የኢትዮጵያ “ኦስካር” ምሽት


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ግሩም ኤርምያስ በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደው በ5ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ ተዋናይ አሸናፊ

በረዥሙ የሚዘረጋ ቀይ ምንጣፍ ከዚህ የለም። በቀይ ምንጣፍ ዳር እና ዳር የተኮለኮሉ አድናቂዎች እና ወፈ ሰማይ ፎቶግራፍ አንሺዎችም በቦታው ላይ አይታዩም።  በእውቅ ሰዎች አለባበስ እና በሚከተሉት ፋሽን ላይ አቃቂር የሚያወጡ የፋሽን ተንታኞችም አይታሰቡም።  በየዓመቱ ሳይለዋወጥ የሚበረከት፣ ግርማ ሞገሱ የሚማርክ እና ዐይነ ግቡ የኾነ ሽልማት ገና አልመጣም። ይኼ ኮዳክ ቴአትር አይደለም፤ ብሔራዊ ቴአትር እንጂ። የክንውኑ ስያሜም “ኦስካር” ሳይኾን  “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” የሚል ነው፤ ሕዳር 27 ቀን 2003 ዓ.ም ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ይኸው ድግስ ተሟሙቆ ነበር።

የቀይ ምንጣፍ ዘመን እስኪመጣ በምትኩ ነጭ የሻማ ጨርቅ አገልግሎት ላይ ውሏል፤ የአዳራሽ መግቢያ መከለያ እና የመድረክ ማስዋቢያ ኾኖ። የሚያደንቋቸውን የፊልም ተዋንያን ወደ አዳራሽ ሲገቡ ለመመልከት ከቀናት በፊት ድንኳን ተክለው በአካባቢው የሚከትሙ አድናቂዎች ቅንጦት የኾነበት የብሔራዊ ቴአትር ወደ አዳራሹ ካልገባን ሞተን እንገኛለን በሚሉ ግርግር ፈጣሪ ተመልካቾች ተጨንናንቋል። ቀንቷቸው ወደ ውስጥ ከዘለቁ ከዚህ አስቀድሞ ሲሰጥ ከነበረው በተለየ ዲዛይን የተሠራ ሽልማት መድረክ ላይ ተደርድሮ ይመለከታሉ።

ሽልማቱን መቁጠር የጀመረ አንድ ብሎ ሰባት ላይ ያቆማል። እያንዳንዱ ሽልማት የተለያዩ ዘርፎችን ይወክላል። ዘርፎቹ ምርጥ ተዋናይ እና ተዋናይት፣ ምርት ረዳት ተዋናይ እና ተዋናይት፣ ምርጥ የፊልም ጽሑፍ፣ ምርጥ ዳይሬክተር እና ምርጥ ፊልም በሚል ተከፋፍለዋል። ዕጩዎች መኾናቸው ከሁለት ቀን በፊት ይፋ የተደረጉ ተዋንያን እና የፊልም ባለሞያዎች በአዳራሹ እዚህ እና እዚያ ተዘበራርቀው ይታያሉ። ከዕጩዎች ይልቅ ሸላሚ ተብለው የተመረጡ አርቲስቶች በአንድ ረድፍ ተሰባስበዋል።

ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር በመኾን የሽልማት ሥነ ሥርዐቱ ሳይቋረጥ እንዲካሄድ ያደረገው ይርጋሸዋ ተሾመ ፕሮግራሙን በንግግር ጀመረ። የዕጩዎች ዝርዝር ተከተለ። ነጻ የመግቢያ ትኬት አግኝቶም ኾነ የመግቢያ ሀምሳ ብር ከፍሎ አዳራሹን የሞላው ተመልካች የዕጩዎችን ስም እየተከተለ በድጋፍ ድምፅ ይጮኻል። ደስታ እና ድጋፍ የተቀላቀለበት ጩኸት ውስጥ ጉጉት ይደመጣል። “ማን ያሸንፍ ይኾን?” ለሚለው ልብ ሰቃይ ጥያቄ እና ጉጉት ለተሞላበት ስሜት የሚኾነው ምላሽ የተገኘው ግን ዘግየት ብሎ ነው። የአሸናፊዎች ዝርዝር ከመገለጹ አስቀድሞ ሦስት አጫጭር ፊልሞች እና ሦስት በተወዛዋዦች የታጀቡ ባህላዊ ዘፈኖችን መመልከት አስፈልጎ ነበር።

