ ልደት ተ/ስላሴ ጋር የመገናኘት ስልጣን ያለው ።» ብየ አስተዋውቂያችሁ ነበር ። [በዚህ ፎቶ ላይ  ከግራ መአዛው ጌጡ ከቀኝ ደግሞ ኮለኔል ፍፁም ይስሃቅ ናቸው የሚታዩት]

ኮለኔል ፍፁም ሰዎችን መጀመሪያ ሲያገኝ ታላቅነቱን ለማሳየት ማነጋገር የሚጀምረው በትእዛዝ መልክ ነው ። ከትእዛዝ ቀጥሎ በአለማችን ላይ በተከሰቱ በአዳዲስ ግኝቶች የእውቀት ችሎታውን ፤ ለማሳየት ይጥራል ፤ ታዲያ እሱ አዳዲስ ግኝቶች ብሎ የሚያቀርባቸው ጉዳዮች በሌላው አለም አምስት ወይም ስድስት አመት ያሳለፉ የግኝቶች ቋንጣውች ናቸው ። እንዲህ አይነቱን ታላልቅ ንግግሮቹን ለማድረግ የሚሞክረው ከሁሉም ሰዎች ጋር አይደለም ። አንብበዋል ያውቃሉ ብሎ ከሚገምታቸው ሰዎች ጋር ብቻ ነው ። ከመጠሪያ ስሙ ይልቅ “ሌኒን” የምትለዋን ቅፅል ስሙን በፍቅር ይወዳታል ። ስለቅፅል ስሙ የሚናገሩለት ሰዎች ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ እንደሌኒን አንባቢ ነው ብለው እንደሚያወሩለት ስለሚያውቅ ነው ቅፅል ስሙን «ሌኒንን» የሚወዳት ። አንድ ምሁራዊ አስተያየት ስትሰጥ «ኮለኔል ፍፁም እንደምታውቀው» የምትል ሃረግ ጨምረህ ከተናገርክ ልቡ በሃሴት ሲሞላና ሃሴቱ ፊቱ ላይ ሲንቦገቦግ ታይበታለህ።

እኔ ወደግንባሩ ማሰልጠኛ ወደ ሃሬና ስወርድ የመጀመሪያዋን ሌሊት ያደርኩባት ንፁህ ጎጆ ኮለኔል ፍፁም «ሌኒን» አዲስ የቆርቆሮ ቤት ከጎጆዋ ከፍ ብሎ ከማሰራቱ በፊት ወደሃሬና ሲወርድ የሚያድርባት ጎጆ ነበረች ። ሻንጣዬን ከማስገባቴ በፊት ይህች ጎጆ ኮለኔል ፍፁም «ሌኒን» ያድርባት የነበረች ጎጆ ነች ተብሎ ተነገረኝ ። ውስጧ ከመንገድ አልጋና ከአንዲት ትንሽ ጠረጴዛ በቀር ምንም የላትም። ጠርጴዛዋ ላይ አንድ “Modern Management in the 21st century” የሚል ርእስ ያለው መፅሃፍና ማሾ ተቀምጧል ። ማሾው ለብርሃን ፤ መፅሃፏ ግን ለአንባቢነት ጉራ የተቀመጠች ይመስላል ።

ኮለኔል ፍፁም መጀመሪያ ስታገኙት ራሱን ለቻለንጅ (Challenge) ያዘጋጀ ሰው መስሎ ለመታየት ቢጥርም ፤ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ፈፅሞ ይህ ባህርይ የለውም ። ዋናው ምክንያት ግን ከአፈጣጠሩ በኢሳኢያስ ተጠፍጥፎ የተሰራ አሻንጉሊት ነውና የራሱ የሆነ ሰብእና የለውም ።

