ሶስተኛው መድፍ (ከተስፋዬ ገብረአብ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


እነሆ! “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለው መድፍ ተሰርቶ ተገባዶአል…
በዚህ አያያዜ ቶሎ የምጨርሰው ይመስለኛል። “ስደት” ርእሰ ጉዳዩ ሰፊ ነው። ይፃፍ ከተባለ 20 ጥራዝም አይበቃው። ሆኖም አጀንዳዬ ከሃገራችን ፖለቲካ ሊያፈነግጥ እንደማይችል ግልፅ ነው። የአብዛኛው የስደት ምክንያቱ ፖለቲካውም አይደል? በመሆኑም ስደትና ፖለቲካውን ከወቅታዊ ጉዳዮቻችን ጋር እያዋሃድኩ እተርካለሁ።

* * *

“የስደተኛው ማስታወሻ”ን የተሟላ ለማድረግ አውሮፓን እየዞርኳት ነው።
ስዊድን፣ ጀርመን፣ ፊንላንድ፣ ሆላንድና ቤልጅየምን ያዳረስኩ ሲሆን፣ ራሺያ እና ፈረንሳይ በቅርቡ የምፈፅማቸው ጉዞዎች ይሆናሉ። “የስደተኛው ማስታወሻ” የትረካ ማእከል ኔዘርላንድስ ናት። ሆላንድ ላይ እንደ ልብ ያገኘሁት የአበሻ ሰው ታሪክ የኛን ዘመን አመፀኛ ስደተኛ መወከል ይቻለዋል። የአመስተርዳም “እሳቶች”ም ታሪክ መስራት ጀምረዋል። ከበረቱ ጅማሬው ለትውልድ የሚያልፍ ይሆናል።

ሆላንድ ላይ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ስደተኛ ሆኜ ገብቼ ነበር።
ዳሩ ምን ያደርጋል? በአንድ ወር ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድ ሰጥተው አሰናበቱኝ። በርግጥ ቁርጥራጭ ወረቀቶቼን ለመያዝ አንድ ወር በቂ ነበር። እና በቀጣዩ ማስታወሻ እውነተኛውን የአውሮፓ የስደት ህይወት ስለማወጋችሁ ከወዲሁ ለመራር ሳቆች ተዘጋጁ።
በተመሳሳይ ወደ ጀርመንም ሄጄ ነበር። ኑረንበርግ፣ ፍራንክፈርትና ሙኒክ ከተሞችን ጎብኝቻለሁ ወይም ሰነባብቻለሁ። ከደብረዘይት ልጆች ጋርም መልካም ጊዜዎች ነበሩኝ።
“ሳታስፈቅደን ታሪካችንን መሸጥ ጀመርክ?” ሲሉም ቀልደውብኛል።

* * *
አውሮፓ ላይ ከጥቂት አንቱ የተባሉ የኛ ሰዎች ጋርም ተገናኝቼያለሁ።
ከነዚህ አንዱ ሌንጮ ለታ ነው። ኡትሬክት የተባለች ከተማ ላይ ተገናኘንና ከግማሽ ቀን በላይ አብረን ቆየን። ሌንጮን እንደጠበቅሁት አገኘሁት። ከሌንጮ ጋር ማውራት ምቾት የሚሰጥ መሆኑ አያጠያይቅም። ባነሳናቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ነክ አጀንዳዎች ላይ በአብዛኛው መስማማት ችለን ነበር። መቸም ነጋሶ ጊዳዳና ሌንጮን ማወዳደር አይቻልም። ዶክተር ነጋሶ በህይወቱ ውስጥ የወሰነው ትልቁ ውሳኔ፣ ከመለስ ወደ ስዬ ያደረገው ሽግግር ነው ማለት ይቻላል። እራሳቸውን መሆን የማይችሉ ሰዎች የሚያስከትሉት ጉዳት ለህብረተሰብ ይተርፋል። እና ሌንጮ የጠበቅሁት አይነት ሰው ሆኖ አገኘሁት። በመሆኑም በቀጣይ መፅሃፌ ላይ፣ “ከሌንጮ ጋር ቡና ጠጣሁ” የሚል አንድ ምእራፍ ይኖረኝ ይሆናል። በርግጥ ከሌንጮ ጋር ቆይታዬን ገና አላበቃሁም። እሱ ወደ ሚኖርባት ወደ ኦስሎ ከተማ ሄጄ በድጋሚ ላገኘው ቀጠሮ ይዘናል።