“ያልጠቀመ መሥመር”፣ “ጥበቡ” እና “ያረፈዱ እጆች” የተሰኙት አጫጭር ፊልሞች በፌስቲቫሉ ወቅት ሥልጠና በወሰዱ የፊልም ባለሞያዎች የተዘጋጁ ሲኾኑ ስለ ትራፊክ ደኅንነት፣ ረኀብ እና ጎዳና ተዳዳሪነት የሚተርኩ ነበሩ። ፊልሞቹ እንደተጠናቀቁ ወደ መድረክ የተጠራው ተሸላሚ ፊልሞችን በመምረጥ ያገለግሉ ዳኞች ሰብሰቢ የኾነው ብርሃኑ ሽብሩ ነበር። “በሕይወት ዙሪያ” በተሰኘው በባለ35 ሚሊሜትር ፊልሙ የሚታወቀው ብርሃኑ በዚህ ዓመት በተወዳደሩ 25 ፊልሞች ላይ ስድስት ሕጻናት መተወናቸውን በማንሳት የየፊልሞቹ ፕሮዲዩሰሮች ሊያበረታቷቸው እንደሚገባ ጠቁሟል::

ዳኞቹ ማን ናቸው?

ከዓመታት በፊት “አግአዚ ኦፕሬሽን” የተሰኘውን ፊልም በአዘጋጅነት ለዕይታ ያበቃው ብርሃኑ በዳኞች ስብስብ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው በግል ሲኾን ደራሲ እና አዘጋጅ ስዩም ተፈራም በተመሳሳይ ኹኔታ ተሳትፏል። የተቀሩት ዳኞች በወከሏቸው አካላት አማካኝነት ስብስቡን የተቀላቀሉ ናቸው። እቴነሽ ጸጋ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ አንዱአለም አባተ ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፣ ሄኖክ ለማ ከአላቲኖስ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ተመርጠው በዳኝነት የተሰየሙ ነበሩ። በዕይታ ላይ የሚገኙትን ፊልሞች በየሲኒማ ቤቱ በመገኘት፤ የዕይታ ጊዜያቸውን የጨረሱትን ደግሞ በልዩ ፕሮግራም አንድ ላይ በመኾን እንደገና መመልከቱን አቶ ብርሃኑ ለአዲስ ነገር ተናግሯል።

ፊልሞችን ለመምረጥ ከተጠቀሙበት መመዘኛ ውስጥ “የአገር እና የሕዝብን ታሪክ፣ ፍልስፍናቸውን፣ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሁኔታ ማወቅ” የሚል እንደሚገኝበት አቶ ብርሃኑ ይገልጻል። ሥነ ውበት፤ የቋንቋ ይዘት፣ የሙዚቃ አመሠራረት እና ሥነ ምግባር ጠብቋል አልጠበቀም የሚለው በመስፈርቱ ውስጥ መካተቱንም ያስረዳሉ። “የሕዝብን ታሪክ ማወቅ ስንል በዚያ ውስጥ የማንነት ጥያቄያቸውን በምን መንገድ ነው የመለሱት የሚለውን እንመለከታለን። በፈለጉት መንገድ ሊመልሱት ይችላሉ። ከፈለጉ በሽሙጥ ወይንም በሌላ ሊገልጹት ይችላሉ። ነገር ግን  ማንነት የሚለውን አምጥተውታል ወይ? የሚለውን እናያለን” ሲሉ ያብራራሉ።

The Oscar goes too…

በእነዚህ መስፈርቶች ተመረጡ የተባሉ ፊልሞች በነጭ ፖስታ እየተደረጉ ለሸላሚዎች ይታደሉ ያዙ።  በምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት ዘርፍ አሸናፊ የኾነቸውን እንስት ለማሳወቅ በመጀመሪያ ወደ መድረክ የመጣው የመዝናኛ የሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጁ እና የማስታወቂያ ባለሞያው ሰይፉ ፋንታሁን ነበር። “ያስፈራል” ሲል ንግግሩን የጀመረው ሰይፉ የአሸናፊዋ ስም የተጻፈበትን ወረቀት ከፖስታ ካወጣ በኋላ “ሙሉ ዓለም ታደሰ” ሲል ከአዳራሹ የሳቅ ምላሽ አግኝቷል። ሙሉ ዓለም በዚህ ዓመት ፊልም ያልሠራች ሲኾን በዕጩነትም አልቀረበችም።

