ኢንተርኔትና ዲሞክራሲ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የቤላረስ ተወላጅ በሆኑት ኢቭጀኒ ሞሮዞቭ ኢንተርኔትና ተምኔታዊ ግንዛቤው፡ የኢንተርኔት ነፃነትና አሉታዊ ተፅዕኖ በሚል ርዕስ የተጻፈ 408 ገፆችን ያካተተ አዲስ መጽሓፍ ገበያ ላይ ውሏል።

በሽህ የሚቆጠሩ የኢራን ወጣቶች ሰኔ ወር 2009 በተደረገው ምርጫ ድምፃችን ተነጥቋል በማለት ሠላማዊ ሠልፍ የወጡ ተቃዋሚዎችን አስመልክቶ ምዕራባውያን የዜና አውታሮች ትዊተር የተሰኘውን ብሎግ የተጫወተው ሚና በተጋነነ መልኩ ዘግበዋል። ለምሣሌ የወል ስትሪት ጆርናል በኢራን የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ያለ ትዊተር ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም ብሏል። ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነ አንድሪው ሱሊቫን የተባለ የብሎግ ፀሃፊ የኢራንን ጨቋኝ ሥርዓት ለመታገል ይቻል ዘንድ ትዊተር ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ይጠቅሳል። የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣም በበኩሉ ሠልፈኞች በትዊተር አማካይነት ደጋፊዎቻቸውን ለአመፅ ሲያነሳሱ የመንግሥት የፀጥታ ቡድኖች ተኩስ የከፈቱባቸው መሆኑን አስታውቋል።

እንደሌሎች የመገናኛ ቴክኖሎጅዎች ሁሉ የኢንተርኔት መረጃ ዐብዮታዊ ትግልን በማፋፋም ግፉዓንን ዲሞክራሲያዊ መብት ያላብሳል የሚለው እሳቤ ሰፍኖ የቆየ አመለካከት ሲሆን ከላይ ለማሳዬት እንደተሞከረው የኢራኑ ምርጫ በዋቢነት የሚጠቀስ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ሞሮዞቭ የጻፉት መፅሃፍ ይህን የሳይበር ተምኔታዊነት በፅኑ ይቃረናል። ደራሲው የሚሰጡት አመክንዮ ኢንተርኔት አፋኝ ሥርዓቶችን ለመገርሰስ የሚያስችለውን ያክል በአንድ አገር ላይ አፈና ተንሰራፍቶ እስከወዳኛው እንድቆይ ጠቃሚ መሣርያ ሆኖም ሊያገለግል ይችላል። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የምዕራቡ ዓለም ፖሊሲ አርቃቂዎች ኢንተርኔት ዲሞክራሲን ለማራመድ ፍቱን ዘዴ ነው የሚል ዕምነት ላይ ሙጭጭ በማለታቸው ድሞክራሲያዊ ሽግግርን ቀላል በማድረግ ፋንታ ከባድ እያደረጉት ይገኛሉ።

ደራሲው የኢራንን የኢንተርኔት ተመክሮ በመንተራስ ጠንካራ ትችት ያቀርባል። በቋታር የሚገኘው አል-ጄዚራ እንደዘገበው ከሆነ በቴህራን ትዊተር ብሎግ የዘወትር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ60 አይበልጥም። በሠላማዊ ሠልፍ የተሳተፉት የዚህ ቴክኖሎጅ ታዳሚዎች የትዊተር ዐብዮት ተብሎ የተነገረለትን ክስተት ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰውበታል። በአንፃሩ የአሜሪካ መንግሥት የትዊተር አብዮት ይሁንታ እንዲያገኝ በማድረጉና ለጥገና ተብሎ ቴክኖሎጅው አመፁ በተፋፋመበት ሰዓት አገልግሎቱ በመቋረጡ የኢራን ባለሥልጣኖች ሁሉንም የሶሻል ኔትወርክ ተጠቃሚዎች ለማደን ዕድል ሰጣቸው። ለምሳሌ ወደኢራን የሚገቡ ትውልደ ኢራናዊያን ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያገናኛቸው የፌስ ቡክ አካውንት ያላቸው መሆኑን ማጣራት ተያያዙት።፡ይህ ክስተት የአሜሪካ የፖሊሲ ጠበብቶች ከጠበቁት ውጤት የተገላቢጦሽ መሆኑን ልብ ይሏል። .

ደራሲ ሞሮዞቭ የችግሩ ምንጭ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ አሳቢዎች ድሮ የሬዲዮ ፕሮፓጋንዳና ሌሎች የብዙሃን መገናኛዎች ሶቬትን ለማፈራረስ ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ሁሉ ኢንተርኔት ለተመሳሳይ ተግባር ሊውል እንደሚችል በሚያራምዱት ተምኔታዊ አስተሳሰብ ነው። ይህ ግልብ የሆነ የታሪክ ንፅፅር
የኢንተርኔት መዘርጋትና የመጠቀም “ነፃነት” በዚህ ዘመን የሚገኙ ጨቋኝ ሥርዓቶችን ለማምበርከክ ይረዳል የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ መድረስ ስህተት ነው።
እንዲያውም ሥልጣን ላይ ሙጭጭ የሚሉ መሪዎች እንደሌሎች መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ኢንተርኔትን ለሥልጣናቸው ማራዘሚያ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ማመን አለብን። ለምሣሌ የምሥራቅ ጀርመን ኗሪዎች የአሜሪካን ቴሌቭዥኖችን እንዲመለከቱ በመደረጉ የተፈጠረው መዘናጋት ብዙ ግለሰቦች ለፖለቲካ የነበራቸው ፍላጎት እንድቀዘቅዝ ምክንያት ሆኗል። ይህንን አስመልክቶ በተካሄደ ጥናት የምዕራባውያንን ቴሌብዥን የሚመለከቱ የምሥራቅ ጀርመን ዜጎች ከማይመለከቱት ጋር ሲነጻጸር በነበረው መንግሥት ላይ የሚያሳዩት ጥላቻ በዕጅጉ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል። አንድ የምሥራቅ ጀርመን የመንግሥት ተቃዋሚ “ዜጎቻችን በሙሉ ከምሽቱ ስምንት ሰዓት ላይ ልክ በአንድ ልብ ሆነው በቴሌቭዥን ተጭነው ከምዕራቡ ዓለም ገብተው ያድራሉ” ሲል ምሬቱን ገልጿል።