ከዶክተር ነገደ ጎበዜ ጋር በስልክ መገናኘት ከጀመርኩም ቆየሁ።
እኒህ አንጋፋ የፖለቲካ ሰው ያልታተመና ተፅፎ ያላለቀ ማስታወሻ እንዳላቸው ሰምቼ ስለነበር፣ ይህንኑ አንስቼላቸው ነበር። ማስታወሻው መኖሩንና በፈረንሳይኛ የተፃፈ መሆኑን ነግረውኛል። እንግዲህ በቅርቡ በድጋሚ ወደ ብራስልስ ሄጄ ያንን ማስታወሻ በእጄ ለማስገባት እጥራለሁ። በ66 አብዮት ዘመን ከነበሩ ወጣቶች፣ በህይወት የቀሩና ብዙ ምስጢር የሚያውቁት እኒህ ሰው ናቸውና ከጊዜ ጋር መሽቀዳደም ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው በርካታ ሰዎችን ለማግኘት የስም ዝርዝር አውጥቼያለሁ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ሌላው ናቸው። እሳቸውም በአንድ መጣጥፋቸው እንደገለፁት ከእኒህ አንጋፋ መምህር ጋር የቃጅማው ጊዮርጊስን ጠበል በመቋደሱ እንዛመዳለን። ከዚያ ባሻገር የእኒህ መምህር መፃህፍት ከሻንጣዬ አይለዩም። “The Time Machine” የተባለውን የሳይንስ ፊልም አይታችሁታል? ጌታቸው ሃይሌ ለኛ እንዲያ ሆነውልናል። አሜሪካኖቹ ቪዛ ከሰጡኝ ሚኒሶታ ሄጄ አገኛቸዋለሁ። የመጪው መፅሃፌ አካልም አደርጋቸዋለሁ።

* * *

ከሳምንታት በፊት ብራስልስ ሄጄ ነበር።
ስለ መለስ እና ብርሃነ ገብረክርስቶስ አንዳንድ ነገሮችን አጊንቼያለሁ። መቼም ብራስልስ መለስ በሚስጥር የሚመላለስባት ከተማ መሆኗን ታውቁ ይሆናል። አንዳንድ ሃገር ወዳዶች ብዙ ተባብረውኛል። ቀጣዩ መፅሃፍ ላይ የሚወጣ ስለሆነ ግን ያገኘሁትን የእሳት ዳር ወግ እዚህ አልናገርም። እስከዚያው ሁለቱ ቱጃሮች ሆዳቸውን ይቁረጣቸው።
ለነገሩ መለስ ሆዱን የሚቆርጠው አይነት ሰው አይደለም።
ቅንድቡን በጨው አጥቦ አዜብ መስፍንን የፖሊት ቢሮ አባል አድርጓት አረፈው። በርግጥ የመለስ ያፈጠጠ ድርቅና ገርሞኝ እንጂ ይህች ነገረኛ ሴትዮ መጣች ቀረች ለውጥ የለውም። ከጀመርኩ ላይቀር ግን አምባሳደር ብርሃነን ትንሽ በሃሜት ብንቦጭቀው ምን ይመስላችሁዋል? ሃሜት የማትወዱ በItalics የተፃፈውን አንቀፅ የመዝለል መብታችሁ የተጠበቀ ነው።

….እንደሚታወቀው አምባሳደር ብርሃኔ እንትን ይወዳሉ።
በ2002 ማብቂያ ላይ በተደረገው የህወሃት ጉባኤ አምባሳደሩን የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባል ከመሆን ያደናቀፋቸውም እንትን የመወደድ ጠባያቸው ውጤት ተኮር በመሆኑ ነው የሚል ሃሜት አለ። ያ ባይሆን ኖሮ አምባሳደሩ ከአዜብ መስፍን ያነሰ ችሎታ አልነበራቸውም። በርግጥ የግል ፋይላቸው የሚያመለክተው “ዩኒቬርሲቲ ገቡ” የሚል እንጂ “ጨርሰው ወጡ” የሚል የለበትም። በዊንጌት ተማሪነታቸው ግን የመለስ ሲንየር ነበሩ። አዜብ ደግሞ መለስን ከማግባቷ በፊት ወጥቤት ሰራተኛ የነበረች ሲሆን፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የበጎች እረኛ ነበረች። እረኛ መሆን መልካም ነው። ከእረኛነት ወደ ቤተመንግስት የሚደረግ ቀጥተኛ በረራ ግን ብዙውን ጊዜ አደጋ አለው። ይህቺ ሴትዮ፣ በሚዲያ ስትቀርብ እንዲህ “ስድአፍ” የሆነችው፣ ፀሃይ እንዳላገኘ ዘንጋዳ ፈጣን እድገት ስላጋጠማት ሳይሆን አይቀርም።
ወደ ዋናው ሃሜት ልመለስና አምባሳደር ብርሃነ ፖሊት ቢሮነቱን ያጣው እንትን በመውደዱ ነው።
ይሄ ሃሜት አይደለም! በርግጥ ሃሜት ነው። “እውነት አዘል ሃሜት” እንለዋለን። አምባሳደሩ እንደሚወራባቸው ከሆነ ብራስልስ ላይ በቢሮአቸው የሚሰሩ ቆንጆ እንትኖችን ፈጅተው ጨርሰው፣ ያንዳንዶቹን ወደ እህቶቻቸው ጭምር ተሻግረዋል። ይህን ስል መቼም ማንን ማለቴ እንደሆነ ሰራተኞቹ ስለሚያውቁ ሳቅ በሳቅ ይሆናሉ።
ሳልነግራችሁ ረስቼ!
አምባሳደሩ ከሚስታቸው ጋር ታረቁ እኮ!!
“አራት ሚሊዮን ዶላር ይበቃሻል፣ ሌላውን መልሺ። አምባሳደሩም ይቅርታ ይጠይቅሽ እና ታረቁ።” የሚሉ ሽማግሌዎች ተላኩባት። (ሽማግሌዎቹ እነማን እንደሆኑ አላውቅም። ያው መቼም ፕሮፌሰር ይስሃቅ ኤፍሬም ይሆናሉ። ሌላ ታዲያ ማን ሽማግሌ አለ?) የሆነው ሆኖ፣ ሽማግሌዎቹም በእግረመንገድ፣
“ሶሎሜ ታደሰም ብትሆን ወንደላጤ አጊኝታ አግብታለች። የሚያሰጋሽ ነገር የለም” ስላሉዋት ተስማማችና አራት ሚሊዮን ዶላር ብቻ አስቀርታ፣ ሌላውን ለህወሃት ተመላሽ አድርጋ ወደ ብራስልስ ገባች አሉ።
ድንቅ ነው!!
የህወሃት አባላት እውነት መስሎአቸው የሞቱለት ትግል፣ የትግራይ ህዝብ በስሙ የሚነገድበት አብዮት፣ እንዲህ የሚሊዮናት ዶላር መቀለጃ ሆኖ አርፎታል። ለነገሩ የህወሃት አባላትም ሆኑ የትግራይ ህዝብ ይህን አያውቁም ማለቴ አይደለም። “እንኳን ይቺን የዝንብ ወያኔ እናውቃለን” ያለው ማን ነበር?…..

