ሁለት ክፉ ካገር ይጥፉ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ሰሞኑን በኢትዮሜዲያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የድረሱልኝ ጥሪ ሳነብ አዘንኩኝ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና የሳይንስ ተቋማት ኮሶ ከተጣባቸው ቆይቷል። አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው ሲሾሙ ማልቀስ፣ ምህላ መግባት፣ ኢትዮጵያ ታበጽህ ዕደዊሃ ሃበ እግዚአብሄር ማለት ያን ጊዜ ነበር። አቡነ ጳውሎስ የክርስትና ዕምነት ተከታያቸውን የመንግሥተ ሠማያት በር ሊያስከፍቱለት ቀርቶ ምድራዊ ህይወቱን አምሳለ ሲዖል አድርገውበት አረፉ። የሲኖዶሱን ህግ የጣሰ የፓትርያርክ ሲመት ሲሰጣቸው ኤሎሄ ኤሎሄ፣ አልሻዳይ፣ ፀባዖት አዶናይ ብሎ ወደሰባቱ ሰማያት መጮህ ያን ጊዜ ነበር።
ልክ እንደ አቡነ ጳውሎስ ሲመት ሁሉ የከፍተኛ ትምህርት መተዳደሪያ ደንብ ተጥሶ በሳያንሱ ህብረተሰብ ጫንቃ ላይ ከየት መጣ ሳይባል ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የሥልጣን ርካብ ሲረግጥ ያን ጊዜ ነበር ለአልበርት አነስታይን፣ ለኒውቶን፣ ለአርኪመዲስና ለአርስቶትል አምላክ ስምዓነ አምላክነ ወመድሃኒነ ብሎ ሱባዔ መግባት ።
የአቡነ ጳውሎስ ጦስ በመዲናይቱ ኗሪ በሆኑ ምዕመናን ብቻ ተወስኖ አልቀረም። በመላ አገሪቱ የሚገኙ አድባራትን በጎሳ ወረርሽኝ እንድለከፉ በማስገደዱ ልጽደቅ ብትል እረስ፣ ልኮነን ብትል ቀድስ የተባለው ደረሰ።፡ይባስ ብሎ ድንበር ዘለል ጠባይ በመላበስ ባህር ማዶ ተሻግሮ አሜሪካንና አውሮፓን ሲንጠው ውሎ ሲንጠው ያድራል። በተመሳሳይ የፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ መዘዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወስኖ አልቀረም። መላው የሃገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች አርማውን አንስተው ተግባር ላይ አውለውታል። የእንድርያስ እሸቴን ፈለግ መከተል የግድ ነው። እንደንጉሡ አጎንብሱ ነዋ!
አቡነ ጳውሎስ ሃውልት ሲያቆሙ ተከታዮቻቸው የመሠረት ድንጋይ ቢጥሉ አያስኮንናቸውም። ተከተል አለቃህን ተመልከት ሰንደቅህን ነው። አዲስ አበባ ያሉ አድባራት ቁልፍ ቦታዎች ለጳጳሱ ታማኝ የሆኑ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሲደለደሉ በተዋረድ የሚገኙ የትንንሽ ከተሞችና የገጠር የሃይማኖት ተቋማት አሠራሩን ኮርጀው መጠቀም ግደታቸው ነው። አባ ጳውሎስም ለዘመናት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ደሴት ሆና የቆየችውን የቤተክርስቲያን የሃላፊነት ቦታዎች እርሳቸውና መንግሥትን ብቻ በሚደግፉ እፉኝቶች መዳፍ ውስጥ ጣሉት። ለሰው ሞት አነሰው የሚለውን አነጋግር መላልሰን የምናነብበት ዘመን ላይ አደረሱን። እንፀልያለን፣ ፈጣሪ ፊቱን ዞሯል። እንዘምራለን፣ ዝማሬ መላዕክትን ለመስማት አልታደልንም።
ፕሮፌሰር እንድርያስና አቡነ ጳውሎስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተደቀነ የምፅዓት ምልክቶች ናቸው። ፕሮፈሠሩ የሳይንስ ጠበብት ነኝ ቢሉም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አያውቁትም፣ አያውቃቸውም። ከአሜሪካ ግዛት ተወርውረው ድንገት አራት ኪሎ ተተከሉ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዘመናዊ ትምህርት ፈር የቀደደ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትና ይዘት ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ልምድ እንዲቀስም አስገደዱት። ልምዱንም ቀሰመ። ሹመት በትምህርት ሳይሆን በፓርቲ አባልነት የሚለውን አቋራጭ መንገድ ከፈተ። በሳይንሱ ጎራ አንቱ የተሰኙ ምሁራን ግን “እያንጓለለ” የሚለው የዛር ድቤ ተጎሰመባቸው። ሳይንስና ሶሻል ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደራሂሎ ተሸኙ። ራሂሎ ሂጅ ቶሎ ቶሎ። ፋከልቲ ተወለደ ፣ ሳይንስ ሞተ። ዶክትሬት ተወለደ፣ ምርምር ሞተ። ተማሪ ተፈለፈለ፣ ትምህርት ሞተ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደፀጉራም ውሻ ክሳቱ ሳይታወቅ እየሞተ መሆኑን ሰበር ዜና ሰማን።
ለማንኛውም ፀረ ሃይማኖተ አበው የሆኑትን ጳጳስና ሳይንስን ሳይገንዙ የቀበሩት ፕሮፌሰር ሁለት ክፉ ካገር ይጥፉ ብለን መፀለይ እንጅ ሞታቸውን መናፈቅ አይበጀንም። ምክንያቱም “ጌታ ሆይ ክፉ ሰው አታምጣብኝ” ብላ ግዑዟ መሬት ፈጣሪዋን ትለምናለች አሉ። ምህላዋ መልስ ካገኘ የኔ ቢጤው ገራገር በነሱ ምትክ መጥሪያ እንዳይላክለት ብናዝንለት መልካም ነው።
ቸር ይግጠመን
ወርቁ ለገሠ (01/26/11)