[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
– ወዴት ልትሄድ ነው?
– ወደ ሥራ ነዋ፡፡
– ሥራ ትሠራለህ እንዴ?
– ምን ዓይነት ጥያቄ ነው?
– ትክክለኛ ጥያቄ ነዋ፡፡
– ምን እያልሽ ነው?
– ስለተጠራጠርኩ ነው፡፡
– ምኑን ነው የምትጠራጠሪው?
– ሥራ መሥራትህን?
– ሴትዮ ምን እያልሽ ነው?
– ግራ ስለገባኝ ነዋ፡፡
– ምኑ ነው ግራ የገባሽ?
– ለመሆኑ በአገር አለህ?
– ደሞ የት እንድሄድልሽ ፈልገሽ ነው?
– ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሠራ የት ነበርክ?
– መንግሥት ግልበጣ ተካሄደ እንዴ?
– መንግሥት ባይገለበጥም ሌላ ነገር ተገልብጧል፡፡
– የጭነት መኪኖቻችን ተገለበጡ እንዴ?
– ቢዝነሳችን እየተገለበጠ ነው፡፡
– የትኛው ቢዝነሳችን?
– ዋናው ቢዝነሳችን፡፡
– በምን ምክንያት?
– ቫይበር እኮ ቆሟል፡፡
– እስካሁን?
– አገር ውስጥ አለህ ወይ የምለው ለዚህ ነው?
– ፈተናው አላለቀም እንዴ?
– የትኛው ፈተና?
– ማትሪኩ ነዋ፡፡
– እሱማ አልቋል፡፡
– ታዲያ ለምን አልተለቀቀም?
– ምናልባት ሌላ ፈተና ይኖር ይሆናላ፡፡
– ምን ዓይነት ፈተና?
– የሚኒስትሮች ፈተና፡፡
– ምናለ ቀልዱን ብተይው?
– ወድጄ አይደለም የምቀልደው ባክህ?
– ምን እየሆኑ ነው ግን?
– እነማን?
– ቴሌዎች፡፡
– ከባለቤቱ ያወቀ ምንድን ነው አሉ?
– ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
– መንግሥት ነኝ ባዩ አንተ አይደለህም እንዴ?
– በጣም ተናንቀናል ማለት ነው?
– ከማን ጋር?
– ቫይቨርን ከዘጉት ሰዎች ጋር፡፡
– መናናቅ ብቻ?
– ጦማችንን ሊያሳድሩን ነው እንዴ?
– አየህ መንግሥት ከኋላ ቀርነት ስላልተላቀቀ በቫይቨር ምናምን ቢዝነስ የሚሠራ አይመስለውም፡፡
– የግንዛቤ ማስጨበጫ መሥራት አለብኝ፡፡
– ምን ዓይነት ግንዛቤ ማስጨበጫ?
– ቫይቨር ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ነዋ፡፡
– ይገባቸዋል ብለህ ነው?
– እንዲገባቸው አደርጋለሁ፡፡
– ያለበለዚያ ችግር ውስጥ ነን፡፡
– የምን ችግር?
– ቢዝናችን ይመታል፡፡
– በምን?
– በኪሳራ፡፡
– መንግሥት እኮ አይታመንም፤ ሊያደርገው ይችላል፡፡
– ምን ሊያደርግ ይችላል?
– ሊያረሳሳን ይችላል!
[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ቴሌ ደወሉ]
– ሄሎ!
– ማን ልበል?
– እኔ ጠፋሁ፡፡
– ኧረ አይጥፉ፡፡
– ምንድን ነው ያልከው?
– ማን ልበል?
– ዛሬም ማን ልበል ትላለህ?
– ይቅርታ ማን ልበል?
– ስልኬን ለምን አትመዘግበውም?
– ማን ልበል?
– በጣም ተናንቀናል፡፡
– ይቅርታ ልዘጋው ነው፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
– ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ሁልጊዜ ስደውል ለምንድን ነው ማን ልበል የምትለኝ?
– ከዚህ በፊት ደውለው ነበር?
– ባለፈው ደውዬልህ አልነበር እንዴ?