የሆነው ሆኖ ብራስልስ ቆንጆ ከተማ ሆና አገኘሁዋት። እንደ ጨርቆስ አይነት ኪስ አውላቂዎች ግን ሞልተውባታል። ብራስልስ ላይ ደስ ካሉኝ ነገሮች አንዱ ካርል ማርክስና ቪክቶር ሁጎ ቡና ይጠጡበት የነበረውን ቦታ መጎብኘቴ ነው። ሁለቱም ሰዎች ንጉሶቻቸው ሲያስቸግሯቸው ብራስልስ እየመጡ ይጠለሉ ነበር አሉ። እነሱ ቁጭ ይሉባት የነበረው ቦታ ላይ ቁጭ ብዬ ማኪያቶ ጠጣሁ። በርካታ ጎብኚዎችም ይህንኑ ያደርጋሉ።

* * *
ስዊድን የሄድኩ ጊዜም ማርክስን አስታውሼዋለሁ።
እዚያ የሄድኩበት እለት የሰራተኞች ቀን እየተከበረ ነበር። ሰልፈኛ ወዛደሮች “Marx Was Right!!” የሚል መፈክር ይዘው አገር ምድሩን በጩኸት ሲበጠብጡ፣ እኔ ግንቡን ተደግፌ በትካዜ እየተመለከትኳቸው ዋልኩ። ከየሃገሩ የመጡ ስደተኞች የአመፅ መዝሙርና ኢንተርናሲዮናልን እየዘመሩ የየሃገራቸውን መንግስት ሲያወግዙ ዋሉ። አላየሁዋቸውም እንጂ በሌላ አቅጣጫ የብርቱካን ሚደቅሳን ምስል የያዙ የኛ ሰዎችም፣ “አትነሳም ወይ!?” እያሉ ነበር። ይህንን ያጫወተኝ ማቴዎስ ከተማ የተባለው ገጣሚ ነው። በነገራችን ላይ “ተነሳ ተራመድ!” የተባለውን የአየር ሃይል መዝሙር የገጠመው ማቴዎስ ነው የሚባለው እውነት ነው?

ለነገሩ ምኑን ተነስተን ተራመድነው?
ተሽመድምደን ቁጭ ብለን፣ እጃችንን ለእግዚአብሄር እንደዘረጋን ቀርተነዋል። አሁንማ ይቺ እጅ መዘርጋቷም ምቀኛ ተነስቶባት፣ አዲስ የሚታተሙት መፅሃፍ ቅዱሶች ላይ፣ “ኢትዮጵያ” የሚለው “ሱዳን” በሚል መተካት ከጀመረ ስንት ጊዜው? መቼም ኢትዮጵያ የሚሏት ሃገር ጠላቷ መብዛቱ? ግን ከምድረ ገፅ አልጠፋ ብላቸው ተቸግረዋል። እንደ ድመት ዘጠኝ ነፍስ ያላት ሃገር!