ከዕጩዎቹ መካከል አሸናፊ የኾነችው ማክዳ አፈወርቅ ስትኾን “ስስት” በተሰኘው ፊልም ያሳያችው ትወና ለምርጫ አብቅቷታል። የድምፃዊ አብነት አጎናፍር ድርሰት በኾነው “ስስት” ላይ ማክዳ ከፍቅረኛዋ ሳታስበው በማርገዟ ባለጸጋ ቤተሰቦቿን ትታ ከወደደችው ጋራ የኮበለለችን ገጸ ባሕርይ ወክላ ተጫውታለች። ማክዳ በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ለመከታተል በክፍለ አገር የምትገኝ በመኾኑ ሽልማቷን በአካል ተገኝታ ለመቀበል አልቻለችም። በትምህርት ላይ መኾኗን የሚያውቁት አዘጋጆቹ በሰይፉ አማካኝነት ከመድረክ ስልክ ደውለው መደነቅን ሊፈጥሩባት ሞክረዋል። ሽልማቷን ግን ወላጅ እናቷ በመድረክ በመገኘት እርሷን ወክለው ከሰይፉ እጅ ተቀብለዋል።

በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደው የ5ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ ረዳት ተዋናይ አሸናፊ

ቀጣይ ዘርፍ የነበረው ምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ ነበር።  በአሁኑ ወቅት እዚያው ብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ ባለው “ሕንደኬ” ቴአትር ታላቁ እስክንድርን ኾኖ በመተወን ላይ የሚገኘው ፈለቀ አበበ “የእግር ዕጣ” በተሰኘ ፊልም የዓመቱ ምርጥ ረዳት ተዋናይ ተሰኝቷል። መሠረት መብራቴ ለፈለቀ የኢትዮጵያ ካርታ መሳይ ከአናቱ ያለበትን የፌስቲቫሉን የእዚህ ዓመት ሽልማት አበርክታለታለች።  ከዚህ ቀደም ቡርኪናፋሶ እና ናይጄሪያ ውስጥ በሚካሄዱ ፌስቲቫሎች መሳተፉን ያስታወሰው ፈለቀ እንደዚያ ዐይነት ባህል በአገሩም እንዲለመድ ይመኝ እንደነበር ተናግሯል። ሽልማቱንም ለታዳጊ ወጣት ፊልም ሠሪዎች ማበረከቱንም ጨምሮ አስታውቋል።

የለቀቀውን መድረክ መልሶ የተረከበው ሰይፉ የዓመቱን ምርጥ ወንድ ተዋናይን ማንነት ለማሳወቅ እየተንደረደረ እያለ ከተመልካች መካከል “ግሩም” የሚል ጩኸት በአዳራሹ አስተጋባ። ገማቹ ተመልካች ትክክል ነበር። “ትዝታህ” እና “ይሉኝታ” በተሰኙ ሁለት ፊልሞች በመሪ ተዋናይነት የተጫወተው ግሩም በሁለቱም ምርጥ ተብሎ መመረጡን በመድረኩ አስተዋዋቂዎች በኩል ተገልጿል። ግሩም “ሄርሜላ” በተሰኘው የዮናስ ብርሃነ መዋ ፊልም በተመልካች ዘንድ እውቅናን ከማግኘቱ በፊት “መስዋዕት” በሚለው የቪዲዮ ፊልም ላይ በመተወን ሥራውን ጀምሯል። በአሁኑ ሰዓት ካሉት ወጣት ተዋንያን በብዙዎቹ ፊልሞች ላይ በመሳተፍ እና በትወናውም የዋና እና የረዳት ገጸ ባሕርያት በመወከል የተዋጣለት ተዋናይ እየኾነ ነው።