ኮለኔል ፍፁም «ሌኒን» ጥሎሽ ይወዳል ። ከውጭ የሚመጡ ሰዎች በተለይ የአርበኞች ግንባር ደጋፊዎች ገንዘብ ይዘው መጥተዋል ከተባለ ፤ የአርበኞች አመራሮች ናቸው ብሎ የሚያዘጋጃቸው ሰዎች አሉት ። ገንዘቡን በነሱ በኩል ይቀበልና አመራሮች ናቸው ያላቸውን ሰዎች ወዲያውኑ ይሰውራቸዋል ፤ በግንባሩ ተፈልገው ወደ ሃሬና ወረዱ ሲል ምክንያት ይሰጣል ። ምን ለማድረግ ወረዱ ብለህ ስትጠይቅ ፤ ምን ነካህ ይህማ ወታደራዊ ሚስጥር ነው አይነገርህም ፤ ይልሃል ። የሰጠናቸውን ገንዘብ ምን ላይ ሊያውሉት እንደፈለጉ ጠይቀን ውጪ ላለው ገንዘቡን ላዋጣው ኢትዮጵያዊ ሪፖርት ማድረግ አለብን እኮ ስትለው፤ «ሌኒን» በጣም ያዝንና ይተክዛል ። ለሌላ ለምን ያውሉታል ብላችሁ ነው ለማጣፈጫ እንጂ ሲልም ቅቤ ያነጉታል ። ለመሆኑ እናንተ በምእራቡ አለም ተንቀባራችሁ እየኖራችሁ እነዚህ ወንድሞቻችሁ የሚከፍሉት የህይወት መስዋእትነት ዛሬ ባመጣችሁት ገንዘብ የሚለካ ነውን ? ሲልም የጉዳዩን አቅጣጫ ያስቀይሳል ። ይህን ሲሰማ ሁሉም ሰው በሃሳብ ተውጦ ዝም ይላል።

እንደነገርኳችሁ ኮለኔል ፍፁም የኢሳኢያስ የቼዝ አሻንጉሊት ነው ።  ኢሳኢያስ ደሞ በኢትዮጵያ ፍቅር አይታማም ። «ኢትዮጵያ» እና «አንድነት» የሚሉት ሁለት ቃላቶች ለኢሳኢያስ ራስ ምታት ናቸው ። ስለዚህ ለኮለኔል ፍፁም የተሰጠው ትእዛዝ ይህን “አንድነት”፤ “አንድነት” ፤ “ኢትዮጵያ” ፤ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ሰው ወያኔን ለማስፈራሪያነት ብቻ ትጠቀምበታለህ ። ትንሽ አደግ ካለ እየከረከምክ ታስቀምጠዋለህ ። በብሄር ላይ ለተመሰረቱት ግን አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ታደርጋለህ ። የሚል  ነው።

ከላይ ለገለፅኩት ሁኔታ ሁለት ማሳያዎችን ላስቀምጥ ። አርበኞች ግንባር ከግንቦት 7 ጋር ከመቀላቀሉ በፊት መጠሪያው «የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር » ነበር ። «ኢትዮጵያ» የሚለው ቃል የአገሪቱን የግዛት አንድነት ሲያሳይ «ሕዝብ» የሚለው ቃል ደግሞ ስለ አንድ ህዝብ እንደምናወራ ይጠቁማል ። «አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ» ሲል ግን ሁለቱን መሰረታዊ መርኾዎች ጥሷል ። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከመጠሪያው ላይ ተገፏል ። ይህ አንድነትና ዲሞክራሲ ማን ላይ እንደሚተገበር አይገልፅም።

ሁለተኛው ደግሞ  2011 እ.ኤ.አ. የግንባሩ ጉባኤ ስለሚደረግ ወጪ ያላችሁ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ደጋፊዎች ሁሉ ለግባሩን ማሻሻያ ይሆናል የምትሉትን ፕሮፖዛል ይዛችሁ መቅረብ ትችላላችሁ ተብሎ ነበር። በኮለኔል ፍጹም በሚሽከረከረው በዚህ ጉባኤ ላይ (ጉባኤ ከተባለ) ለሁላችንም ሹመቱ ተነሰንሶልናል ።  አሁንም በምርጫ አልነበረም ። በትእዛዝ ነበር የተደረገው ። ኮለኔል ፍጹም ገንዘብ ይኖራቸዋል ይዘውም ይመጣሉ በሚል ግምትም በቦታው ያልነበሩ አሜሪካ የሚኖሩ ሰው በሊቀመንበርነት እንዲመረጡ በአሻንጉሊቶቹ በኩል ገፋፋ ። በአስቸኳይ መጥተውም ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ አስወሰነ። ይህ ግለሰብ ግን ጥሩ መረጃ እንደነበራቸው መገመት ይቻላል። ወደ አስመራ ለመምጣት ዝግጁ የነበሩት ግለሰብ ምንም እንኳ ድርጅቱ ማሰልጠኛና ማረፊያ ከሻእቢያ እየተሰጠው ሙሉ ለሙሉ ከሻእያ ቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል ተብሎ ባይጠበቅም  በተወሰነ ደረጃ ነፃነቱን እንዲያገኝና ሌሎቹንም ጉዳዮች ከሻእቢያ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር በመጠየቃቸው  የተናደደው የሻእቢያው ሿሚና ሻሪ ኮለኔል ፍፁም በጉባኤ ተሾሙ ለተባሉት ሰው ሊቀመንበርነት፤ ያለ ምርጫና ያለ ጉባኤ ሌላ ሰው ሾመበት።