* * *
የስቶክሆልም ቆይታዬ መልካም ነበር።
ፅጌረዳ ከተባለች የደብረዘይት ጓደኛዬ ቤት ሁለት ሌሊት አደርኩ። ጣት የሚያስቆረጥም የጉራጌ ክትፎ ሰርታ አበላችን። ፅጌረዳ ሽበቷ ከመብዛቱ በቀር፣ ውበቷ እያንፀባረቀ ጠበቀኝ። ትክ ብዬ ሳስተውላት ፅጌረዳ “ኢትዮጵያ”ን ራሷን መስላ ታየችኝ። እድሜ ውበቷን ያልነካው፣ ትካዜና የወገኖቿ ናፍቆት የተጫጫናት!
….እና ፅጌረዳ ገና ስታየኝ እንባዋ ገንፍሎ ፊቷን አለበሰው።
የልጅነት ጓደኛን በድንገት ማግኘት እንዴት ደስ ይላል? ፅጌረዳን ረሳችሁዋት እንዴ? “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ ስለሷ ተርኬ ነበር እኮ? ባለቤቷም ታዲያ መልካም ሰው ሆኖ አገኘሁት። ሌሊት እንዲያውም እስከ አውሮፕላን ማረፊያው የሸኘኝ እሱ ራሱ ነበር። ስለዚያች የቢሾፍቱ ቀጤማ በመግባባት ማውራት በመቻላችን በጣም ደነቀኝ! ስልጣኔ ማለት እንዲህ ነው። የፅጌረዳ ነገር ለዘልአለሙ ያከተመ ነው። ስሜቱ ግን አብሮኝ ዝንተአለም ይኖራል። ለመሆኑ የሚስታችንን የቀድሞ የከንፈር ወዳጅ ቤታችን የመጋበዝ ችሎታ ያለን ሃበሾች ስንት እንሆን? እኔ በበኩሌ የማደርገው አይመስለኝም። እንኳን ቤቴ ልጋብዘው ገና ሳየው እንደ ፊጋ በሬ የማገነግን ይመስለኛል። ይህን ካላደረግሁማ ምኑን አበሻ ሆንኩት?

* * *

ወደ ሩሲያ የማደርገው ጉዞ ከአሁኑ ናፍቆኛል።
ራሺያ እንደገባሁ በቅድሚያ የማደርገው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ባቡር ወይም አውቶብስ ይዤ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድ እሄዳለሁ። ይቺ ከተማ ከቅዱስ ፒተርስበርግ ቀጥሎ ሶስተኛዋ የራሺያ ትልቋ ከተማ ናት። ማክሲም ጎርኪይ የተወለደባትና የህይወትን መራራ እሬት የጨለጠባት ከተማ። ኒዥኒይ ኖቭጎሮድ የቢሾፍቱ ያህል ትታየኛለች። ጎርኪይ እንዴት አድርጎ ነው በቃላት የሳላት? የጎርኪይን ትረካዎች አንብባችሁ ከሆነ፣ ጎርኪይ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድ ላይ ቆሻሻ ለቃሚ ነበር። በሚለቅመው ቆሻሻና የወዳደቀ አጥንት ምክንያት ታዲያ እጁ ጠቆረበት። በሳሙና ፈግፍጎ ቢታጠበውም ሊለቅለት አልቻለም። ጎርኪይ ምንም እንኳ የነጣ ድሃ ቢሆንም፣ የከንፈር ወዳጅ ለማበጀት መሞከሩ ግን አልቀረም።
ኮረዶቹ ከተዋወቁት በሁዋላ እየተጠየፉት እንዲህ ሲሉ ይጠይቁታል፣
“እጅህን ለምን አትታጠበውም?”
“ታጥቤዋለሁ። ግን አይለቅም!” ሲል ይመልሳል።
ከዚያም ኮረዶቹ ሰበብ ፈጥረው ጥለውት ዘወር ይላሉ።
ጎርኪይ እንዲህ ያሉ ታሪኮችን በውብ ብእሩ ያጫውተናል። እና ጎርኪይ ያቺ የናቀችውን ኮረዳ ደግሞ ከ20 አመታት በሁዋላ የአንድ የፖሊስ ሚስት ሆና ተጎሳቅላ እንዳገኛት እንደዋዛ ያወጋናል። የጎርኪይን የህይወት ታሪክ ማንበብ ማለት ቀኑን ሙሉ መሳቅ ማለት ነው። ጎርኪይ በ1936 በ68 አመት እድሜው ሞስኮ አጠገብ ከሚገኝ መኖሪያ ቤቱ አረፈ። እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ በርናንድ ሾው የማክሲም ጎርኪይን የእረፍት ዜና መጥተው ሲነግሩት እንዲህ ሲል መናገሩ ተመዝግቦለታል፣
“ጎርኪይ ሞተ? በሉ የኔንም የመቀበሪያ ሳጥን አዘጋጁልኝ። የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፀሃፍት የመሰናበቻችን ጊዜ እንደደረሰ ለመናገር እድፍራለሁ።”
እነሆ! ኒዥኒይ ኖቭጎሮድን ለማየት መጓዜ ነው።
ቮልጋ ወንዝን እስካየውም ቸኩያለሁ። ኦካ ዳርቻም ቁጭ እላለሁ። የበረዶው ወቅት ሳይገባ እንድፈጥንም ጓደኞቼ መክረውኛል። በረዶው መውረድ ከጀመረ ቮልጋ እንደ አለት በረዶ ይሆናል አሉ። ጉድ ነው። ወንዝ ደንዝዞ፣ እንደ አስፓልት መኪና ሲሄድበት እግዜር ያሳያችሁ። የኛው ጀግናው አዋሽ ግን መደንዘዙን አያውቅበትም። ከአመት አመት እያቅራራ የሚጓዘው አዋሽ!! ሃገር ወዳዱ አዋሽ!! ስደትን የተጠየፈው አዋሽ!! በሃገሩ ላይ ዘምሮ፣ በሃገሩ መሬት ላይ የሚቀበረው አዋሽ! ፀጋዬ ገብረመድህን ትዝ አላችሁ? እንዲህ ሲል…

