ከመቀሌ ወደ ሳምረ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል

“ወረዳችን ይመለስልን” በሚሉ የሕንጣሎ ነዋሪዎች ደንጎላት በሚባል አካባቢ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በአካባቢው ወጣቶች መንገድ እንደተዘጋ ተገለጸ።’ሕንጣሎ ወጀራት’ ተብሎ ይጠራ የነበረው ወረዳ ለሁለት ተከፍሎ፤ ወጀራት እራሱን የቻለ ወረዳ ሲሆን ሕንጣሎ ደግሞ ሒዋነ ከምትባል ሌላ ወረዳ ጋር እንዲካተት ተደርጓል።
ሒዋነ ከምትባለው ወረዳ ጋር እንዲቀላቀሉ የተደረጉት የሕንጣሎ ነዋሪዎች፤ እራሳችንን የቻለ ሕንጣሎ የተባለ ወረዳ ሊኖረን ይገባል እንጂ ከሒዋነ ወረዳ ጋር መቀላቀል የለብንም የሚል ቅሬታ ነው የሚያነሱት።ከነዋሪዎቹ እንደሰማነው አሁን በተጀመረው አዲስ የአስተዳደር መዋቅር፤ ወጀራት ከ1-9 ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን ሕንጣሎ ግን ሒዋነ ወደሚባል ወረዳ እንዲቀላቀል ተደርጓል።ታዲያ ነዋሪዎቹ የራሳችን ወረዳ ይኑረን ሲሉ ነው እየጠየቁ ያሉት።

የአካባቢው ነዋሪዎች ኮሚቴ ወኪል አቶ ደሱ ፀጋየ፤ “ጥያቄያችን ወረዳችን ይመለስልን የሚል ነው፤ ህንጣሎ ውጀራት ወረዳ ነበረች። ወጀራት ተመለሰች ነገር ግን ህንጣሎ ተሰጠች።” ይላሉ።አቶ ደሱ ይህንን ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ስድስት ወራት መቆጠራቸውን ይናገራሉ።እርሳቸው እንደሚሉት ቅሬታቸውን ለማቅረብ ያልሄዱበት፤ ያልደረሱበት ቦታ የለም። በወረዳ እና በዞን የሚገኙ የፍትሕም ሆነ የፀጥታ አካላትን አዳርሰዋል። ነገር ግን ያገኙት ምላሽ የለም።

“እኛ መንግሥት በደነገገው ሕግ መሠረት ሁሉንም አሟልተናል። አንደኛ ከ115 ሺህ ሕዝብ በላይ ነን። ሁለተኛ መንግሥት ‘ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ የወረዳ አገልግሎት ማግኘት የለበትም’ ነው የሚለው እኛ ግን ከ30 በላይ ኪሎ ሜትር በላይ ሄደን ነው ይህንን አገልግሎት የምናገኘው፤ ስለዚህ የልማት ጥያቄያችን እንዲመለስልን ነው የምንፈልገው” ሲሉ ጥያቄያቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ነገር ግን ይህንን ጥያቄ ማንሳት ከጀመሩ መንፈቅ ቢሞላቸውም፤ የፖለቲካ አስተዳዳሪዎችን መልስ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም ጆሮ የሰጣቸው የለም።
አቶ ደሱ “በተቃራኒው በዞንና በወረዳ ፖሊስ አማካኝነት ያስፈራሩን ገቡ፤ ወደ ገበያ የሚሄዱ ከብቶችሳይቀሩ መንገድ ላይ ነው የዋሉት፤ መንገድ ዝግ ነው፤ ይሄው እንዲህ ከሆነ ሦስት ቀን ሆኖታል” ብለዋል።ከአከባቢው ነዋሪዎች እንደሰማነው መንገዱ በመዘጋቱ ትናንት እስከ 150 የሚደርሱ መኪኖች መንገድ ላይ ሲጉላሉ ውለዋል።
በሌላ በኩል “ወረዳችን ይመለስልን” የሚሉ የዓዲ ነብሪ ኢድ ነዋሪዎች መንገድ ዘግተው ነበር የሚሉ መረጃዎች ተሰምተዋል።በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን የሰሜን ምዕራብ ዞን ኃላፊዎችና የክልሉን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።ሲል የዘገበው ቢቢሲ የአማርኛ ዜና ክፍል ነው፡፡