ኢሳኢያስ አፈወርቂ በኤርትራ ላይ ፍጹም የሆነ ስልጣን እንዳለው ሁሉ፤ ኮለኔል ፍፁምም በሃሬና በአርበኞች ግንባርና በድምህቶች ላይ ፍፁም የሆነ ስልጣን አለው።  ( የድምህትን ጉዳይ ባለፈው ፅሁፌ ላይ እንደገለፅኩት ተመልሼ እመጣበታለሁ።)

ኢሳኢያስ ፊት አሻንጉሊት የነበረው ሰው፤ አርበኞቹና ድምህቶች ላይ ግን ከመለኮት የማይተናነስ ሙሉ ስልጣን አለው ። ሠውን መፍጠር አይችል ይሆናል እንጂ ያለ ማንም ጠያቂ ፤ ሕይወቱን ማስቀማት ማሰቃየት ማስራብ ማስገረፍ ይችላል።

ስለዚህ በተለይ ገንዘብ ከውጪ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ገንዘቡን ለተዋጊዎቹ የሰጡ ከመሰላቸው ተሳስተዋል ። በዘመነ ባርነት የአሜሪካ ባሪያዎች የነጭ አሳዳሪዎቻቸውን አይን አይተው እንደሚኖሩ ሁሉ የድምህትና የአርበኞች ግንባር ተዋጊዎች የኮለኔል ፍፁምን አይን አይተው በሱ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው ። ስለዚህ በአርበኞች ስም የሚላከውን ገንዘብ አሳዳሪያቸው ኮሌኔል ፍፁም ነው የሚቀበላቸው ። ኮለኔሉ ከውጪ የተሰበሰበ ገንዘብን በተመለከተ ያደርግ የነበረውን የሚያሳዩ መረጃዎች በብዛት ላቀርብ እችላለሁ። ሌሎች ወገኖችም እንደዚሁ መረጃዎች እንዳላቸውም አውቃለሁ ። ለጽ/ቤት ክራይ ፤ ለመብራት ፤ ለውሃ ለአስቸኳይ የግንባሩ የዘመቻ ስራዎች በሚል በሰሜን አሜሪካ ተቋቁመው ከነበሩ ሶስት የተለያዩ ቡድኖች ፤ በአውሮፓ ተቋቁመው ከነበሩ ሌሎች ሶስት ቡድኖች ፤ እስራኤል ከሚገኝ አንድ ቡድን እና አውስትራሊያ ይገኝ ከነበረ ሌላ ቡድን ፤ በተመሳሳይ ሰአት ተመሳሳይ የገንዘብ ጥያቄ እየቀረበላቸው አርበኞቹን የረዱ እየመሰላቸው ገንዘባቸውን ሲያፈሱ ቆይተዋል ። ገንዘቡም በነመአዛው በኩል ወደ ኮለኔል ፍጹም ይተላለፋል ። ጥሩ ገንዘብ ያስተላለፉ ቡድኖች ደግሞ የአለም አቀፉ የአርበኞች ግንባር ተወካዮች ናችሁ የሚል ደብዳቤ በኮለኔል ፍፁም ትእዛዝና በመአዛው ጌጡ ፊርማ ይላክላቸዋል ። በአንድ ወቅት ሶስት የአርበኞች ግንባር ደጋፊ ቡድኖች በተመሳሳይ ጊዜ የአርበኞች የአለም ቀፍ ውክልና ተሰጥቷቸው ተወካዮች እኛ ነን በሚል አተካሮ ውስጥ እንዲገቡ የተደረገበትን ሁኔታም አስታውሳለሁ ። ኮለኔል ፍፁም በነመአዛው ጌጡ በኩል በሚፈጥረው በዚህ ሁኔታ አማክይነት ፤ ቡድኖቹ በፉክክር የመዋጮ ኮታቸውን በራሳቸው ከፍ በማድረግ የኮለኔል ፍፁምን ገቢ ያዳብሩ ነበር።

