ትውስታዬ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር – ክፍል 1


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከይሁን ነጻነት

በ1993 ዓ.ም በዋናው መሥሪያ ቤት “ትልቅ” ብለው የጠሩት ሥብሰባ ይካሄዳል በመባሉ አምባሳደሮች ከያሉበት አዲስ አበባ ገስግሰው ደርሰዋል።ወጪያቸውም በሙሉ በመሥሪያ ቤቱ ይሸፈናል በመባሉም ደስታቸው ልክ አጥቷል። በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥም ከሶስተኛ ጸሃፊ በላይ ያሉ ብቻ በስብሰባው እንዲሳተፍ ማስተወቂያ በመለጠፉ ለስብሰባው ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው።

አምባሰደሮቹ አንገታቸውን በካራባት አስረው ለንጉስ ሰርግ የተጠሩ እድምተኞችን መስለውና ከጣሪያ በላይ እየተሳሳቁ በተራ በተራ ወደ አዳራሹ እየገቡ ፊት ለፊት ከተደረደሩ ወንበሮች ላይ ይኮለኮላሉ። ከዚያም ግማሹ እየተሳለቀ፤ ቀሪው እየተሳተፈ ፤ሌላውም እያሳተፈ ስብሰባው ለድፍን አስራ አምስት ቀናት ተካሄደ።ቀሪዎቹ ደቂቃን ደግሞ አለቆቻቸው በሙሉ በሥብሰባ ስለተጠመዱ አስራ አምስቱን ቀን በሙሉ ሥራ ሳይሰሩ አሳላፉ።

የመጨረሻውን ቀን ስብሰባ መለስ ዜናዊ ስለሚመራው ተሰብሳቢው በሙሉ እርሱ ወደአለበት ተጠራ።እርሱ ህዝብ ወደአለበት መመጣትን ባለመፍቀዱ ብዙሃኑ ወደ እርሱ በሰልፍ ሄደ።ስዩም መስፍንም ከዚያ አለ።አንዴ ምንስቴር ዴእታ ሌላ ግዜ ደግሞ አምባሳደር ሲሉት ሁሉንም ይሁን ብሎ ባስቀመጡት የሚገኝ የቤቱ ጌጣ ጌጥ ተቀዳ ዓለሙም ከዚያ አለ።

መለስ ያለማቋረጥ ሲናገር ስዩም መስፍን በግንባሩ ወደ ቁልቁል የሚንዥቀዥቀውን ላብ ጠረጴዛ ላይ ባስቀመጣት መሃረብ መልሶ መላልሶ እየጠረገ ሳይታክት ይጽፋል።ከመለስ አንደበት ይሄ ነው የሚባል በጎ ነገር አይወጣም ስዩም ግን አንዷንም ቃል አይገድፍም።ተጀምሮ እስኪፈጸም በተመስጦ ይጽፋል።ከስብሰባው ታዳሚዎች መካከል በመለስ ንግግር ሳይሆን በስዩም መስፍን እንዲያ ሳይታክት መጻፍ በጣም የተገረሙ ብዙ ነበሩ።

መለስ እንዲህ አለ “ዛሬ የጠራናችሁ ውጤታማ ሥራ አለመሥራታችሁን ልንነግራችሁ ነው።በእናንተ ምክንያት እየከሰርን ነው።ዲፕሎማሲያችንን ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ብለን ስትራቴጅ ነድፈን ብንሰጣችሁም የሠራችሁት ይሄ ነው የሚባል ነገር የለም።ለምኖ ገንዘብ ማምጣትን የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ ብለው ሲያቆላምጡት አለማፈራቸው ይገርማል።መለስ ዜናዊም ቀጠለ ማምጣት የሚገባችሁን “ሃርድ ካሽ” አላመጣችሁም።በዓመት 240ሚሊዮን ብር በጀት እየበላችሁ ምንም “ሃርድ ካሽ “ አላመጣችሁም።ዋና ስራችሁ “ሃርድ ካሽ” ማምጣት ነው ሌላ ምንም ስራ የላችሁም።ዝም ብሎ ባንዲራ ማውለብለብ ምንም ዋጋ የለውም።በእናንተ ምክንያት ከስረናል።እስኪ ለምን መሥራት እንዳቃታችሁ አስተያየት ካላችሁ እንስማ” ብሎ አምባሳደሮቹ ላይ አፈጠጠ።

ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ስዩም ምስፍንም ሳያቋርጥ እየጻፈ ነው።ምን እንደሚጽፍ እላይ ከሰማይ ያለው ከእግዜር በቀር ሌላ ማንም አያውቅም።

አንድ አምባሳደር እጁን አውጥቶ እንዲህ ሲል ጠየቀ “የኢኮኖሚው ዲፕሎማሲ ያልተሳካልን ምናልባት ፖለቲካው ላይ አተኩረን ይሆን ?” ሲል በሚንቀጠቀጥ ድምጽ ጠየቀ።

