መደመር በአማርኛና በኦሮምኛ

መደመር በአማርኛና በኦሮምኛ

መደመር በአማርኛ፤

«መደመር ማለት ትናንት ከኖርንበትና ዘመናት ከገፋንበት የእርስ በእርስ ሽኩቻ፣ ጥላቻ፣ ትንቅንቅ፣ መጠፋፋት፣ መወነጃጀል፣ የቂም በቀል ኋላቀር ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በመውጣት፤ ሁሉንም የትናንትን መጥፎ ቅሪቶች በማራገፍና በመርሳት በአዲስ መንፈስ፣ ለአዲስ ሀገራዊ ግንባታ በሰላም፣ በፍቅር፣ በወንድማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በመነሳት ወደቀድሞው ገናናነት መወንጨፍ እንችል ዘንድ የሚያሸጋግረን መወጣጫ መሰላል ነው»

[ ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከተናገረው ]

መደመር በኦሮምኛ፤

«መደመር የኦሮሞ ሕዝብ እሴቶችን [ገዳን መሆኑ ነው] ከኦሮሚያ አልፎ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ብሎም በአፍሪካ እንዲስፋፋ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው»

[ ሽመልስ አብዲሳ በነቀምቴ ከተማ እየተካሔደ ባለው የመደመር መጽሐፍ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ከተናገረው]

መደመር በቅጡ ያልተጤነ እንጭጭ ዝባዝንኬ ነው ያልነው ለዚህ ነው። የመለስ ዜናዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲም እንደዚያ ነበር። ለዚያም ነው ሽግሽጉ ከመለሲዝም ወደ ዐቢይዝም ነው ያልነው። ለዚያም ነው መደመር እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የማይለያዩት። ሁለቱም ወጥ ትርጉም የሌላቸው፣ ቃላትን የሚያባክኑ፣ ሕዝብን ግራ የሚያጋቡ ቅዠቶች ናቸው።

ዐቢይ እና ሽመልስ እርስ በርስ የሚምታታባቸውና የሚያምታቱት ለዚህ ነው። መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲናገር አብዮታዊ ዲሞክራሲ ይል ነበር፤ በትግርኛ ሲናገር ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የትግራይ እሴት ለማስመሰል «ወያናይ ዲሞክራሲ» ይለው ነበር። እነ ዐቢይና ሽመልስም በአማርኛ መደመር እያሉ በኦሮምኛ ሲያወሩ ግን ገዳ፣ ሞጋሳ፣ ኦሮሙማ የሚሉት በግብርም በአስተሳሰብም የሱ ዲቃሎች ስለሆኑ ነው።