በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ለኦፔራ አቀንቃኟ ሃና ግርማ የሰጣት ዕድል በአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ክፍል እክል ገጠመው
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ለኦፔራ አቀንቃኟ ሃና ግርማ የሰጣት ዕድል በአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ክፍል እክል ገጠመው
‹‹አሜሪካዊ የቪዛ ክፍል ሠራተኛ ሞራላዊ ጉዳት አድርሶባታል›› ቴዎድሮስ መኮንን (ቴዲ ማክ)
ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የኦፔራ ሙዚቃን በማቀንቀን ትልቅ ዕውቅና ያገኘችው የ16 ዓመት ታዳጊዋ ሃና ግርማ፣ በዓለም መድረክም ተቀባይነት እያገኘች በመምጣቷ ከሰሞኑ ታዋቂው የበርክሌ ዩኒቨርሲቲ የሰጣትን የሥልጠና ዕድል ሊያበላሽ የሚችል እክል በአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ክፍል እንደገጠማት ተሰማ፡፡
የታዳጊዋ የኦፔራ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሃና ሕጋዊ ሞግዚት አርቲስት ቴዎድሮስ መኮንን (ቴዲ ማክ) ለሪፖርተር እንዳስታወቀው፣ ታዳጊዋ ወደ አሜሪካ የሚወስዳትን ዕድል ያገኘችው ቦስተን በሚገኘው ታዋቂው የበርክሌ ዩኒቨርሲቲ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በመሆኑም የትምህርት ቤቱን ግብዣ በመቀበል ቪዛ ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ቢያቀኑም፣ ‹‹የኤምባሲው ቪዛ ክፍል ባልደረባ የሆነ አሜሪካዊ ሥነ ምግባር በጎደለው ሁኔታ ታዳጊዋን ድምፃዊ አጉላልቷል፣ ሞራሏን በሚነካ መንገድ አስተናግዷታል፤›› ሲል ቅሬታውን የገለጸው ቴዲማክ፣ ጉዳዩን ለአምባሳደሯና ለወኪላቸው፣ እንዲሁም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ማሳወቁን አስታውቋል፡፡
ቴዲ ማክ ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በጻፈው ቅሬታ፣ ‹‹እርስዎ የሚወዷት፣ ያሳደግኳት የኦፔራ ሙዚቀኛዋ ታዳጊ ሃና ግርማ የቦስተኑ በርክሌይ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለአምስት ሳምንታት የሰጣትን ሙሉ ስኮላርሺፕ ለመጠቀም ቪዛ ለማግኘት አሜሪካ ኤምባሲ አብሬያት ብሄድም፣ በኤምባሲው የቪዛ ክፍል ሠራተኛ ያልተገቡ ጥያቄዎች ሳቢያ ተጎድታ እያለቀሰች ለመሄድ ተገዳለች፤›› ብሏል፡፡ በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን እንዲመለከቱት በማለት ጠይቋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ በዋትስአፕ በላኩለት መልዕክት በተፈጠረው ነገር ማዘናቸው እንደገለጹት የጠቆመው ቴዲ ማክ፣ ሥርዓት የጎለደው የቪዛ ክፍል ባልደረባ በታዳጊዋ ሥነ ልቦና ላይ ያደረሰው ጉዳት በምን ዓይነት ተቀባይነት የሌለውና ኃላፊነቱን በአግባቡ ከማይወጣ ሰው የተሰነዘረ ድርጊት በመሆኑ ኤምባሲው ባልደረቦቹን ሊያርም እንደሚገባው ጠይቋል፡፡ እንዲህ ባሉ ሠራተኞች በታዳጊዋ ላይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ቪዛ አመልካቾች ላይ የሚደርስ ያልተገባና መስመሩን የለቀቀ ተፅዕኖ የኤምባሲውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነው ያለው ቴዲ ማክ፣ ሃና የደረሰባትን የሞራል ጉዳትና የሥነ ልቦና ጫና በቀላሉ የሚመለከተው አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ቴዲ ማክ ያቀረበውን ቅሬታ በማስመልከት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበለት ሲሆን፣ ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ የሚሰጡ ኃላፊዎች ዘንድ እንዲደርስ መደረጉንና ይፋዊ ምላሽ እንዲሰጡበት እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡ በቪዛ ክፍሉ ሠራተኞች በርካታ አመልካቾች መመናጨቅና ሌሎች ተገቢነት የጎደለው ተግባር እንደሚፈም ሲገለጽ፣ ከዚህ ቀደም ከአመልካቾች ጉቦ ሲቀበሉ የነበሩ የቪዛ ክፍል ባልደረባ መባረራቸው አይዘነጋም፡፡
የበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የኦፔራ አቀንቃኟ ሃና ግርማን ተሰጥኦ በመመልከት፣ በበጋው ወራት ከሚሰጣቸው በርካታ ፕሮግራሞች መካከል ለአምስት ሳምንታት የሚቆየውን ትምህርት ሙሉ ወጪዋን በመሸፈን እንድትማር መመረጧን የሚገልጸውን የኢሜይል መልዕክት፣ ቴዲ ማክ በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምበሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ፣ ጂል ፓርከር ለተባሉ የአምባሳደሯ ረዳት፣ እንዲሁም ለዶ/ር ቴድሮስ አያይዟል፡፡