አንጋፋው አርቲስት አባተ መኩሪያ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የኢትዮጵያ የትያትር አባት አባተ መኩሪያ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

 ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ የትያትር ጥበብ ውስጥ ያገለገለው አርቲስት አባት አባተ መኩሪያ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

አርቲስት አባተ መኩሪያ ከአርባ አመታት በላይ በኢትዮጵያ የትያትር ጥበብ ውስጥ የራሱን ተፅእኖ ማሳረፍ የቻለና “የኢትዮጵያ የትያትር አባት” የሚል ስያሜን ያተረፈ ተወዳጅና አንጋፋ ባለሙያ ነበር።

አርቲስት አባተ ከወራት በፊት ባጋጠመው የፕሮስቴት ካንሰር ሳቢያ ቀዶ ጥገና ህክምና አድርጎ ነበር።

የተሻለ ህክምና ለማግኘትም ወደ ግብጽ በመሄድ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ፥ ከአንድ ወር በፊት ወደ ሃገር ቤት ተመልሷል።

ይሁንና ካጋጠመው ህመም ማገገም ባለመቻሉ፥ ህክምናውን በሃገር ውስጥ በአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ሲከታተል ቆይቷል።

ትናንት ማምሻውንም በ72 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

አርቲስት አባተ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።

የአርቲስት አባተ መኩሪያ ውልደትና የትምህርት ሁኔታ

አርቲስት አባተ መኩሪያ ህዳር 10 ቀን 19 36 ዓ.ም በአዲስ አበባ አቧሬ አካባቢ ከአባቱ አቶ ስለሺ ማንደፍሮ እና ከእናቱ ወይዘሮ ውብነሽ መኩሪያ ተወለደ።

ከስድስት ወሩ ጀምሮም አያቱ አቶ መኩሪያ ዳመና ወንድ ልጅ ስለሌላቸው፥ ከወላጆቹ በመውሰድ አሳድግውታል።

የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በቀድሞው ቀ.ኃ.ስ በአሁኑ ኮከብ ጽብሃ ተከታትሏል።

የከፍተኛ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝኛ የትምህርት ክፍል በመከታተል የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ከዚያም በተለያዩ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ትምህርት ተቋማት መካከለኛ እና አጫጭር ትምህርት እና ስልጠናዎችን ወስዷል።

ዳይሬክቲንግ፣ አክቲንግ፣ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን፣ ፕሮዳክሽን፣ የአዘጋጅነት ክህሎት እና የህጻናት ትያትር ጋር የተያያዙ ትምህርቶች አርቲስት አባተ ካገኛቸው ትምህርቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በአውሮፓ ታላላቅ የኪነ ጥበብ መናገሻዎች በሆኑት ፓሪስ፣ ለንደን፣ ኮሎኝ፣ ሞስኮ፣ በቀድሞዎቹ ዩጎዝላቪያና ቼኮዝሎቫኪያን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች እና በአሜሪካ ታላላቅ ተቋማትም ትምህርቶችን ተከታትሏል።

ከዚህ ባለፈም በኪነ ጥበቡ አለም በተዘጋጁ አለም አቀፍ አውደ ጥናቶች እና መድረኮች ላይ በመሳተፍም የሙያ ክህሎቱን ማዳበርም ችሏል።

የአርቲስት አባተ መኩሪያ ስራዎች፦

1- ሀሁ በስድት ወር – በ19 66 ዓ.ም

2- አቦጊዳ ቀይሶ በ19 71 ዓ.ም

3- መልዕክተ ወዛደር በ19 71 ዓ.ም

4- የመንታ እናት በ1971 ዓ.ም

5- መቅድም በ19 72 ዓ.ም

6- ጋሞ በ19 73 ዓ.ም

7- ኦቴሎ በ19 73 ዓ.ም

8- ቴዎድሮስ በ19 73 ዓ.ም

9- ሐሙስ በ19 78 ዓ.ም

10- አሉላ አባ ነጋ በ19 79 ዓ.ም

11- ያላቻ ጋብቻ በ19 80 ዓ.ም

12- ታርቲይፍ በ19 80 ዓ.ም

13- ኤዲፐስ ንጉሥ በ19 88 ዓ.ም

14- በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ በ19 96 ዓ.ም

15- አፋጀሽኝ በ2003 ዓ.ም

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ትያትር ውስጥ ፈር ቀዳጅ የሚባለውን ‹‹ሊስትሮ ኦፔራ›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔትም አዘጋጅቷል፡፡

ይኼው ሙዚቃዊ ተውኔት “ሊስትሮ ኦፔራ” በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ውድድር ቀርቦ አሸንፏል፡፡

የትያትሩ አባት አርቲስ አባተ መኩሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትርና ጥበባት ለአምስት ዓመታትም አስተምሯል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የአርት ዳይሬክተርነት እና በአዲስ አበባ ባህል ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖም አገልግሏል፡፡

በ19 57 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመቀጠር የመዝናኛ ክፍል ከፍተኛ አዘጋጅና በተቋሙ እስከ ዳይሬክተርነት በደረሰ ደረጃም ሠርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚለቀቀውን ‹‹የአድዋ ጦርነት ዘመቻ›› ታሪካዊ ፊልም ያዘጋጀውም አርቲስት አባተ መኩሪያ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ እና በኢጣሊያ መካከል የተደረገውን የአድዋ ጦርነት የሚዘግበውን ፊልምም አርቲስት አባተ ነበር የሰራው።

በየአመቱ የአርበኞች መታሰቢያ ወይም የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን ሲከበር የሚታየው ባለ ነጭ እና ጥቁር ተንቀሳቃሽ ምስል፥ የአዲስ አበባ ከተማን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በ19 79 ዓ.ም በአባተ መኩሪያ አማካኝነት የተዘጋጀ ነበር።

4 ሺህ ሰዎች እንደተሳተፉበት የሚነገርለት ይህ ዘጋቢ ፊልም በታዋቂው የትያትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ የተዘጋጀና “አድዋ ድልድይ” በሚባለው አካባቢ የተቀረፀ ነው፡፡