በሄኖክ ሰማ እግዜር ላይ የተደረገውን ወከባ አወግዛለሁ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Henock Sema Egzerከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ

ትላንትና ምሽት ላይ ሁሌ እንደማደርገው ፤ የኢንተርኔት መረጃ መረቦችን ዜና መፈተሽ ጀመርኩ ። ያው እንደሚታወቀው በዋሽንግተን ዲሲ 32ኛው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ዝግጅት በየፈርጁ እየተከናወነ ስለሆነ ፤ ያሉትን ዜናዎች ለመመልከት እየተጣደፍኩ ነበር ወደ ቤቴ የገባሁት ። የፖለቲካ ፤ የሙያ ፤ የወጣቶች ፤ የሴቶች ማህበራቱና ሌሎቹም ጭምር በየፊናቸው ማንነታቸውን ለማስተዋወቅ ሽር ጉድ የሚሉበት ሳምንት ቢኖር ይህ የወርሃ ጁን የመጀመሪያ ሳምንት ነው ። እኔም ዋሽንግቶን ዲሲ በአካል ባልገኝም ፤ ለረጅም ጊዜ የኖርኩበት አካባቢም ስለሆነ ብዙ ትዝታዎች አሉኝና ፤ አሁን ካለሁበት ስቴት በሃሳብ ዲሲን ቃኝቻለሁ ።

በሰአታት ውስጥ የተለያዩ አይነት ዜናዎች ይጎርፋሉ ። አንዱን ሳልጨርስ ሌላው ይከተላል ።እናም ቦታው ላይ ባልገኝም ካለሁበት ቦታ ሆኜ በሃሳብ ደረጃ የደገፍኩት የፕሬዚደንት ኦባማን የኢትዮጵያ ጉዞ የሚቃወመውን ሰልፍ ነበር ። ድምፁ ከተዘረፈበት ፤ የሰላማዊ ታጋዮቹ ታንቀውና በዱላ ተደብድበው ከሞቱበት ፤ በነጻነት ሃሳባቸውን በመግለፃቸው አሸባሪ ተብለው ብሎገሮቹ ከታሰሩበት ህዝብ ጎን ይቆሙ ዘንድ የሚጠይቀው ይህ ሰላማዊ ሰልፍ በነጩ ቤተመንግስት መግቢያ ላይ እየተደረገ ነበር እንደደረሰኝ መረጃ ።

የሰልፉን ውጤት አያለሁ ብየ እንደጓጓሁ ዜናውን ከመረቡ ላይ ተጭኜ ስከፍተው የሰልፉ ዜና ቀርቶ ርእሱ የአሜሪካው ድምፅ ራዲዮ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ሆኖ አገኘሁት ። የሰልፉ አቢይ አላማ እዚህ ላይ ከሃዲዱ እንደዋጣ ባቡር እውር ድንብሩን በደም ፍላትና በባዶ ጭኽትና ጫጫታ ታጅቦ እንክትክት ብሎ ተሰባበረ ።

አሜሪካኖች የማያዩ መስለው የሚያዩ ትላልቅ አይኖች አላቸው ። የማይሰሙ መስለው በደንብ የሚያዳምጡ ጆሮዎችም አላቸው ። ከፋም ለማም እነዚህ አይኖችና ጆሮዎች ፤እንኳን ነጩ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት አይደለም በመላ ሃገሪቱ ብሎም በመላው አለም የሚደረገውን ክንዋኔ ሁሉ መዝግበው ያስቀምጣሉ ። ስለኛም ውሳኔዎች ሲሰጡ እንደመረጃ የሚያቀርቡት እነዚህኑ አይነት ተግባራቶቻችንን ነው ። እንደ ሲፒጄ የመሳሰሉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶችም ነገ በኛ ላይ ውግዘት ያቀርባሉ ። ይህ ደግሞ ለወያኔ መደብደቢያ ዱላችንን ማቀበል ይሆናል ።

ሄኖክ ሰማእግዜር የሚያቀርባቸው ዝግጅቶቹ ወያኔ ዘመምነት ይስተዋልባቸዋል ብለን ብናምን እንኳ ፤ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የሚመራባቸው መርሆዎች ሄኖክን እድንደልቡ ሊፈነጭበት እንዳይችል ሊገድቡት እንደሚችሉ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ ። በዚህ ላይ ሄኖክ ሰማእግዜር የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ወክሎት የመጣ ግለሰብ ነው ። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ህዝባችን ያለበትን የመረጃ እጥረት በተወሰነም ደረጃ ቢሆን እየቀረፈ ያለ የመረጃ አውታር ነው ። ሄኖክን እንደግለሰብ ብንጠላው እንኳ በአሜሪካ ድምፅ ተወካይነቱ ብቻ በህገ ልቡና አክብሮት የመስጠቱ ጨዋነት እንዴት ይጠፋናል ?

