ከዚህ አምባገነን ስርአት ኢትዮጵያን እንዴት ነፃ እናውጣት? (ከገረመው አራጋው ክፍሌ ከኖርዌ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከገረመው አራጋው ክፍሌ ከኖርዌ
አምባገነናዊ ወይንም ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አስወግዶ በምትኩ ለሀገርና ለሕዝብ ደህንነት የሚቆም ስርዓትን ለመታደግ ሰላማዊም ሆነ የትጥቅ ትግል ወደ መፍትሔ የሚመሩ መንገዶች ናቸው፡፡
ከሰላማዊ ትግል እና ከትጥቅ ትግል ማማረጥ በስልጣን ላይ ባለው ስርዓትና ባህሪ የሚወሰን ቢሆንም በየትኛውም መመዘኛ ግን ከትጥቅ ትግል ይልቅ ህዝባዊ መሠረት ያለው
ሰላማዊ ትግል ምንያህል ተፈላጊና አዎንታዊ እንደሆነ በተለይም የዘመናት የጦርነት ታሪክን ላስተናገደች ሀገር ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው እኛም የሠላማዊ ትግል አምባሳደሮች ጦርነትንና ጦረኛ መሆንን አጽንኦት ሰጥተን የምንቃወመው፡፡ ይህን እውነታ መሠረት በማድረግ ዛሬ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስናስተውል
ግራ መጋባትና ምስቅልቅል ያለ ሆኗል፡፡ ይህም ችግር በዛሬዎቹ ገዢዎቻችን የመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ተገንዝቧል፤ አውቋልም፡፡ ይህን ሁሉ ችግር አስወግዶ ትክክለኛውን የማያዳግም የሕዝብ የበላይነት ለማምጣት ዛሬም እንደትላንቱ ከባድና መራራ ትግል ያስፈልጋል፡፡
ዋጋው ይለያይ እንጂ አምባገነኖች ባሉበት ሀገር የሚደረግ መብት የማስከበር ትግል ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የሚከፈለው መስዋዕትነት እንደ አምባገነኖቹ ጭካኔና እንደ
ታጋዮቹ የትግል ስትራቴጂ ይለያያል፡፡ የወያኔ አምባገነንነት ባያከራክርም ከዚህ አምባገነን ስርአት ኢትዮጵያን እንዴት ነፃ እናውጣት የሚለው ጥያቄ ላይ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ይዘው በተለያየ ፅንፍ የተሰለፉ ኃይሎች መበራከት ማለትም በአንድ ጎራ ስርአቱን በትጥቅ ትግል ለመጣል የተሰለፉ፣ በሌላ ጐራ ደግሞ ስርዓቱን በየትኛውም መንገድ በትጥቅም ሆነ በሰላም ማስወገድ በሚል የትግል ስትራቴጂ የነደፉ ኃይሎች ሦስተኞቹ በሰላማዊ ትግል እና በሀገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ስርአቱን ለማስወገድ የተነሱ ናቸው፡፡
የመጀመሪያዎቹ ሁለት አማራጮች አንባገነኖች የሚያደርሱትን ጭቆና ሰላባ የሆኑ ሰዎች በእልህ የሚገቡበት የበቀል መንገዶች በመሆናቸው የትግል ስትራቴጂዎቹ አዋጪነት አጠያየቂ ነው፡፡ በዘመኑ ትውልድ ተመራጭም አይደሉም፡፡ ነገር ግን ከሰላማዊ ትግል እና ከትጥቅ ትግል ማማረጥ በስልጣን ላይ ባለው ስርዓትና ባህሪ የሚወሰን ቢሆንም በየትኛውም መመዘኛ ግን ከትጥቅ ትግል ይልቅ ህዝባዊ መሠረት ያለው ሰላማዊ ትግል ምንያህል ተፈላጊና አዎንታዊ እንደሆነ በተለይም የዘመናት የጦርነት ታሪክን ላስተናገደች ሀገር ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡
ሰላማዊ ትግል ከትጥቅ ትግል በእጅጉ ይለያል፡፡ በባህሪው ከነፍጥ (ከጦር መሳሪያ) ንኪኪ የራቀ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህም አምባገነን ስርዓትን በመቃወም ሰላማዊና ህጋዊ የስልጣን ሽግግር እንዲመጣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ የትምህርት፣ የርሃብና የስራ ማቆም አድማ ማድረግን ጨምሮ 100 – 200 የሚጠጉ ስልቶችን በመጠቀም ጫና ለማሳደር የሚያስችል ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ የትግል ስልቶች የበለጠ ፍሬያማ የሚሆኑት ከተናጠል ይልቅ በሙያ ማኅበርም ይሁን በፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስና በመታገል ነው፤ለስኬታማነቱ ግን መስዋዕትነት መክፈልንም ይጠይቃል፡፡ በርግጥ በኢትዮጵያ በተቃዋሚዎች ሰላማዊ ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ምን ያህሉ በአግባቡ ተተግብረዋል የሚለው መታየት ያለበት ቢሆንም የመታገያ ስልቶቹን ከማኅበረሰቡ ባህልና ወግ እንዲሁም አኗኗር ጋር የሚሄዱትን እንኳን ለይቶ ያለማወቅና ያለመጠቀም ችግር እንዳለ መናገር ይቻላል፡፡ ሰላማዊ ትግል የዜጐችን ለቅሶ ከማቆምና አምባገነን ሥርዓትን ከማስወገድ በተጨማሪ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ለማምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዚህም የህዝቡን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ህይወት ተሳትፎ ንቃተ ህሊናን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡
