በጠ/ሚ አቢይ ‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ ስሌት ውስጥ ያሉ ውዥንብሮችን ማፅዳት!

በጠ/ሚ አቢይ ‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ ስሌት ውስጥ ያሉ ውዥንብሮችን ማፅዳት! (ሐይሉ አባይ ተገኝ)

የጠ/ሚ አብይ ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ፖለቲካዊ ሂሣብና ሃሣብ ነው:: ‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ ግንዛቤ መነሻ ሃሣብ መሠረት ወያኔ ሰራሹ “የጎሣ ፌደራሊዝም” በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የጋረጠውን የፀረ-ኢትዮጵያና የፀረ-ኢትዮጵያዊነት ጥቁር ደመና ገፎ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ማብሰር ነው:: የጋራ እምነት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ላይ በመደመር ‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ ውጤት በግብዐትነትና በአንድነት ለመቆም የተሰላ አጭር መሪ ቃል ወይም መርሆ (motto) ነው:: ለኢትዮጵያውያን የተላለፈ የማንቂያ ደወል ነው። ትላቁ ዊሊያም ሼክስፒር “ማንነታችንን እናውቃለን። ምን እንደምንሆን ግን አናውቅም” [ We know who we are, but not what we may be] ይላል። ልብ እንበል።

ጠባብ የጎሣ ፓለቲከኞች ሰሞኑን እንደሚነግሩንና እንደሚቀጥፉት ይህ ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ የጠ/ሚ አቢይ አዲስ ፅንሠ-ሃሣብ ወይም ርዕዮተ-ዓለም (concept or ideology) አይደለም:: ሊሆንም አይችልም:: ይህ ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ልክ እንደ ሂሣቡ ቁጥሮችን መጨፍለቅ ሳይሆን የዜጎች ቁጥርን በተናጠል ባህርያቸውና መገለጫዎች በአንድ ስብስብ ውስጥ (set) በማስቀመጥ አንድ ዓይነት ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ውጤት ማምጣት ነው:: በኢትዮጵያውያን ላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚቀበሉ ዜጎችን በመጨመር ኢትዮጵያ የተሰኘችውን የስብስብ ወይም ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ውጤትን ማጠናከር ነው:: ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ ሃገራቸው የሚደመሩበትና የሚሰጡት ድምፀ ውሣኔም ነው።

[ኢትዮጵያዊነት + ኢትዮጵያዊ = ኢትዮጵያ]

‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ስሌት ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተመሣሳይ አመለካከትና አስተሣሰብ ያላቸውን (Individuals on the same page) እንዲሁም የሚናበቡ ኢትዮጵያውያንን አንድ ላይ መደመር ነው:: የመግባቢያ ሠነድም ነው። ይህ ማለትም ድምሩ ፍፁም የሆነ ፓለቲካዊ ስምምነትንም (absolute agreement) አይፈልግም:: ይህ ስለሌለና ስለማይኖር:: ይህን እናስታውስ። ኦርሳን ስካት ካርድ ‘የሚያልቀው ግጥሚያ’ በተሰኘው መፅሃፉ ” ምናልባትም የምናስመስለውን እስከምንሆን የማንነትን ካባ ማጥለቅ አንችልም” ይላል።

ለመሆኑ የዚህ በመናበብ የሚሠላው ‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ እሣቤ ባሕርይ ምንድነው?

ይህ ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ የማንነት ኪሣራ ለደረሰባቸው፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በፖለቲካዊ መሸንገያና ፕሮፖጋንዳ የተጠየፉ፣ የተጠራጠሩ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያላሉና የካዱ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያዊነታቸው ፀንተው ከሚኖሩ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መገለጫና ማንነት ካደረጉ ብዙሃን ጋር በፍቅርና በሰላም ምልክት በመደመርና በመደማመር ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን በኢትዮጵያውያን ድምር ውጤት ማጠንከር ነው:: ሐገረ ኢትዮጵያን በዜጎች ህብረትና አንድነት በማፈርጠም የዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም የሕግ የበላይነት የሚሠፍንበት የጋራ አድራሻና መቀመጫ ሃገርን ብሎም የነፃ ህዝብ መኖሪያ የሚሆን ምቹ ስፍራን ማነፅ ነው:: መብትና ነፃነቱ ተገፎ በግፍና በመከራ ገዢዎቹ በመፈራረቅ በባርነት የሚገዙትን ህዝብ መብትና ነፃነቱን በትግሉ ነጥቆና አስከብሮ በእኩልነትና በነፃነት በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለሁሉም ዜጋ በእከልነትና ያለአድልዎ የሚተገበርበት፣ መብትና ነፃነቱ የሚነግስበትና የሚገለፅበት ስፍራ የሆነችውን ኢትዮጵያ ሐገሩን ተደምሮና ተደማምሮ የሚያንፅበት ስልት ነው::

‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ የኢትዮጵያንና የህዝቧን ፍቅር፣ መተሳሰብና አብሮነት የማይፈልጉ በታኝ የፓለቲካ ሃይሎችን (political centrifugal forces) በመቀነስ በምትካቸው እርስ በእርሣቸው በኢትዮጵያ ዜግነት የተናበቡ ባጭሩ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያዊነት ጋር በማዛመድና በማከል የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ጥንካሬ ማበጀት ነው:: ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያዊነትን በጠነከረና በማይብረከረክ ማገርና ምሰሶ ማጠንከር (enforcement) ነው::

‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ውጤትም ኢትዮጵያን የሕግ የበላይነት የሰፈነባት የፍትሕ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ሃገር እንድትሆን ማስቻል ነው::

‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ በጎ ገፅታና ውጤት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ኢ-ፍትሃዊ ሥርዐት በማስወገድ የዜጎቿ መብት በሕግ የተረጋገጠበትና በሕግ ከለላ የሚጠበቅበት ሃገርን ለመገንባት የሚችለውን ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥና ስርዐት በእርስ በእርስ መናበብ ማዘጋጀት ነው:: ለአርነቱና ለነፃነቱ በነፃነት እንዲቆም ማቀናጀት ነው::

‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ሌላው ገፅታና ውጤት ዴሞክራሲያዊ መርሆን ተቀብሎና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ተርጉሞ የሚንቀሳቀስ ዜጋን ማሰባሰብ ነው:: መብትና ግዴታውን አውቆና ላለመስማማት ተስማምቶ ልዩነቱን በጠመንጃና በፍጥጫ ሣይሆን በውይይትና በመቻቻል የሚፈታን የሰለጠነን ዜጋ ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ነው::

‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ሌላው ገፅታና ውጤት ሲቋጭ ‘በመደመር’ ከዘር: ጎሣና ሃይማኖት የቁጥር አብላጫነት (Numerical Majority) ይልቅ በዴሞክራሲያዊ ብዝሃንነት (Democratic Majority) የሚያምን ዴሞክራሲያዊ ዜጋ የማሰባሰብ ሂደት ነው::

ይህ የጠ/ሚ አቢይ ‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ መሪ ቃል ከላይ በዘረዘርኩት አግባብና መግባቢያ ካፈነገጠ መደመር ሣይሆን ስልታዊ መቀነስ ነው። ከዚህም እሣቤ ውጭ የሚደረግም ‘በኢትዮጵያዊነት የመደመር’ ስሌት መደመር ሣይሆን ቁጥርን ለዜሮ ማካፈልና ያልተገለፀና ትርጉም ዐልባ ውጤት መቃተት ነው (number over zero is undefined)።

በዚህ ላሣርግ።

ጆርጅ ማርቲን ‘የዙፋኑ ፍልሚያ’ መፅሃፉ ይህን ይላል “ሌላው ዓለም ስለማያስታውስህ ምን እንድሆንክ አትዘንጋ። ምንነትህንና ማንነትህን ጥንካሬህ አድርገህና እራስህን በማንነትህ ካስታጠከው አልተሣሳትክምና ማንነትህን ተጠቅሞ ማንም ሊጎዳህ ከቶውንም አይችልም።” [ Never forget what you are, for surely the word will not. Make it your strength. Then it can never be your weakness. Armour yourself in it, and it will never be used to hurt you. (George R.R. Martin)]

‘በኢትዮጵያዊነት መደመር’ ኢትዮጵያን ለመበተን የተሠለፉ ሃይሎችን መርዝ ማምከኛ ፍቱን መድሐኒት ነው።

‘ኢትዮጵያዊነት የማንነታችን ማህተም ነው’
‘ኢትዮጵያዊነት ማንነት ብቻ ሣይሆን ምንነትም ነው’

‘ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያውያን፤ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ውስጥ ማውጣት አይቻልም’

#AbeiAhmedAliEthiopianPrimeMinister