ኢትዮጵያውያን በጃፓን እንደምን ይኖሩ ይኾን?
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋዜጠኛ አንተነህ ዘውዴ የአርብ ማርች 11 ቀን ውሎውን ሲያያዘው፤ እለቱን እንደማንኛውም ባተሌ አርብ “አስቀያሚ እና ሥራ የበዛበት” ከመኾን አልፎ የጃፓንን እጣ ፈንታ የሚፈታተን ይኾናል ብሎ አልገመተም ነበር። በእለቱ ወደ ነበረውን የሆስፒታል ቀጠሮ ከሔደ በኋላ ወደ ቤቱ አቀና። በሳሎኑ ሶፋ ላይ ጋደም አለ፤ እንቅልፍም አሸለበው። ከእንቅልፉ የቀሰቀሰው ነገር ቴሌቪዥኑ ከቁምሳጥኑ ላይ ወድቆ መሬት ሲያርፍ ያሰማው ከባድ ድምጽ ነበር። አንተነህ ነገሩን ቶኪዮን ደጋግሞ ከሚጎበኛት ዝቅተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አንዱ አድርጎ ለቅጽበት አስቦት ነበር። በቤቱ ውስጥ ያሉት ሌሎች እቃዎች በብዛት መውደቅ ሲጀምሩ ግን የተለየ ኀይል ያለው ርእደ መሬት መከሰቱን ተገነዘበ።
ከቤቱ መውጣት እንዳለበት ያሳሰበችው ደመ ነፍሱ ወዴት መሔድ እንዳለበት ግን የጠራ ምሪት ለመስጠት አልቻለችም። የሚንዘፈዘፈውን ሕንጻ ለቆ ለመውጣት ረጅም መንገድ ይቀረዋል። ከአራተኛ ፎቅ ወርዶ ሕንጻ ወደሌለበት እና ለጥ ወዳለው ሜዳ መድረስ ነበረበት። አንተነህ “እንደወረቀት ተርገበገበ” በሚለው የመኖሪያ ሕንጻ ውስጥ ግራ እና ቀኝ የሚያላጋውን የርእደ መሬቱን ኀይል ተቋቁሞ ቀጥ ብሎ ለመራመድ እጅግ አስቸጋሪ ኾኖበት ነበር። ሁለት ጊዜ ከወደቀ እና ከተነሳ በኋላ አራቱን ፎቅ ወርዶ ጨረሰ። “ከመርገብገቡ የተነሳ ወዴት አቅጣጫ እየሔድኩ እንደነበርኩ እንኳን አላወቅኩም ነበር ” የሚለው አንተነህ፤ ከየመሥሪያ ቤታቸው ወጥተው ከሚወድቁ ነገሮች ራሳቸውን ለማዳን ሜዳው ላይ በከቆሙ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ መቸገሩን ዐይቶ ሊረዳው እንደመጣለት ያስታውሳል። የዚህን ሰው ማንነት በእርግጠኝነት አሁን ለማስታወስ ባይችልም። “መልአክ ነው ብለው ይሻለኛል” የሚለው አንተነህ የዚህ ባለውለታው ርዳታ አሁንም በልቡ እንደታተመ ይናገራል። “እጄን ይዞ በብዛት ኢትዮጵያውያኑ ወደቆሙበት ሜዳ መሮጥ ጀመርን” ይላል፤ በሕይወቱ እጅግ ረጅም ኾና ያለፈችውን አንድ ደቂቃ ሲያስታውስ።
በሜዳው ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን በአካባቢው ካሉ የተለያዩ ፋብሪካዎች ከተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች የወጡ ነበሩ። ሜዳው ላይ እንደቆሙ በዙሪያቸው ያሉት ሕንጻዎች ዳግመኛ በተከሰተው መንቀጥቀጥ የደረሰባቸውን ከባድ መናጥ ሲመለከቱ የመሬት መንቀጥቀጡን ክብደት አስተዋሉ። “ወዲያውም ከመካከላችን አንዱ እጅለእጃችን እንያያዝ ብሎ ተናገረ” ይላል አንተነህ። እጅ ለእጅ የመያያዙም ምክንያት ከመሬት መንቀጥቀጡ የማለፍ ብልሃት አልነበረም። በኅብረት ኾኖ ፈጣሪን ለመጥራት እና “ነፍሳችንን ተቀበል” ብሎ ለመጸለይ እንጂ። ምን ያህል ሰቆቃ የሞላው እና እንዴት አስፈሪ ጊዜ እንደ ነበር አንተነህ ያስታውሳል።