ግሩም በ“ትዝታህ” ፊልም በ1960ዎቹ የነበረን  ወጣት ወክሎ ይጫወታል። ፊልሙ ይህ ወጣት የደስታ በሽታን ለማጥፋት በዘመተ ጊዜ ያጋጠመውን የፍቅር ሕይወት የሚተርክ ነው። በአስቂኝ የፍቅር ፊልም ዘርፍ በተመዘገበው “ይሉኝታ” ደግሞ ሰው የሚለውን በመፍራት እና በእናቱ ጉትጎታ ካልፈለጋት ሴት ጋራ ለመጋባት ቀጠሮ የያዘ ጎልማሳ ኾኖ ይጫወታል። እንደ እርሱ ቤተሰቧ የሚላትን በመፍራት የውሸት ባል እንዲኾናት ከምትለምነው የቡና ቤት አስተናጋጅ ጋራ በይሉኝታ ኑሮ ጀምሮ የሚያጋጥመውን ምስቅልቅል ፊልሙ ይተርካል። ቲሸርት፣ ጂንስ እና ስኒከር ያደረገው ግሩም አዘጋጆቹ ላዩ ላይ ጣል ያደረጉለትን ካባ ደርቦ በመድረክ ታይቷል። ይህ የአዘቦት ቀን አለባበስ በዕጩነት ቀርበው በነበሩት በአብዛኞቹ ተዋንያን ላይም ተስተውሏል።

ሽልማቱ የእርሱ ብቻ እንዳልሆነ የተናገረው ግሩም አብረው የሠሩትን በሙሉ አመሰግኖ በተለይ በሜክ አፕ አርቲስቲነት በሁለቱም ፊልሞቹ የሰራውን ተስፋዬ ወንድማገኘሁን አወድሷል። “አብረውኝ የተወዳደሩት ጎበዝ ባይኾኑ ኖሮ ይኼን አላገኝም ነበር” ሲል ተፎካካሪዎቹን አሞካሽቷል። የሴት ምርጥ ተዋናይ ዘርፍ ለመሸለም ወደመድረክ የመጣችው መሠረት መብራቴ በግሩም ብቃት ከተደነቁት መካከል ትመስላለች። አቅፋ ደስታዋን ገልጻለታለች። መሠረት እንደግሩም ሁሉ ምርጥ ተዋናይ የተባለችውን ሳያት ደምሴንም አስተዋውቃለች።

የ1996 ዓ.ም “ሚስ ኢትዮጵያ” የነበረችው እና ነጠላ ዜማ በማውጣት ወደ ሙዚቃው ዓለም የተቀላቀለችው ሳያት የዓመቱ ምርጥ ሴት ተዋናይ የሚለውን ካባ የደረበችው “ላውንደሪ ቦይ” በተሰኘው የፍቅር ፊልም ነው። ሳያት ባለፈው ዓመትም በዚሁ ዘርፍ ዕጩ ኾና ቀርባ የነበረ ቢኾንም ሳይሳካላት ቀርቷል። በዚህ ዓመት ማሸነፏ ቢገልጽም በአዳራሹ ውስጥ ባለመገኘቷ ሽልማቷ በተወካይ ተወስዷል። እንደ ሳያት ሁሉ በቦታው በመገኘት ሽልማታቸውን ያልወሰዱ ሌሎች ተሸላሚ ተዋንያኖችም ነበሩ። በተወዳደሩበት ፌስቲቫል ላይ ለተሳትፎ የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት እንኳ ያልተቀበሉ በርካታ ፊልም ሠሪዎች ነበሩ።

ተዋናይት መሠረት መብራቴ ለግሩም ደስታዋን ስትገልጽ

ከተዋናዮች የሽልማት ሥነ ሥርዐት የተከተለው የፊልም ባለሞያዎች ዘርፍ ምርጥ የፊልም ጹሑፍ፣ ምርጥ ዳይሬክተር እና ምርጥ ፊልም በሚል ተከፋፍሎ ቀርቧል። ቢኒያም ወርቁ “ሰባተኛው ሰው” በተሰኘው ፊልሙ የምርጥ የፊልም ጹሑፍ ሽልማት ሲወስድ ዮናስ ብርሃነ መዋ በዚህ ዓመት ከሠራቸው ፊልሞች መካከል በ“ማክቤል” የዓመቱን ምርጥ ዳይሬክተርነት ማዕረግ አግኝቷል። “የእግር ዕጣ” የዓመቱ ምርጥ ፊልም ተብሏል። ዓለማየሁ ታደሰ፣ ሠራዊት ፍቅሬ እና ፈቃዱ ተክለ ማርያም ለአሸናፊዎቹ ፊልሞች ሽልማቶቻቸውን አበርክተዋል።

