ሃሰትን እንድናገር ያስገደደኝ መንግስት ነው ማለት አያዋጣም!!!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በዘረኛው ቡድን አማካኝነት የአገራችን የሞራል እሴቶች ሆን ተብለው እየተዋረዱ ነው።ድሮ ድሮ “እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር” የሚባል መልካም አባባል ነበረን። ዛሬ ይህን የመሰሉ አባባሎች ከል እንዲለብሱ በመደረጉ እውነትን የሚናገር በግዞት ተይዞ የመከራ እንጀራ ይበላል የመከራ ውሃም ይጠጣል።
እንደ ንጉስ አክዓብ በዙሪያው ብዙ ሃሰተኛ መማክርትን የሰበሰበው መለስ ዜናዊ የእውነትን ድምጽ የመስማት ልምድ የለውም።ሃሰት የኑሮው መሠረት ነች። ሃሰት አገርን እንደሚሰብር መለስ ጠፍቶት አይደለም በሃስት መሰረት ላይ መቆምን የመረጠው ይልቁንስ አገሪቷን ፈጽሞ ለመሰባበር ካለው እምነት የተነሳ እንጂ። መለስ ዜናዊ የተጠራበት በእውነትና በጽድቅ ላይ የቆመችን አገር ለመፍጠር ሳይሆን በሃሰት ላይ የታነጸች መሠረቷ የሚናወጥ አገርን መፍጠር ነው። መለስ የተጠራበትን ምግባር የቆመለትን ዓላማ እያስፈጸመ በመሆኑ የእርሱ ውሸታምነት አይደንቀንም። እኛን የሚደንቀን የመለስ ዜናዊን ውሸት ለማስፈጸም የሚሸቀዳደሙ ምናምንቴ ግለሰቦች እንደ አሸን መፍላታቸው ነው።
አንዳንዶች ምን እናድርግ ተገደን ወይም ፈርተን ነው እውነት ያልሆነውን የምንናገረው ሲሉ ይደመጣሉ። እውነቱ ግን እውነት ያልሆነውን አለመናገር እምቢ ማለት ሲችሉ ሃሰትን ለመምረጥ ፈቃደኛ መሆናቸው ነው። ሃሰትን አልናገርም፤ ያላየሁትንም አልመሰክርም ለማለት ሰው መሆናቸው ብቻ ያስገድዳቸው ነበር። ሃይማኖታቸው እና ሂሊናቸውም ከእውነት ጋር ብቻ እንዲተባበሩ ይመራቸው ነበር። እነዚህ ግን የውሸትን መንገድ መርጠዋል።ውሸትን በመናገራቸው ዛሬ ሆዳቸውን ሞልተው ለማደር ችለዋል። እንዲህ ያሉቱ ያልሆነውን ሆኗል፤ ያልሰሙትን ሰምተናል፤ ያላዩትን አይተናል ባሉ ቁጥር ብዙ ንጹሃን ዜጎች ለመከራ እንደሚዳረጉ ለማወቅ የሚያንሱ አልነበሩም። ግና ምን ያደርጋል ልባቸው በእግዚአብሄር እምነት ያልጸና፤ሂሊናቸውም በሆዳቸው የተሸነፈ በመሆኑ ከሃሰተኞች ጋር መተባበርን ሙያ አድርገውታል። ይህን ነውራቸውንም “ስማርት” አካሄድ እያሉ ይሞከሻሹበታል። እነርሱ “ስማርት” አካሄድ የሚሉት ነውር ምግባራቸው በወገኖቻቸው ላይ የተፈጸመ ክህደት መሆኑን አበክረን ለማሳወቅ እንወዳለን።
በማንኛውም መንገድ በሃሰት ወገንን ለሚከሱ ቡድኖች የሃሰት መስካሪ ሁኖ መገኘትና ዜጎችን ለመከራ መዳረግ ተቀባይነት ያለው ተግባር አይደለም።ሆድን ለመሙላት ብሎ ያላዩትን እንዳዩ፤ ያልሰሙትን እንደሰሙ አድርጎ መናገር የሃሰት አባት ለሆነው መለስ ዜናዊ ጀሌና ደጀን መሆኑን እያንዳንዱ ሃሰተኛ ሊረዳው ይገባል። መለስ ሳይፈለግ ሃያ ዓመት በሙሉ በአገራችን ጫንቃ ላይ የተጫነ ጨካኝ ገዢ ነው። ይህን ዘረኛና ዘራፊ ግለሰብ እየዋሹ ለመርዳት መሞከር እውነትን መግደል ሃሰትን ማንገስ ነው።ይህ ደግሞ ከሥነምግባር አኳያ የሰውን ክብርና ማንነት የሚያሳንስ ተግባር ብቻ ሳይሆን እውነት እራሷን ገልጻ ለፈራጅነት እድል በምታገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ በወነጀለኝነት የሚያስጠይቅ ነው። በፈረሃ እግዘአብሄር ለሚኖር የእምነት ሰው ደግሞ ወንጀሉ እላይ እሰማይ ቤት ድረስ የሚዘልቅ እንደሆነ የእምነት መጽሃፍትና አባቶች ያስተምራሉ። በምድራችን ህግ ሳይቀር ነውር ከሆነው የሃሰት ምስክርነት ተግባር ውስጥ አለመዘፈቅ እየተቻለ በዚህ ወይም በዚያ ተገድጄ መለስ ዜናዊ በተቀነባበረ የሃሰት ክስ በዜጎች ላይ ለሚፈጽመው ሰቆቃ መሳሪያ ሆንኩ ማለት በምንም መልኩ ተቀባይነት ያለውና ይቅርታ ሊያሰጥ የሚችል ተግባር አይሆንም።
