መርካቶ የዘይት ወረፋው አይሏል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(ኤፍሬም ካሳ)
በትናንትናው እለት ማልዶ የተነሳ ሰው ሲኒማ ራስ አካባቢ ረዣዥም ሰልፎችን በመመልከቱ ሊገረም ይችላል፡፡ ከመቼ ወዲህ ነው የማለዳ ቴአትር የተጀመረው ሲል ራሱን ሊጠይቅ ይዳዳው ይኾናል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ነጋዴዎች ዘይት ሲኒማ ራስ አካባቢ ከሚገኙ ማከፋፈያዎች ለመግዛት በሚያደርጉት ጥረት ነው የትያትር ቤት የሚመስሉት ረዣዥሞቹ ሰልፎች የሚፈጠሩት፡፡ ላለፉት ስድስት ቀናት ሰልፎቹ ከማለዳው አስራሁለት ሰአት ጀምሮ መፈጠር ይጀምራሉ፡፡ እስከ ቀትር ድረስ ከዘለቁ በኋላም ቢኾን አከፋፋዮቹ መጋዘኖቻቸውን ለምሳ ሲዘጉ ሰልፎቹ የመቀነስም ኾነ የመበተን አዝማሚያ አያሳዩም፡፡

መንግስት በተወሰኑ የፍጆታ እቃዎች ላይ ግሽበቱ የፈጠረውን የኑሮ ንረት ለመከላከል የዋጋ ተመን ካደረገ በኃላ አንዳንዶቹ እቃዎች ከገበያ እየተሰወሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ መሀል ስኳርና ዘይት ይገኙበታል፡፡ ላለፉት ሁለት ቀናት ‹‹ሀያት›› የተሰኘው ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይት ገበያ ላይ በመጥፋቱ ብቸኛው አከፋፋይ ‹‹ጌት አስ ኢንተርናሽናል›› ለመኾን ተገዷል፡፡ ሌላኛው አከፋፋይ ‹‹አልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር›› ብዙ ሰዎችን ስለመዘገብኩ እነርሱን ሳላስተናግድ ለጊዜው አገልግሎት አልሰጥም በማለት በዚህ ሳምንት ዘይት ማከፋፈል በማቆሙ ከፍተኛ ክፍተት እንደተፈጠረ ነው ነጋዴዎቹ የሚናገሩት፡፡

‹‹ጌት አስ ኢንተርናሽናል‹‹ በበኩሉ ማንኛውንም ዘይት ‹‹ቲን ነምበር›› ወይንም መለያ ቁጥር ለሌላቸው ነጋዴዎች እንዳይሸጥ በመንግስት ስለተነገረው ዘይቱን ከመሸጥ ጎን ለጎን ነጋዴዎቹ ንግድ ፍቃዳቸውንና የመለያ ቁጥሮቻቸውን በክላሰር እየያዙ እንዲያመጡ በመጠየቁ ብዙ ነጋዴዎች ዶክመንቶቻቸውን በእጆቻቸው አንጠልጥለው ወረፋ ለመጠባበቅ ተገደዋል፡፡

ዘይት ጥበቃ

ዛሬ ረፋዱ ላይ በአቶ ጌቱ ገለቴና በወንድማቸው አቶ አስራት የሚመራው ጌት-አስ ኢንተርናሽናል እንደ ‹‹አልሳም›› ሁሉ ከሳምንት በፊት የተመዘገቡ ደንበኞቼን ሳላስተናግድ አገልግሎት አልሰጥም በማለቱ ጥቂት ነጋዴዎች በብስጭት ሰልፉን ጥለው ሲሄዱ ብዙዎቹ ግን ሁኔታው ሊለወጥ ይችላል በሚል ሰልፋቸው ባለበት ቦታ ድንጋይ እያመጡ በመቀመጥ የሚኾነውን ሲጠባበቁ ነበር፡፡

ሃያት ሀያ ሊትር ዘይት ጌት አስ ኢንተርናሽናል በ417 ብር ለመሸጥ ነጋዴዎች ከሳምንት በፊት መመዝገብና ወረፋ መያዝ እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡
ባለፉት ቀናት እንደታየው አንዳንድ ነጋዴዎች ሰልፉ ሲረዝምባቸው በአካባቢው በጉልበት ስራ ከሚተዳደሩ ወጣቶች ሰልፍ በሀምሳ ብር እየገዙ ዘይት ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ ቸርቻሪዎቹ ነጋዴዎች ትርፋቸው የተወሰነና አነስተኛ ኾኖ እንዴት አንድ ሰልፍ በሀምሳ ብር ለመግዛት እንደሚደፍሩ ሲጠየቁ ምላሽ ለመስጠት አይደፍሩም፡፡ ኾኖም ነገሩን ለማጣራት ባደረግነው እንቅስቃሴ ዘይቱን በ417 ብር ነጋዴዎቹ በእጃቸው ካስገቡት በኋላ በጥቁር ገበያ እንደሚቸበችቡት ይነገራል፡፡
አልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአቶ ሳቢር አረጋ የሚተዳደር ሲሆን ጌት አስ ኢንተርናሽናል ደግሞ የጌቱ ኮሜርሻል ባለቤት በሆኑት በአቶ ጌቱ ገለቴና በወንድማቸው የሚተዳደር ድርጅት ነው፡፡ ሁለቱም የድርጅቱ ባለቤቶች ለገዢው መንግስት ልዩ ልዩ እርዳታዎችን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡

የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የቆርቆሮ ዋጋዎች በቅርብ ቀናት ጭማሪ ሊያሳዩ እንደሚችሉ በመርካቶ የሚገኙ አከፋፋይ ነጋዴዎች ግምታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያትም ፋብሪካዎች የመንግስት ተመን አያዋጣንም በማለት መንግስት እርምጃ እንዳይወስድባቸው ብቻ በመስጋት ጥቂት ምርቶችን እየቆነጣጠበ መሸጥ በመጀመራቸው ነው፡፡ ‹‹በምንፈልገው መልኩ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ሊሸጡልን አልቻሉም፤ በመኾኑም የዋጋ ንረት እና እጥረት የማይቀሩ ነገሮች ናቸው፡፡›› ይላሉ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች፡፡