ሌሎቹ የኮለኔል ፍፁም የገቢ ምንጮች ድምሕቶች ናቸው ። ሴቶቹን ለከብት ጥበቃና ለእርሻ ጉልጓሎ ይለዩአቸዋል ። ወንዶቹን ደግሞ ለአዝመራ ስብሰባና ለአጨዳ እንዲሁም ለመንገድ ስራ እንደየቁመናቸውና እንዳቅማቸው ይደለድሏቸዋል ። በተሰነይ አካባቢ ላሉ የግል እርሻ ባለቤቶች ድምህቶችን ያከራያቸዋል ።  ከወር ገቢያቸው እየተሰላ የተወሰነው ለድምህት ገቢ ሲደረግ ፤ በነፍስ ወከፍ በገቢያቸው መጠን የግል እርሻ ባለቤቶቹ ለኮለኔል ፍፁም ኮሚሽን ያስባሉ ።  ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የመጡትን ከብቶችና ፍየሎችንም የሚጠብቁት እነዚሁ የድምሕት ሰዎች ናቸው ። ይህ ብቻ አይደለም ትግርኛ ስለሚችሉ ተሰነይ ገበያ ላይ አውጥተው የሚሸጡም እነሡ ናቸው ። የከብቶቹንና የፍየሎቹን ሽያጭም ለኮለኔል ፍፁም ያስረክባሉ ።

ኮለኔል ፍፁም አንዴ እኔንና ሌሎች ሁለት ለአርበኞቹ ጉዳይ አስመራ እንገኝ የነበሩ ጓደኞቼን በራሱ መኪና ከአስመራ ወጣ እርድጎ ወስዶ ሻይ ጋብዞን ነበር ። እንዴት ጨዋታው እንደተነሳ ዛሬ ላይ ባላስታውሰውም ፤ ዱባይ ዘመዶች እንዳሉት ከነገረን በኋላ ለስራ ወደዱባይ ሲሄድ ግን የሚያርፈው ባለ 5 ስታር ሆቴሎች ውስጥ እእንደሆነ ነገረን (ምናልባት ለጉራ) ። ይህ ለኤርትራ ባለስልጣናት የተለመደ አይደለም ።

አንድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለውና ከወያኔዎች አምልጦ ኤርትራ የገባ ሰው በፍፁም አማካኝነት ከኤርትራ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር ። አስመራ ኤርፖርት አውሮፕላን ላይ ከወጣ በኋላ ፤ ፍፁም ከሸራ ቦርሳ ውስጥ በጋዜጣና በስኮች ቴፕ በደንብ የተጠቀለለ እቃ (ገንዘብ ነው) አውሮፕላኑ ውስጥ የትቀመጠበት ወንበር ድረስ በመምጣት ይሰጠዋል ። የመንግስት ሰነድ ነው ዱባይ እንደደረስክ የመንግስት ሰዎች ኤርፖርቱ ድረስ መጥተው ይቀበሉሃል ካለው ይለዋል ። መጥተው የተቀበሉት ሰዎች ግን የኮለኔል ፍፁም ዘመዶች መሆናቸውን ክሚኖርበት ከአውሮፓ ደውሎ አጫውቶኛል ። ጋዜጠኛ ነኝና ለፋክት (Fact) ፍለጋ እነዚህ ሰዎች ዘመዶቹ መሆናቸውን በምን አወቅህ ብየ ጠየቅሁት ። ከአውሮፓው በረራዬ በፊት 12 ሰአታት በላይ ዱባይ መቆየት ነበረብኝና ከነዚሁ ሰዎች ጋር አብሬ እንድቆይ ጋብዘውኝ  የቅርብ ዘመዶቹ መሆናቸውን ነገሩኝ ሲል አጫውቶኛል ። ስለዚህ ብዚህም  በዚያም ኮለኔል ፍፁም የሚያስገባውን ገንዘብ ኤርትራ ማስቀመጥ ስለማይችል ፤ ወደ ዱባይ ያሻግራል ማለት ነው ።

