ዕንቅልፍ ያጣች ንብ ማር አትሠራም ተባለ (ወርቁ ለገሰ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ንብ ብዙ ጊዜ የታታሪነት ምሳሌ ሆና ትጠቀሳለች። አበቦች ቀስማ ማር ለመፈብረክ ጥበብ የተካነችውን ንብ ወያኔ በ2005ቱ ብሔራዊ ምርጫ አርማው አድርጎ ተጠቅሞባታል። የኢትዮጵያ ህዝብና ንብ ሆድና ጀርባ የሆኑበት ጊዜ ቢኖር ያን ጊዜ ብቻ ነው። በተረፈ ግን “ይሠሯል ከልብ እንደንብ” እየተባለ ሥራ ወዳድነቷ ትውልድ የማይሽረው ምሳሌያዊ አነጋገር ሆኖ ይኖራል።
ሰሞኑን የተደረገ ምርምር እንደጠቆመው ንብ ለሥራ ትጉህ መሆኗ አዘውትሮ ይነገር እንጅ ደከመኝ ሰለቸኝ የማትልና እንደሮቦት ስትከንፍ የምትኖር ፍጡር እንዳልሆነች አስምሮበታል። ሰው ዕለታዊ ተግባሩን በትክክል እንዲያከናውን ዕንቅልፍ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ንብም መተኛት፣ አስፈላጊ ሆኖም ሲገኝ ማንኮራፋት አለባት። ይህ በግኝትነቱ የመጀመሪያ መሆኑ የተነገረለት ጥናት የተካሄደው ንዝረት የሚፈጥር መሣሪያ በመጠቀም ንቦቹን ሌሊቱን ሙሉ እንዳያንቀላፉ ሆን ብሎ በመረበሽ ነው። እንዲህ ዕንቅልፋቸው የተቆራረጠውን ሠራተኛ ንቦች ተመራማሪዎቹ ቀን ምግብ ፍለጋ ሲሰማሩ ተከታተሏቸው። እንደሚታወቀው ንቦች ማር የሚሰሩበትን አበባ ሲያስሱ ውለው በለስ ከቀናቸው ተመልሰው ለባልደረቦቻቸው ይነግሩና እንደገና ወደቦታው ይተማሉ። የአበባውን ቦታ መጀመሪያ ያገኘችው ንብ ያስከተለችው ሠራዊት ረጅም በረራ ካደረገ በኋላ ከቦታው የደረሰ መሆኑን የምታመላክተው በምታሳየው ዳንስ ነው። እዚህ ላይ ነው ዕንቅልፍ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ የተገለጠው። ንቧ ያሳየችው ዳንስ ከወትሮው የተለዬ በመሆኑ አበባው ያለበትን ትክክለኛ ቦታ ለተከታዮቿ ማሳወቅ ተሳናት። ያ ማለት በንብ ዓለም ለከፍተኛ ኪሣራ ይዳርጋል። ለሠራተኛውም ሆነ ለንግስቲቷ ንብ ምግብ በወቅቱ አይቀርብም። ዕጭ አይፈለፈልም። ስለዚህ ሊዋለዱና የቀፎው ቁጥር መጨመር ቀርቶ የነበረችው አንድ ቀፎ ንብ አልባ ትሆናለች። የዕንቅልፍ ዕጦት መዘዝ ከንቡ ህብረተሰብ አልፎ ሰው የማር እሸት እንዳይቆርጥ ደንቃራ ይሆናል ።
ይህን የምርምር ውጤት ተንተርሰን ዕንቅልፍ ማጣት በአዳም ዘር ላይ ሊኖረው የሚችለውን ጉዳት በአጭሩ እንመልከት። ሰው በህይወት መኖር ይችል ዘንድ በቂ ዕንቅልፍ ማግኘት አለበት። እኛ ስንተኛ ሰውነታችን ውስጣዊ ጥገና ያካሂዳል። የዛለ የአካል ክፍል አገግሞ ለነገ ዝግጁ የሚሆነው ሌሊቱን ዕረፍት ሲያደርግ ነው። ግምታችን ወደገሃዱ ዓለም የሚጠጋው ንቁና ከዕንቅልፍ መጫጫን ነጻ ስንሆን ነው። ካልሆነ ግን እንፈዛለን። ቀይና አረንጓዴ መብራት ልዩነታቸው አይገባንም። የዕንቅልፍን አስፈላጊነት ለመረዳት የሃኪም ምክር መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም። ሳይተኙ ካደሩ መልሱን ወዲያውኑ ያገኙታል።
ኢትዮጵያውያን አገራችን በኖርንበት ዘመን ዕንቅልፍ ማጣት ጥቃት ሰንዝሮብን አያውቅም። እኔ ሥጋቴ ጎኔ እንዳይላጥ ነበር። የአሜሪካው ህይወታችን ግን ከዕንቅልፋችን ጋር አጥፊና ጠፊ ሆነው ይታያሉ። ቤት የገዛንም ሆነ የተከራዬን በየወሩ ዕዳችንን የመክፈል ግዳጅ ውስጥ ገብተናል። ቀኑ እንደ ጄት ይወረወራል። አንዳንድ ጊዜ በአሜሪካ አገር አንድ ቀን 24 ሰዓት መያዙ የሚያጠራጥር ነው፡፡ የጥር ወር ኪራይ ተከፍሎ ሳያልቅ የየካቲት ብቅ ይላል። ታዲያ እንድህ ዓይነቱን አበሳ ለመወጣት ሁለት ሥራ መሥራት ግድ ነው። እዚህ ላይ ነው ዕንቅልፍ ደህና ሰንብች የምንለው። ንቧን ያንገላጀጀ ዕንቅልፍ ማጣት እኛን አዙሮ አይደፋንም ትላላችሁ? የናንተን አላውቅም። እኔ ካልተኛሁ የሰው ድምፅ ቀርቶ የራሴ ያስጠላኛል። መኪና መንዳት ይደብረኛል። በአገራችን የትራፊክ ደንብ ላይ በጉልህ ተጽፎ የሚነበብ አንድ ቁም ነገር አሁንም ትዝ ይለኛል፡ “ከጠጡ አይንዱ”። አሜሪካ ያለው የትራፊክ ደንብ “ካልተኙ አይንዱ” ቢል መልካም ነበር።
ወርቁ ለገሰ