ሞሮዞቭ ልክ እንደ ቴሌቭዥን ሁሉ ጨቋኝ ሥርዓቶች ኢንተርኔትን የህዝባቸውን ቁጣ ማርገቢያ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሆነ በርካታ ምሳሌዎችን በጥንቃቄ አጠናቅረዋል። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገለጽ ህገወጥ ቪዲዮ፣ ፖርኖግራፊ፣ አስቂኝ የቪድዮ ክሊፖች እነሆ፣ የፖለቲካ ጥያቄ ከማንሳትም ሆነ ከማራገግ ራቁ የሚል መልዕክት በሥውር ለህዝባቸው ያስተላልፋሉ። በዚህ መልኩ የተቀፈደደ ህብረተሰብ ስለፖለቲካ ደንታ ቢስ መሆኑን ደራሲው አስምረውበታል።

በተለምዶ ከሚሠራበት የስለላ ዘዴ በኢንተርኔቱ ህብረተሰብ ታዳሚ የሆነውን ተቃዋሚ ለይቶ ለማወቅ ቀላልና ብዙ ወጭ የማይጠይቅ ነገር ነው። ከቻይና ተመክሮ እንደምንረዳው የሴንሰርሽፕ ቴክኖሎጅ ምጥቀት የፖለቲካ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ብቻ ነጥሎ በማወክ ኢንተኔት የኢኮኖሚ አገልግሎት ፋይዳው ሳይተጓጎል መጠቀም ተችሏል። ይባስ ብሎ ኢንተርኔት ለፕሮፓጋንዳ ተግባር የመዋል ባህርይ ስላለው አፋኝ ሥር ዓቶች የራሳቸውን አጀንዳ ማራመጃ ያደርጉታል። ለምሳሌ ቻይና ሥርዓቱን የሚደግፉ የሰላ ብዕር ያላቸው የብሎግ ፀሃፊዎች አሏት። በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተአማኒነት ባጡበት ህብረተሰብ ኢንተርኔት የተሻለ አማራጭ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል እሙን ነው።

የአፋኝ ሥርዓት መሪዎች የኢንተርኔት ዕውቀታቸው ውሱን ነው የሚለውን አቋም ደራሲው አይስማሙበትም። ኢንተርኔት በፖለቲካ ህይዎት ውስጥ የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ከምብዕራባውያን አቻወቻቸው የተሻለ ግንዛቤ አላቸው ይሉናል። ስለኢንተርኔት የተዛባ ግንዛቤን አስመልክቶ የሩሲያ መንግሥት ወጣት አማካሪዎች የሚጫወቱትን ሚና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ቀድሞ የተፈለሰፉ የመገናኛ ብዙሃን ቴክኖሎጅዎች ማለትም ቴሌግራፍ፣ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድሞክራሲን ለማጠናከር ይረዳሉ ተብሎ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር። ተስፋችን ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። የቴሌቭዥን ቻነሎች መሥፋፋት እንደተጠበቀው የተመልካቹን ቁጥር እንዲያሻቅብ አላደረገውም፣ እንዲያውም አሽቆለቅለ። የትዊተር፣ ፌስ ቡክ እና ጉግልን አገልግሎት ልቅ በማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ገለልተኛነቱን ከማጣቱ ባሻገር እነዚህ የብዙሃን መገናኛዎች ለግፈኛ ሥርዓቶች የውጭ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነው እንዲያገለግሉ አመቻችተውላቸዋል።

ደራሲ ሞሮዞቭ የኢንተርኔትን አጠቃቀም አስመልክቶ የሰነዘሩት አማራጭ ምንድነው? ቴክኖሎጅ በትክክል ሥራ ላይ ከዋለ ዲሞክራሲን ለማስፋፋት ያግዛል። ስለሆነም “cyber-realism” በአስቸኳይ “cyber-utopianism”ን ሊተካው ይገባል ነው የሚሉት። እያንዳንዱ ሥርወ-መንግሥት የራሱ ልዩ ባህርያት ስላሉት የሚወሰደው ዕርምጃ እነዚህን ክስተቶች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ከማለታቸው በስተቀር በዝርዝር ያስቀመጡት መፍትሄ የለም።

ውድ አንባብያን፦ ከቀረበው ፅሁፍ አንፃር ኢንተርኔት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የተጫወተው ሚና ምን ይመስላል? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ከናንተ እጠብቃለሁ። ዽምፅ ካጠፋችሁ ብዙ አልቀየማችሁም። ነገር ግን እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም የሚለውን ባህላዊ ዘፈን እንዳንጎራጉር ይፈቀድልኝ።

ወርቁ ለገሠ (ምንጭ፡ ዘኢኮኖሚስት)