ከአስመራ ጉዞዎቼ አንዱ የኢሕአግን ራዲዮ የማስጀመር አላማ ነበር ። በዚህ ጉዞዬ ላይ አስመራ ከደረስኩ በኋላ ፤ ከዋሽንግቶን ዲሲ እኔ ልኬው የነበረውን የራዲዮ ስቱዲዮና ከለንደን በሌሎች ወንድሞች በካርጎ (Cargo) የተላኩ መሳሪያዎችን አስመራ እስኪደርሱልኝ ድረስ ለሳምንታት መጠበቅ የግድ ነበር ። አርበኞች ግንባር ፅ/ቤት ቤት ወስጥ ሁለተኛው ፎቅ ላይ አንድ ማደሪያ ክፍል ውስጥ ከአርበኞች ጋር አድር ነበር ። የፊኖ ቂጣቸውን ፤ የቀይ ማሽላ እንጀራቸውን  አብሬያቸው በልቻለሁ ።

ያኔ በቆየሁባቸው ቀናት በአንዱ ፤ የያኔው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር መሪ መአዛው ጌጡ ዛሬ ማታ ኮለኔል ፍፁም እኔና አንተን ራት ጋብዞናል ሲል ጥሪውን አስተላለፈልኝ ። እራት መጋበዣው ሬስቶራንት ዘንድ መአዛው ጌጡና እኔ ቀድመን ደረስን ። ለምን ጉዳይ እንደሚፈልገኝ መአዛው የሚያውቀው ነገር እንዳለ ጠየቅኩት ። መአዛው ምንም ነገር እንደማያውቅና ጋብዘው ብቻ እንደተባለ ነገረኝ ። ኮለኔል ፍፁም ዘግይቶ መጣ ። ራት ቀርቦ ከበላን በኋላ ፍፁም አንድ ጉዳይ አነሳ ።

“አሜሪካን አገር ውስጥ እገሌ እገሌ የሚባሉትን ሃብታሞች (በራሱ በኮለኔል ፍጹም ቃል ልጠቀምና “ባለፀጋዎች” ታዋቃቸዋለህ አይደለምን ?” ሲል ጠየቀኝ ።

“በሚገባ አውቃቸዋለሁ አልኩት”።

“ተቃዋሚውን ይደግፋሉ አይደለም?” ሲል ደግሞ ጠየቀኝ።

“አዎ እኔ እስከማውቀው ድረስ ይደግፋሉ” አልኩት።

“እነዚህን ሰዎች ወደአስመራ እንዲመጡ ብታደርግ ለትግሉ ትልቅ እርዳታ ነው” ፤ ካለኝ በኋላ ፤ “ወደአስመራ መምጣት ባይፈልጉ እንኳ ዱባይ ድረስ እንዲመጡ ካደረግክ መአዛውና እኔ እዚያ ድረስ ሄደን ልናነጋግራቸው እንችላለን” አለኝ ። ቀደም ብሎ ጉዳዩን እንደማያውቅ ነግሮኝ የነበረው መአዛው ጌጡ ኮለኔል ፍፁም በተናገረ ቁጥር በአዎንታዊ ራሱን ይነቀንቃል ። አሻንጉሊቶች ማለት እንዲህ የተቀረጹ ሰዎች ናቸው ።

ኮለኔል ፍፁም ሃብታሞቹ ሰዎች ተቃዋሚውን እንደሚረዱና ድጋፍ እንደሚሰጡ ከተለያዩ ወደ ኤርትራ ከገቡ ኢትዮጵያውያን ሰምቷል ። ለትግሉ ድጋፍ በሚልም ከነሱና  ወደፊት በነሱ በኩል ከሚመጡ ሰዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ አስቧል። ኮለኔል ፍፁም ሁሉን ኢትዮጵያዊ መሸወድ የሚችል መስሎ ይታየዋል ፡፡