መለስ ለአምባሳደሩ ጥያቄ እንዲህ ምላሽ ሰጠ ”እናንተ ፖለቲካውን ሰርታችሁት አይደለም እስከ ዛሬ ይህች አገር የቆየችው።ከእናንተ በላይ የዚህችን አገር ፖለቲካ የሚሰሩልን አሉ።እርሱን በተመለከተ የምንፈልገውን ነገር በተሻለ ፍጥነትና በተሻለ የጥራት ደረጃ እዚህ ካሉ ከየአገራቱ አምባሳደሮች ማግኘት ስንችል እናንተ እርሱን ሰራችሁ አልሰራችሁ ብለን አንጠይቃቻሁም።”
ሌላም ጥያቄ ተከተለ ለምሳሌ ጋና ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምን ዓይነት “ሃርድ ካሽ ማግኘት እንችላለን።እዚያ ያለው ኤምባሲ ባንዲራችንን እያወለበለበ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ ውጪ ምን ሊሰራ ይችላል?”
መለስ ዜናዊ ነፍሱ በተቃርኖ የተሞላች ነች።ዛሬን እስካደረ ድረስ ለነገ የሚል ደግ አስተሳሰብ ያለው ጤነኛ ሰው አይደለም።እናም ከጋና ምን ዓይነት “ሃርድ ካሽ” እናገኛለን ተብሎ የተጠየቀውን ጥያቄ እንዲህ ሲል መለሰ “እኛ እያልን ያለነው ገንዘብ ሊሰጡ የሚችሉ አገራት ውስጥ የምትሰሩትን አምባሳደሮች ነው።ሃርድ ካሽ የማታመጡ ከሆነ ምን ልትሰሩ ነው ታዲያ ? ካሁን በኋላ ኪሳራውን ይዘን ለመቀጠል አንችልም” ብሎ አስፈራራ።

በዲፕሎማሲው መንደር ውለው የማያውቁ ካድሬዎችን አምባሳደር ናችሁ ብሎ ሹሞ ሲያበቃ ይህን አልሰራችሁም ያን አላደረጋችሁም ብሎ መቆጣት ድንፋታ ይባላል።ከመለስ ድንፋታ በኋላ ስብሰባው ተፈጸመ ተባለ።
አንዱ አምባሳደር “እንግዲህ “ሃርድ ካሽ” ካልተገኘ የራሴን ደሞዝ አጠራቅሜ ይዤ እመጣለሁ” ብሎ ቀለደ ሲባል ሰምተናል።ይህ ግን ቀልድ አይመስልም።

ያን ግዜ ከደቂቃኑ መካከል እኔ አንዱ በመሆኔ በዚህ ስብሰባ ላይ አልተጋበዝኩም።ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብሮ ከመስራት ተሰድጄ ርቄ ብኖር ይሻለኛል ብሎ ቀየውን መንደሩን ጥሎ ወደ ሩቅ አገር የተሰደደው የዚያን ግዜ አለቃየ ከስብሰባው በኋላ ስንጫወት የነገረኝን መንደርደሪያ አድርጌ ወደ ራሴ ሌላ ትዝታ እዘልቃለሁ።

ትዝታየ እንዲህ ይጀምራል፤

እግዜርን ፍራ።እግዜርን መፍራት ስታውቅ ሰው ትሆናለህ።ልጄ እባክህ ሰው ሁን እያለ ያሳደገኝ አባቴ አሁን በህይወት የለም።እግዜሩን ፈርቶ እኔንም እንድፈራ አድርጎ ኑሮ ሲያበቃ በቅርቡ አረፈ።

ማህበረ ሰቡም ገና ድሮ ህጻን ሳለሁ ፈሪሃ እግዚአብሄር ከሚገለጽባቸው ነገሮች መካከል አንዱ በአገር ላይ የተሾመን ሁሉ ማክበር ነው ብሎ አስተምሮኛል።መንግስቱ ኃ/ማሪያምን ያስነሳው አምላክ ነው።መለስ ዜናዊንም ያመጣው እርሱ ፈጣሪ ነው።እርሱ ያመጣውን እርሱ እስኪመልሰው ድረስ ጸጥ ለጥ ብለን ተገዝተን እንድንኖር ትእዛዝ እንዳለ እየተነገረኝ ለአቅመ አዳም ደረስኩ።

ታልቁ መጽሃፍም ትእዛዙን የሚጠራጠር አንዳች አያገኝም ብሎ አስፈራርቷል።የተሾመን ማክበር ለእርሱም መታዘዝ ፈጣሪን መፍራት እንደሆነ ከመቀበል ወጪ የተለየ እውቀት የሌላቸው ወላጆቼ ይሄን እውነት ነው ብለው ተቀብለውና መክረው አሳድገውኛል።