“…እስከመቼ ይሆን አዋሽ፣
አዋሽ ቡርቃው፣ መጫ ምንጩ፣ ዳዳ ፅንሱ፣ ሸዋ ፍንጩ፣
ውጠህ ተውጠህ እርጩ፣
ንግርትህ ምንድነው አዋሽ? አባ ብቻ፣ አባ እንቅጩ፣
ዘልአለምህን ፈሰህ ላታልቅ፣
ምነው ተስፋ መቁረጥን አታውቅ?
እስከ መቼ ይሆን አዋሽ?
አዋሽ ቡቡ፣ ሮሮ ብርቁ፣
የዘልአለም ንዳድ ስንቁ፣
እነ ዋቢሸበሌማ ሰብረው ውቅያኖስ ሲዘልቁ፣
እነ ግዮን አልፈው ወርደው፣ ሱዳንን ምስርን ሲያጠምቁ፣
ምነው ያንተ ጉዞ ብቻ በረሃ ላይ መታነቁ?…”

“አዋሽ” የብዙ ነገር ምሳሌ ነው። “ሃገር ወዳድ” የሚሉት አሉ። ፀጋዬ ገብረመድህን በ“አዋሽ” የመሰለው ግን የኢትዮጵያን ህዝብ ሳይሆን አይቀርም። ጉዞው በረሃ ላይ የታነቀበት ህዝብ! ግን ደግሞ ተስፋ መቁረጥን የማያውቅ ህዝብ! ለነገሩ የጀግኖች መፍለቂያ የነበረ፣ የአዋሽ አባት ሃገር እንዲህ በአረም ተውጦ እንደሚቀር፣ ሎሬት ፀጋዬ ታይቶት ነበርን? ማን ያውቃል? ለማንኛውም ቮልጋን ልጎበኝ ወደ ሩሲያ መሄዴ ነው። እዚያ ሄጄ የሚያጋጥመኝንም “የስደተኛው ማስታወሻ” ላይ አወጋችሁዋለሁ።

(….በነገራችን ላይ ሳልረሳው…
በምፅፋቸው መፃህፍት ምክንያት የሚናደዱ የወያኔ ደጋፊዎች አስተያየታቸውን ለምን በስማቸው እንደማይፅፉ ሳላስብ አልቀረሁም። የብእር ስም መጠቀም ነውር አይደለም። አብዛኞቹ ግን ከኔ ጋር እንደሚተዋወቁ ሆነው ይፅፋሉ። እኔ ግን አላውቃቸውም። ለምን ይሆን የሚሸሸጉት? ማንን ይሆን የሚፈሩት? ያው መቼም አስተናጋጃቸው የኢትዮሚዲያው አብርሃ በላይ ነው። ቀንዱንም ሸኮናውንም እየሰበሰበ ይለጥፈዋል።
ሰሞኑን ደግሞ፣ “የጋዜጠኛው ማስታወሻን የፃፈው የማነ ገብረአብ ነው” የሚል ፅሁፍ ለጥፎ ነበር።
ይሄ ሰውዬ ጤና የለውም እንዴ? “ገብረአብ” የሚል ስም እየፈለገ አስቸገረ እኮ! ባለፈው “ንዋይ ገብረአብ ታላቅ ወንድሙ ነው” ብሎ ፃፈና አጋለጥኩት። አሁን ደግሞ የማነ ገብረአብ ሆነ የኔ መፅህፍ ደራሲ!? ይሄ ሰውዬ “ገብረአብ” የሚባል ሰይጣን ለክፎታል እንዴ? “የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል” ይባላል። ትንሽ ከጠበቃችሁ የኔ ግጥሞች ሁሉ የይልማ ገብረአብ ይሆናሉ።
ዶክተር ሼክስፒር ፈይሳ! በቅድሚያ እንደምን ከርመሃል? ደህና ነህ ወይ? ጤናህስ? ወደ ዋናው ጉዳይ ልግባና….አብርሃ በላይ ጓደኛህ ነው አይደለም? እባክህ ቀስ ብለህ ምከረው። “ገብረአብ” የሚል ስም እየፈለገ ከኔ ጋር የሚያያይዘውን ነገር ይተወኝ ብያለሁ ይተወኝ! እንቢ የሚል ከሆነ ግን፣ ምን አደርጋለሁ? ያው መተው ነው። ገብረአቦች ሲያልቁበት ምን እንደሚውጠው አየዋለሁ። ለነገሩ አሁን አሁን አብርሃ ቆዳው ስስ መሆኑን ስላየሁ፣ እሱን ማብሸቅ ደስ ይለኝ ጀምሮአል። አብርሃን ለማብሸቅ ስዬን በጨረፍታ ነካ ማድረግ በቂ ነው። ስዬን ከምትነካበት ሚስቱን ብትነካበት ይመርጣል።)

