ከወያኔ ዛፍ የወይን ፍሬ አይለቀምም (ወርቁ ለገሠ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከወያኔ ዛፍ የወይን ፍሬ እንደማይለቀም ሁሉ የውሸት ምንጭ ከሆነች ነፍስ ሃቅ አይፈልቅም። የምትዋሽ ነፍስ የህሊና ክስ ስለሚመሰረትባት ሁልጊዜ ታፍራለች። ከገሃዱ ዓለም ጋር ባለው ቁርኝት የተነሳ ዕውነትን ለማስታወስ ብዙ አንቸገርም። ውሸት ግን የራሳችን ፈጠራ በመሆኑ ማስታወስ እንችል ዘንድ ዕንቅልፍ አጥተን መሥራት አለብን። በተጨማሪ ሰዎች ዕምነት ስለማይጥሉብን በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ መጥላት እንጀምራለን። ሌባ እናት ልጇን አታምነውም እንድሉ ተጠራጣሪ ስለምንሆን በጥላችን መደንበር እንጀምራለን። ስንዋሽ የሁለት ዓለም ሰዎችን ለማሳመን መታገል አለብን። 1ኛው ከኛ ውጭ የሚኖረውን ሰው ሲሆን 2ኛው የራሳችን የህሊና ዳኝነት ነው። ሰው ሃያል ፍጡር ነው። ውሸትን ቢግቱት አንቅሮ ይተፋዋል እንጅ አይውጠውም። የመጀመሪያውን ነጥብ ለማጠናከር የሚቀጥለውን ምሳሌ እንመልከት።
ሰውዬው የቅርብ ጓደኛው እናት ይሞቱና ዛሬ ነገ ሲል ለቅሶ ሳይደርስ ድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ ሁለቱ ጓደኛሞች ይገናኛሉ። “ይገርምሃል እናትህ ለቅሶ ቦሌ መድሃኔዓለም መጥቼ ሳልሰናበትህ ሄድኩ” ይለዋል፡ በጓደኛው መዋሸት የተበሳጨው ግለሰብ” እኔ እናቴን ቦሌ መድሃኔዓለም መቼ ቀበርኳት?” ብሎ መለሰለት። መዋሸቱ እንደተነቃበት ቶሎ ገባውና “አዬ የኔ ነገር አሁን ቦሌ መድሃኔዓለም ምን የመቃብር ቦታ አለ? ይቅርታ ቀራኒዮ ማለቴ ነው” ሲለው “ኧረ በፈጠረህ ለቀቅ አድርገኝ! እኔ እናቴን ቀራኒዮ አልቀበርኳትም” ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ። መቸም ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ ነውና “ቀልብ ካጣሁ ቆይቻለሁ፣ ብሥራተ ገብሬል ለማለት እኮ ፈልጌ ነው” በማለት እድሉን እንደገና ሞከረ። በነገሩ የተሰላቸው ግለሰብ “እኔ ብስራተ ገብሬልም እናቴን አልቀበርኩም፣ አስቸኳይ ጉዳይ ስላለኝ እንድሄድ ብትፈቅድልኝ” ሲለው እሱም በተራው ብስጭት ብሎ “ ታዲያ ወዴት አደረሳችኋት?” አለው ይባላል።
የህሊና ዳኝነት ዕውነት እስከተናገርን ድረስ ችሎቱን ዘግቶ ለጥ ብሎ ይተኛል። ስንዋሽ ከሰማ ግን ከመቅጽበት ይነቃና እኛን ለማሸማቀቅ ይተጋል። የሥነ ልቡና ሊቃውንት የምንዋሽበት ዋነኛው ምክንያት ዕውነቱን ስንናገር ሊከተል የሚችለውን መዘዝ በመፍራት ነው ይላሉ። ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ያድሯል እንድሉ መዋሸት ለጊዜው ጠቃሚ መስሎ ይታየን እንጅ ውሎ አድሮ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይልቃል። ውሸት ሰውነታችንን መርዞ፣ መንፈሳችንን አንቅዞ እንደሻህላ ይበላናል። ዋሾ ሰው ህይዎቱን የሚገፋው ውሸት በፈበረከው ካቴና እጅ ከዎርች ታሥሮ ነው። የውሸት ፍርድ ከርቼሌ ሲያወርደን ይግባኝ በመጠየቅ ነጻ መውጣት የምንችለው በዕውነት የዳኝነት ችሎት ሲፈረድልን ብቻ ነው።
ተፈጥሯችን ለመዋሸት የተመቻቼ አይደለም። በ5ቱ ህዋሳቶቻችን በመታገዝ፣ ዓይኖቻችንን እንደካሜራ ተጠቅመን ገሃዱን ዓለም ፎቶ አንስተን በአዕምሮ ሰሌዳችን እንስለዋለን። ያለፈው ልምዳችንን ከአሁኑ ጋር እያመሳከርን የወደፊቱን ለመተንበይ በዋቢነት የምንጠቀመው ያንን የገሃዱን ዓልም ሥዕል ነው፣ አካባቢያችንን በመቃኘት እንማራለን፣ ግንዛቢያችንን እናዳብራለን። ከቀሰምነው ልምድ በመነሳት ለአሁኑም ሆነ ለመጭው ትውልድ የዕውቀት ጮራ በመፈንጠቅ የተሻለ ዓለም በመፍጠሩ ሂደት ጉልህ ሚና ተጫውተን እናልፋለን ። ይህ በትውልድ ጸንቶ የሚኖር መስተጋብር የሚሠምረው ተመክሯችን በሃቅ ላይ ሲመሠረት ብቻ ነው። የምንዋሽ ከሆነ ግን ውጤቱ ለየቅል ነው።
ስንዋሽ በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱ ኬሚካላዊና ፊዚካላዊ ለውጦች ሰውነታችን የተለምደ ሥራውን በትክክል እንዳያከናውን ያውኩታል። ቁጡ፣ ብስጩና ተሳዳቢ እንሆናለን። ቃላት ስሜታችንን፣ ስሜታችን ደግሞ አስተሳሰባችን ላይ ጎጅ ተጽዕኖ በማሳደር ጤንነታችንን ያቃውሳል፣ ሥነ ምግባር ያስጥሳል። ጤና ስናጣ ደሥታም ይርቀናል፤ ዕኩይ አስተሳሰብና የብቀላ ጠኔ ያለልጓም ይጋልበናል።
“ኢትፍርህዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢዓት” ተብሎ እንደተጻፈው ሃቀኛ ሰው በዚች ዓለም ሲኖር ሠላም አለው፣ በወገኑ ላይ ሤራ አይጠነስስም። በአንፃሩ ውሸታም ሰው ፈሪ ነው። ከሞት አጥብቆ በመሸሽ እየሞተ ይኖራል። ጤና፣ ሠላምና ፍቅር ከሱ ደጃፍ አይረግጡም። የወገንም ሆነ የአገር ፍቅር የለውም። ዕምነት አይጣልበትም፡፡ ከሰው ቀርቶ ከራሱ ጋር ስለማይስማማ የሠላም ዕንቅልፍ አይተኛም፤ ራሱ በፈጠረው የውሸት ውቅያኖስ ላለመስጠም ያለ ዕረፍት ሲቀዝፍ ያድራል። ከወያኔ ዛፍ የወይን ፍሬ እንደማይለቀም ሁሉ ውሸት ከተጣባት ነፍስ ሃቅ አይፈልቅም።
ወርቁ ለገሠ (11/21/10)