– ክቡር ሚኒስትር ብዙ ኦፕሬተር እኮ ነው ያለው!
– እና እኔ ራሴን ለሁላችሁም ማስተዋወቅ አለብኝ?
– ታዲያ ምን ይሻላል?
– ለምን ለራሴ የግሌ መስመር አትሰጡኝም?
– ልክ እንደ 994 ቁጥር ማለትዎ ነው?
– አዎና፤ 995ትን ለምን አትሰጡኝም?
– እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
– ቀልድ መሆኑን አሳይሃለሁ፡፡
– ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለመሆኑ ቫይበርን ለምን ዘጋችሁት?
– ውሳኔው የእናንተ አይደል እንዴ?
– እኔ ስወስን አይተሃል?
– ያው አለቆቻችን ናቸው እኮ የወሰኑት፡፡
– እኮ እኛ እንዴት ሥራ እንሥራ?
– እኔ’ጃ፡፡
– ለነገሩ የማደርገውን እኔ አውቃለሁ፡፡
– ምን ሊያደርጉ ነው?
– ድርጅታችሁን . . .
– ምን?
– አዘጋዋለሁ!
[ክቡር ሚኒስትሩን አንድ ባለሀብት ወዳጃቸው ምሳ ይጋብዛቸዋል]
– ዛሬ እንዴት ትዝ አልኩህ ባክህ?
– ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ ሁሌም ነው ትዝ የሚሉኝ፡፡
– ፎጋሪ ነገር ነህ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ተሳካልኝ እኮ?
– ምኑ?
– በእርስዎ በኩል የሄድኩበትን መሬት አገኘሁ፡፡
– እንኳን ደስ አለህ፡፡
– ለዛም ነው ዛሬ ምሳ ልጋብዝዎት የፈለኩት፡፡
– ኪራይ ሰበሳቢ ሆነሃል ልበል?
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– አዲስ አበባን የሚያክል መሬት አስጥቼህ በምሳ ልትገላገለኝ?
– ኧረ እንደዛ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለዛውም በሽሮ?
– አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ታዲያ እንዴት ነው?
– እዚሁ ቤት ያለውን ሰው ይመለከቱታል?
– ይኼ ሁሉ ሰው ምንድን ነው?
– እዛ ጋ ያለው በከተማችን ዋነኛ ብረት አስመጪ ነው፡፡
– እሺ፡፡
– ከጎናችን ካለው ጠረጴዛ ቀጥሎ ያለው ላይ የተቀመጠው ደግሞ የከተማችን ዋነኛ ዕቃ አስመጪ ነው፡፡
– እሺ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር በቃ አሁን ሽሮ ቤት ፋሽን ሆኗል፡፡
– ኧረ ባክህ?
– በርካታ ቢዝነስ እንደዚህ ዓይነት ሽሮ ቤት ነው የሚሠራው፡፡
– እና ምን እያልከኝ ነው?
– እኔም ላደረጉልኝ ውለታ አሪፍ ሽሮ ቤት ልከፍትልዎት አስቤያለሁ፡፡
– እውነት?
– አዎ፣ ከዛ የከተማችን ወሳኝ ሰዎች በእጅዎ ያስገቧቸዋል፡፡
– በጣም ደስ የሚል ሐሳብ ነው፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ገቢውም ቀላል አይደለም፡፡
– አሁን ከሽሮ ምን ይገኛል?
– እንዴ አንድ ሽሮ መቶ ብር ነው፡፡
– ለምን ሲባል?
– የክላስ ጉዳይ ነዋ፡፡
– የምን ክላስ ነው?
– አዎን፣ በቃ ልክ እንደ iphone የሽሮ ቤት ክላስ አለው፡፡
– እና የምትከፍትልኝ ሽሮ ቤት ምንድን ነው የሚባለው?
– iሽሮ ቤት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ስልክ ደወሉ]
– ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እንዴት ነህ ባክህ?
– እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
– ለመሆኑ አንተ ደስተኛ ነህ?
– በምኑ ክቡር ሚኒስትር?
– በሥራህ?
– ሕዝብን እንደማገልገል የሚያስደስት ምን ነገር አለ?