ወደ ቁምነገሩ ልመለስና…
በመሰረቱ በፖለቲካ ጉዳይ ግለሰቦች ላይ መንጠልጠል በጣም አደገኛ ነው። ግለሰቦች ሰዎች ናቸው። ነገ ከአቋማቸው ሊንሸራተቱ ይችላሉ። ያን ጊዜ ደብቁኝ ይመጣል። ለዚህ መፍትሄው በአላማ ዙሪያ መሰባሰብ ነው። የግንቦት 7 አባል ባልሆንም፣ በሩቅ እንደማያቸው ከሆነ አካሄዳቸው ተስፋ እና እምነት ያሳድራል። አመራሩ ሲተማማ ሰምቼ አላውቅም። የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፈው፣ ባስቀመጡት መርህ መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ። በወሬ የተጠመዱ አለመሆናቸው ይታያል። ወደ ተግባር በመግባታቸው ወያኔም ተደናግጦአል። መለስ ዜናዊ የግንቦት7ን ስም መጥራት መጀመሩ፣ በደካማ ጎኑ ገብተው ስጋት እንደፈጠሩበት ይጠቁመኛል።

ወያኔ የሚንቅህ ከሆነ ስምህን አያነሳም።
የነገደ ጎበዜን ስም ከአፋቸው የማይለዩት፣ ዶክተር ነገደ ከካስትሮ ጋር ተሻርከው፣ የሙስሊም ጀለቢያ ለብሰው አዲሳባ በመግባት፣ መንግስቱ ሃይለማርያም ላይ መፈንቅለ መንግስት እንደሞከሩት ሁሉ፣ ከዛሬ ነገ አንድ ተንኮል ሰርተው ዙፋኔን ጉድ ያደርጉኛል ብሎ ስለሚጨነቅ ይመስለኛል። በርግጥም ወያኔን ለማስወገድ ፍላጎቱ ካለ ጊዜው አሁን ነው። ከወያኔ ወደ ወያኔ የሚደረገው ሽግግር ስር ከመስደዱ በፊት መንቃት ብልህነት ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ የጠሩትን “የክተት አዋጅ” ከግንቦት7 የሰሞኑ “ወያኔን የማግለል” ጥሪ ጋር ማዋሃድ ግድ ይላል። ጥምረትም በጥንቃቄ ከተሰራበት ወጤት ያስገኛል…

* * *

“የስደተኛው”ን ለመፃፍ ወደ ለንደን የመሄድ እቅድም ይዤያለሁ።
ለንደን ላይ ፍራሹ ተፈርሾ፣ ከርቤና ቀበሪቾ የተባሉ እጣኖች ጢሳቸው እየተንበለበለ፣ የአየርባየር ትግሉና ፖለቲካው የጦፈበት፣ ወያኔ እንደ ሽንኩርት ድቅቅ ተደርጎ የሚከተፍበት በርጫ ቤት መኖሩን ነግረውኛል። እዚያ በርጫ ቤት ተሰይሜ አንድ የዘመናችንን የትግል ታሪክ እፅፋለሁ። የነዚያ በርጫ ቤቶች አስቂኝ ጠባይ አብዛኞቹ ጫት ቃሚዎች የወያኔ ተቃዋሚዎች መሆናቸው ሲሆን፣ የጫቱ ገቢ ደግሞ በተዘዋዋሪ ለአዜብ መስፍን መሆኑ ነው። እዚህ ላይ አንድ የዘመነ ደርግ ጄኔራል ትዝ አለኝ። ሰራዊቱ እየሸሸ ሲያስቸግረው ምን ነበር ያለው?

“ታሪክ ዋሽቶአል፣ አሊያም ትውልድ ተኮላሽቶአል!”