ሌላው ጠቀሜታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው የሚያጠፉትን የሰው ህይወት፣ ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብና ለዚህ የሚውለውን ሃብት ለሀገር ሰብዓዊና ቁሳዊልማት እንዲውል በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም ገዥው ፓርቲን ለመደበለ ፓርቲ ሥርዓት ያለውን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ በገዥው ፓርቲ ይሁንታን ባያገኝ እንኳ ለተግባራዊነቱ ተቃዋሚዎችም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ስለሆነም ሰላማዊ ትግል ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ቢሆንም የዜጐችን ኑሮ ለማሻሻልና የሀገርን ዕድገት ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ይልቅ በተግባርም ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡
በርግጥ ሰላማዊ ትግል ከትጥቅ ትግል ያላነሰ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል ቢታወቅም አዋጭነቱ ላይ ግን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህም አምባገነን ሥርዓትን በማስወገድና በማንኛውም እንቅስቃሴ ህዝባዊ ተሳትፎን እንደሚያጐለብት ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ለዜጐች ተጠቃሚነት ሰላማዊ ትግል ትልቅ አስተዋፅዖ አለው፡፡
ለአብነትም የአሜሪካው ማርቲን ሉተርኪንግ፣ የህንዱ ማህተመ ጋንዲና የደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላንና ሀገሮቻቸው አሁን ያሉበትን ደረጃ ማየት በቂ ይመስለኛል፡፡ኢህአዴግና አመራሮቹ ግን የመጡበት መንገድ የትጥቅ ትግል በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን አምኖ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉትንና የሚፈልጉትንም ወደ ሌላ የትግል አቅጣጫ (ወደ ትጥቅ ትግል) እንዲያዘነብሉ እያስገደደ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ቀድሞም ቢሆን ኢህአዴግ የሰላማዊ ትግል እውነታን የሚረዳው በህግ እንዳፀደቀው ሳይሆን እንደራሱ ፍላጐትና ልምድ በመሆኑ ነው፡፡
ሌላው ሰላማዊ ትግል ከአመጽ ትግል በላይ ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎም ቢሆን ሰላማዊ ትግል ብቻውን ድል ማቀዳጀት የሚችል ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። እንዲያውም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እና ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ አንዱ ያለሌላኛው ዋጋ የለውም።
በአንዳንድ ሰዎች አነጋገር በሰላማዊ ትግል ብቻ ወያኔን ከስልጣን አውርዶ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መገንባት እንደሚቻል ሲነገር ይሰማል።ሆኖም በአለፈው ሃያ ሁለት አመታት በህጋዊነት ተመዝግበው ሃገር ውስጥ በሰላም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ምን እንደደረሰባቸው በምን ደረጃ ላይ እንዳሚገኝዑና ወያኔም ሰላማዊ ትግል እንደሚደግፍ መስሎ ስልጣን ላይ ተደላድሎ እንደቆየ ግልጽ ነው።
በአለፈው ሃያ ሁለት አመታት ወያኔ በህዝባችን ላይ የሚያካሂደው ግፍ ሞልቶ በመፍሰሱ የተነሳ ወያኔ ይወገድልን እንጂ የፈለገው ይምጣ የሚል አመለካከት አልፎ አልፎ ሲንጸባረቅ ይታያል። የዚህ ዓይነቱ አመለካክት በሥርዓቱ የመማረር ውጤት እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም፣ ወደምንፈልገው ዘላቂ ሰላም፣ ብሄራዊ ጥቅምና የህዝብ መብት መከበር ሊያደርስ መቻሉ ግን እጅግ አጠራጣሪ ነው። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ወያኔን ከስልጣን ለማውረድ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ የወሰዱ ፓርቲዎች የትጥቅ ትግል ለብዙ ዓመታት ስንተላለቅ የኖርንበትና የምናውቀው ሲሆን ፤ በትጥቅ ትግል አንዱን ጨቋኝ በሌላው እየለወጥን የአገዛዝን ባህል አጠነከርነው እንጂ ስልጣንን ለመጋራት አልቻልንም።ይህን ሁኔታ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ የወሰዱ ፓርቲዎች ጠንቅቀው ሊረዱት ይገባል። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ወያኔ የኢትዮዽያን ህዝብ የሰላምና ህጋዊ ትግሉን ቢከረችመውም አሁንም ቢሆን የኢትዮዽያ ህዝብ የሰላሙን ትግል ወደ አርዕድ _ አንቀጥቅጥ ሀይል ለመለወጥ የሚያችለው ዕምቅ ሀይል አለኝ ብሎ ያምናል። ይህ ከሆነ ዘንድ ነፃነታችንን ለማስመለስ የምናደርጋው ትግል በአዲስ ስልትና ዘዴ አቀነባብሮ መታገልና ማታገል የተቃዋሚ ሁይሎች አይነተኛ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ። ይህ የትግል ስልት ተግባራዊ ከሆነና የኢትዮዽያን ህዝብ በሞላ ካሳተፈ በድንቁርና በትቢት የተወጠሩትን የወያኔ መሪዎች ከስልጣን የማይወገዱበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም።
ኢትዮጲያና ኢትዬጲያዊነት ለዘላለም ይኖራል። ወያኔ ግን በተባበረ የ ኢትዮጲያዊያን ጠንካራ ክንድ ይወገዳል!!