[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ከቤታቸው ሊወስዳቸው ሲመጣ ግቢው ውስጥ ድንኳን ተጥሎ ይመለከታል]

  • ሰላም አይደለም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • በጣም ሰላም ነው፡፡
  • የምን ለቅሶ ነው?
  • ምንድን ነው የምታወራው?
  • ማን ሞቶ ነው ድንኳን የተጣለው?
  • ምን ዓይነት ሟርተኛ ነህ?
  • የምን ሐዘን ነው ብዬ ነዋ?
  • ኧረ እኔ ቤት ፌሽታ ነው እንጂ ሐዘን የለም፡፡
  • አገር ሐዘን ላይ ሆኖ የምን ፌሽታ ነው?
  • ስማ እኔ ጋ ሁሌም ፌሽታ ነው፡፡
  • አገር እንደዚህ እየተበጠበጠ?
  • የእኔ ፀረ ሰላም፣ አገሪቷ ራሷ ሰላም ናት አልኩህ እኮ፡፡
  • በአገሪቷ የሉም እንዴ?
  • የእኔ ቤት አገሪቷ ውስጥ አይደል እንዴ ያለው?
  • አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ታዲያ የምን ፌሽታ ነው ቤትዎ ያለው?
  • የፆም መያዣ ነዋ፡፡
  • ምን?
  • ስማ በውስኪ ተራጨን፡፡
  • እየቀለዱ ነው?
  • አትሰማም እንዴ በውስኪ ታጠብን አልኩህ እኮ?
  • እኔ የምታጠብበት ውኃ አጥቼ በዝናብ ውኃ እየታጠብኩ ነው፤ እርስዎ…
  • ምን ታደርገዋለህ? ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ሲባል አልሰማህም?
  • እርሱስ ልክ ብለዋል፤ የታደሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ስማ ድል ያለ ድግስ ደግሼ ነበር፡፡
  • እስቲ ትንሽ ይንገሩኝ?
  • ትልቅ የሐረር ሠንጋ ነው ያረድኩት፡፡
  • እሺ፡፡
  • ከዛ በቃ በብላክ ሌብል ነው የተጀመረው፡፡
  • ብላክ ሌብል ሲሉ ጥቁር ፊሊተሩን ማለትዎ ነው?
  • ምን ይላል ይኼ ውስኪ ነው እንጂ?
  • እ…የሀብታሞችን ፊሊተር ነው የሚሉኝ?
  • ከዛ በቃ ብሉ ሌብልና ጐልድ ሌብል ነበር ሲጠጣ የነበረው፡፡
  • ጐልድ ሌብል?
  • አዎን፡፡
  • ወርቅም ትጠጣላችሁ?
  • ስማ ከተመቸህማ አልማዝም ልትጠጣ ትችላለህ፡፡
  • እሺ፡፡
  • ከዛ ደግሞ መሀል ላይ አንድ ሁለት ሙክት ታረደ፡፡
  • ይኖሩታል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ስማ ኢንቨስተር በል ባለሥልጣን ቤቴ ሲጋፉ ነበር፡፡
  • እንዴ እርስዎ ቤት ነበራ ታዲያ ሰላማዊ ሠልፉ የነበረው?
  • የምን ሰላማዊ ሠልፍ ነው?
  • ይቅርታ እርስዎ መቼ እንደዚህ ዓይነት ነገር ይገባዎታል?
  • እኔ ልማት ብቻ ነው የሚገባኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር እንዴት ግን አልጠሩኝም?
  • የት ነው የምጠራህ?
  • እንደዚህ ዓይነት ድግስ ሲደግሱ ነዋ፡፡
  • ማንን?
  • እኔን ነዋ፡፡
  • በምን አስታውሼህ?
  • አያስታውሱኝም?
  • ኧረ በፍጹም፡፡
  • ለነገሩ በእንትንስ ተረስቼ የለ?
  • በማን?
  • በመንግሥት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር በከተማችን ውስጥ በቅርቡ በተከፈተ ሆቴል ምሳ እየበሉ ነው]