ክፉውን እንድሠራ ከሚያስገድዱኝ ሃይሎች የሚያድነኝ ማን ነው? አይባልም። የእምነት ሰዎች ከሆንን ከክፉ ጋር እንዳንተባበር የሚያግደን የእግዚአብሄር መንፈስ አለ። ከእምነት ውጪ ከሆን ደግሞ ሂሊና የሚባል የስብዕናችን ምሶሶ አለ። ከዚያም አለፍ ብሎ “ሰው ምን ይለኛል የሚባል” በማህበረሰባችን ውስጥ ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ “ይሉኝታ” አለ።እነዚህን ሁሉ አልፎ እውነትን ከል አልብሶ ሃስተን አስጊጦ መናገር ራሱን ሰው ነኝ ብሎ ከሚቆጥር አካል የሚጠበቅ ተግባር አይደለም።
በአገራችን የነጻነት ጎህ የሚቀድበት ዘመን ሩቅ አይደለም። አሁን የጨለመ የሚመስለው ሊነጋ ሲል እንደሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል።እነመለስ በዚያች አገር እንዳላጋጡ የሚቆዩ አይደሉም። እጅግ ሲፈራ የነበረው ጋዳፊ ዛሬ የለም። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ “እንደ ጋዳፊ አይቀርልህም” እያሉ ወጣቶች መጮሃቸውንም ልብ ማለት ያስፈልጋል። ሃስት እድሜው አጭር ነው። የሃሰት አባት የሆነው መለስ ዜናዊና ቡድኑም እድሜያቸው ረዥም አይደለም። እነዝህን በክፋታቸው ጸንተው ለመኖር የሚመኙትን ቡድኖች ታግሎ ከአገሪቷ ጫንቃ ላይ ማባረር የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ ነው።ለእነመለስ ውሸት እምቢ ማለት ትክክለኛና የሚያስመሰግን ተግባር ነው። እነርሱ የሚፈጽሙትን ዝሪፊያ መቃወም፤ በዘረኝነት ላይ በተመሰረተ መዋቅር “ከወርቅ ተገኘን” ያሉን የአገሪቷን የፖለቲካ ሥልጣንና የኢኮኖሚ ዘርፎችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው በገዛ ሃገራችን ባይተዋር ሲያደርጉን እምቢኝ ማለት ለራሱ ተፈጥሮአዊ ማንነት ክብር ከሚሰጥ እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ድርጅታችን ግንቦት ሰባት የፍትህ፤ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ፤ አገራችንን ከል አልብሶ ሊያዋርዳት ቆርጦ የተነሳውን ዘረኛውን የትግራይ ገዢ ጉጅሌ በመፋለም ለሁላችንም እኩል የሆነች አገር ለመመሥረት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። አገራችን መለስና ቡድኑ ከፈጠሩት ሕፀፅ እንድትፀዳ ቀንና ማታ እየሰራ ነው። ሁሉንም የሚያስኬዱ መንገዶች እየሄደበት ነው። እኛ እንደ ግንቦት 7 አንግበን የተነሳነውን አላማና ግብ ለማሳካት በዘረጋናቸው መንገዶች ሁሉ ተጉዘን መለስና ግብረአበሮቹ ያሰፈኑትን ፍርሃትና ሽብር በመናድ፤ ፍትህና እኩልነት የነገሰባት፤ የሰው ልጆች በነጻነትና በደስታ የሚኖሩባት፤ የበለጸገችና ሉአላዊነቷ የተጠበቀ አገር ለመመሥረት የሚያስፈልገውን መሰዋዕትነት በቁርጠኝነት ለመክፈል ስንዘጋጅ እያንዳንዱ ዜጋ ባለበት ሆኖ አቅምና ጉልበቱ የፈቀደውን ሁሉ ለዚህ የነጻነት ትግል እገዛ ያውላል የሚል እምነት ይዘን ነው።
የግንቦት 7 ድምጽ ዝግጅት ክፍል ዘረኛው መለስ ዜናዊና ጥቂት ግብረአበሮቹ በወገኖቻችን ላይ እየፈጸሙ ያለውን ሰቆቃ ለማስቆም በብሄር፤ በቋንቋ፤ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ ልዩነት ሳንከፋፈል ሁላችንም በጋራ መነሳት ያለብን ጊዜው አሁን መሆኑን አብክሮ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!!