ሁለት መሰመር ያለባቸው ትላልቅ ነጥቦች – ግርማ ካሳ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ሁለት መሰመር ያለባቸው ትላልቅ ነጥቦች – ግርማ ካሳ
ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ …እየተባባልን በመከፋፈላችን ተጎድተናል። ከስረናል። በምትኩ ግፈኞች አልፎላቸዋል። በተናጥል እየደበደቡን፣ እየገደሉን፣ እያፈናቀሉና እና እያሸበሩን ይከው ንቀዉን እየተንደላቀቁ ናቸው።

ከትላንትና ወዲያ በአዲስ አበባ ጥይቶች ተተኩሰው እነ ሽብሬ ደሳለኝ ወደቁ። በግፈኞች እጅ። በአጋዚ። ( አጋዚ ስል ፌዴራል ፖሊስን ጨመሬ ነው፤ ለምን ሁለቱም የሚታዘዙት በአንድ አይነት ሰዎች ስለሆነና አንዱ የሌላው ዩኒፎርም እየለበሰ ብቅ ስለሚል) ። ትላንት በጀልዱ፣ በአምቦ፣ በአርሲ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ፣ ሕጻናትና አረጋዊያን ሳይቀሩ ብዙዎች ወደቁ። በነዚሁ ግፈኞች እጅ። ዛሬ ደግሞ የጎንደር ወገኖቻችን እነዚሁ ግፈኞች እየገደሉ ነው። በአሁኑ ሰዓትም አፈሙዛቸዉን፣ የበለጠ ለመጨፍጨፍ፣ ህዝቡ ላይ እያነጣጠሩ ነው።
ኢትዮጵያዉያ ከተባበሩ ጥቅምና ስፍራ እናጣለን የሚሉ አንዳንድ ልሂቃን፣ ያሉ ልዩነቶቻችንን አስፈተው እያቀረቡ፣ በመካከላችን ድልድዮች እንዳይገነቡ እንቅፋት እየሆኑ አስቸገሩን እንጅ፣ የኦሮሞው፣ የጎንደሬው(አማራዉም)፣ የኮንሶም፣ የጋንቤላውም ፣ የቅይጡ ኢትዮጵያዊም..የሁላችንም ጥያቄዎች፣ ከስር መሰረቱ ከተፈተሹ፣ የሰላም፣ የመብት፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና ጥያቄዎች መሆናቸውን እናረጋግጣለን።
በመሆኑም በተናጥል ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎሽ አልፈን መሄድ መቻል አለብን። የአጋዚ ጦር በሁሉም ቦታ መሆን አይችልም። በተናጥል ከመመታት በጋራ በመንቀሳቀስ አጋዚን ጥርስ የሌለው ዉሻ ማድረግ እንችላለን። በመሆኑም ሁሉም ከተሞች በአንድ ጊዜ መንቀሳቀስ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ላይ በአስቸኳይ ስራ ቢሰራበት ጥሩ ነው። ይሄ አድነኛው ነጥብ ነው።
በሁለተኛነት ሌላ በጣም መሰመር ያለበት ነገር አለ። ወያኔዎች በዘጠና ሰባትም ትግሬዎችን ሲያስፈራሩ ነበር፡፡ኢንተርሃምዌ እያሉ። የትግራይ ህዝብ በተለይም ከጎንደሬው እና ወለዬው (አማራዉ) ጋር ተዋልዷል። ስለ “አማራው” የትግራይ ህዝብ የወያኔው ጌታቸው ረዳ ምክር አያስፈልገውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ጨዋ ህዝብ ነው። የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው እንጂ አብዛኛው ወገን እንደሌላው ኢትዮጵያዊ የወያኔ ዱላ የቀመሰ ነው። ማንም ሰው፣ ነጋሪ ሳያስፈልገው፣ በትግራይ እየተመላለሰ ጉብኘት ቢያደርግ፣ በትግራይ ስላለው ሁኔታ ይረዳ ነበር። ህወሃት ከትግራይ የወጣ ስለሆነ ብቻ፣ የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ በስህተት የሚወራዉም ስህተት እንደሆነ ማወቅ ይቻል ነበር።
ወገኖች፣ ትግሉ ጸረ-የሗእሃት ግፍ እንጂ ጸረ-ትግራይ አይደለም። ትግሉ የግፍ ቀንበር የተሸከሙትንም የትግራይ ወገኖቻችንንም ያካተተ መሆን አለበት። ሕወሃትን እንታገላለን እያልን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ የወያኔዎች ወጥመድ ውስጥ በመግባት በትግራይ ወገኖቻችን ላይ አላስፈላጊ አስተያየቶችን የምንሰጥ ከሆነ፣ እንታገለዋለን የምንለውን ህወሃት እየጠቀምን እንደሆነ መርሳት የለብንም። ትግሉ ማስተዋልንም ይጠይቃል። የሕዝብ ጠላት የለንም።