በጀኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የወሰደውን አቋም በመደገፍ ግንቦት7ና ጥምረት መግለጫ አወጡ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጥላ ሥር ከሌሎች የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመታገል መወሰኑን ገሃድ ማድረጉን ተከትሎ ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከትናንትና በስቲያ መግለጫ አውጥቶአል።

“የጋራ ትግል የጋራ አገር” በሚል ርዕስ ግንቦት7 ባወጣው በዚህ መግለጫ “በኢትዮጵያ የሰፈነውን ዘረኛ አምባገነን ሥርዓት አስወግደን በምትኩ የግልና የወል መብቶች የተከበሩባት፤ ፍትህና እኩልነት የሰፈኑባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በምናደርገው ትግል ውስጥ በጀኔራል ከማል ገልቹየሚመራው ኦነግ አዎንታዊ የሆነ ወሳኝ እርምጃ መውሰዱ “በጋራ ትግል የጋራ ጠላታችንን አስወግደን፤ የጋራ አገራችንን ተባብረን ለመገንባት ወደ ሚያስችለን ምዕራፍ ሊያሸጋግረን ይችላል የሚል እምነት እንዳለው ገልጾአል።

“የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በአንድ ጠንካራ አመራር ሥር ሆኖ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅምና መብት ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱን ዜጎችና ሕዝቦች በሙሉ መብቶችና ጥቅሞች በጋራ ለማስከበር በሚደረገው ትግል ተሳታፊ ቢሆን ኖሮ ሊገኝ የሚችለውን ሕዝባዊና ሃገራዊ ጥቅም ግዙፍ እንደሚሆን ማንም አይስተውም ነበር” ያለው የግንቦት7 መግለጫ፤ የኦሮሞ ምሁራን በተለይ የፖለቲካ ልሂቃኑና ኦነግ በአንድነትና በአንድ ድምጽ እየተናገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ በሚያደርገው የጋራ ትግል የኦሮሞን ሕዝብ ታላቅነት የሚመጥን ሃገራዊ የኃላፊነት ሚና እንዲጫወቱ ግንቦት 7 እና በርካታ ወገኖች ሲያደርጉት የቆዩት ጥረት የተፈለገውን ውጤት በተፈለገው ጊዜ ሊያመጣ አለመቻሉ እንዳላስደሰተው አልሸሸገም።

ሁሉም የአገራችን ሃይሎች አንድ ላይ ሆነው የህዝባችንን ስቃይና መከራ እድሜ ለማሳጠር በጋራ እንዲታገሉ ዘወትር የሚወተውተው ግንቦት 7 በዚህ መግለጫው፤ ምንም እንኳ የኦሮሞ ሃይሎችን አንድ ላይ ለማምጣት እስከዛሬ የተደረጉ ጥረቶች ለጊዜው ባይሳኩም በአጭር ጊዜ ይሳካ ዘንድ ሁሉም ወገን አቅም የፈቀደለትን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል የሚል እምነት እንዳለው ገልጾአል።

ጥምረት ለነጻነት፤ ለፍትህና ለ እኩልነትም በበኩሉ፤ በጀኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦነግ ቡድን ከሌሎች የዲሞክራሲ ሃይሎች ጋር ተባብሮ በአገራችን ውስጥ የተንሰራፋውን ኢፍትሃዊነት ታግሎ ለማስወገድ የሚያስችለውን ይህንን ደፋር እርማጃ በመውሰዱ የተሰማውን ደስታና አድናቆት ገልጾ፤ በአገራችንንና በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰቆቃ እድሜ ለማሳጠር የሚሹ ሌሎች የኦነግ ሃይሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው የዲሞክራሲ ትግሉን ያጠናክራሉ ብሎ እንደሚያምን አስታውቆአል።