ከዚያም ሀ ሁ ብየ ፊደል ቆጥሬ አ ቡ ጊዳንም ዘልቄ የእውቀቴን ልቀትና ጥልቀት ላሳፋ ተመኝቼ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ገባሁ።ከዚያ የዘላለም የሰው ልጆች ማደጊያ ሥፍራ ከፍ ባለ ማእረግ ተመረቅሁ።ከዩንቨርስቲ ካገኘሁት እውቀት ላይ የአቶ ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር መልካም ፈቃድ ታክሎበት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተቀጠርኩ።ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር ውጭ ጉዳይ የሚቀጠሩ ሰዎችን የጀርባ አጥንት/ታሪክ የሚያጠና ነው።ይህ ሰው በአቦጊዳ ላይ ሸፍቶ የኖረ ቢሆንም ትንጥየ “ጌታ” ሁኖ በሰዎች እድል ፈንታ ላይ ወሳኝ ሁኗል። ይቀጠር ያለው እየተቀጠረ፤ አይቀጠር ያለው ደግሞ እየተከለከለ ለረዥም ግዜ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሰርቷል።አቶ ሃዱሽ ክፉ አይደለም።ታዞ ሥራውን የሚሰራ በሰገባው የተገኘ ታማኝ አገልጋይ ነው።የጌቶቹን ትእዛዝ ተቀብሎ በራሱም ትንሽየ “ጌታ” ሆኖ እድል ፈንታቸውን የሚወስንላቸውን እጩ ተቀጣሪዎች የስም ዝርዝር ጽፎ የያዘበትን ዶሴ ይዞ ታች ላይ ሲል ከፍ ያለ የሥራ ኃላፊነት ያለውን ሰው ይመስል ነበር።ህወሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ወዲህ ያገኘው የሞራል ልዕልና ካልሆነ በቀር በኑሮው የደላው ነገር ያለ አይመስልም።ህወሃቶች “አማራ ብርቱ ጠላትህ ነው ኦሮሞም ቢሆን አይተኛልህም” ብለው የነገሩትን ነውር ትምህርት አምኖ እርሱንም ትጥቅና ስንቁ አድርጎ የጀርባ አጥንት እያጠና በዜጎች እድል ፈንታ ላይ ውሳኔ ሰጪ በመሆኑ ደስ ብሎት የሚኖር ምስኪን ሰው ነበር።አሁን የት እንዳለ አላውቅም ምን አልባት የአንዱ አምባሰዳር ጠባቂ አድርገውት ይሆን ይሆናል።ምንአልባትም በአንዱ ኤምባሲ የጸጥታ ጉዳይ አማካሪ ሁኖም ይሆናል።በቦታውና በሰገባው የተገኘው አቶ ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር ይቅርና ዘውዱ የተባለው ነፍሰ ገዳይ በአማካሪ ማዕረግ ኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመድቦ እስከ ኡጋንዳ ድረስ እየተጓዘ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ሲገድል አልከረመም ? አሁንስ ዱባይ ላይ የህወሃት ተወካይ ሆኖ “እየሰራ” አይደል ? በዱባይ “ዜድ” ቴሌቶን አቋቁሟል የሚባለውስ እርሱ አይደል ?የጸጥታ አማካሪ ማለት ዜጎችን በጭካኔ ለመግደል ድፍረት ያለው ማለት እንጂ ሌላ አይደለም።አቶ ሃዱሽ ግን ደክሟል ሩጦ ለመያዝ፤ አልሞ ለመቶኮስ፤ ጨብጦ ለመያዝ ጉልበቱ ያለው አይመስለኝም።ዘውዱ የሚባለው ሰውየ የሚሰራውን ሥራ ሊሠራ አይችልም።የቀረው እድሜም ለንስሃ ከመሆን የሚዘል አይደለም።

ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ውስጥ መስራት ገንዘብ ምንስቴር ወይም ደግሞ ት/ት ምንስቴር ውስጥ እሰራለሁ እንደማለት ቀላል አይደለም።ውጭ ጉዳይ መሥራት ማለት በሁለት ስለታም ጥርሶች ውስጥ እንደመኖር ነው።የውጭ ሰዎች እንደ ህወሃት ካድሬ እየቆጠሩ በጎ ባልሆነ ዓይን ያዩሃል እዚህ ውስጥ ያሉት ደግሞ የድርጅታቸው አባል መሆንን ባለመውደድህ በጥርጣሬ እየተመለከቱህ በገዛ አገርህ ሃዘን በዝቶብህ ትኖራለህ ።የሃዘናችን ምንጭ ያው የ”ትግራይ ነጻ አውጪ ነኝ” የሚለው ቡድን ነው።

አንድ የህወሃት ካድሬ በአንዲት ምሽት የሚያጠፋትን የምታክል ደመወዝ እየተከፈለኝ ለመስራት ተስማምቼ በዚህ መሥሪያ ቤት ስቀጠር በርቀት ያየሁትን ተስፋ እውን ለማድረግ አስቤ ነበር።
ይቀጥላል፤