ህይወትን ሰውቶ ህይወት መለገስ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ንብ ቀፎው ሲነካበት ግው ብሎ ይተማል። ፉክክር የለም። አባቶቻችን ይህን ፈለግ በመከተል ዳር ድንበራቸው በተደፈረ ቁጥር ልክ እንደንብ በመቆጣት ግዳይ ጥለው አልፈዋል። እነሱ ሞተው እኛን አኖሩን ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ መስዋዕትነት በተለያዩ የ እንስ ሳት ዝርያ የሚስተዋል ሲሆን በዕፅዋት ዓለም እንዲሁ ድንቅ በሆነ መንገድ ይከናወናል።ተክሎች እንደንብ ተፈጥሮ መርዝ አላደለቻቸውም። እንደሰው ደግሞ ጎራዴ፣ ጠመንጃ ወይም ተዋጊ ጄት ተጠቅመው ከጥቃት መከላከል አይችሉም።  ስለዚህ የሚጠቀሙበት የመከላከል ዘዴ አጥፍቶ መጥፋት ነው። እንመልከተው።

አብዛኞቹ ዕፅዋት እንደዝርያቸው በተለያዬ በሽታ ይጠቃሉ። ከነዚህ በሽታዎች አንዱ ባይረስ ነው። ከዐቅማቸው በላይ ሆኖ ካላገኙት በስተቀር ከመኖር ምዕራፍ ሊፍቃቸው የዘመተውን ዕልፍ የቫይረስ መንጋ ዝም ብለው አይመለከቱትም። ቫይረሱ መጀመሪያ የሚያጠቃው ያረፈባትን ቅጠል ነው። ከዚያች ቅጠል ውስጥ ተደብቆ ምሽጉን ካጠናከረ በኋላ ሌሎች ቅጠሎችን ላይ ያላሰለሰ ጥቃት ይሰነዝራል። በለስ ከቀናውና ሁኔታዎች ከተመቻቹለት በተክሉ የምግብና የውሃ ማስተላለፊያ ክፍል በመዛመት ሥሩን፣ ግንዱንና ቅጠሉን በመመረዝ ትልቁን ዋርካ ሊገነድሰው ይችላል። 

ይህ መጠነ ሠፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ግን መጀመሪያ ጥቃት የተሰነዘረባቸው የቅጠል ህዋሳት ለጎረቤቶቻቸው በሚገባቸው ቋንቋ ቫይረሱ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ሹክ ይሏቸዋል። ጤናማ የሆኑት አጎራባች የቅጠል ህዋሳት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዜጎቻቸው ላይ የደረሰውን ጥፋት ረጋ ብለው ይገመግማሉ። ጥለው አይሸሹም። ጎኑና ርዝመቱን ቀይሰው ካጠኑ በኋላ ቫይረሱ የነሱን በር ገና ሳያንኳኳ ራሳቸውን ማጥፋት ይጀምራሉ። ይህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አጥፍተህ ጥፋ ፖሊሲ የቫይረሱን መንጋ በዙር ገጠም መሸጋገሪያ ድልድይ ያሳጣዋል። ቫይረስ ደግሞ በህይወት መኖር ይችል ዘንድ ህይዎት ያለው የተክል ህዋስ ይፈልጋል። መከበቡን ያልጠረጠረው የቫይረስ ሠራዊት ዕጁ የገቡለትን ህዋሳት በሙሉ ከፈጀ በኋላ ወደሌላው ለመዛመት ሲሞክር ዙሪያውን የከበበው አስከሬን ሆኖ ያገኘዋል። መግደል ምንም መስሎ የማይታዬው ቫይረስ በተራው የሞትን ፅዋ ይጎነጫል።  የበሽታው ሥርጭት በዚህ የረቀቀ ዘዴ ከተገታ በኋላ መሃሉ ላይ ጠባሳ የወጣበት ቅጠል ሳይቀር ይለመልማል። ጤነኞቹ ቅጠሎች የተሰውላቸውን ሰማዕታት ክብር በነፋስ ሃይል እየደነሱ ያስቧቸዋል። ተክሉም የተለመደ ሥራውን በሚገባ በማከናወን ከራሱ አልፎ ለእንስሳትና ለሰው ልጆች ህይዎትን ይለግሳል።

ሰው እኮ…..? ማለታችሁ አይቀርም። ሰውም ቢሆን ያው ነው። አባቶቻችን አድዋና ማይጨው ሞተውልን እኛ እንኖራለን። መሬት ላራሹ ያሉ ተማሪዎች ፊዳ ሆነውልን እኛ አርሰን እንበላለን፤ የ4 ኪሎ ተማሪዎች ሞተውልን እኛ እንማራለን።  ኢየሱስም በመስቀል የዋለው ለሰ ልጆች ሲል መሆኑን መጽሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ርግጥ ነው በህይዎት መኖር መብት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት በህግ አስቀምጦልናል። ይህ መብት ሲሸራረፍ ስናይ ግን እናስከብረው ዘንድ ትንሽ ትንሽ መሞት ግድ ይለናል።

እንደበሬ ሻኛ ከሰው በላይ ያውላችሁ። መልካም ገና፣ መልካም አዲስ ዓመት!!!

ወርቁ ለገሠ (12/21/10)