ልዩነቱን ያውቃሉ?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የተወሰኑ ሰዎች በጮርቃነቱ የተነቀለ ካሮት (Baby carrot) የተሻለ የምግብ ይዘት፣ ጣዕምና መስህብ አለው ብለው ስለሚያምኑ ከጎመራው ካሮት በላይ አዘውትረው ይመገቡታል። ይህን የተመጋቢ ምርጫ ልብ ያለው ማይክ የተባለ  የካሊፎርኒያ ገበሬ አንድ ቀን ለዬት ያለ ሃሳብ መጣለት። መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የጎመራ ካሮት ከጫፉ ትንሽ የመበስበስ ምልክት ሲታይበትና ቅርጹ ከተለመደው ተጣሞ ሲገኝ ፈላጊ የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ችግር ተከስቶ ለሽያጭ አመች ባልሆነበት ወቅት በሞተር ሁለት ቦታ በመቁረጥና በማለስለስ ጮርቃ ካሮትን አስመስሎ ለተጠቃሚ ማቅረብ እንደሚቻል ተገነዘበ። ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ተፈላጊውን መሣሪያ በማሳዎቹ ጥግ ተከለና አንዱን ካሮት ከሁለት ቆርጦ ቅርጽ በማውጣት በላተኛው ሊለያቸው የማይችል ጮርቃ ካሮቶችን አስመስሎ በመሥራት “Baby-cut carrots ብሎ ሰየማቸው።

የሌላውን ሰው አስተያዬት ባላውቅም በኔ ግምት Baby-cut carrots የካሮት ብክነትን ለመቀነስ ግሩም የሆነ የፈጠራ ሥራ ነው። በ2006 ዓም  ካሊፎርኒያ 3/4ኛውን የዚህ “ሰው ሠራሽ ካሮት” ምርት ለገበያ አቅርባለች። በገበያ አዳራሽ በፕላስቲክ ታሽጎ የምታዩትና ለመግዛት የሚያማልላችሁ ካሮት በዚህ መልኩ የተሠራ ነው። ታዲያ ምንድነው ችግሩ? ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም።

ችግሩ እንዲህ ነው። በማሽን የተፈጠሩት ካሮቶች የተፈጥሮ ቅርጽ ተሰጥቷቸው ከመፈብረካቸው በፊት ቆዳቸው ይገለፈፋል። ያ ማለት ደግሞ ለመበስበስም ሆነ ለመበላሸት የተጋለጡ ናቸው ማለት ነው። ስለሆነም ብልሽትን ተከላክሎ ከበላተኛው ዘንድ ለማድረስ ዘዴ መቀዬስ ያስፈልጋል። ለጊዜው የተገኘው ዘዴ ልክ ለመዋኛ ገንዳችን እንደምናደርገው በክሎሪን ማከም ነው። ክሎሪን ደግሞ ለፊኛና ሌሎች የካንሰር በሽታዎች ያጋልጣል ተብሎ የብዙ ሳይንቲስቶች ጣት ተቀስሮበታል። ክፉን ከኛ ያርቀውና ማንም ሰው ካንሠር እንዲይዘው አይፈልግም። በተለያዬ መልኩ ወደሆዳችን የምናስገባው ኬሚካል አንሶ ደግሞ በካሮት በኩል ቀዳዳ መክፈት አላዋቂነት ነው። ከረጅሙ ባጭሩ መፍትሄው ምንድነው? ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ መልሱ እንደሚከተለው ነው።

ልትገዙት ያነሳችሁት የታሸገ ካሮት “ Baby carrot” የሚል ጽሁፍ ከተለጠፈበት ይሄ ትክክለኛው ምርት ስለሆነ ሌሎች ሳያነሱባችሁ ግዙ።  Baby-cut carrot ካለ ግን ይህ እንደ አገሬ ዳቦ ቆሎ በሞተር ቅርጽ የወጣለትና በክሎሪን የታከመ ስለሆነ ይቅርባችሁ። ለዚህ ሁሉ ስሌት ጊዜየን አላጠፋም ካላችሁ ግን ጆሮው ላይ ቅጠል ያንጠለጠለውን ትልልቁን ካሮት ገዝታችሁ የራሳችሁን ቅርጽ አውጡና ተመገቡ። ሲልጡትና ሲሰሩት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን ወደሆዳችን የምናስገባውን ነገር ሁሉ ሰውነታችን እንድንቆጣጠርለት ሃላፊነቱን ስለሰጠን መሰላቸት አይገባም።

ላሳጥረው። በክሎሪን ያልታከመ፣ በማሽን ያልተሰቃዬ ትኩስ ካሮት እመኝላችኋለሁ።

ምንጭ፡ http://www.snopes.com/food/tainted/carrots.asp

ወርቁ ለገሠ (12/11/10)