ታሪክ እንኳ አልዋሸም። ትውልድ ሳይኮላሽ ግን አልቀረም። ገና ሳይወለድ የሚሰደድ ትውልድ። በልመና የሚኮራ ዜጋ የተፈለፈለበት ዘመን። ዳሩ! ልጆቻቸውን አሜሪካዊ ለማድረግ የሚሻሙ መሪዎች ከነገሱበት ዘመን ምን ይጠበቃል? ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጥ መሪ! ቃል የእምነት እስትንፋስ መሆኑን ያማያውቅ ንጉስ! …

* * *

በተቀረ “ስደተኛው ማስታወሻ” ላይ በርካታ ተነባቢ ታሪኮች ሳይኖሩ አይቀሩም።
33 ምእራፋትን ያቀፈ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ፣ “መለስና ብርሃኑ”፣ “የመንገዴ ላይ አበቦች”፣ “የአመስተርዳም እሳቶች”፣ “በጭጋጋማ ጉም ውስጥ”፣ “አስቀያሚ ገፅታችን”፣ “የሳጥናኤል ጉዳይ”፣ “የሻምቡ ንጉስ”፣ “የጁገል በርጫ ላይ”፣ “የታማኝ ሸክም” (ታማኝ በየነን ይመለከታል)፣ “አረጋዊ እና ግደይ”፣ “በቃሊቲ ጣራ ስር”፣ እና “የስለላ ስራ” ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

“የስለላ ስራ” የሚለው ርእስ በጣም ተነባቢ ሊሆን ይችላል።

በጋዜጠኛነት ሙያ ብዙ የሰራሁ እንደመሆኔ ስለ ስለላ ስራ ጠለቅ ያለ ልምድና እውቀት አለኝ። በመሰረቱ “የስለላ ስራ” ማለት “ጆሮጠቢነት” ማለት አይደለም። ባጭሩ “የተደበቀ መረጃ ፈልጎ ማግኘት” ማለት ነው። ከዚያ ዝቅ ያለ ሌላ ትርጉም የለውም። የስለላ ባለሙያዎችን በሁለት ከፍሎ ማየትም ይቻላል። የመጀመሪያዎቹ የፖለቲካ አላማ ሰላዮች ናቸው። ሌሎቹ ጋዜጠኞች እና ደራስያን ናቸው። ጋዜጠኞችና ደራስያን የስለላ ስራ የሚሰሩት አንድ የተደበቀን እውነት ፈልፍለው በማውጣት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ነው። የፖለቲካ አላማ ያላቸው ሰላዮች ደግሞ፣ መንግስታቸውን አለያም የሚያምኑበትን አላማ ከጥቃት ለማዳን ስለላ የሚያካሂዱ ናቸው። በሁለቱም ጎራዎች ዘንድ የተደበቀ መረጃ ለማግኘት የረቀቀ ሙያዊ ስራ ይሰራል። ለአብነት ህወሃት መሃል አገር ከሚገኙ አባላቱ የሚያገኘውን የኢትዮጵያን ሰራዊት የሚመለከት መረጃ በመለስ ዜናዊ በኩል ለዚያድባሬ ያቀብል እንደነበር መረጃ አለ። ዛሬ ግን መለስ የኢትዮጵያ መሪ ነው። በርግጥ ይህ ርእሰ ጉዳይ ሰፊ ነው። በቀጣይ መፅሃፌ በሰፊው ተንትኜዋለሁ። በጋዜጠኛነት የስራ ዘመኔ መረጃ ለማግኘት የምጠቀምባቸውን ዘዴዎችና የፖለቲካ አላማ ሰላዮችን አስደማሚ ፖለቲካዊ የቁማር ጨዋታ አወጋችሁዋለሁ።

በመጨረሻ ….
መፃፍ እንደምቀጥል ማረጋገጥ እሻለሁ። እንደ አባኮዳ የሚያክላሉና ስማቸውን መግለፅ የሚሰጉ ጥልማሞቶች፣ ምን ያህል በፍርሃት ጉድጓድ ውስጥ እንደሰመጡ ይታዩኛል። የቢሾፍቱ ቆሪጥ ምህረቱን ያውርድላቸው። በኔ በኩል ከሞት በቀር የሚያቆመኝ ሃይል የለም! አያ ሞት ደግሞ ካንዴም ስንቴ ስለሳተችኝ፣ አሁን ተላምደን ቤተሰብ ሆነናል። ተራ ግለሰብ ብሆንም መንፈሴ ብርቱ ነው። ስለዚህ በህይወት ዘመኔ የማምንበትን እንደልቤ ተናግሬ ለማለፍ የወሰንኩ ሰው ነኝ። የኔን እምነት የሚጋሩ በሚሊዮናት ወገኖች እንዳሉኝ ማወቄ ደግሞ ብርታት ሆኖኛል። ወጣቶች በኔ ስልት መፃፍ ጀምረዋል…

“ብሾፍቱን ዳግም አታያትም!” እያሉ የሚዝቱብኝ እንዴት የዋህ ናቸው?