  • እየበሉ ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰላጣው ይቅርብኝ ብዬ ነው፡፡
  • ለምን?
  • ያው አተት ምናምን ብዬ ነው፡፡
  • መተት ማለትዎት ነው?
  • የምን መተት ነው?
  • ማለቴ መደበኛ ተቅማጥና ትውከት ነዋ፡፡
  • ቀልደኛ ሆነሃል ልበል?
  • ክቡር ሚኒስትር በዚህ ዓመት በጣም ቀናዎት አይደል?
  • እኔ ሁሌም እንደቀናኝ ነው፡፡
  • አይ ክቡር ሚኒስትር፣ እርስዎ ግን የሚገርም የቢዝነስ ጭንቅላት ነው ያለዎት፡፡
  • ለምን ይምስልሃል እንደዚህ የከበርኩት?
  • ሁሉም ባንኮች እኮ የሚገርም ትርፍ ነው የተንበሸበሹት?
  • ስማ ያኔ ሼር ግዛ ብዬ ነግሬህ ነበር እኮ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎንማ ምክር ሰምቼ ቢሆን ኖሮ፣ እንደ እርስዎ አሁን ከአምስትና ከስድስት ባንኮች ዲቪደንዴን በተቀበልኩ ነበር?
  • ምክሬን ስማ የምልህ ለዚህ ነው፡፡
  • አሁን ነው የገባኝ፡፡
  • ሁሉንም እንቁላሎችህን በአንድ ቅርጫት አታስቀምጥ ሲባል አልሰማህም?
  • ኧረ ሰምቻለሁ፡፡
  • ስለዚህ ኤክስፖርቱ ሲቀዘቅዝ፣ ባንኩ ይደግፍሃል፡፡
  • ብልህ እኮ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሞኝ መሆንማ አያዋጣም፡፡
  • ጠፍተዋል ግን ክቡር ሚኒስትር?
  • ዕድገቱ ነዋ፡፡
  • ውርደቱ ማለትዎ ነው?
  • የምን ውርደት ነው? የአገር ዕድገት ነው ያጠፋን፡፡
  • ኧረ ብዙ ውርደት ሊኖር ይችላል፡፡
  • የምን ውርደት?
  • ለምሳሌ ኦሊምፒክ ተጀምሯል፡፡
  • ኦሊምፒክ ተጀምሯል እንዴ?
  • እንዴ መጀመሩን አልሰሙም?
  • ስማ ስንት ነገር እያለ እሱን ልከታተል?
  • ለነገሩ ሥራ ይበዛብዎታል፡፡
  • በነገራችን ላይ አንድ ነገር በራልኝ፡፡
  • ምን ክቡር ሚኒስትር?
  • መጋዘኖች አሉ አይደል?
  • አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ታዲያ ማተሚያ ማሽኖች ለምን አናስመጣም?
  • የምን ማተሚያ ማሽን?
  • የቲሸርት ማተሚያ ነዋ፡፡
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር እያወቁት?
  • ምኑን?
  • ኤልሲ እኮ ችግር ነው፡፡
  • እሱንማ በእኔ ጣለው፡፡
  • ለነገሩ እርስዎ ምን ተስንዎት?
  • ስሜ ራሱ ምንተስኖት ነበር መባል ያለበት፡፡
  • ለነገሩ ቲሸርት ማተሚያ ማሽን ምን ያደርግልናል?
  • ኦሊምፒክ ተጀምሯል አልከኝ እኮ?
  • እሱማ ተጀምሯል፡፡
  • ስለዚህ ወርቅ የሚያመጣውን አትሌት ፎቶ በቲሸርት አትመን መቸብቸብ ነዋ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ወርቅ ባናመጣስ?
  • ብር ያመጣውን ፎቶ እንሸጣለና፡፡
  • እንዴ ብር ባናመጣስ?
  • ነሀስ ማምጣታችን አይቀርማ፡፡
  • እሱንስ ባናመጣ?
  • ለእንትን ብለን እንሸጣለን፡፡
  • ለምን?
  • ለተሳትፎ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]

  • ያ ሰውዬ መጥቷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የቱ ሰውዬ?
  • የኮርፖሬሽን ኃላፊው፡፡
  • የምን ኮርፖሬሽን?
  • የኪራይ ሰብሳቢ ኮርፖሬሽን ምናምን የሚለው፡፡
  • እ… የፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ኮርፖሬሽን ኃላፊው?
  • አዎን፡፡
  • አስገቢው፡፡

[የፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ኮርፖሬሽን ኃላፊው ቢሯቸው ገባ]

  • በቃኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • መቼ ብላ አልኩህ?
  • በቃኝ፣ በቃኝ አልኩኝ፡፡
  • መቼ ብላ ተባልክ?
  • እኮ አልበላም ነው የምለው፡፡
  • መጀመሪያስ ማን ብላ አለህ?
  • የሚበሉትም ግን ማቆም አለባቸው፡፡
  • ምን?
  • ሁሉም እኮ ነው የሚበላው፡፡
  • ምንድን ነው የምታወራው?
  • ከላይ እስከ ታች ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡
  • እኔን ጨምሮ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን?
  • ሁሉም እዚህ መሥሪያ ቤት ያለ ሰው ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡
  • እና ምን ልታደርግ ነው?
  • በቃ ለበላይ ኃላፊዎች አጋልጣለሁ፡፡
  • ከዛስ?
  • የሚሆነውን ማየት ነዋ፡፡
  • ስማ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡
  • እንዴት?
  • ምንም አታመጣም፡፡
  • ካላመጣሁማ በቃ እለቃለሁ፡፡
  • አንዴ ከገባህማ መልቀቅም በቀላሉ አይቻልም፡፡
  • በቃኝ አልኩኝ አልሠራማ፡፡
  • ቀላል አይደለም አልኩህ እኮ፡፡
  • ካልሆነ ኮርፖሬሽኑ ይፍረስ?
  • እንዲያውም ይኼ ኮርፖሬሽን ፈርሶ ሌላ ኤጀንሲ ማቋቋም አለብኝ፡፡
  • ምን የሚሉት?
  • ሙስናን የሚያሳልጥ ኤጀንሲ!

[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ደወለችላቸው]

  • ወይኔ ጋሼ፤ ወይኔ ጋሼ፡፡
  • ምን ሆነሻል?
  • ወሰዱት እኮ?
  • ማንን ነው የወሰዱት?
  • ልጄን ወሰዱት ጋሼ፡፡
  • ማን ነው የወሰደው?
  • ወሰዱት ጋሼ፣ ወሰዱት፡፡
  • በስኮላርሽፕ ነው የወሰዱት?
  • ወሰዱት ልጄን ወሰዱት፡፡
  • በፌሎሺፕ ነው የወሰዱት?
  • ኧረ ፌዴራሎች ነው የወሰዱት፡፡
  • ፀረ ሰላም ነው እንዴ ልጅሽ?
  • ኧረ ሰላማዊ ነው፡፡
  • ታዲያ እንዴት ወሰዱት?
  • ወሬ ሊያይ ወጥቶ ነው የወሰዱት፡፡
  • ሥራ እንጂ ወሬ ምን ያደርጋል?
  • ሥራ የለውማ ጋሼ፡፡
  • ለምን የለውም?
  • ምን ወጣቱ ሁሉ ተመርቆ ቁጭ ብሏል አይደል እንዴ?
  • ታዲያ የአንቺ ልጅ እንዴት ሥራ ያጣል?
  • ሥራ የለማ፡፡
  • እኔ ሥራ እሰጠዋለኋ፡፡
  • ለማንኛውም አስረውታል፡፡
  • ምን አድርጐ?
  • ከሌሎቹ ጋር ነው ቀላቅለው የወሰዱት፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ፖሊስ ጋ ደወሉ]

  • ማን ልበል?
  • ማን ልበል እንዴት ትለኛለህ?
  • ማን ልበል ጌታዬ?
  • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር ምን ልርዳዎት?
  • ምን እየሠራችሁ ነው?
  • ሥራችንን ነዋ፡፡
  • ሰው ዝም ብላችሁ ማፈስ ጀመራችሁ?
  • የበጠበጡትን ነው ያሰርነው፡፡
  • ሰላማዊ የእኔ ሰዎች ታስረዋል፡፡
  • ሰላማዊ ከሆኑ ብጥብጡ ውስጥ ምን ያደርጋሉ?
  • ሰላማዊውንና ፀረ ሰላሙን ማጣራት አለባችሁ፡፡
  • እሱን ማጣራት ከባድ ሆኗል፡፡
  • እንዴት?
  • በመንግሥት ውስጥ ራሱ ሰላማዊውን ከፀረ ሰላሙ መለየት ከባድ ሆኗል፡፡
  • አሁን በአስቸኳይ ልቀቁት፡፡
  • ማንን?
  • የእኔን ሰው፡፡
  • እሱማ አይቻልም፡፡
  • ለምን?
  • ማጣራት አለብን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ ፖሊሱ መልሶ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ደወለ]

  • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማን ልበል?
  • አሁን ተደዋውለን ነበር፡፡
  • እኮ ማን ልበል?
  • ፖሊሱ ነኝ፡፡
  • ይኼ እኮ የግል ስልኬ ነው፡፡
  • ቢሆንስ ታዲያ?
  • እንዴት እዚህ ላይ ትደውላለህ?
  • ሕዝብን ለማገልገል የተሾሙ መሰለኝ፡፡
  • በጣም ተናንቀናል፡፡
  • ቆየን እኮ፡፡
  • ምን ካልን?
  • ከተናናቅን!