የዓመቱ ምርጥ ፊልም የተሰኘው “የእግር ዕጣ” በደርግ ጊዜ ወጣቶች ይደርስባቸው በነበረው እንግልት ምክንያት አገር ጥለው በሱዳን በኩል ይሰደዱ እንደነበር ይተርካል። በፊልሙ ፕሮዲዩሰር ዳንኤል አርጋው እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ የተሠራው “የእግር ዕጣ” በስደት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥመን አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ገጠመኞች የሚያሳይ ነው። ዳንኤል የፊልሙን ሽልማት ከተቀበለ በኋላ ስሜታዊ በኾነ እና ሳግ በሚተናነቀው ድምፅ ንግግር አሰምቷል። ፊልሙን ከአገር ውስጥ ይልቅ በውጭ የፊልም ፊስቲቫሎች የማወዳደር ዕቅድ እንደነበረው የገለጸው ዳንኤል የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል አዘጋጆች “ምንም አያመጡም” በሚል ላለመሳተፍ አንገራግሮ እንደነበር ገልጿል። በጓደኛው ጎትጓችነት በፌስቲቫሉ መካፈሉን የተናገረው ዳንኤል አዘጋጆቹን “ተሳስቻለሁ እና ይቅርታ” ብሏል።

ፌስቲቫሉን ሽሽት

የዳንኤል ዐይነት አመለካከት ያላቸው በርካታ ፊልም ሠሪዎች እንዳሉ በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉ ፊልሞችን ቁጥር ጠቋሚ ነው። በፌስቲቫሉ 25 ፊልሞች ቢሳተፉም 40 ያህል ፊልሞች ከባለፈው ፊልም ፌስቲቫል በኋላ ተሠርተው ለዕይታ ቀርበዋል። ይህ የተሳትፎ ሽሽት ከሁለት ነገር ሊመነጭ እንደሚችል በ2010 የዲሞክራሲ ቪዲዮ ቻሌንጅ ውድደር ላይ በአንድ ደቂቃ ከ48 ሰከንድ አጭር ፊልም አሸናፊ የኾነው ያሬድ ሹመቴ ያስረዳል። የመጀመሪያው ከእምነት ማጣት የመጣ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ለምዝገባ የሚጠየቀው ገንዘብ መጋነን ነው ባይ ነው። “ገንዘቡን መክፈል ያልፈለገ ሰው ሌሎቹ ሰዎች አንደኛ ሲባሉ ወደ ኋላ ሊቀር ነው” ይላል ያሬድ። “መደረግ ያለበት ከመነሻውኑ ዕጩ የኾኑ ፊልሞችን እንዲታወቁ አድርጎ ወደ ምዝገባ እንዲመጡ ማድረግ ወይንም ደግሞ ምዝገባውን ነጻ ማድረግ ነው።”

ያሬድ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚያስነሱ ነገሮች በፌስቲቫሉ ይከሰቱ እንደነበር ይናገራል። “የዛሬ ዓመት ዳኞቹ እነማን እንደኾኑ ሁሉ የማይታወቁበት ኹኔታ ነበር” ሲል ምሳሌ ይጠቅሳል። እንደዚህ ዐይነት ስኅተቶች ግን ከዓመት ወደ ዓመት እየተቀረፉ እንደመጡ ያምናል። “አዘጋጆቹ ስኅተቶቻቸውን እያረሙ እየሄዱ እንደኾነ ተሰምቶኛል” ሲል ለአዲስ ነገር ገልጿል። “ስኅተቶቹን እየነቀስን ጥሩውን ነገር ደግሞ ማበረታት ያስፈልጋል” የሚለው ያሬድ የአካዳሚ አዋርድ እንኳ አሁን የደረሰበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት “አወዛጋቢነቱ ከፍተኛ” እንደነበር ያስረዳል። ሲድኒ ፖይቴ እ.ኤ.አ በ1963 በሠራው Lilies of the Field” በተሰኘው ፊልሙ የመጀመርያው ጥቁር አሜሪካዊ የኦስካር ተሸላሚ እስኪኾን ድረስ አካዳሚ አዋርድ “የዘረኛ ቤት” ሲባል እንደነበርም ያስታውሳል።

አምስቱንም የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የተከታተለው ያሬድ የዘንድሮው የተሻለ እንደነበር ይመሰክራል። “ይኼኛው እስከዛሬ ከነበሩ ፌስቲቫሎች በእኔ እምነት እና ግምት ‘ፌየር’ የነበረ እና በደንብ ዝግጅት የተደረገበት ነው። የዳኞቹ ማንነትም፣ የዳኝነት መሥፈርቱም በአጠቃላይ ግልጽነት የነበረው ነው” ይላል። ደራሲ እንዳለጌታ ከበደም በዚህ ይስማማል። የዘንድሮው “ሞቅ ደመቅ” ያለ እንደነበርም ያክላል።

ምርጫው እንዴት ነበር?