– እኔ የምልህ በገቢህ ነው?
– ከእሱ በላይ ሕዝብ የሚያገኘው እርካታ ነው ለእኔ ገንዘቤ፡፡
– አየህ የአንተ ችግርህ ይኼ ነው፡፡
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– መውድቂያህን ማሰብ አለብህ፡፡
– ምን ማለት ነው?
– እዚህ ወንበር ላይ ለዘለዓለም የምትቀመጥ መሰለህ እንዴ?
– አልገባኝም?
– ስማ እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ አወዳደቄን አሳምርልኝ እያልኩ እፀልያለሁ፡፡
– ፀሎትዎ ተመለሰልዎት ታዲያ?
– እህሳ፡፡
– በምን?
– ይኸው ሪል ስቴቱ ብትል፣ ፋብሪካው ብትል፣ ንግዱ ብትል ያልገባሁበት ዘርፍ ምን አለ?
– ምን?
– ከዚህ በላይ አወዳደቅህ እንዴት ሊያምር ይችላል?
– ክቡር ሚኒስትር እውነትም አብዝተውታል፡፡
– ስማ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ነው ተረቱ፡፡
– ምን እያሉኝ ነው?
– አንድ ቀለል ያለች ቢዝነስ አምጥቼልሃለሁ፡፡
– የምን ቢነዝነስ?
– የሽሮ ቤት ቢዝነስ፡፡
– እና ምን ላድርግ?
– ሥራውን አንድ ላይ እንጀምረው፡፡
– የሽሮውን?
– አዎን፡፡
– እና ምን እናድርግ?
– እንደራጅ፡፡
– በምን?
– በአነስተኛና ጥቃቅን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሽሮ ቤቷ ተከፈተችላቸው፡፡ የምረቃው ቀን ከአንድ ነጋዴ ጋር እያወሩ ነው]
– እንዴ ክቡር ሚኒስትር እዚህ ምን ያደርጋሉ?
– አንተ ራስህ ምን ታደርጋለህ?
– እኔማ ልመርቅ ነው የመጣሁት፡፡
– እኔ ደግሞ ላስመርቅ ነው የመጣሁት፡፡
– በነገራችን ላይ ከተማችን ላይ አሁን የሽሮ ቢዝነስ ደርቷል፡፡
– እኔም እሱን አውቄ አይደል እንዴ የገባሁበት?
– የእርስዎ ነው እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
– እህሳ፡፡
– አይ ክቡር ሚኒስትር በቃ አሪፍ አሪፍ ነገር አያመልጥዎትም አይደል?
– አካሄዴ የተጠና ነው፡፡
– ቢዝነስ እኮ እዚሁ ነው የሚሠራው፡፡
– በሚገባ አውቃለሁ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ቲማቲሟን መብላት ግን ፈራሁ፡፡
– ለምን?
– ያው ከተማችን ውስጥ ወረርሽኝ ገብቷል አይደል?
– ችግር የለውም ይኼ ከውጭ ነው የመጣው፡፡
– ያዋጣዎታል?
– በደረጃ ከፋፍለነዋል፡፡
– እንዴት?
– ለደረጃ ‹ሀ› ግብር ከፋይ ከእስራኤል የመጣ ቲማቲም በኦሊቭ ኦይል ነው የሚሠራው፡፡
– እሺ፡፡
– ለደረጃ ‹ለ› ግብር ከፋይ ደግሞ በአገር ውስጥ ቲማቲም በሰን ፍላወር ኦይል ነው የሚሠራው፡፡
– ለደረጃ ‹ሐ› ግብር ከፋይስ?
– ለእነሱ ደግሞ ባደረ ቲማቲም በጭቃው ዘይት ነዋ፡፡
– በደንብ የክላስ ልዩነት የሚታይበት የሽሮ ቤት ነዋ፡፡
– ለዛ እኮ ነው ስሙን iሽሮ ያልኩት፡፡
– እኔ ግን ስሙ ቢቀየር ደስ ይለኛል፡፡
– ምን ይባል?
– ሚኒስትሩ ሽሮ!
በሙስና የሰከሩት የቀዥቃዣው ሚኒስትር ውሎ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።