ለሽወዳ ተግባሩ እንደናሙና እቃ የሚያቀርባቸው የአርበኞች ግንባር ተዋጊዎችን ነው። ገንዘብ ይዞ ከመጣ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ጋር ተኙ ሊላቸው ይችላል።

ሌላው ኮለኔል ፍፁም የሚታማበት በራሻይዳዎች በኩል ኤርትራውያንን ከአገር ማስወጣት ነው። ይህን የሰው ልጆችን የማዘዋወር ስራ የኤርትራ ወታደራዊ መኮንኖች እንደሚፈፅሙት አለም አቀፍ ድርጅቶችም ሪፖርት አቅርበውበታል። ራሻይዳ የሚባሉት የአረብ ዝርያ ያላቸው ሰዎች በኤርትራና በሱዳን ድንበሮች አካባቢ እይተዘዋወሩ የሚነግዱ ሰዎች ናቸው ። ከኢትዮጵያና ከሱዳን ኮንትሮባንድ በማስገባት ነው የሚተዳደሩት ። ሌላው ቀርቶ ነዳጅ በኮንትሮባንድ ያስገባሉ ። ባለፉት ቅርብ አመታት ደግሞ ከዚህ ንግድ ሌላ ከኤርትራ ሰዎችን በኮንትሮባንድ ያስወጣሉ ።

ኤርትራውያኑ ከትውልድ ቀያቸው ለስደት ሲወጡ ራሻይዳዎቹ ጋ ለመድረስ ብዙ ኬላዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል ። እዚያ የሚያደርሷቸው ደግሞ ኬላ ላይ ፍተሻ የማይመለከታቸው እነ ኮለኔል ፍፁም ናቸው ። ኤርትራውያኑ ገንዘባቸውን ለነኮለኔል ፍፁም በመክፈል ማንም የማይጠይቃቸው የይለፍ ወረቀት ይሰጣቸዋል። ተሰነይ ላይ የኮለኔል ፍፁም ተወካይ የድምሕት ሰዎች ለስደተኞቹ የተሰጣቸውን የይለፍ ወረቀቶች ይቀበሏቸዋልና በፒካፕ መኪና ጭነው ከተሰነይ በ5 ግፋ ቢል በ6 ኪሎ/ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የራሻይዳዎች የድንኳንና የገሳ ከተማ ድረስ በመውሰድ ለራሻይዳዎቹ ያስረክቧቸዋል ። ይህ ጉዞ እስከ 150 ሺህ ናቅፋ ወይም $3000 ዶላር ያስከፍላል ። ሁለት ሺህ ዶላሩ በአቀባባዮቹ አማካይነት ኮለኔል ፍፁምና መሰሎቹ እጅ ሲገባ ቀሪው $1000 ሺህ ዶላር ለአሻጋሪዎቹ ራሻይዳዎች ይሰጣል ። ይህ እንግዲህ የነኮለኔል ፍፁም ሌላው የገቢ ምንጭ ነው።

ራሻይዳዎቹ ደግሞ በዚህ ብቻ አያበቁም ።  ሱዳን ውስጥ ከሰሜናዊ ሱዳን እስከ ግብፅ ሳይናይ በረኻ ድረስ ለሚገኙት በደዊን አረቦች በገንዘብ ይሸጧቸዋል ። በሳይናይ በረኻ እርትራውያኑ ላይ የሚደርስባቸውን መከራ  ቀጥላችሁ ተመልከቱ ፤ የማንንም ሰው ልብ ያደማል።

በደዊን አረቦች ደግሞ አንጡራ ገንዘባቸውን ከፍለው የገዟቸውን ሸቀጦች ( የሰው ልጆች ) ኩላሊታቸውን በመሸጥና ዘመዶቻቸው ዘንድ በማስደወል ገንዘብ ይሰሩባቸዋል።

