በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጵጵስና ለመሾም “500 ሺህ ብር ጉቦ እየተከፈለ ነው”
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
(በፍቃዱ አድነው)
በዚህ ሳምንት የሚጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ጵጵስና ለመቀበል በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር በጉቦ መልክ የሰጡ እጩዎችን እንዳይሾም ተሰግቷል። “ደጀሰላም” የተባለው ለቤተክርስቲያኒቱ ቅርበት ያላቸውን አወዛጋቢ ዘገባዎች በማቅረብ የሚታወቀው ድረ ገጽ ሰሞኑን እንደዘገበው የጵጵስና መእርግ ለማግኘት ተስፋ የተሰጣቸው ግለሶቦች ከ300000 እስከ 500000 ብር የጉቦ ቀብድ ሰጥተዋል። ነገሩን እጅግ አሳፋሪና አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ጉቦ ተቀባዩና የሙስናው መሪ የቤተ ክርሲቲያኒቱ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ መሆናቸው ነው።
በሕግ ደረጃ ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራል የሚባለው ሲኖዶስ በፓትርያርኩ የጠነጠቀውን ሥልጣን ለማስመለስ ከሁለት ዓመት በፊት የጀመረው ትግል ከሞላ ጎደል በአባ ጳውሎስ አሸናፊነት መደምደሙ ይታወሳል። ፓትርያርክ ጳውሎስ “የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደርና አመራር ወደቤተ ዘመድ ኩባንያነት ቀይረውታል፣ ሙስናና መንፈሳዊ ዝቅጠት ስር እንዲሰድ አድርገዋል” በማለት የሚከሷቸው የሲኖዶሱ አባላት አባ የጳውሎስን ሥልጣን በሕግና በአሰራር ለመገደብ ያደረጉት ጥረት በዋናነት የከሸፈው በመንግሥት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ነበር። በሲኖዶሱ ውስጥ የተነሳው ውዝግብ የሕዝቡን ትኩረት መሳብና ቁጣ መቀስቀስ እንደጀመረም መንግሥትም የሲኖዶሱን አባላት በመሰብሰብ በአቶ አባይ ፀሐዬ በተመራ ቡድን አማካይነት ማስፈራሪያ አከል መመሪያ ሰጥቶ ነገሩን “በእንጥልጥል እንዲቀር” መስገደዱ የሚታወስ ነው። በወቅቱ አካሄዱ ያላመራቸው አቶ አባይ ፀሐዬ በተደጋጋሚ በሲኖዶሱ ጉባዬ መገኘት በማብዛታቸውና ውሳኔዎችን አቅጣጫ እስከማስያዝ በመድረሳቸው “አቡነ አባይ” የሚል ቅጽል እንደወጣላቸው የአዲስ ነገር ምንጮች ያስታውሳሉ። በወቅቱ በተነሳው ልዩነት ፓትርያርክ ጳውሎስን የተቃወሙ የሲኖዶሱ አባለት ተደብድበዋል፣ በመንግሥት የጸጥታ ኅይሎች ታፍነው ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸዋል።
ከመንግሥት ከሚያገኙት ፖለቲካዊና የጸጥታ እገዛ በቀር በሲኖዶሱም ይሁን በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዳጡ የገባቸው ፓትርያርክ ጳውሎስ ታማኞቻቸው የሆኑ በርካታ ጳጳሳትን በመሾም ሲኖዶሱን በድጋሚ የመቆጣጠር ዘመቻ ከጀመሩ መቆየታቸውን ተቺዎቻቸው ይናገራሉ።
ለጵጵስና የሚታጩ ሰዎች ‘ለፓትርያርኩ “የእጅ መንሻ” የማቅረባቸው አሳፋሪ ልማድ አዲስ ባይሆንም፣ የዘንድሮው ጨረታ መሰለ’ ብለዋል አንድ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ግለሰብ። አንድ ሌላ ታዛቢ “ይህ ክስተት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአሳሳቢ አስተዳደራዊና መንፋሳዊ መላሸቅ ውስጥ እንደምትገኝ የሚያስታውስ ነው። ችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ ካልተበጀለትም የአገር ሃብት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን የከፋ አደጋ ላይ ሊጥላት ይችላል” ብለዋል።
“ደጀ ሰላም” እንደዘገበው ከሆነ ለአሁኑ ጉባኤ በእጩነት የቀረቡት 30 የሚሆኑ ሰዎች ናቸው። ይሁንና የእጩዎቹን ስምም ይሁን ጉቦ የሰጡት እነማን እንደሆኑ ድረ ገጹ አልገለጸም። ድረ ገጹ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አንባቢዎች እንዳያዩት መደረጉን ገልጿል። ይህም በሲኖዶሱ ጉባኤ ወቅት የተደበቁ ዘገባዎችን እንዳያቀርብ ሆን ብሎ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።