እንዳለጌታ በፊልሙ ላይ ለውድድር ከቀረቡት ውስጥ አብዛኞቹን ተመልክቷቸዋል። በብዙዎቹ አመራርጥ ላይ ተቃዎሞ የለውም። ሽልማቶቹ “በእውነትም በትክክል ለሚገባው ሰው ተሰጥተዋል” ሲል ለአዲስ ነገር ተናግሯል። ያሬድም ተመሳሳይ ሐሳብ ያንጸባርቃል። “በግሌ የተሸለሙት ፊልሞች እና ተሸላሚዎቹ የሚገባቸው ናቸው ብዬ አስባለሁ። 98 በመቶ በውጤቱ እስማማለሁ” ይላል። በሁለቱም በኩል ግን ይሸለማሉ ብለው ጠብቀው ነገር ግን ሳይሸለሙ የቀሩ ፊልሞች አሏቸው።

ያሬድ “መላክ” የተሰኘውን ፊልም ወይ በዳይሬክቲንግ አሊያም በጽሑፍ ያሸንፋል ብሎ ጠብቆ የነበረ ቢኾንም ፊልሙ በሁለቱም ዘርፍ ሳይሳካለት ቀርቷል። እንዳለጌታ በበኩሉ “በራሪ ልቦች” የተሰኘ እና በአንድ አርቲስት ሕይወት ላይ ያጠነጠነ ሙስና ተኮር ፊልም በምርጥ የፊልም ጽሑፍ  ያሸንፋል ብሎ ገምቶ ነበር። ኾኖም “በራሪ ልቦች” በ“ሰባተኛው ሰው” በመበለጡ ያሰበውን በመድረክ ለማየት አልቻለም። “የዓመቱ ምርጥ ፊልም ተብሎ የተሸለመው “የእግር ዕጣ” ምርጥ ድርሰት የተባለው ከስደት ጋር የተገናኘ ነው” ይላል እንዳለጌታ ምክንያት የሚለውን ሲያስቀምጥ። “ገምጋሚዎቹ አገራዊ ስሜት የተንጸባረቅበት እንዲኾን ሐሳብ ነበራቸው።”

ፈለቀ አበበ ከመሠረት መብራቴ ሽልማት ሲቀበል

ገምጋሚዎቹ በበኩላቸው ባስቀመጡት መሥፈርት ያለውዝግብ መሥራታቸውን ይናገራሉ። ኾኖም በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ  ተስፋዬ ገብረማርያም በ “የእግር ዕጣ” እንዲሁም ዮናስ ብርሃነ በ“ማክቤል” እኩል ነጥብ በማምጣታቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር። “ከዚያ በኋላ ያለው አማራጭ በድምፅ መለየት ነው። ለምሳሌ ስንት ፊልም ነው የቀረበው የሚለውን ተመልከተናል። ሦስት ፊልሞች ነው ዮናስ ያመጣው” ይላል አቶ ብርሃኑ አሸናፊው ለውድድሩ ያቀረባቸው ፊልሞች ብዛት እንደ አንድ መሥፈርት እንደተወሰደ ሲያስረዳ። በስተመጨረሻ ውጤቱ በድምፅ ብልጫ መለየቱንም ለአዲስ ነገር አስረድተዋል።

ማንም ያሸንፍ ማን መረሳት የሌለበት አሸናፊው ሽልማቱን ያገኘው የተወዳደሩትን ብቻ መብለጥ በመቻሉ መኾኑ መዘንጋት የለበትም ባይ ነው እንዳለጌታ። “መሸለም ማለት ከተወዳደሩት መሀል የተሻለ እና የተለየ ነጥብ ማግኘት ማለት ነው እንጂ ስኅተት የሌለበት ሥራ መሥራት ማለት አይደለም” ይላል። “አሁን አንዳንድ ጊዜ “እከሌ ምን ስለኾነ ነው የተሸለመው ዐየኹት እኮ አልወደድኩትም” ይላሉ። ግን እኮ ከተወዳደሩት ነው የተሸለመው እንጂ ስኅተት የሌለበት ማለት አይደለም። ከሌሎች ጋራ ሲተያይ የስኅተት ቁጥሩ ያነሰ ማለት ነው” ሲል አስተያየቱን ያጠቃልላል።