በኤርትራ ቴሌቪዥን አንዴ ኢሳኢያስ ቃለመጠይቅ ሲደረግለት ወጣቶች እየተሰደዱ ነው መፍትሄው ምንድነው ? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ «ድርብ ጥርስ ድሮስ ምን ያደርጋል ፤ አያኝክ ወይ ጌጥ አይሆን ነቅሎ መጣል ነው ። በራሱ ተነቅሎ ከሄደ ደግሞ እሰየው » ሲል መልሶ ነበር ። እነዚህን ድርብ ጥርሶች (ትርፍ ዜጎች) ታዲያ ኮለኔል ፍፁም ሸጦ ቢያተርፍባቸው ምን ችግር አለበት ? ለኮለኔሉ እነዚህም ሌላው የገቢ ምንጮቹ ናቸው።
አንዴ ከወልቃይት አካባቢ በወያኔ የተገፉና የተከፉ ወጣቶችና ጎልማሶች አርበኞች ግንባርን ለመቀላቀል ድንበር ተሻግረው ወደ ኤርትራ ይገባሉ ። ኮለኔል ፍፁም ከነዚህ አዲስ ከመጡት ሰዎች ውስጥ ሁለቱን ይመርጥና የሁለት ቀን የፈንጂ ስልጠና ይሰጣቸዋል ። ከዚያም በሱዳን በኩል አስርጎ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባቸዋል ። እነዚህ ቦንብ አስታቅፎ የላካቸው ገና ወደአገር ሳይገቡ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ ሲጠብቋቸው በነበሩ የወያኔ ወታደሮች ይያዛሉ ። ወያኔም በቴሌቭዥን እንዲቀርቡ አድርጎ እንዴት እንደሰለጠኑና ማን እንደላካቸው ፕሮፓጋንዳና ዜና ይሰራባቸዋል።

ኮለኔል ፍፁም ኢትዮጵያውያኑን ያለበቂ ዝግጅት ወደ ኢትዮጵያ ሲያሰርጋቸው ምን እያደረገ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል ። ሰዎቹ በቀላሉ በወያኔ እጅ እንደሚገቡም ያውቃል ። ወያኔም በቴሌቭዥን እንደሚያቀርባቸው ያውቃል ። ኮለኔል ፍፁም ይህን በማድረጉ ምን ይጠቀማል? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም ። ወያኔ በቴሌቪዥን ሲያቀርባቸው ፤ የኤርትራው «እንዳ ዜና» የሚባለው መስሪያ ቤት ስለኤርትራ የተጻፉትንና የተነገሩትን ዜናዎች ሁሉ እየሰበሰበ ለፕሬዚደንቱ ፅ/ቤት ሹም ለኮለኔል ተስፋ ልደት ተ/ስላሴ ይሰጣል ። ኮለኔል ተስፋ ልደትም ለኢሳኢያስ አፈወርቂ ማለዳ ላይ ሪፖርት ያቀርባል ። ኢሳኢያስም ይህን ሲሰማ ኮለኔል ፍፁም የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥርለታል ። ለኮለኔል ፍፁም የኢትዮጵያውያን ሕይወት የማገዶ እንጨት ነው ። የራሱን ተልእኮ እስካሟላባቸው ድረስ የነሱ ህይወት በጫማው ስር እንደተደፈጠጡ ነፍሳት እንኳ አይቆጥራቸውም።

ኮለኔል ፍጹም አሜን ብለው የሚቀበሉትን አሻንጉሊቶች እንጂ ቻሌንጅ (Challenge) የሚያደርጉትን ሰዎች እንደ ዋና ጠላት ነው የሚያያቸው ፡፡ በተለይ የአርበኞች ግንባር የሚጠናከርበትን የተለያዩ ሓሳቦች የሚያቀርቡና በራሳቸው የአመራር ብቃት የሚያሳዩ ወገኖች  በኮለኔል ፍፁም ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርጓል።

የአርበኞች ግንባር ሊቀመንበር የነበረው ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ አስመራ በቁም እስር ከሚኖርበት ከቤቱ ታስሮ ተወስዶ የደረሰበት ያልታወቀ።

ተስፋዬ ጌታቸው የአርበኞች ግንባር የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የነበረና በሓሬና ማሰልጠኛ እስር ቤት በድብደባ ብዛት ህይወቱ ያለፈ።

ስለሺ የሚባል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤሌትሪካል ኢንጂኔሪንግ 5ኛ አመት ተማሪ የነበረ የት እንደደረሰ ያልታወቀ።