በቦታው ተገኝተው ሲጮሁና ሄኖክን ሲያዋክቡ የነበሩት ወገኖች ደግሞ ለብሰውት የነበረው ቲ-ሸርት ኢሳት የኔ ነው የሚል ነው ። ኢሳት ወያኔ ሃሳቤን በነጻነት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዳላስተላልፍ ከለከለኝ ብሎ የሚከስ ሚዲያ ነው ። የኢሳት ዜናዎች ሁሉ ብሎገሮች ታፈኑ ፤ ጋዜጠኞች አሳባቸውን በመግለፃቸው ተሳደዱ ታሰሩ ፤ የሚል ነው ። ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ ምልክት በሆነችው ዋሽንግቶን ዲሲ ፤ የዚህ መብት አስከባሪ ፕሬዚደንት በሚኖሩበት ነጩ ቤተመንግስት መግቢያ ላይ የኢሳት አባላት በምን የሞራል የበላይነት ነው ጋዜጠኛውን ሄኖክ ሰማእግዜርን ያን ያህል ወከባ ሊያደርሱበት የቻሉት ?

ሔኖክ እንደ ማንኛውም ዜጋ በዚች ሃገር ወስጥ ሙሉ መብት አለው ። መብት ስል ደግሞ ፤እንደጋዜጠኝነቴ ፤ በትውልድ ሃገሬም ሆነ በሌሎች ህይወቴ ይዛኝ በነጎደችበቱ አገራት ሁሉ ኖሮኝ የማላውቀውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እዚህ አሜሪካ በሚገባ ተጠቅሜበት ስላረጋገጥኩ የሌሎችን መብትም አከብራለሁ ፤ እንዲከበርላቸውም እጥራለሁ ። እንደኔ ፈቃድ አሰቡም አላሰቡ ፤ ብወዳቸውም ብጠላቸውም ፤ መብታቸው እንዲከበር አብሪያቸው እቆማለሁ ። ስለዚህም ዛሬ በሄኖክ ሰማ እግዜር ላይ የተደረገውን ወከባ አወግዛለሁ ። የዚህች የነፃዋ አሜሪካ አገር ህግ ለሄኖክ ባጎናፀፈው መብቱ ላይ የሚገዳደር ካለም ከጎኑ እቆማለሁ ። ይህ የጋዜጠኝነት ብቻ ሳይሆን የዜግነትም ግዴታየ ነው ።

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሕገ-መንግስት አንደኛው አመንድመንት (First Amendment) ለማንኛውም ሰው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይሰጠዋል ። ይህ መብት ታዲያ ተናጋሪውን ብቻ ሳይሆን የመረጃ ተቀባዩንም መብት የሚጠብቅ ነው ። መረጃ ተቀባዩ የማንበብ ፤ የማድመጥ ፤ የማይጣጣሙ አስተያየቶችን የመመልከትና የመመርመር መብትን እንዲሁ ፤ አንደኛው አሜንድመንት (First Amendment) ይጠብቅለታል ።

የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፉ የሰባዊ መብት ኮንቬንሽን አንቀጽ 19 እንዲህ ይላል ። “ማንም ሰው በነጻነት የማሰብና ያሰበውን የመግለፅ መብት አለው ፤ ይህ መብት አንድ ሰው ሃሳብን ያለ ምንም (ማንም) ጣልቃ ገብነት የመግለፅ የመጠየቅና የመመርመር ብሎም መረጃን የማግኘትና በማንኛውም ሜዲያ ሃሳቡን የማስተላለፍ ያልተገደብ መብት ያጎናጽፈዋል ።”