በዚህ የፊልም ፌስቲቫል ላይ መሳተፍን አንዳንድ ፊልም ሠሪዎች አናንቀው ይመለከቱታል። ሸላሚው ድርጅትም ኾነ የሽልማቱ ዐይነት ያን ያህል ምገስ የሚያሰጥ እና ከበሬታን የሚያጎናጽፍ ነው ብለው ስላልወሰዱ። በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ ኾኖ መገኘትን ደግሞ በተቃራኒው የሚያዩ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከተሠሩት ፊልሞች ሁሉ የተሻሉ እና መለኪያዎቹም እነርሱ እንደኾኑ አድርገው የሚወስዱም አይታጡም። ይኹንና የውድድሩ አሸናፊ ኾኖ መገኘት በራሱ የሚያመጣው ጥቅም ያለ የመሰላቸው አሸናፊነታቸውን የሚያውጁት ከጥቂቶች እና ለመወዳደር ከተመዘገቡት ጋራ ብቻ ነው በሚል ዐይነት አይደለም።

ይልቁንም በየፊልም ማስታወቂያዎቻቸው ላይ ውድድሩን እንደ “ኦስካር” ያለ አድርገው የምርጥነታቸው መለያ ማስመሰል ይዘዋል። ይኼ የማስታወቂያ ዘዴ የተመልካችን ቁጥር እንደሚጨምር ባለፈው ዓመት አሸናፊ በኾነው “ስላንቺ” ፊልም መታየቱ በፊልም ፕሮዲዩሰሮች እና በፊልም ሠራተኞች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ችሏል። “ስላንቺ” በአራተኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ ድርሰት፣ በምርጥ ተዋናይ እና በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፎች ሽልማቶችን መሰብሰብ በመቻሉ በአገር ውስጥ ካገኘው የተመልካች ቁጥር መብዛት ባሻገር ኒውዮርክ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይም እንዲሳተፍ በር ከፍቶለታል።

በፊልሞች ዘንድ ከታየው የገቢ ለውጥ ባሻገር ሽልማቱ በተወናዮችም ዘንድ መነቃቃትን እየፈጠረ ያለ ይመስላል። በአንድ የፊልም ምርቃት የተሰጠውን ሽልማት አልቀበልም በማለት መድረክ ረግጦ መውጣቱ የሚታወሰው ፈለቀ አበበ በዚህ የሽልማት ሥርዐት በመሸለሙ ያሳየው የነበረው ደስታ ማሳያ ይኾናል። እንባ እስኪተናነቃቸው ድረስ ስሜታዊ የኾኑ ተሸላሚዎችም ተስተውለዋል። ፌስቲቫሉ በአሁኑ አካሄዱ የሽልማት ሥነ ሥርዐቱን ለአምስት ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ ሳያቋርጥ ወደፊትም የሚስቀጥል ከኾነ ለሽልማት መታጨት በራሱ ብርቅ የሚኾንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይኾን የፊልም ባለሞያዎች ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት የዓመቱ ምርጥ ፊልም በመባል አሸናፊ የነበረው የ“ወንዶች ጉዳይ” አስቂኝ ፊልም ደራሲ አድማሱ ከበደ ይህንኑ ሐሳብ የሚያንጸባርቅ አባባል በፌስቲቫሉ አዘጋጆች አማካኝነት በታተመ መጽሔት ላይ ተናግሮ ነበር። “ወደፊት እያደገ ተዐማኒነቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ርግጠኛ ነኝ። እንዲያውም በሚቀጥለውም ኾነ በመጪው ጊዜ ከሽልማቱ መራቅ አልፈልግም። በዕጩነትም ደረጃ መጠራት እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ይኼ ታሪክ ሲነሳ እኔ ለልጄ የማሳየው ነገር ነው” ይላል አድማሱ። ለልጅ የሚያወርሱት ሽልማት ምን ያህል ዕድሜ ይኖረው ይኾን…?