ብአዴን ከግንባሩ ቢወጣ ይቀለዋል
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አቶ ንግሱ ጥላሁን ይባላሉ።፡ የአማራው ክልል የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ናቸው። በፌዴራል ደረጃ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊውን መቼም የማያወቅ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም። በኦሮሚያው ተቃዉሞ ጊዜ ጠንቋይ፣ ጋኔን ማናምን እያለ ሲቀባጥር የነበረው፣ ዱርዬው ጌታቸው ረዳን።ሁለቱም ሰሞኑን በጎንደር በተነሳው ቀውስ ዙሪያ ቃለ ምልልሶች ሰጥተዋል። የሁለቱ ሰዎች አገላለጽ በይዘት የሚመሳሰል ነገር ቢኖረውም በአቀራረብ ግን የትዬ ለሌ ናቸው። የአቶ ንጉሱን አቀራረብ በጣም ወድጄዋለሁ። ሰከን ያሉ፣ የተረጋጉ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ ይመስላሉ። ጨዋነትና ትህትና ይታይባቸዋል። የጌታቸው ረዳ አቀራረብ የጥጋብ ነበር። ጌታቸው ረዳ፣ በጎንደር የተነሳዉን እንቅስቃሴ የሻእቢያ እጅ አለበት በማለት ተቃዉሞ ያሰሙትን በሺሆች የሚቆጠሩትን የሻእቢያ አሽከሮች ሲል ነው የተሳደበው። አቶ ንጉሱ የተነሳው ተቃዉሞ የሕዝብ ተቃዉሞ እንደሆነ፣ የቀረቡ ጥያቄዎች የሕዝብ ጥያቄዎች እንደሆኑና፣ ጥያቄዎቹንም ህዝብን በማክበር፣ ከሕዝብ ጋር በመወያየት መፈታት እንዳለባችው ነው የገለጹት።
ጌታቸው ረዳ የብሄረሰብ ግጭት አለ በሚል በሕወሃቶች ዘንድ የተለመደውን፣ ህዝብ ከሕዝብ የማጣላት ርካሽ ፖለቲካ ሲያስተጋባ ነበር። አቶ ንጉሱ ግን ምንም አይነት የብሄረሰብ ግጭት እንዳልተፈጠረ አስረድተው የሚያቀራረብ መልእክት ነበር ሲያስተላልፉ የነበሩት።ጌታቸው ረዳ፣ በወልቃይት የተነሳዉን የማንነት ጥያቄ እንኳን ሊያምኑ ስለርሱም አንዲት ቃለት እንኳን ማንሳት አልፈለጉም። አቶ ንጉሱ ግን በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ፣ ጥያቄ እንዳለ ከመናገር አልፈዉም፣ ጥያቄው ተገቢና ሕገ መንግስታዊውም እንደሆነ ነው የገለጹት።ከሃያ የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ስድስቱ ወንጀል ሰርተዋል ከተባለ፣ ሕወሃቶች በቀን ለክልሉ ፖሊስ አሳውቀው ፣ ረብሻ ሳይፈጠር ወንጀል ሰሩ የተባሉትን መያዝ ይቻሉ ነበር። ያንን ግን አላደረጉም። ከመጥገባቸው፣ ከማን አለብኝነታቸውና ሌላውም ካላቸው ትልቅ ንቀት የተነሳ፣ በጎንደር ከተማ ትልቅ ረብሻ እንዲነሳ አደረጉ። ለብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኑ።፡
አቶ ንጉሱ ግን ድርጅታቸው ብአዴን (ሕወሃቶች የቀሰቀሱትን) ረብሻና ቀውስ ለማረጋጋት ትልቅ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ነው ያስረዱት። ህወሃት ሲረብሽ፣ ብአዴን አረጋጊ ሆኖ ብቃ አለ ማለት ነው።እንግዲህ የሕወሃቱን ጌታቸው ረዳና የአቶ ንግሱን ቃለ ምልልስ ለተከታተለ፣ በጎንደሩ ቀዉስ የህወሃትን አጥፊና አፍራሽ ሚና የብአዴንን “ገንቢና አረጋጊ” ሚና ለተመለከተ፣ ሁለቱ የኢሕአዴግ “አጋር” ድርጅቶችን የተለያዩ አካሄዶች እንዳሏቸው መረዳት ይቻላል። አሰራራቸው፣ አቀራረባቸው፣ አክላሄዳቸው በምንም መልኩ አብሮ የሚሄድ አይደለም።
በመሆኑም አጋር መሆናቸው ብዙም ቁም ነገር ላይኖረው ይችላል። ብአዴን ከህወሃት ጋር መስራት ካልቻለ፣ እስከ መቼ በህወሃት ምክንይታ እየተጠላ፣ ህወሃት የጣለዉን እየለቀመ ይቀጥላል ? ከኢሕአዴግ ወጥቶ ፣ ከሌሎች ደርጅቶች ጋር በማበር ከህወሃት ጋር ያልተገናኘ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ቢጀርም ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሕገ መንግስቱ ይፈቅዳል። ብአዴን የግድ ኢሕአዴግ ዉስጥ መሆን የለበትም። በፓርላማ 138 መቀመጫ አለው። የአማራውን ክልል ያስተዳድራል። የበለጠ ተጠናክሮ ፣ አገር አቀፍ ሆኖ ሊወጣም ይችላል።ብአዴኖች አስቡበት። ህወሃት ለናንተ ሸክማና ሕመም እንጂ አይጠቅማችሁም።(በነገራችን ላይ አቶ ንጉሱ የተናገሩትን በሙሉ እስማማለሁ ማለቴ አይደለም። ግን ብአዴን አሁን ያለበትን አጣብቂኝ ከግምት በማስገባት፣ የብአዴኑ ተወካይ ልክ እንደ መኢአድ ወይም ሰማያዊ ሰው ሙሉ ለሙሉ እኛ መስማት የምንፈለገውን ነገር እንዲናገሩ መጠበቅ የለብንም። ነገሩን በአንጻራዊነት ነው ማየት ያለብን)።
http://amharic.voanews.com/a/wolkayt-tegede-ethiopia/3421278.html
ግርማ ካሳ