ታዲያ እንደማንኛውም ባለ መብት ጋዜጠኛም ሃሳቡን ያለ ምንም (ማንም) ጣልቃ ገብነት የመግለፅ የመጠየቅና የመመርመር ብሎም መረጃን የማግኘትና በማንኛውም ሜዲያ ሃሳቡን የማስተላለፍ ያልተገደብ መብት ተጎናፅፏል ።

ሄኖክ ሰማእግዜር ተገቢ መረጃ አላቀረበም በተባለበት ወቅት እንኳ ባለሙያው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የinvestigative journalist ስራውን ሰርቶ የሄኖክ ሰማእግዜርን ዘገባ በአገሪቱ ህግ መሰረት በሚገባ ተሟግቶታል ። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮም እስከመብታችን ጣራ ድረስ በመሄድ በቦርድ ደረጃ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ መስጠቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው ።

መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደለም የሚባለው ! በቅርቡ በጋዜጠኛ አበበ በለው ላይ በአትላንታ የደረሰውና በፓልቶክ የግንቦቶች ደጋፊዎች ነኝ በሚለው የመግረፊያና የመዝለፊያ አፌርስ ሩም ውስጥ ይከናወን የነበረው አሳፋሪ ተግባር እጅግ የሚዘገንን ነው ።

አበበ በለው እኔ ወደኤርትራ በተመላለስኩባቸው ጊዜያት ከመጀመሪያው ጉዞየ አንስቶ ፤ በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያ ነፃ ትወጣለች ብየ አላስብም እያለ ይሞግተኝ የነበረ ሰው ነው ። ታዲያ ሁል ጊዜ እኔም የሱን ሃሳብ አክብሬ እሱም የኔን አሳብ አክብሮ ነው የምንለያየው ። ከወራት በፊት እነ ልኡል ቀስቅስንና እነጋዜጠኛ ክንፉ አስፋን በራዲዮው አቅርቦ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር ኤርትራን በተመለከተ ። ያ ሁሉ ውርጂብኝ አበበ በለው ላይ የደረሰበት በግንቦቶች ሙዚቃ መደነስ ባለመፈለጉ ነው ። አርበኞች የሚለውን ስም ያልጨመርኩት እዚህ እነሱን የሚወክላቸው ወይም ጥሩንባውን የሚነፋላቸው አንድም ወገን አለመኖሩን ስለማውቅ ነው ።

አበበ በለው ራሱ ባይልክልኝም ጉዳዩን አስመልክቶ ለነአምን ዘለቀና ለብርሃኑ ነጋ የጻፈው ደብዳቤ ደርሶኛል በጎንዮሽ ። ነአምን ዘለቀ ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ልያልፈው ቢሞክርም ለአበበ በለው ደብዳቤ በፅሁፍ መልስ ሰጥቷል እንደኢሳት ተውካይነቱ ። ብርሃኑ ነጋ ግን እስካሁን ድረስ በፅሁፍ መልስ እንዳልሰጠው እርግጠኛ ነኝ ። በስልክ አነጋግሮት ሊሆን ይችላል ብየ እገምታለሁ ። ግን ጨዋ መሪ የእድርም ይሁን የእቁብ በፅሁፍ ለተላከ ደብዳቤ በፅሁፍ መልስ መስጠት ተገቢነው ። ያ ካልሆነ ግን ስልጡኑን የአለም ስርአት እንዴት ልንቀላቀልና ህዝባችንን ይዘን ልንራመድ እንችላለን ?

በአጠቃላይ የሰዎችን የማይሻርና የማይገሰስ መብት የማክበር ልምድ ይኑረን ። ስለሰብአዊ መብት እንከራከራለን እያልን እኛው የምንጨፈልቀው ከሆነ ፤ የመናገርና ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን በተግባር ሳይሆን ለፕሮፓጋንዳ ብቻ የምንጠቀምበት ከሆነ ፤ የሰዎችን የመሰብሰብ ነፃነት መብት የማንቀበል ከሆነና የሰዎችን የእምነት ነጻነት የምንጋፋ ከሆነ ፤ እኔ በበኩሌ ጨቆኞችን አንስቼ ሌላ ጨቋኞች ትከሻየ ላይ የምጭንበት ምክንያት ስለሌለ ትግሉ ባፍንጫየ ይውጣ ።

ጁላይ 4 ቀን 2015 እ.አ.አ