ሸፍጠኛ የመሬት ፖሊሲውና ወያኔ-በወርቁ ለገሠ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ቹክቺ የተባሉት ዘላኖች ሩሲያ በሚገኘው ቹኮትስኪ የባህር ሠላጤ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ እያደኑ ወይም በባህር ላይ እያሠገሩ የኖሩ ሰዎች ናቸው። የሶቬት ህብረት በ1920ዎቹ የአምራቾች የህብረት ሥራ ማህበር እንዲያቋቁሙ ያስገደዳቸው ሲሆን የሶቬትን ውድቀት ተከትሎ የህብረት እርሻው ፈርሷል። የፖሊሲው ውጤት? አብዛኞቹ የቹኩቺ ጎሣዎች አሁን በህይወት ለመኖር የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋሉ። የዚህ ብልሹ የሶቬት ህብረት ፖሊሲ በደርግ ዘመን ተኮርጆ ኢትዮጵ ላይ ተሞክሯል። ከወሎና ትግራይ በግዴታ እየታፈሱ በጋምቤላ፣ በመተከልና በሌሎች አጎራባች ክልሎች ተፈትሾ የከሸፈ መሆኑን ብዙዎቻችን እናስታውሰዋለን። አሁን ደግሞ በወያኔ ፖሊሲ መልኩን ቀየር አድርጎ ስህተቱ እየተደገመ ይገኛል። መሬት ለኢንቨስተሮች እየተቸበቸበ ነው። ዘላኖች /አርብቶ አደር/የሆኑት ሰዎች የዚህ ፖሊሲ ዕንቅፋት ስለሚሆኑ በዘዴ ከመሬቱ ላይ ማንሳት ያስፈልጋል። በተጨማሪ ለተቃዋሚ ሃይሎች ምሽግ እየሆኑ አገልግለዋል የሚሉም አሉ። ስለዚህ የለመዱትን የአኗኗር ዘይቤ ለቀው እንዲከትሙ ግድ ይላል። የዚህ ፖሊሲ ትጉህ አራማጅ የሆኑት ክቡር አበራ ደሬሳ “እኛ ዘላኖች ወደተሻለ ህይወት እንዲመጡ እንፈልጋለን። በዚህ መልክ ሲኖሩ ዝም ብሎ የሚመለከት ጨካኝ አንጀት የለንም” ይሉናል። ክቡር ሚኒስትሩ በመቀጠል “ይህን የተቀደሰ የመንግሥት ዓላማ የሚያራክሱ ሁሉ ፖሊሲውን ለመረዳት የተሳናቸው ደናቁርት ናቸው” በማለት ይዘልፋሉ።
ፖሊሲውን በተግባር ለመፈፀም በተደረገው ዕንቅስቃሴ ህንድ በቀሉ የካሩቲሪ ካምፓኒ በጋምቤላ ትልቅ የርሻ መሬት ወስዷል። ሲፈልግ አበባ፣ ካልሆነም ሩዝ ሊያመርትበት ይችላል። በአካባቢው ከሚገኙ ወንዞች ለሚጠልፈው ውሃ ገደብ አልተጣለበትም። የጊሎም ሆነ የባሮ ወንዝ ጀልባ ሊሸከም ቀርቶ ቅጠል ይዞ መጓዝ እስከሚያቅተው ውሃውን ሊያሟጥጠው ይችላል። ወንዞችና አካባቢው በኬሚካል ሲበከል ተቆጣጣሪ አይኖርም። ከዚህ ኢንቨስትመንት የሚተርፈን ምንድነው? ወዮ ባሮ፣ ወዮ ጊሎ ብቻ ነው። የጋምቤላ ጫካም ተረት ተረት ይሆናል። በመሠረቱ የጋምቤላ መሬት አረንጓዴ እንደመልበሱ ለም አይደለም። ልማቱ ከጫካው ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው። ጫካው ከተቆረጠ የጨረቃ መሬት ለመሆን ጊዜ አይፈጅበትም።
ያ ማለት ደግሞ አኟኮችን ጨምሮ ብዙ ጎሳዎች መፈናቀል አለባቸው። አርብቶ አደሩ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የሥጋና የወተት ተዋጽኦ እንደሚያቀርብ እየታወቀ ልክ አሳፋሪ ዜጋ አስመስሎ ማቅረብና ለዘመናት ጸንቶ የኖረውን አኗኗር ማፍረስ ለማንም አይበጅም። በሶቬት አልሠራም። በሌሎች አፍሪካ አገሮች ተሞክሮ አልሠራም። ኢትዮጵያ ላይ የሚሠራበት ተአምር ምንድነው?
የካሩቱሪ የጋምቤላ ኢንቨስትመንት ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል? የሚል ጥያቄ አንስቶ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የተወሰኑ ሰዎችን አስተያየት ሰብስቦ ነበር። ብዙዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባሆኑም ከመለሱት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት አይጠቅምም፣ 20 በመቶ ይጠቅማል፣ 10 በመቶ ደግሞ አናውቀውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የፕሮጀክቱ ሰለባ ከሆኑት አንደበት ደግሞ እዚህ ያዳምጡ።
በሠለጠነው ዓለም ግብይት ውስጥ ገብተው በቅጡ የሚሠራ የጺም መላጫ ለመግዛት ክህሎቱ የሌላቸው መሪዎቻችን የኢንቨስትመንት ፖሊሲያቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ሊያስጠብቅ ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይባስ ብሎ ዕውቀት እንደ ደም ያጠራቸው የወያኔ ሹማምንት ክፋት፣ ብቀላና ተንኮል ይጨምሩበታል። ከዚህ ዓይነት እኩይ ሥርዓት የሚመነጭ ፖሊሲ በሥራ ሲተረጎም የሚሰጠው ጥቅም ቀጥሎ የተዘረዘሩትን እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም፡
- ዳጎስ ያለ ጉቦ ለመቀበል የወጭ አርዕስት ይከፍታል። መሬት በሄክታር በዚያ ዋጋ ይሸጣል?
- መንግሥትን የሚፋለሙ ሃይሎች ካሉ ለማዳከም ይበጃል-ኦጋዴን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው
- የ5 ዓመቱን ዕቅድ አስመልክቶ ጠ/ሩ ዕርዳታ፣ ብሎም ለፓርላማ የሚያቀርቡት ሪፖርት ያገኛሉ- ዋናው ሪፖርቱ ነው!
- ድሃንና ድህነትን በአንድ ድንጋይ ለመግደል ያለጥርጥር ያስችላል-ኧረ እሪ በል ድሃ የሚለውን ግጥሜን አትርሱብኝ።
ወርቁ ለገሠ (12/19/10)