መፃህፍቶቼ ገና ድሮ መላ ኢትዮጵያን አጥለቅልቀውት የለም እንዴ? ለመሆኑ ከዚህ በላይ በሃገር መገኘት አለ? የስንቱን ወጣት ኢትዮጵያዊ አይን እንደገለጥሁ እነዚህ ጥቋቁር ሰዎች ቢገነዘቡ ቆመውም መሄድ ባልቻሉ። “የደራሲው ማስታወሻ” አዲስ አበባ ላይ በድብቅ እየታተመ 150 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ማን እያተመ እንደሚሸጠው ግን እንኳን እኔ የወያኔ የፀጥታ ክፍልም ሊደርስበት አልቻለም።

(…አዲስአበባ ከወያኔ ቁጥጥር ውጭ ስለመሆኗ የሚጠራጠር ካለ፣ እሱ የትም የለም። ሳሞራ የኑስና ጌታቸው አሰፋ ነቅተው መጠበቅ የቻሉት ቤተመንግስቱን ብቻ ነው። በተቀረ ወያኔ እንደ ጉም ተንሳፎአል። አንዲት የትግራይ ልጅ የሆነች ጓደኛዬ እንዳጫወተችኝ፣ እናቷ የትግሬ ሹሩባ ተሰርተው መርካቶ መሄድ አልቻሉም። የህዝቡን አይን ፈርተውና ተሳቀው ትተውታል። የትእዝብት አይን ከጦር በላይ ይዋጋል። ይሄ የማይፈለግ እውነታ የወያኔ ሰዎችን ፍርሃት ለቆባቸዋል። እንደምንሰማው ከሆነ፣ በግድ ተይዘው እንጂ፣ የመልቀቂያ ማመልከቻ የሚያስገቡና ዲፕሎማት ሆነው ውጭ ሃገር ለመሄድ የሚጠይቁ የወያኔ የአመራር አባላት እየበረከቱ ሄደዋል። ጎርፉ ሳይውጣቸው ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ፣ ከነጫጩቶቻቸው ለማምለጥ መላ ጎርጓሪዎች ሆነዋል። እውነታቸውን ነው። መንግስቱ ሃይለማርያም እነ ለገሰ አስፋው ላይ ያደረሰውን ቅሌት መቅመስ አይሹም…)

የወያኔ ካድሬዎች ራሳቸውም “የደራሲው ማስታወሻ”ን በድብቅ ከአዟሪ ላይ እየገዙ፣ የገዛ ሃጢአታቸውን በማንበብ ላይ እንዳሉ ሰምቼያለሁ። ካነበቡት መካከል ጄኔራል ባጫ ደበሌ (ደስተኛው ጄኔራል) አንዱ ነው። ካነበበ በሁዋላ ሰዎች ሲጠይቁት የተናገረውን ፅፈው ልከውልኛል። እንዲህ አለ አሉ፣

“ስለኔ የተፃፈው ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው። እኔ ጄኔራል የሆንኩት ከአስር አለቃነት ተነስቼ ነው። ከእረኛነት ተነስተው ጄኔራል የሆኑ የህወሃት አባላት አሉ አይደለም ወይ?”

በባጫ ደበሌ አባባል በጣም ተስማምቻለሁ። ባጫ 100 % ልክ ነው። ስለዚህም አንድ አሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ወያኔ ሲወድቅ ጄኔራል ባጫ በወንጀል መጠየቅ የለበትም። እስካሁን ለፈፀመው ጥፋት አንድ ነገር እንዲያደርግ ግን እንጠይቀዋለን። ይህም የሜጄር ጄኔራልነት ማእረጉን እንደለበሰ፣ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝብ በተሰበሰበበት የማይክል ጃክሰንን Moon Walking ይደንስልናል። ከዚያም ከነገንዘቡ ከነንብረቱ በነፃነት ወደቤቱ ይሄዳል! ባጫ የስርአቱ ሰለባ እንጂ ወንጀለኛ አይደለም። መጪው መንግስት ይህን በማስታወሻው እንዲይዘው እፈልጋለሁ።

እኔን በተመለከተ የትውልድ ሃገሬን ዳግም አየሁ አላየሁ አሳሳቢ አይደለም።
ርግጥ ነው፣ በህይወት ወደ ቢሾፍቱ የመመለስ እድል አላገኝም ይሆናል። ገብረክርስቶስ ደስታም ወደሚወዳት ሃገሩ ሳይመለስ ነው ህይወቱን ያጣው። ሙሴም 40 አመታት ከተጓዘ በሁዋላም እንኳ እስራኤል የተባለች ሃገሩን መሬት ሳይረግጥ ነው የሞተው። እና ሊያጋጥም ይችላል። የነፃነት ትግል ጠባይ እንዲያ ነው። እስከ እለተ ሞቴ ግን እግዚአብሄር የሰጠኝን የነፃነት መድፍ “ግማሽ ነጋዴ! ግማሽ መደዴ!” ከሆኑ ሰዎች አናት ላይ አምበለብለዋለሁ…

(ደራሲውን ለማግኘት በሚከተለው ኢሜይል አድራሻ ይላኩ፡ [email protected])
መስከረም፣ 22 2010