በደብረ ኤሊያስ ገዳም ከሚኖሩ 600 ሰዎች በመከላከያ ድብደባ ከ95 ከመቶ በላይ ቆስለዋል፣ ተገድለዋል፣ ተበትነዋል

[addtoany]

ሰሞኑን በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ በተለያዩ ምክንቶች በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የህክምና ተቋማት አመለከቱ። በግጭቱ በአንድ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ የነበሩ ምዕመናን ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይም የአካል ጉዳት መድረሱ ተነግሯል፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ ካለፈው ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ ም ጀምሮ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ ደገሎ ቀበሌ፣ ብሐረ ብፁዓን ሥላሴ መልከአ አንድነት ገዳም አካባቢ መነሻው በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት በምዕመናን እና በፀጥታ ኃይሉ መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካታዎቹ ምዕመናን በከባድ መሳሪያ በታገዘ ጥቃት ህይወታቸው ማለፉንና ሌሎቹ መበተናቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል። ግጭቱ ለተከታታይ አምስት ቀናት ከተካሄደ በኋላ ትናንት እኩለ ቀን አካባቢ መቆሙን ተናግረዋል። በገዳሙ ከ600 በላይ ሰዎች ይኖሩ እንደነበረ የተናገሩት አስተያየት ሰጪው ከ95 ከመቶ በላይ ቆስለዋል፣ ተገድለዋል አሊያም ተበትነዋል ነው ያሉት፡፡

በነበረው ግጭት ከባድ የጦር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ቤተክርስቲኑ ጉዳት እንደደረሰበትም አስረድተዋል። ሌላው የአካባቢ ነዋሪ የግጭቱ መነሻ የወረዳ አመራሩ እና የገዳሙ አባቶች በተከሰተ አለመግባባት ችግሩ እንደተፈጠረ ተናግረዋል። የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት መደረጉን የሚናገሩት እኚሁ አስተያየት ሰጪ መግባባት አለመቻሉንም አመልክተዋል፡፡ አንድ የደብረ ኤሊያስ ሆስፒታል አስተያየት ሰጪ ሰሞኑን በነበረው ግጭት ከ200 በላይ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ቆስለው በሆስፒታሉ መታከማቸውን ተናግረዋል፡፡ ከወራት በፊትም በዚሁ ገዳም አካባቢ በተፈጠረ ግጭት 10 ያህል ምዕመናን መገደላቸውን አንድ የሀገር ውስጥ ሰብአዊ መብት ድርጅት ገልፆ ነበር። ስለጉዳዩ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ እንዲሁም ለምሥራቅ ጎጃም ዞን የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ስልክ ብንደውልም ለጊዜው አልተሳካም፡፡