አዳነ መኳንንት የአርበኞች ግንባር ዋና ፀሐፊ የነበረና የተረሸነ ።

ዮሴፍ ሁነኛው በህይወት ያለ ግን ከተሰነይ ከተማ እንዳይወጣ ተደርጎ በቁም እስር ላይ ያለ ።

ሽባባው አበበ በውጪ ሚዲያዎች መገደሉ ከተነገረ በኋላ ሻእቢያ  በራዲዮ አቅርቦት በህይወት አለሁ እንዲል ካስደረገው ብኋላ  የተገደለ ።

አዘዘው ይርጋ አዋጊ የነበረና በሻእቢያ የተረሸነ ። እነዚህ ብቻ አይደሉም ሌሎችም አሉ ።  እነዚህንና ሌሎች በኮለኔል ፍፁም የተገደሉ ወገኖች በሌላ ፅሁፌ እመጣበታለሁ ።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን በድርጅቱን ነፃነት ጉዳይ ኮለኔል ፍፁምን (Challenge) ቻሌንጅ በማድረጋቸውና የኮለኔል ፍፁም አሻንጉሊት መሆን ባለመፈለጋቸው ደብዛቸው እንዲጠፋ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በመጨረሻም !

በኢሳኢያስ አፈወርቂ ጭንቅላት ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባለው ግዙፍ ሃገር ከኤርትራ ጎን እያለች ኤርትራ በሰላም አትኖርም ። የኤርትራ ነፃነት አንደኛው ደረጃ ተጠናቋል ይኸውም ኤርትራ ነጻ መንግስት ሆናለች ። ሆኖም የኤርትራ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ የሚረጋገጠው ኢትዮጵያ የምትባለው ሐገር ፈራርሳ ትናንሽ ሃገሮች ሲፈጠሩ ብቻ ነው ፤ የሚል እምነት አለው ። ለዚህም ትልቁ ፕላን የብሄር ድርጅቶችን ማጠናከር ነው ። «ኢትዮጵያ» «ኢትዮጵያ» «አንድነት» «አንድነት» የሚለውን ወገን ለወያኔ ማስፈራሪያነትና የኢትዮጵያውያ የቃዋሚ ጎራን ሰርጎ ለመግባት  የሚጠቀምበት  ነው ። ቀንበሩን እያከበድክ እርምጃውን እያሰናከልክ፤ እንዳይሞትም እንዳይጠናክርም አድርገህ ያዘው የሚል መመሪያ ነው ለኮለኔል ፍፁም ከኢሳኢያስ አፈወርቂ የተሰጠው ።

ኮለኔል ፍፁም ከላይ የተሰጠውን መመሪያ በሚገባ የተረዳ በመሆኑ ስለኢትዮጵያ አንድነት በኤርትራ በኩል የሚዳክረውን ሁሉ የትም እንደማይደርስ ያውቀዋል ። ሆኖም ግን ይህን በየተራ እየመጣ እግሩ ስር የሚነጠፈውን ሁሉ እንዴት ለግል ፍላጎቱ እንደሚጠቀምበት ያውቃል።

ከእኛ ቀድመው ወደ ኤርትራ የሄዱ ከእኛ ቀድመው ተመልሰዋል ። እዛው አግኝተናቸው የተቀላቀልናቸው ወገኖችም ነበሩ ። እንሱም ተመልሰዋል ፤ እኛም በተራችን ሄደን ተመልሰናል ። ከኛም በኋላ የሄዱ ተመልሰዋል ። ሁላችንም ግን በጋራ ግልፅ የሆነልን ጉዳይ አለ። በሻእቢያ አዋላጅነት ኢትዮጵያን ከወያኔ ነፃ ማውጣት እንደማይቻል  ተረድተናል። መንገድ ይወስዳል ፤ መንገድ ያመጣል ። በተርኝነት የሄዱትም የእኛኑ ዘፈን እየዘፈኑ በሄዱበት መንገድ ተመልሰው ይመጣሉ። አለዚያም ካፈርኩ አይመልሰኝ በማለት ፈፅሙ የተባሉትን እየፈፀሙ አሻንጉሊቶች ሆነው እዛው ይቆያሉ።

በሚቀጥለው ፅሁፌ ሰላም ያገናኘን !

ጁላይ 27/2015

ከላስ ቨጋስ ኒቫዳ ።