የመሬት መንቀጥቀጡ በረድ ካለ በኋላ የነበረውም ትእይንት እንዲሁ የሚያስከፋ ነበር። ወላጆች ልጆቻቸውን ፍለጋ በፍርሃት ሲራወጡ ሕጻናት እየጮሁ ሲያለቅሱ የነበረውን ጭንቀት አስከፊ መኾን አንተነህ ይተርካል። ይህ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች የሚኖሩበት አካባቢ፤ “Ethiopian City” (የኢትዮጵያ ከተማ) በመባል ይታወቃል። በአካባቢውም ኢትዮጵያውያን በብዛት ተቀጥረው የሚሰሩባቸው ፋብሪካዎች ይገኛሉ። የነዋሪዎቹንም ፍርሃት ያባባሰው የእነኚሁ ከምግብ ዘይት ተረፈ ምርት የነዳጅ ዘይት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በብዛት መገኘት ነው። ሁሉም ነገር በአፍታ ውስጥ ጨለመ፤ የባቡር፣ አውቶቡስ እና የታክሲ አገልግሎቶች በይፋ ሥራ አቆሙ። መብራት እና ውኃ ተቋረጠ። ተራፊውን ሕዝብ ውስጡ ገብቶ ከሚያላቅሰው ፍርሃት እና ጭንቀት በተጨማሪ አጥንት የሚሰብር ብርድ ወደቀበት።
ይህ ሁሉ ከኾነ ከአንድ ሰዓት በኋላ ጭንቀቱን እንደገና ሰማይ ጥግ እንዲነካ የሚያደርግ ሌላ ማስታወቂያ ተነገረ። በርእደ መሬቱ በተቆጣው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ከፍታው 10 ሜትር የኾነ የሱናሚ ማእበል ተነስቶ ወደ ምድር እየገሰገሰ ነበር። ወዴት እንደሚኬድ ለአብዛኛው ሰው ግራ ሚያጋባ ነገር ነበር። ተመልሶ ወደሕንጻው እንዳይገባ የመሬት መንቀጥቀጡ ተመልሶ መምጣት ብዙዎችን የሚያስፈራ ነገር ነበር። ከዚያም በላይ 250 የሚኾኑ የኒኩሊየር ኀይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙባት የሚነገርላት ቶኪዮ የሞት ጥላ ያጠላባት እንደኾነች እንድትታሰብ አድርጓታል።
ለሌላዋ የቶኪዮ ከተማ ነዋሪ ለሳምራዊት ተፈሪ፤ እለቱ በጃፓናዊው አሠሪዋ የበለጠ እንድትገረም ያደረጋት እለት ነበር። እረፍት የሚባል ነገር የማያውቁት አሠሪዋ በርእደ መሬቱ ምክንያት የሚቋረጠው ሥራ ከነፍሳቸው ይልቅ ያሳሰባቸው ይመስላል። መንቀጥቀጡ ሲያርገፈግፋቸው ሥራቸውን እያቆሙ ነፍሳቸውን ለማዳን የሚሮጡትን እነሳምራዊትን የሚታዘቡት አለቃ ሳምራዊት እና ባልደረቦቿ ከሕንጻው ሮጠው ወጥተው ውጪ የሚቆሙበትን የሥራ ሰዓት እየተንቀጠቀጡ ይመዘግባሉ። አንዳንዴም ብቅ እያሉ “ውጪ ከመቆም ለምን ሥራችሁን አትሠሩም?” እያሉ ይጠይቃሉ። ጥቂት ጊዜ ይህን ካሉ በኋላ እንዲያውም “ስትወጡ እና ስትገቡ የሰዓት መቆጣጠሪያውን እያስመዘገባችሁ ውጡ” የሚል ትእዛዝ ይሰጣሉ። ፍርሃቱ ጀግና ያደረጋት ሳምራዊትም “ሥራው ሲቀር ይቀራል” ብላ ጥላቸው ወደቤተሰቦቿ አመራች።
ሳምራዊት ከሥራ ወጥታ እየተላቀሱ እና አንገታቸውን ደፍተው የሚጓዙትን መንገደኞች ተቀላቀለች። ወትሮ የምትጠቀምበት ባቡር ዛሬ ባለመኖሩ ሁለት ሰዓት ያህል የሚወስደውን መንገድ በእግሯ ለመጓዝ ተገደደች። “እንዲያውም እድለኛ ነኝ” ትላለች ሳምራዊት ራሷን 13 ሰዓት ተጉዞ ቤቱ ከገባው አማቿ ጋር እያወዳደረች። “ሰዉ ሁሉ እንዲሁ ነበር ሲጓዝ የነበረው፤ በብርድ እና በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመቀላቀል ረጅም መንገድ በእግር ለመጓዝ ተገዷል” ትላለች። ሳምራዊት እንደብዙ የቶኪዮ ነዋሪዎች ቤቷን ዘግታ ለመቀመጥ ተገዳለች። ምግብ ነክ ነገሮች በሱፐር ማርኬቶች ማግኘት እንደሚያስቸግር ትናገራለች ሳምራዊት። እንደማንኛውም የቶኪዮ ነዋሪም በየአካባቢው የሚገኙት የኒኩሊየር ኀይል ማመንጫ ጣቢያዎች በጣም ያስፈሯታል። ቶኪዮንም ለቃ ለመውጣት ከምን ጊዜውም ይልቅ አሁን ታስባለች። ጃፓናዊው አሠሪዋ አሁንም ለምን ከሥራ እንደምትቀር ይገርማቸዋል። እሳቸው የትራንስፖርት አገልግሎቱ መቋረጥ ሳያሳስባቸው አምስት እና ስድስት ሰዓት በእግር እየተጓዙ ይሰራሉና ነው።
አስከፊዎቹን ተፈጥሯዊ ቁጣዎች ያስተናገደችው ጃፓን 250 የሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ይኖሩባታል።
እስካሁን በአንዳቸውም ላይ ጉዳት ባይደርስም የተፈጥሮ አደጋዎቹን ተከትሎ ይከሰታል ተብሎ የሚታሰበውን ኒኩሊየር አደጋ እነኚህ ኢትዮጵያውያን እንዴት እንደሚያመልጡት አያውቁም። አንዳንዶቹም በአደገኞቹ ቦታዎች ላይ ይኖራሉ። እነዚህ ትዮጵያውያን እጆቻቸውን ወደፈጣሪያቸው ከማንሳት በቀር ለጊዜው ያደረጉት ነገርም የለም። እንደሌላው አገር ኤምባሲዎች የጃፓኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለዜጎቹ ያደረገው ማስጠንቀቂያም ኾነ ከአደጋ የሚያመልጡበት መንገድ አላዘጋጀም። ምክንያቱን አንተነህ ሲገልጽ “ዜጎቹን እንደ ጠላት ከሚቆጥር ኤምባሲ ምን ይገኛል ብለህ ነው?” የሚል መልስ የማይፈልግ ጥያቄ በማስቀደም ለመመለስ ይሞክራል። “ኤምባሲው እዚህ ያሉትን ስደተኞች እንደ ፖለቲካ ስደተኞች ለመቀበል አይፈልግም” ይላል። እንዲህ ያሉ ነገሮች ላይ ከመሥራት ይልቅም በስደተኞቹ የስደተኝነት ጥያቄ ላይ ማስተባበያ በመስጠት መሰናክል ለመፍጠር የሚያደርገው ሥራ እንደሚበልጥ ያስረዳል አንተነህ። ለአንተነህ ከኤምባሲው ይልቅ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው “አደይ አበባ የኢትዮጵያውያን ማኅበር” በመባል የሚታወቀው ማኅበር ነው።
እንደ አንተነህ ገለጻ ማኅበሩ የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው ሊያደርጉ ያሰቡትን ጥንቃቄ ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። በአደጋው ሰሞን ሕንጻዎች ይናዳሉ የሚል ፍርሃት ስለነበረ፤ ሁሉም ዜጎቻቸውን ከአደጋው ቦታ ለማራቅ ተዘጋጅተው በነበረበት ወቅት ማኅበሩም ራሱን አዘጋጅቶ ነበር። አውቶቡሶችን በማዘጋጀት በብዛት ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩበት አካባቢ ወደ ደቡባዊ ጃፓን ለማጓጓዝ ተዘጋጅቶ እየተጠባበቀ ነበር። አሁንም ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ዜጎቹን ለመታደግ ዝግጁ መኾኑን አሳውቋል። ብቻ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ “የኢትዮጵያውያን ከተማ” ተብላ ወደ ተሰየመችው “ዮት ሱኪ” ያቅና። ቀጠሮው እዛ ነው።